የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ)፣ ግብይትን በኢንተርኔት አማካኝነት ማካሄድ የሚያስችል አገልግሎት ነው። የንግድ ልውውጡ እጅ በእጅ በጥሬ ገንዘብ ሳይሆን ክፍያዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት መለዋወጥን ምርጫው ያደርጋል። ግብይቱም በክሬዲት ካርድ፣ ወይም በዴቢት ካርድ ካልሆነም በኢንተርኔት ባንኪንግ የመጠቀም አማራጮችን ያስቀምጣል።
በዚህ መልኩ የሚፈፀመው ግብይት ከጊዜም ሆነ ከሻጭ አኳያ የራሱ አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት ባለሙዎች ያስረዳሉ። የግብይቱ 24 ሰዓት ክፍት መሆን፣ የትም መሄድ ሳያስፈልግ ባሉበት ቦታ ሆኖ የፈለጉትን መርጠው መገበያየት ማስቻሉና በዚህም ሰዓት፣ ጊዜና ገንዘብን መቆጠቡ ከአዎንታዊ ጎኖቹ መካከል በማለት ይጠቅሳሉ።
ከሽያጭ የሚሆኑ ዕቃዎች ተጨባጭ የመሆን ውስንነት፣ ደንበኞች ተደራድረው የሚፈልጉትን መሸመት አለመቻላቸው፣ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ መሆኑ፣ የደንበኞች ታማኝነት ውስንነት ደግሞ ከአሉታዊ ጎኖቹ መካከል ይዘረዘራሉ።
ከዓለም ንግድ ምህዋር ጋር ከተዋወቀ ግማሽ ምዕተ ዓመት እንዳስቆጠረ የሚታመነው የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ)፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዓመት ዓመት ከፍተኛ እምርታ እያስመዘገበ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በፈረንጆቹ ባለፈው መጋቢት የተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ኮንፍረንስ ዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አጠቃላይ ሽያጩ እ.ኤ.አ 2017 29 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቶ፣ ተጠቃሚዎቹም ወደ ሁለት ቢሊዮን መጠጋታቸው ይጠቁማል።
የኤሌክትሮኒክ ግብይት በአህጉራችን አፍሪካም በተለይ ደቡብ አፍሪካን፣ ናይጄሪያን ህንድን በመሳሰሉ አገራት ይበልጡን ተግባራዊ መደረጉ ይገለፃል። ኢትየጵያም ምንም እንኳን ጎልቶ የሚጠቀስ ባይሆንም፣ በአንዳንድ አገልጋሎቶች ላይ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን መተግበር ጀምራለች። ከሰሞኑም የግብይቱን ኡደት ለማሳለጥ ትኩረት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ የሚመሰክሩ እርምጃዎች ውስጥ እንደምትገኝ ተገልፀል።
አዲስ ዘመንም የአገሪቱና የኤሌክትሮኒክ የግብይቱን ትስስር ወቅታዊ ተክለ ቁመና እና ከትግበራው በተጓዳኝ ታሳቢ ሊደረጉ ስለሚገባቸው አበይት ተግባራት ያነጋገራቸው ባለሙዎች መንግሥት በቅድሚያ ግብይቱን ለማሳለጥ ለሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ያስገነዝባሉ።
የአፍሪክ ንግድ ምክር ቤቶች አስተዳዳሪ አቶ ክቡር ገና፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይት በኢትዮጵያ ተጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር እንደማቻል ይገልፃሉ። ‹‹በአገሪቱ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን ወደ ተግባር ማሸጋገር የሚያስቻሉ መደላደሎች ቢኖሩም መንግሥት እንደ አንድ ኢንዱስትሪ ለዚህ አይነቱ ግብይት ቴክኖሎጂ የሰጠው ትኩረትና ድጋፍ በጣም ደካማ ነው›› የሚሉት አቶ ክቡር፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ መሰል ግብይት ለመፍጠር የሚታትሩትም በራሳቸው ጥረት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ያመለክታሉ። ይህም ኢንዱስትሪውን በሚፈለገው መጠን ለመገንባት የሚደረገውን ሙከራ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይጠቁማሉ።
ዘርፉን በአግባቡ ለመምራትና በለሱን ለመቋደስ በሚያስችል መልኩ የፖሊሲ፣ የሥርዓተ ትምህርት፣ የሰው ሃይል፣ የፈቃድ አሰጣጥ እንዲሁም ንግዱን ለማሳለጥ የሚረዱ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ውስንነቶች፣ ቴክኖሎጂውን ተከትሎ ለመራመድ ዋነኛ ማነቆ መሆናቸውን አቶ ክቡር ያብራራሉ።
እነዚህን ተግዳሮቶች መፍታት ከተቻለና የመንግሥት ትኩረት ከጎለበተ ግብይቱን ውጤታማ ማድረግ የማይቻልባቸው ምክንያቶች እንደማይኖሩ አጽዕኖት ሰጥተው የሚናገሩት አቶ ክቡር፣ በተለይ ግብይቱን የማሳለጥ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የሚስተዋልባቸውን ውስንነት ሳይውል ሳይድር ለማስተካከል መትጋት እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ።
የአፍሮ ግሎባል ኮንሰልታንሲው ፕሮፌሰር ፍሰሃፂዮን መንግሥቱ፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ባደጉት አገራት ከዕለት ወደ ዕለትም የሚጎለብትና በንግዱ ምህዋር ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ስለመሆኑ ይገልፃሉ። የኤሌክትሮኒክ ግብይት ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ፣ ለግብይቱ ትግበራ ትኩረት መስጠትም የሚደነቅ መሆኑን የሚገልፁት ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹በቅድሚያ መሄድ ሳንጀምር መሮጥ አንችልምና ወደ ትግበራው ለመሸጋገር ወሳኝ የሆኑ ቀደም ተከተሎችን በአግባቡ መቃኘት ያስፈልጋል ››ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ መሰል የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ለመግባት ሲታሰብ መሆን የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ መሬት ላይ ካለው ጋር መጣጣሙን መቃኘት፣ ለዚህም ከማህበረሰቡ ግንዛቤ እስከ ተቋማት ጥንካሬ በአግባቡና በጥንቃቄ መፈተሸ ብሎም ደረጃ በደረጃ ማገዝ የግድ ይላል።
በኢትዮጵያ ኢ ኮሜርስ አገልግሎት እንዲስፋፋ ከተፈለገ በዚሁ መጠን ግብይቱን ለማሳለጥ የደም ሥር ለሆኑ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች ልዩ ትኩረት መስጠት ግድ መሆኑን የሚያስገነዘቡት ፕሮፌሰሩ፣ የአገልግሎት አሰጣጡንና ህጋዊነቱን በማስጠበቅ ረገድ የአጠቃላይ ግብይቱ ሕግ እንዴት ተፈፃሚ መሆን አለበት የሚለውን ታሳቢ ማድረግ ግድ ስለመሆኑም ያሰምሩበታል። ከዚህ ሁሉ ባሻገርም ግብይቱን ከታክስ ኡደቱ ጋር እንዴት ማስተሳሰር እንደሚቻል ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባም ያመለክታሉ ።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴም ባለፈው መስክረም ወር መጨረሻ ሳምንት አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የዓመቱ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ባቀረቡበት ወቅት የኢንፎርሜሽና ኮሙኒኬሽን ቴክሎጂ በተመለከተ በዓለም ላይ ካለው ሀብት ከ65% በላይ የሚሆነው የሚመነጨው ከአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን መጥቀሳቸው ይታወቃል።
ዓመቱ ለኢንፎርሜሽና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ትኩረት የሚሰጥበት እንደሚሆን መግለፃቸው ይታወቃል። ዘርፉን ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራት የሚከናወኑበት መሆኑን በመጥቀስም ‹‹የኢ-ኮሜርስ ጥረቶችም ፍሬ የሚያፈሩበት ይሆናሉ ›› ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት በሀገራችን ከአገልግሎት ዘርፉ የሚመነጨውን ኢኮኖሚ ለማሳደግና በቴክኖሎጂ እንዲመራ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎች የፀደቁና በመጽደቅ ሂደት ላይ ያሉ በመሆናቸው በያዝነው ዓመት በርካታ የኢ-ኮሜርስ ጥረቶች ፍሬያማ የሚሆኑበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2012
ታምራት ተስፋዬ