የምስራቅ አፍሪካ የፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር
ኢትዮጵያ ከደርግ መንግስት መገርሰስ በኋላ ነጻ ገበያ ስርዓት መከተል የጀመረች ቢሆንም የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ ሊጫወት የሚገባውን ሚና አልተጫወተም፡፡ ለዚህም አንዱ ችግር በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል ሊኖር የሚገባው የተሳለጠ ግንኙነት አለመፈጠሩ ነው የሚሉት ዶክተር አንዳርጌ ታዬ ናቸው፡፡ ዶክተሩ መሰረቱን አሜሪካ (ካሊፎርኒያ) ያደረገው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር እና ከኢንስቲትዩቱ መስራቾች አንዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እና በመንግስት መካከል ባለው ጤነኛ ባልሆነ መስተጋብር፤ መልካም ግንኙነት ያለመኖር መንስኤዎች እና የመስተጋብሩ ችግሮች እያስከፈለ ባለው ዋጋና የመፍትሄ እርምጃዎች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እነሆ ብለናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አንዳርጌ፡- በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል በተግባር ያለው ግንኙነት የተሳካ ነው ለማለት ያስቸግራል። በጣም ደካማ ግንኙነት ነው ያለው። የግሉ ዘርፍ ከመንግስት ሊያገኝ የሚገባውን በቂ እገዛ እያገኘ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። የግሉ ዘርፍም እንደ ግል ዘርፍ ሊጫወት የሚችለውን ሚና ለመጫወት መንግስት እንደተቋም ስራዎቹን የሚያካሄድበት አካሄድ ለግሉ ዘርፍ በጣም አስቸጋሪ ነው ማለት ይቻላል።
ለዚህ በዋነኛነት መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ልማታዊ መንግስት ብሎ የያዘው ፖሊሲ መንግስት እንደሀብት ፈጣሪ እና እንደ ስራ ፈጣሪ አድርጎ ወስዶ እስከ ዛሬ ድረስ በዚህኛው ስርዓት እንኳ ባለፉት 28 ዓመታት ያየነው ውጤት በተግባር ኢኮኖሚያችን እና የግሉ ዘርፍ ያለበትን ደረጃ ለገመገመ ሰው ሌላ መረጃ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። የተሳካ እንዳይደለ እርግጥ ነው። መንግስት ከድህነት ሀብት ፈጥሬ አወጣለሁ፤ ስራም እፈጥራለሁ ያለው በፍልስፍና የያዘው የማይሄድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ሀብትና ስራ እድል መፍጠሩ ችግሩ ምኑ ላይ ነው?
ዶክተር አንዳርጌ፡- መንግስት በተፈጥሮው ሀብት አከፋፋይ እንጂ ሀብት ፈጣሪ አይደለም። መንግስት የተፈጠረውን ሀብት ያከፋፍላል። ታክስ በመሰብሰብ ካለው ወደ ሌለው፣ ከበዛበት ወዳነሰበት፣ የማስተላለፍና የማደላደል ስራ ነው የሚሰራው። ሀብት የመፍጠር ስራ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ነው። የመንግስት ሚና በዋናነት ይህ የግል ዘርፍ በተነሳሽነት መጥቶ የሚያስፈልገውን በቂ ድጋፍ አግኝቶ ሀብት እንዲያፈራና ስራ እንዲፈጥር ማድረግ ብቻ ነው የመንግስት ሚና። ከዚያ ሀብቱ ከተፈጠረ ሀብቱን ደግሞ ቅድም ባልኩት መሰረት ማከፋፈል ነው። ይህ ነው የመንግስት ስራ ሊሆን የሚችለው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራት በአንዳንድ ዘርፎች የገበያ ክፍተት ሊኖር ይችላል። እነዚህን ዘርፎች እንዴት ማሟላት ይቻላል ?
ዶክተር አንዳርጌ፡- በአዳጊ ሀገሮች በኢኮኖሚ ግንባታ የመንግስት ድርሻ የምንላቸው በሌሎችም ሀገሮች ከአዳጊ ወዳአደገ ሀገር የተሸጋገሩበትን ሂደት ስናይ የመንግስት ድርሻ የምንለው አለ። ይህም የግል ዘርፉ ለመግባት የማይበረታታበት፣ ትርፍ አገኝበታለሁ ብሎ የማያስብበት አካባቢዎች ላይ መንግስት እነዚያ አካባቢዎች ገብቶ የግል ዘርፉን የሚስብ መሰረት መጣል የመንግስት ድርሻ ሊሆን ይችላል።
በዚህ ረገድ መንግስት የተወሰነ ሚና ይኖረዋል። ነገር ግን በፍልስፍና ደረጃ ለህዝቤ ስራ ፈጥሬ፣ ህዝቤን መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ አድርሼ ብሎ ራሱ ፖሊሲ አውጥቶ፣ ራሱ ፈጽሞ፣ ይህን አደርጋለሁ የሚል በዓለም ላይ ያለ ተሞክሮ ያንን አስተሳሰብ የሚደግፍ ሆኖ አናይም። የኢንዱስትሪ ሼድ ሰርቶ ለሰዎች አከፋፍሎ ያደገ ሀገር ተሞክሮ እኔ በግሌ አላውቅም።
ነገር ግን የመንግስት ትልቁ ሚና በፍልስፍና ደረጃ እኔ ሀብት መፍጠር አልችልም ብሎ መንግስት ማመን አለበት። ስራ መፍጠር አልችልም ብሎ መንግስት ማመን አለበት። ነገር ግን ሀብት አፍሪውን፣ ስራ ፈጣሪውን እፈጥራለሁ፣ እንዲፈጠር፣ እንዲወለድና እንዲያድግ እሰራለሁ ብሎ ግን መስራት አለበት። የፍልስፍና ለውጥ መምጣት አለበት። የግንኙነት ችግር ብቻ አይደለም በሁለቱ መካከል ያለው። ዋናው ደንቃራ የሆነው አስተሳሰቡ ጭምር ነው ብዬ ነው የማምነው።
ከዚያ በኋላ ግን የመንግስት ሚናን በግልጽ ካስቀመጡት በኋላ መንግስት ለግሉ ዘርፍ ማደግ ሊጫወት የሚገባውን ሚና በብቃት መጫወት እንዲችል በአስተሳሰብም፣ በሰው ሀይል፣ በስርዓትም ራሱን ወደዚያ ማሳደግ ቢችል ኢኮኖሚ እፈጥራለሁ፣ ሀብት እፈጥራለሁ ብሎ በማይሆን ቦታ ላይ ሀብትን፣ ጉልበትንና ጊዜን ከማጥፋት ይልቅ ከመንግስት የሚጠበቅበትን ቢሰራ የግሉ ዘርፍ የራሱን ሚና ይጫወታል። መንግስት ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠው ድጋፍ በብቃት ራሱን ለማሳደግ እና አቅሙን ቢጠቀም ውጤታማ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
በውጤቱም ስናየው የግሉ ዘርፍ እስካሁን ቀጫጫ ነው። የግሉ ዘርፍ በብዙ መልኩ የሚጠበቅበትን እየተወጣ አይደለም። በዋናነት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት የሚባለውን ተቋም ወይም የመንግስት አገልግሎት የሚባለውን ሳትነካ አየር ከመተንፈስ በስተቀር ምንም ነገር ማድረግ አትችልም። በማስረጃ ማስቀመጥ ይቻላል። እንኳን አይደለም የግሉ ዘርፍ አንድ ግለሰብ ጠዋት ነግቶ እስከሚመሽ ድረስ አየር ከመተንፈስ ውጪ እጅ የሚታጠብበት ውሃ ከመንግስት ነው የሚመጣው፤ አምፖሉን ሲያበራ በመንግስት ነው የሚመጣው፤ የሚንቀሳቀስበት መንገድን ጨምሮ እያንዳንዱ ነገር የሚሰራውም፣ የሚጠግነውም፣ የሚመራውም፣ የሚያስተዳድረውም መንግስት ነው።
በአጭሩ እንዲህ አይነት ኢኮኖሚክ እና የመንግስትና የፖለቲካ አደረጃጀት ባለበት ሀገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ ምን ያህል በመንግስት ብቃት፣ በመንግስት ቅልጥፍናና፣ በመንግስት አለመብቃትና አለመቀላጠፍ እንቅስቃሴው ሊገደብ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። በዋናነት ሲስተሙንና የሰው ሀይሉን በአጠቃላይ ቢሮክራሲ የምንለውን ዳግም መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል።
አሁን ባለው የቢሮክራሲ አሰራር፣ አሁን ባለው የቢሮክራሲ ባህል፣ አሁን ባለው የቢሮክራሲ አቅምና ስርዓት የግሉን ዘርፍ የ100 ሚሊየን ህዝብን ገበያ አንቀሳቅሶ ትልቅ ስራ መስራት አንቅቼ ስራ ሰርቼ ይህን አደርጋለሁ ብሎ ለማመን እጅግ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ መንግስት ራሱን እንደገና ይስራ፣ መውጣት ካለበት እጁን ያውጣ፣ መሆን ያለበትን ለመሆንና መስራት ያለበትን ለመስራት ቢሮክራሲውን ዳግም መቃኘት አለበት።
እነዚህ ነገሮች ከሆኑ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። ምን አይነት ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል አንድ ምሳሌ ልሰጥህ እችላለሁ፤ ሆቴሎች ከግል ወደ መንግስታዊ መዋቅር ከተቀየሩ በኋላ ሆቴሎች ለረጅም ዘመን ምን አይነት ሆነው እንደኖሩ እናውቃለን። ሆቴል ኢንዱስትሪው ወደ ግሉ ዘርፍ ተላልፎ የግሉ ዘርፍ ሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ እንዲገባ መንግስት አንዳንድ እርምጃዎችን በወሰደ ጊዜ ግን ምን አይነት ለውጥ እንደመጣ መመልከት ይቻላል። ከዚያ በኋላ አንተ ለአንድ ቀን ራስ ሆቴል ሂድና፤ በዚያው ቀን ተመልሰህ አንድ ሁለት ሶስት ካሳንችስ አካባቢ ያሉ የግል ሆቴሎች ገብተህ የመንግስትና የግል ዘርፍ ምን ማለት እንደሆነ ማንም ምንም ሳይልህ፣ ወይም የኢኮኖሚክስ ተማሪ መሆን ሳያስፈልግህ ሁሉንም ነገር አይተህ ትወጣለህ።
አዲስ ዘመን፡- ለግሉ ዘርፍ መዳከም በዋናነት መንግስትን ኮንነዋል። መንግስት በበኩሉ የግሉ ዘርፍ ከአገልግሎት ዘርፍ ውጪ ባሉት ዘርፎች ላይ የመሳተፍ የፍላጎት ማነስ እንዳለበት ያነሳል። እነዚህ ሁለቱ አይጋጩም?
ዶክተር አንዳርጌ፡- እኔ እሱንም ችግር የግሉ ዘርፍ ሳይሆን የመንግስት ነው የምለው። ለምን እንደሆነ ላስረዳህ እችላለሁ። ለምሳሌ አንድ ሰው በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ሲገባ የሚፈልጋቸው ግብዓት እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲገባ የሚያስፈልገው ግብዓቶች ይለያያሉ። ለምሳሌ አንድ ባለሀብት አንድ ሆቴል ቢገነባ አንሶላ ማንጠፍና ሳሙና መግዛት ከቻለ እና ደንበኛ ማስተናገድ ከቻለ ሰዎች ገብተው ይተኛሉ። ገንዘብም መሰብሰብ ይችላል።
ነገር ግን አንድ ባለሀብት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቢሰማራና ጨርቅ የሚያመርት ቢሆን ግብዓት በቅጡ አያገኝም። ግብዓት ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አለበት። እንደሚታወቀው በእኛ ሀገር የውጭ ምንዛሬ በመንግስት ቁጥጥር ስር ነው ያለው። እሱ በጊዜ ካልተገኘ ፋብሪካው ስራ ያቆማል። ከቆመ ኪሳራ መምጣቱ አይቀርም።
መለዋወጫም እንደዚሁ ነው። አንድ ባለሀብት ከዚህ እቃ አንስቶ የሚሸጥበት ሀገር ወስዶ ሸጦ ለማትረፍ የሎጂስቲክ ጉዳዮችም የሚታወቁ ናቸው። ይህ የሚያሳው አንድ ሰው በአገልግሎት ዘርፍ ቢሰማራ ችግሩ አነስተኛ ነው። ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ቢሰማራ ግን ችግሩ ብዙ ነው። በመሆኑም ባለሀብቱ ከማኑፋክቸሪንጉ ይልቅ የአገልግሎቱን ዘርፍ ለመምረጥ ይገደዳል። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያሉ ችግሮች ቢቀረፉ ግን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከአገልግሎት ዘርፉ በላይ ሊያብብ የሚችልበት እድል አለ። እኔ ብዙ በግሉ ዘርፍ ያሉ ሰዎችን አግኝቼ ብዙ ነገሮች ላይ የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ብዙዎቹ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ሰዎች ማሽኑን ገዝተው ተክለው ስራ ሲጀምሩ ምን ያህል ለስራ እንደተነሳሱ መገመት ትችላለህ።
በግሉ ዘርፍ ካየሁትና ካደረግኩት ዳሰሳ ለመረዳት የቻልኩት የግሉ ዘርፍ በአገልግሎት ዘርፍ ሲሰማራ በአንጻራዊነት በሌሎች ዘርፎች ገብተው ከምታልፉባቸው ውጣ ውረዶች ያነሳ ውጣ ውረድ አለ። በመሆኑም ወደ አገልግሎቱ ዘርፍ የማዘንበል ነገር ይታያል።
አዲስ ዘመን፡- በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል በርካታ ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል። መንግስትም በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገ ነው። በማሻሻያው እነዚህ ችግሮች እንዲቀረፉ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
ዶክተር አንዳርጌ፡- በዋናነት የፖሊሲ አስተሳሰቡ ዳግም መቃኘት አለበት። በዋናነት የመንግስት ሚና ምንድን ነው የሚለው በቅጡ መቀመጥ አለበት። መንግስት ሚናው ካልሆኑ ነገሮች ወጥቶ ሚናው በሆኑ ነገሮች ላይ ጠንክሮ የሚሰራበትና ለግሉ ዘርፍ በቂ ድጋፍ ወደ ማቅረብ ራሱን ማምጣት አለበት። ትልቁ ነገርም ይኸው ነው። በሁለተኛ ደረጃ በግሉ ዘርፍና በመንግስት፣ በግሉ ዘርፍና የግሉ ዘርፍ በሚንቀሳቀስበት ማህበረሰብ መካከል ያለውን ሁለትዮሽም ሆነ ሶስትዮሽ ግንኙነቶች በተሻለ መልኩ ሊዳብሩ የሚችሉበትንና የተሻለ ግንዛቤ ሊኖር እንዲችል መስራት ያስፈልጋል።
ዋና ዋና ማነቆ ናቸው የሚባሉትን ነገሮች ከፖለቲካዊ ንግግሮችና ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ ብለን ከምንናገራቸው ንግግሮች አልፈን ጠንከር ያሉ ስራዎችን መስራት ያለብን ይመስለኛል። ለምሳሌ የውጭ ምንዛሬን ጉዳይ በተመለከተ፣ እስከዛሬ ልንቀርፍ ከሞከርንበት ወጣ ባለ መልኩ ወጥተን ይህንን ነገር ከስሩ መቅረፍ እንችላለን ብሎ መመልከት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
መንግስት በዚህ ዘርፍ ላይ የሚሰሩትን ሰዎች አቅም ማሳደግ አለበት። የደንበኛ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ የኢንቨስተሩ ፍላጎቶች፣ ኢንቨስተሮችን ለማስተናገድ የሚችል አቅም ያለው የሰው ሃይል ማፍራት፣ ቴክኒካል እውቀት ብቻ ሳይሆን፤ የአመራር፣ የተግባቦት፣ ሰዓት አጠቃቀም፣ አስተሳሰብ፣ ለስራ ያለውን ፍላጎት፣ ከኢንቨስተሩ ጋር ያለውን ግንኙነት ተያያዥነት ያላቸውን ክህሎቶች ለማሳደግ መሰራት አለበት።
የፖለቲካ ንግግሮችን ማድረግ አንድ ነገር ሆኖ በመሬት ላይ ያሉ ባለሙያዎች ለግሉ ዘርፍ የሚገባውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ራሱን የቻለ ሌላ ስራ ነው። በመሆኑም ከፖለቲካ ንግግሮች ዝቅ ተብሎ እታች ስራ መሰራት አለበት። ከላይ የሚሰሩትና የሚወሩት ነገሮች አንድ ደረጃ ወደ ታች እስኪወርድ ብዙ ነገሮች በነበሩበት ሁኔታ ነው የቀጠሉት። ስለዚህ ቢሮክራሲውን ዳግም የመቃኘት ስራ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- እናመሰግናለን።
ዶክተር አንዳርጌ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2012
መላኩ ኤሮሴ