ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቀጣይነት ያለው ባለሁለት አሀዝ ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ ከአህጉረ አፍሪካ አልፎ የዓለም ማህበረሰብን እያስደመመች ትገኛለች። አገሪቱ እያስመዘገበች የሚገኘውን ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረቷን ለመቅረፍ እና ያለባትን የውጭ ብድር ለማቃለል ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ምርትና አገልግሎት ከሌሎች አገሮች ጋር በጥራትና በዓይነት፤ እንዲሁም በዋጋ ተወዳዳሪ በሚሆን መልኩ አምርታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት እንዳለባት የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ነገርግን አሁን ላይ በአገሪቱ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበውም ሆነ ወደ ውጭ አገር የሚላከው ምርትና አገልግሎት ከፍተኛ የጥራት መጓደል ችግር እየተስተዋለበት ከመሆኑም በላይ፤ አንዳንድ ለውጭ ገበያ የቀረቡ ምርቶች በጥራት ጉድለት ምክንያት ከተላኩበት አገር እየተመለሱ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ ተግዳሮት ከሌሎች መሰል ችግሮች ጋር ተደማምሮ የውጭ ገበያውን በማዳከም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንዳታገኝ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። መንግሥትም ችግሩን በመረዳት በወጪ ንግዱ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፤ ከጥቅምት 5/2012 ዓ.ም ጀምሮ ከቄራ ድርጅቶች የአገልግሎት ፈቃድ ተከራይተው የስጋ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ሲያቀርቡ የነበሩ 80 የሚደርሱ ኩባንያዎች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ እንዳያቀርቡ መንግሥት እገዳ አስተላልፏል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ስጋ አምራችና ላኪዎች ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ አበባው መኮነን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የስጋ ምርት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የግብርና ምርቶች ላይ የአገልግሎት ፈቃድ ተከራይተው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አያሌ ኩባንያዎች አሉ። ከነዚህ መካከል ከቄራ ድርጅቶች የአገልግሎት ፍቃድ ተከራይተው የስጋ ምርት ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ 80 የሚደርሱ ኩባንያዎች ይገኛሉ።
የእነዚህ ኩባንያዎች አፈጻጸም ሲታይ አገሪቱ ለውጭ ገበያ በዓመት ከምታቀርበው የስጋ ምርት ከሁለት በመቶ በታች የሚሆነውን የሚሸፍኑ ሲሆን፤ ኩባንያዎቹ በዘርፉ የሚፈጠረውን ወቅታዊ የገበያ መነቃቃት ሲኖር ጊዜያዊ ጥቅምና ትርፍ ለማግኘት ፈቃድ አውጥተው በዘርፉ ይሰማራሉ።
በመሆኑም፤ ኩባንያዎቹ በዘርፉ ላይ ጥሩ ገበያ ሲኖር ወደኢንዱስትሪው ይገባሉ። በዘርፉ ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ ጥለው ይጠፋሉ። እንዲሁም፤ በዘርፉ ላይ ለመቆየትም ፍላጎት የላቸውም። ስለዚህ ኩባንያዎቹ በዘርፉ ላይ ምንም እሴት ሳይጨምሩ ትርፋቸውን ብቻ ለማሳደድ ወደ ዘርፉ የሚመጡ በመሆኑ የሚያመጡት ፋይዳ የለም።
በዚህም፤ የአብዛኞቹ ኩባንያዎች ጀርባቸው ሲጠና ከሚልኩት የስጋ ምርት በሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ የተለያዩ ዕቃዎችን እና ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በአገር ውስጥ በውድ ዋጋ በመሸጥ ያላግባብ ትርፍ ከማግበስበስ ባለፈ በአገር ውስጥ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሆነዋል።
በአጠቃላይ እነዚህ ኩባንያዎች አላማ አድርገው ወደዘርፉ የሚገቡት የውጭ ምንዛሬ ፍለጋና ከውጭ የተለያዩ ዕቃዎችን ለማስገባት እንጂ፤ በስጋ ኢንዱስትሪው ላይ የተሻለ ልምድና እውቀት ኖሯቸው በዘርፉ ላይ አወንታዊ የገበያ ውድድር ለመፍጠር አለመሆኑን ጸሐፊው ይናገራሉ።
ነገር ግን፤ ስጋ አምራች የሆኑ የቄራ ድርጅቶች ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው ዘርፉን ለማሳደግና ለማዘመን፤ እንዲሁም ከእንስሳት ተዋጽኦ የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ የአገርን የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ከፍ ከማድረግ ባሻገር ከሴክተሩ ተጠቃሚ ለመሆን ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት፤ እነዚህ ኩባንያዎች የቄራ ድርጅቶች ተመን አውጥተው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡበት ዋጋ በታች በመሸጥ፤ በአገር ውስጥ ጤነኛ ያልሆነ የንግድ ውድድር በመፍጠር የእንስሳት መሸጫ ዋጋን በማናር እና አንዳንዶቹ ደግሞ የምርት ጥራት ደረጃ ሳያሟሉ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ በዘርፉ የተሰማሩ የቄራ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጪ እያደረጉ በመምጣታቸው፤ ሁሉም የማህበሩ አባላት ተወያይተው ለየትኛውም ኩባንያ የአገልግሎት ፈቃድ ላለማከራየት መወሰናቸውን አቶ አበባው ተናግረዋል።
ስለዚህ፤ እነዚህ ኩባንያዎች ለአገር ከሚያበረክቱት ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የማህበሩ አባላት ፍንትው አድርገው በመረጃ አስደግፎ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በማስረዳትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በችግሩ ዙሪያ በሰፊው በመወያየት ከጥቅምት 5/ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም የቄራ ድርጅቶቹን ፈቃድ ተኮናትረው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚልኩ ካምፓኒዎች ላይ መንግሥት እገዳ መጣሉን ገልጸዋል።
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለስላሴ ወረስ በበኩላቸው፤ የቄራ ድርጅቶችን የአገልግሎት ፈቃድ ተኮናትረው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ካምፓኒዎች ጥሩ የገበያ አየር ሲኖር ፈቃድ አውጥተው ወደገበያው የሚገቡ ሲሆን፤ ገበያው ሲቀዘቅዝ ደግሞ ከገበያው ይወጣሉ።
እንዲሁም፤ የውጭ ምንዛሬ አግኝተው ከውጭ የተለያዩ ዕቃዎችን ለማስገባት ሲፈልጉ ፈቃድ ወስደው የስጋ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚልኩ ሲሆን፤ የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሬ ካገኙ በኋላ ኩባንያዎቹ ከገበያው ይወጣሉ። የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲገጥማቸው ደግሞ መልሰው ፈቃድ አውጥተው ወደ ዘርፉ ይገባሉ።
በዚህም የተለያዩ ዕቃዎችን ከውጭ በማስገባት በአገር ውስጥ በውድ ዋጋ በመሸጥ ያላግባብ ትርፍ ከማግበስበሳቸው ባሻገር በአገሪቱ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ያደርጋሉ። በተጨማሪም እነዚህ ካምፓኒዎች ጤናማ ያልሆነ የንግድ ውድድር በመፍጠር የአገር ውስጥ የእንስሳት ዋጋ እንዲንር በማድረግና የስጋ ምርቱን ከተተመነው ዋጋ በታች ለውጭ ገበያ በማቅረብ በአጠቃላይ ገበያውን ማወካቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ ኩባንያዎች ሌላ ገቢ የሚያገኙበት አማራጭ ያላቸው ሲሆን፤ በስጋ ምርት ላይ የተሰማሩ የቄራ ድርጅቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በዚህ ዘርፍ ብቻ ስላፈሰሱ ሌላ የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው፤ ገበያው በመታወኩም ከገበያው ለመውጣት በር ላይ ቆመዋል። እነዚህን ድርጅቶች ከገበያው ወጡ ማለት ደግሞ አገሪቱ በየዓመቱ ከዚህ ዘርፍ የምታገኘውን እና እስከ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሬ አጣች ማለት ነው።
ስለዚህ እነዚህ ለትርፍ ብቻ የተቋቋሙ ድርጅቶች በሚፈጥሩት የገበያ አለመረጋጋት ምክንያት መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው የስጋ ምርት ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ የቄራ ድርጅቶች ከገበያው ውጪ እንዳይሆኑና አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እንዳታጣ መንግሥት የአገልግሎት ፈቃድ ወስደው/ተከራይተው ስጋ ለውጭ ገበያ በሚያቀርቡ ኩባንያዎች ላይ እገዳ ለመጣል መገደዱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2012
ሶሎሞን በየነ