5‹‹ጥበብ ይናፍቀኛል፤
ተቻችሎ የሚኖር ህዝብ ያስቀናኛል፤
ድንቁርና ያስፈራኛል፤
ጦርነት ያስጠላኛል››
የሚለው የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ዘመን ተሻጋሪ ስንኞች በጉልህ ይነበባሉ። የሎሬቱ ምስልም እንዲሁ ፊት ለፊት ለገጠመው ቀልብን ይስርቃል። ይሄ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ለሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ የተቋቋመውን የባህል ማዕከል በማስመረቂያ ዕለት በአዳራሹ መግቢያ ላይ አይኔን የሳበው የዕለቱ መልዕክት ነው።
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ከአምቦ የበቀለ የጥበብ አባት ነው ። ስራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ፣ መልዕክት አድራሽ እና ኮርኳሪ መሆኑን በሁሉም የጥበብ ስራዎቹ አሳይቷል። ግጥም ሲነሳ ሎሬት ጸጋዬ ይነሳል። ፣ቲያትር፣ ሂስቶግራፈር፣ ሃያሲ፣ደራሲ፣ ተርጓሚ፣አርቲስቲክ ፣ዳይሬክተርነት፣ …. ሲነሳ ሎሬት ጸጋዬ ከፊት ይቀድማል።
ዘመን የማይሽራቸው፣ ወቅት የማይገድባቸው በአንድነት እና በፍቅር ላይ የተሞሉ ስራዎቹን በአማርኛ፣ በግዕዝ፣ በኦሮሚኛ እና በአንግሊዝኛ አስነብቧል። ማንም ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ሳያነሳ እሱ ስለ አንድነት ጽፏል። ኢትዮጵያዊነትን ወደ ውስጡ የከተተው እንዳይወጣ አድርጎ ነው። በስራዎቹ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ይታያል። ስለ አድዋ፣ ስለ ማይጨው ፣ስለ አዋሽ ፣ስለ አፋር … ጽፏል። በበሳል ብዕሮቹ የዓለም ሎሬትነት ማዕረግ ባለቤት ሆኗል። ይሁን እንጂ ለውጪው ዓለም ጸሀፍት ለእነፑሽኪን የባህል ማዕከል ሲቋቋም ለኢትዮጵያዊው ሎሬት ጸጋዬ ግን በስሙ ምንም መታሰቢያ የለም። ለአገሩ እንደሰራና እንደለፋ ምሁር በሚገባው ልክ ሳይከበርና ሳይታወስ ኖሯል።
ከዚህ ቁጭት መነሻነት ይመስላል የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በፕሬዚዳንቱ ዶክተር ታደሰ ቀነአ አነሳሽነትና በሌሎችም ተባባሪነት የባህል ማዕከል ለማቋቋም እንቅስቃሴ የተጀመረው። ይሄም ዕቅድ ሰምሮ ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም በአንድ ህንፃ ላይ የሚገኝ አንድ ፍሎር በስሙ ቤተመፃህፍት፣ አዳራሽ እና ጽህፈት ቤት ተሰይሟል። በቤተመጽሀፍቱ ውስጥም የሎሬቱ ስራዎች የተሰበሰቡ ሲሆን በእሱ ዙሪያ ማንኛውንም ምርምር ማካሄድ ለሚፈልጉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ አብስረዋል።
ሎሬት ጸጋዬ የጥበብ ሰው ብቻ ሳይሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንደነበሩ ስራዎቻቸውን የመረመሩ ግለሰቦች ይናገራሉ። በስራዎቹ በሀገራችን የተዛቡትን ታሪካዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች ሲተችና እንዲስተካከሉ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የነበረ ሰው ነው ።
ዶክተር ታደሰ እንዳሉት በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ ስም የባህል ማዕከል ለማቋቋም ሲወስን ሁለት መሰረታዊ ዓላማዎችን አንግቦ ነው። አንዱ አዲሱ ትውልድ ትልልቆቹ የሰሯቸውን ስራዎች አውቆ ማክበር ስላለበት ነው። ትልልቆቹን የምናከብረው ታላቅ ስራ ሰርተው ያለፉትን ጀግኖች በሚገባው ልክ የሚያከብር ትውልድ ለመፍጠርና የነሱን ፈር ተከትሎ የተሻለ ስራ የሚሰሩ ጀግኖችን ለማፍራት እንጂ የአባቶቻችንን ገድል በማንሳት ብቻ የሚኖር ከንቱ ትውልድ ለመፍጠር አይደለም።
“ሌላው ደግሞ” ይላሉ ዶክተር ታደሰ አዳዲስ ጸጋዬዎችን ለማፍራት ነው። ይሁን እንጂ አዳዲስ ጸጋዬዎችን ለመፍጠር ስለ ጸጋዬ ትልቅነት ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። እሱን ትልቅ ያደረገውን ዕውቀት መጨበጥ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ማዕከሉ ጠንክሮ ይሰራል።
ማዕከሉ በስነጽሁፍ፣ በቲያትርና አጠቃላይ ኪነጥበብ ላይ ባህላችንንና ዘመናዊነትን መሰረት ባደረገ መልክ ትምህርት የሚሰጥበት፣ ምርምር የሚደረግበትና በአጠቃላይ የዘርፉ ዕውቀት የሚዳብርበት በመሆኑ በጣም በርካታ አዳዲስ ጸጋዬዎችን እንደምናፈራ ይታመናል። ከተለያየ የሀገራችን አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች ባህሎቻቸውን የሚለዋወጡበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ ስለሚፈጠርም የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማጎልበት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። እናም እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት በስነ ጽሁፍ ፣በስዕል፣ ቅርፃ ቅርጽ ፣በቲያትር ፣ በፊልም ፣ ድራማ ፣ በባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ ዘርፍ ለማደራጀት ታስቧል። በመሆኑም በእነዚህ ዘርፎች ዙሪያ ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት ካላቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት ጥሪ አቅርበዋል።
“ሎሬት ጸጋዬ በተወለደበት አካባቢ በስሙ የባህል ማዕከል መቋቋሙ ጥሩ ነው። ይህንን ያደረገው የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሊመሰገን ይገባል። ነገር ግን ይሄ በቂ አይደለም” ሲል በቁጭት የሚናገረው አርቲስት ተፈሪ አለሙ ነው። ሎሬት ጸጋዬ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሀብት ነው። በመሆኑም በየክልሉ ማስታወሻ ሊቆምለት ይገባል ብሏል።
ስለሀገር አንድነት፣ ስለ ፍቅር የእሱን ያህል የሰበከ ፣ ግጥምና ድርሰት የጻፈ የለም የሚለው አርቲስት ተፈሪ ዛሬ ሁሉም ሰው የሚጠቀምበት “እናት ኢትዮጵያ ፣ እማማ ኢትዮጵያ ፣ እምዬ ኢትየጵያ” የሚሉት በብዛት የሚታወቁት በእሱ ድርሰት ውስጥ ነው። ያኔ የሰበከው፣ ይፈራና ይሰጋ የነበረው አንድነቱ እንዳይበተን ፤ እርስ በእርሱ እንዳይጠላላ ነበር። አሁንም የእሱ ስራዎች እንደገና ወደ መድረክ መምጣት እሱን ማክበር፣ ወደ እዛ ወደምንፈልገው ፍቅርና አንድነት ይመልሰናል ብዬ አስባለሁ ። ፀጋዬ የኦሮሚያ፣ የአማራ ፣የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች ነው። ብዙ ጊዜ ለአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች ሲታገልና “ታሪካችን ተወስዶብናል፤ እኛ ነበርን ባለታሪክ” ሲል የነበረ ሰው በመሆኑ እሱን ማከበር ወደ ታላቅነታችን መመለሻ መንገዳችንን እንደመጀመር ነው ሲል አስተያያቱን ሰጥቷል።
በመድረኩ ላይ የተገኘው የኦሮሚኛ ድምጻዊ አጫሉ ሁንዴሳ ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ጋር የስጋ ዝምድና እንዳለው ገልጾ ይሁን እንጂ ሎሬቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ዘመድ ናቸው መወለድ ቋንቋ ነው ሲል ተርቷል። “እርሳቸው በሰሩት ስራ ሁሉም ህዝብ ይኮራል፤ እኔም እኮራባቸዋለሁ። እንደስራቸውና እንደስማቸው በትውልድ አካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ላይ የእሳቸውን ሀውልት ማየትን እሻለሁ” ብሏል።
ተዋናይ እና ጠበቃ አበበ ባልቻ የሎሬት ጸጋዬን ገድል የገለጹት ስሜት ውስጥ ገብተው ከእንባ ጋር እየታገሉ፤ ሲያመልጣቸውም በሳግ እየተናነቁ ነበር። “ይሄ ምጡቅ ያልጻፈው፣ ያልዳሰሰው የለምና ሊከበር ይገባል” ሲሉ ነው ቁጭታቸውን የገለጹት።
የማይድን በሽታ ሳክም፣
የማያድግ ችግኝ ሳርም፣
የሰው ህይወት ስከረክም፣
እኔ ለእኔ ኖሬ አላውቅም።… የሚለውን የሎሬቱን ሙሉ ግጥም አንብበውም
“እውነቱን ነው አንድም ጊዜ ለራሱ ኖሮ አያውቅም” ሲሉ ግጥሙን በማጣቀስ ስለ ሎሬት ጸጋዬ አጠቃላይ ስራዎች፣ የህይወት ቆይታ፣ የህመሙን ጊዜና ህልፈቱን ዳስሰዋል። ስለዚህ በስሙ እኔን ከሚተባበረኝ ጋር በመሆን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሀውልት እናቆማለን ሲሉ አዳራሹን በጭብጨባ አስደምቀውታል። በሁሉም ክልል ውስጥ ቢያንስ መንገድ ሊሰየምለት ይገባል። እሱ ስለ አሰብ፣ ስለ አባይ ፣ ስለ አድዋ፣ አዋሽ ፣ አፋር፣ ድሬዳዋ፣ ሀረሪ፣ ባሌ፣ ሲዳማ፣ ዶርዜ … ጽፏል። ያልፃፈውን ጠይቁኝ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ፣…። ብለው መድረኩን ለቀዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
አልማዝ አያሌው