የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ለስድስተኛ ጊዜ በአዘጋጀው ‹‹ህያው የጥበብ ጉዞ›› ወደ ታሪካዊቷ ሸዋ ምድር ለማቅናት ጥቅምት አምስት ከጠዋቱ 2 ሰአት ገደማ በቀጠሮው ስፍራ ተገናኝተናል። ከአንጋፋና ወጣት ደራሲያን፣ ከሙዚቃ እና ቲያትር ባለሙያዎች እንዲሁም ከሰአሊያን እና ቀራፂያን ማህበር የተውጣጡ ልኡካን ከማህበሩ ጋር የሚጓዙ ነበሩ።
በርከት ያሉ የጥበብ ቤተሰቦች በማህበሩ ፅህፈት ቤት ደጃፍ ተሰብስበው የጉዞውን መጀመር ይጠባበቃሉ። በድንገት ግን የልኡክ ቡድኑን የሚያነቃቃ አንድ ክስተት ተፈጠረ። የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በስፍራው በመገኘት ተጓዦችን በማበረታታት እና ታሪካዊ ንግግር በማድረግ በሰላም የምኞታቸውን ፈፅመው እንዲመለሱ ሽኝት አደረጉ። ሚኒስትሯ ስለ ታሪካዊቷ ምድር ሸዋ የአገረ ምስረታ ግዙፍ ድርሻ እና የጥበብ መፍለቂያነቷ እንዲህ በማለት ነበር ንግግራቸውን ያደረጉት።
‹‹ሸዋ ከስርአተ መንግስት ምስረታ ገድሏ ባሻገር በአሁኑ ወቅት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ፅሁፍ ለማቅረብ የሚጠቅሙ የምርምር የታሪክ እና የስነ ፅሁፍ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ እንዲሁም ለዓለም የተረፉ የጥበብ ሰዎች የፈለቁባት ነች›› ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ በአስራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የነገሱትን አፄ ዘርያቆብን በማንሳት በጥበብ ስራቸው ያበረከቱትን የፍትሀ ነገስት እና ክብረ ነገስት የአስተዳደር እና የመንፈሳዊ መፅሀፍት እንደ ምሳሌ አንስተዋል። ከግእዝ ወደ አማርኛ በርካታ መፅሀፍትን በመተርጎም ከፊደል ገበታ እስከ ታላላቅ መፅሀፍት በመድረስ ለኢትዮጵያውያን ያበረከቱት ተስፋ ገብረስላሴን በማወደስ ሸዋ የነዚህና የሌሎች በርካታ ጠቢባን መፍለቂያ መሆኗንም አንስተው የሙዚቀኞች፣ የሰአሊያን ፣ የቀራፂያን እና ደራሲዎች ይህን ታላቅ ስፍራ የማነቃቃት ስራ እንዲሰሩ በማሳሰብ አደራ ሰጥተው ሸኝተዋል።
ጉዞው ተጀምሯል። የልኡክ ቡድኑ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት (በ130 ኪሎ ሜትር) የምትገኘው የሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ደርሰዋል:: በዚያ ጥቂት እንደቆዩ ግን መዳረሻቸውን መንዝ ማማ ሞላሌ ከተማ ነበር ያደረጉት። በዚያ የልኡክ ቡድኑን ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተቀብለው ደማቅ ሥነሥርዓት አደረጉ። በቆይታቸው የተለያዩ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስፍራዎችን የመጎብኘት እድሉ አጋጠማቸው።
ጉዞ በመንዝ ማማ ጀምሮ መንዝ ላሎ፣ በሞጃና ወደራ፣ በመንዝ ጌራ፣ በአንኮበር ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ባህላዊ ጉብኝት ተደረገ። በጉዞው ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በሚተዳደረው ዘብር ገብርኤል የአንድ መቶ ስድስት ዓመት የእድሜ ባለጸጋ እና የአብነት መምህር የኔታ አክሊሉ የህያው ጥበብ ተጓዦች አግኝተዋቸዋል። ከዚያ በተጨማሪ የመንፈሳዊ ዳኝነት ሥርዓት ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
በመንዝ የሚገኘው ጓሳ ምድር እና ማህበረሰብ አቀፍ ሎጅ፣ አቡነዘራብሩክ አፍሮ አይገባም የአንድነት ገዳም፣ ዳግማዊ ጎሎጎታ የመድሃኒያለም ፍልፍል ገዳም፣ የምኒልክ መስኮት እየተባለ የሚጠራው ተፈጥሯዊ መልካምድር፣ የአንኮበር ቤተ መንግስት፣ የነገስታት ልጆች በግዞት ይቆዩበት የነበረው አፍቃራ የጉብኝቱ አካል ነበሩ። በሰሜን ሸዋ ዞን ማጠናቀቂያ ታሪካዊቷ ምድር ሸዋ በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት አምስት ጀምሮ ጥቅምት ስምንት ተጠናቀቀ።
‹‹በፖለቲካ በሥነ ጽሁፍ እና በሥነ ጥበብ ህልቆ መሳፍርት ሰዎችን ያፈራችው ሸዋ ናት›› ያሉት የልኡክ ቡድኑን በመምራት ታሪካዊ ጉዞ አካል የሆኑት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ ናቸው። ማህበሩ ከዚህ ቀደም በህያው የጥበብ ጉዞ የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎች መጓዙንም አንስተዋል። በተለይ በሥነ ፅሁፍ ይዘቱ የሚደነቀው የደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ መፅሃፍ ‹‹ከቡስካው በስተጀርባ›› መቼት ወደሚገኝበት ደቡብ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ ላይ የጎላ አሻራ ወዳሳረፈው የደራሲ ሃዲስ አለማየሁ ልብ ወለድ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› መቼት ጎጃም ተጉዘው እንደነበር የሚታወስ ነው።
ድንገት ሳይታሰብ በአዳራሹ ተገኝተው የልኡክ ቡድኑን ያስደመሙት፤ ‹‹ታሪካዊቷ ምድር ሸዋ›› በሚል መሪ ቃል ስድስተኛው ህያው የጥበብ ጉዞ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ነበሩ።በቆይታቸው የሰሜን ሸዋ ዞን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው መሆኑን አንስተዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በህያው የጥበብ ጉዞ ወደ ሸዋ ምድር ተጉዞ ያደረገው ምልከታ እና የፈጠረው መነቃቃት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሊለመድ ይገባል በማለትም ጠንከር ያለ መልክት አስተላልፈዋል።
‹‹ባለፉት ዘመናት ኢትዮጵያን ሊበታትን በሚችል ፈተና ውስጥ የነበረችበት ወቅት ቢኖርም ከሸዋ የወጡ ታላቋን ኢትዮጵያ መገንባት የቻሉ መሪዎች የፈለቁባት ነች›› ያሉት ሚኒስትሩ አሁን ባለው ፖለቲካ የአገር አንድነት ፈተና ውስጥ እንዲገባ እያንገዳገደ ያለው ለታሪክ የማይመጥን የሆይ ሆይታ ፖለቲካ ቢኖርም በዚያን ዘመን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የተቋጠረው ቋጠሮ እስካሁን ድረስ ሳይፈታ አቆይቶናል በማለት የሸዋ ምድር ያላትን ጉልህ ስፍራ አወድሰዋል።
በጉዞው ላይ ታላቁ የታሪክ ተመራማሪና ምሁር ተክለጻዲቅ መኩሪያ እና ሌሎች ታላላቅ ሰዎች ተዘክረዋል። የጉዞው አላማ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማነቃቃት እና የኪነ ጥበብ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች እምቅ ችሎታቸውን ወደ መድረክ እንዲያወጡ ማድረግ እና አንጋፋዎቹን እንዲተኩ ማመቻቸት መሆኑንም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታውቋል። ‹‹ያላነበበ ትውልድ አውራ የሌለው ቀፎ ሙሉ ንብ ነው›› በማለትም ትውልዱ በንባብ ታሪኩን ባህሉን መርምሮ ከማወቅ ባሻገር እውቀቱን እንዲያንጽ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ በጉዞው ማጠቃለያ ላይ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
ዳግም ከበደ