ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት የእብድ ውሻ በሽታ ከክርስቶስ ልደት በፊት 2000 ዓመት በፊት ይታወቅ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚያን ጊዜ አንድ ሰው የቤት ውሻው ካበደ ሰዎችን እንዳይነክስ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ እንደነበረ እና ይህንን የማያደርግ ሰው ላይም ከበድ ያለ ቅጣት ይጣል እንደነበርም ጥናቶች ይናገራሉ፡፡
የእብድ ውሻ በሽታ በቫይረስ የሚመጣ እና በልዩ ልዩ እንስሳት ንክሻ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው:: ይህ በሽታ በአጠቃላይ በዓለማችን ላይ በሁሉም ሀገራት ላይ የሚገኝ እና ከያዛቸው ሰዎች ውስጥ 99% ያህሉን ህይወት የሚቀጥፍ ነው፡፡ ይህንን በሽታ 99% ያህል ወደ ሰው የሚያስተላልፈው በዚህ በሽታ የተያዘ/ የተለከፈ የቤት ውሻ ሲሆን፤ ወደ ሰው የሚተላለፈውም ያበደው ውሻ ሰውን ሲነክስ ነው፡፡
አንዳንድ ምርምሮች እንደሚያስረዱት የእብድ ውሻ በሽታ የሰውን ህይወት በብዛት ከሚቀጥፍባቸው ሀገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ 10ሺህ እና ከዚያ በላይ ሰዎችን እንደሚይዝ ይነገራል፡፡
ይህንን የእብድ ውሻ በሽታን ወደ ሰው የሚያስተላልፈው ‹‹ያበደ ውሻ›› ብቻ ነውን?
ይህንን በሽታ ብዙውን ጊዜ ያበደ ውሻ ወደ ሰው ስለሚያስተላልፍ በውሻ ስም ይጠራ እንጂ በዚህ ቫይረስ የተያዙ እንደ ድመት፣ ከብት፣ ፍየል፣ ቀበሮ፣ ጥንቸል፣ የሌሊት ወፍ፣ ጦጣ፣ ዝንጀሮ እና የመሳሰሉት የቤት እና የዱር እንስሳት ሰውን ቢንክሱ ምራቃቸውን ወይም ደማቸውን ወደ ሰው አካል ካስተላለፉ በሽታውን በቀላሉ ያስተላልፋሉ፡፡
ይህንን የእብድ ውሻ በሽታ መከላከል የምንችለው በምን አኳኋን ነው?
1. ውሻ በዚህ በሽታ እንዳይያዝ ማድረግ ፤
በዚህ ዘዴ በመጠቀም ይህንን በሽታ በማስወገድ የብዙ ሰዎች ህይወትን ከዚህ በሽታ መታደግ ይቻላል፡፡ ይህንን በሽታ ለማከም በዚህ ምክንያት ወጪ የሚደረገውን ከፍተኛ ገንዘብ መቆጠብ ይቻላል፡፡ ይህም በቀላሉ ማድረግ የሚቻለው የቤት ውሾች በዚህ በሽታ እንዳይያዙ ክትባት በመስጠት ነው፡፡
2. በዚህ በሽታ ላይ ማህበረሰቡ ያለውን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ እና የእብድ ውሻ ንክሻን መከላከል ነው፤
ውሻ አብዶ ሰውን እንዳይነክስ ለማድረግ አንድ ያበደ ውሻ የሚያሳያቸውን ምልክቶች ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ያበደ ውሻ ወይም በዚህ በሽታ የተያዘ ውሻ ሙሉ በሙሉ ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም አንድ ያበደ የቤት ውሻ ከሚያሳያቸው ምልክቶች በተለይም ወደ መጀመሪያ አካባቢ፣ ውሻው ከቀድሞ ሁኔታው በተለየ ሁኔታ እረፍት አጥቶ ወዲህ እና ወዲያ መንከላወስ፣ ቀደም ሲል የማይተናኮላቸውን ነገሮች ወይም ሰዎች እና እንስሳትን መተናኮል፣ መብራት ሲበራበት እና ድምጽ ሲሰማ መፍራት ናቸው፡፡
በዚሁ መሰረት ይህ በሽታ በውሻው ላይ እየጠናበት በሚሄድበት ጊዜ ጨለማ ቦታ ሄዶ መደበቅ፣ ምግብ ሲሰጠው መዋጥ አለመቻል፣ ምራቁን ማዝረክረክ/ ማንጠባጠብ፣ መድከም (አቅም ማጣት)፣ ቀደም ሲል የማይበላውን (የማይመገበውን) አንዳንድ ነገሮች መብላት እና ውሃን ካየ ወይም ቢረጭበት ከመጠን በላይ መፍራት ናቸው፡፡ በዚሁ መሰረት እነዚህ አይነቶችን ምልክቶች ያየንባቸው ውሾች ይህንን በሽታ የማስተላለፍ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡
3. ይህንን በሽታ ለመከላከል የሚሰጠውን ክትባት ለዚህ በሽታ ሊጋለጡ ለሚችሉ ሰዎች መስጠት
ይህ ክትባት ሰዎች ለዚህ በሽታ ከመጋለጣቸው በፊት ማለትም ባበደ ውሻ ከመነከሱ በፊት የሚሰጥ ክትባት ነው:: ይህም ክትባት በዚህ በሽታ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ለሆኑ ሰዎች፤ ይህንን በሽታ በሚመረምር ላብራቶሪ (ቤተ- ሙከራ) ለሚሰሩ ሰዎች፣ በእንስሳት ጥበቃ እና እንክብካቤ ላይ የተሰማሩ ሰዎች፣ ይህ በሽታ በብዛት የሚገኝበት ቦታ የሚሄዱ ህፃናት (እንደ ውሻ፣ ድመት እና ከመሳሰሉት የቤት እንስሳት ጋር የመጫወት እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ) እና በሌሎች ምክንያቶች ይህንን በሽታ የሚያስተላልፉ እንስሳት ጋር ረጅም ጊዜ አብሮ ለሚቆዩ ግለሰቦች ክትባቱን መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡
የእብድ ውሻ በሽታ ምልክቶች ምን ምን ናቸው?
ይህ ያበደው ውሻ ከላይ በተገለጸው መሰረት መከላከል ካልተቻለ እና ሰውን ከነከሰ በኋላ ደግሞ በአስቸኳይ ክትባት መውሰድ ካልተቻለ፣ በበሽታው የተጠቃው ሰው የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል፡፡ ይህ በሽታ ያለበት ውሻ ሰውን ከነከሰ በኋላ የበሽታው ምልክት የሚታይበት የቆይታ ጊዜ ውሻው የነከሰው የሰውነት ክፍሎችን መሰረት የሚያደርግ ነው:: በዚሁ መሰረት ከአንጎል ርቆ የሚገኝ እንደ እግር ያለውን የሰውነት ክፍል ከነከሰው ዘግይቶ ምልክት የሚያሳይ ሲሆን፣ ወደ አንጎል ቀረብ ብሎ የሚገኝ የሰውነት ክፍል እንደ የራስ ቅል (Head) ከነከሰ ደግሞ ወደ አንጎል ገብቶ ምልክት ለማሳየት አጭር ጊዜ ብቻ ይወስዳል፡፡ በዚሁ መሰረት ውሻ ሰውን ከነከሰ በኋላ በሽታው ምልክት የሚያሳይበት ጊዜ በአማካዩ ከ2-3 ወራት ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ከላይ በተገለፀው መሰረት በአንድ ሳምንት ውስጥ ሊከሰት የሚችል እና እስከ 1 ዓመት ጊዜም ሊቆይ ይችላል፡፡
ይህ በሽታ ሰውን ከያዘ በኋላ ልዩ ልዩ ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን ከነዚህም ምልክቶች ውስጥ በተለይ መጀመሪያ አካባቢ ላይ የሰውነት ትኩሳት፣ የሰውነት መቃጠል እና ውጋት ስሜት በቁስሉ አካባቢ መሰማትን ያሳያል፡፡ በመቀጠልም ወደ አንጎል በሚገባበት ጊዜ የሚያሳያቸው እንደ የባህርይ ለውጥ፣ ውሃ መፍራት፣ ከቤት ለመውጣት መፍራት እና የመሳሰሉት ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ እነዚህን ምልክቶች ከታዩ በኋላ ይህ በሽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ህይወትን ይቀጥፋል፤ ይህ በሽታ አንድ ጊዜ ከያዘ በኋላ የሚደረገው ህክምናም ህይወትን ማትረፍ አይችልም፡፡
አንድ ሰው በእብድ ውሻ ወይም በዚህ በሽታ በተጠረጠረ ውሻ ቢነከስ ምን ማድረግ አለበት?
አንድ ሰው በአበደ ውሻ ወይም በዚህ በሽታ በተያዙ ሌሎች ነፍሳቶች ቢነከስ፣ የተነከሰው ቦታ ወዲያውኑ ጊዜ ሳይሰጥበት በትክክል በንጹህ ውሃ እና በሳሙና ቢያንስ ለ15 ደቂቃ ማጠብ ግዴታ ነው:: ከዛ ቀጥሎም በፍጥነት አቅራቢያ ወዳለ የጤና ተቋም በመሄድ ክትባት መውሰድ ይገባል:: ይህም ክትባት እንደ ዱሮው ጊዜ ለ14 ቀናት የሚሰጥ ሳይሆን ለ5 ቀናት የሚሰጥ እና አወሳሰዱም በጣም ቀላል የሆነ ነው፡፡ ይህ ክትባት የሚሰጥበት 5 ቀናትም በመጀመሪያው ቀን፣ በ3ኛ ቀን፣ በ7ኛ ቀን፣ በ14ኛ ቀን እና በ28ኛ ቀን ላይ ነው፡፡ የጤና ባለሙያ ባዘዘው መሰረት Immunoglobulin የሚባል ተጨማሪ መድሃኒትንም መውሰድም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
ስለዚህ በአጠቃላይ ብንችል የቤት ውሻን ማስከተብ ካልሆነም ካበደ የሚያሳየውን ምልክት በማየት መጠንቀቅ፣ ይህ ሁሉ ካልተቻለ ደግሞ ወዲያውኑ ወደ ሀኪም በመሄድ የዚህን በሽታ ክትባት መውሰድ የግድ ነው፡፡ ይህ ካልተደረገ በሽታው ሰው ላይ ምልክቶችን ማሳየት ከጀመረ በኋላ የሚደረገው ዕርዳታ ወይም ህክምና ህይወትን ማትረፍ እንደማይችል መታወቅ አለበት::
1. Petful Health 26 Warning Signs of Rabies in Dogs
2. PubMed: Incidence of Rabies in Humans and Domestic Animals and People’s Awareness in North Gondar Zone, Ethiopia,2013 May 9.
3. World Health Organization: Key facts, prevention and symptoms of Rabies
4. History of Rabies: Dunlop, Robert H; Williams, David J (1996). Veterinary Medicine: An Illustrated History. Mosby.
ዶ/ር ጉርሜሳ ሂንኮሳ
አርሲ ዩኒቨርሲቲ
ሆራ ቡላ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012