በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ግብርናው ቀዳሚ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻዎች ሲናገሩ ይደመጣል። ይህ ሲባል ግን ያለምክንያት አይደለም። አንድ ማሳያ እንኳን መጥቀስ ቢቻል፣ በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ ያላነሰው ህዝብ ኑሮው በግብርና ላይ የተመሰረተ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው። ከዚህ ባለፈም ግብርናው ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እና ሌሎችም በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ጉልህ ድርሻ አላቸው በሚባሉ መስኮች ሁሉ ምሰሶ በመሆን ደግፎ የሚይዝ ነው።
ግብርና ሲባል ደግሞ አንድም በሰብል ልማቱ፣ ሁለተኛም በእንስሳት ሀብቱ የሚገለጽ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ለሁለቱም ምቹ ከመሆኗ ባለፈ እምቅ አቅምም ያላት ናት። ለምሳሌ፣ በእንስሳት ሀብት ረገድ ኢትዮጵያ በቁጥር ደረጃ በአፍሪካ በቀዳሚነት የሚያሰልፋት ሀብት አላት። ለእንስሳት ልማቱ የሚሆን ሰፊና ምቹ መልክዓ ምድርም ባለቤት ናት። ይሁን እንጂ አገሪቱ ባላት ሃብት ልክ በተለያየ ምክንያት ተጠቃሚ አለመሆኗ ይነገራል። ለዚህ ደግሞ አንድም ከምርታማነትና ጥራት፣ ሁለተኛም ከገበያ ሰንሰለቱ ብልሹነት ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ያነሳሉ።
አቶ ኃይለስላሴ ወረስ፣ የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ሰፊ የእንስሳት ሀብት ያላት ቢሆንም በሚገባት ልክ ተጠቃሚ አልሆነችም። መንግሥትም ይሄን ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፣ የስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መቋቋምም የዚህ እርምጃው አንድ አካል ነው። ኢንስቲትዩቱም በተለይ በሥጋና ወተት ዘርፍ የሚታየውን ችግር ከማቃለል አኳያ የሚሰሩ ባለሃብቶችን በማበረታታትና በመደገፍ ለዘርፉ ውጤታማነት እየሰራ ሲሆን፣ የአግሮ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ፣ በሥጋና ወተት እንዲሁም ከቁም እንስሳት ግብይት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝም ያላሰለሰ ጥረት እያከናወነ ይገኛል።
ለምሳሌ፣ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስ ፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከሥጋና ቁም እንስሳት ግብይት 969 ነጥብ 48 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት እቅድ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ለዚህም በየዓመቱ 94ሺ ቶን ስጋን ለኤስያ፣ በተለይም ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት እንዲሁም አፍሪካ አገራት በጥራት የማቅረብ አቅጣጫን አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል። በአራት ዓመታት ሂደቱም 410 ነጥብ 49 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ በቀሪው ጊዜም ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት ይሆናል። በተለይም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ አኳያ ከምርት እስከ ግብይት ያለውን ሂደት ዘመናዊና ውጤታማ ለማድረግ ይሰራል። ዘርፉ የሥራ መፍጠሪያና የገቢ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግልም ይደረጋል። ለዚህ ደግሞ የግሉን ዘርፍ በስፋት የማሳተፍ፣ የማበረታታትና ተገቢውን ድጋፍ የመስጠት ተግባራት ይከናወናሉ።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የግብርና ሚኒስትሩ አማካሪ ዶክተር ኢያሱ አብርሃም በበኩላቸው እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ግብርናው የማይተካ ድርሻ ያለውና የኢኮኖሚውም የጀርባ አጥንት ነው ሲባል 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ኑሮውን በግብርናው ላይ የመሰረተ መሆኑ፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ወዘተ. መስኩ ሰፊ ድርሻ የያዘ በመሆኑ ነው። ከዚህ አኳያ ሲታይ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ሌሎች ዘርፎችን ይዞ የሚነሳ ነው።
ምክንያቱም ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ጥሬ እቃ ከማቅረብ፣ ለወጣቱ የሥራ እድል ከመፍጠር፣ የውጭ ገበያን ከማሳደግና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች አኳያ ግብርናው መሰረታዊ ነው። በመሆኑም ይሄን ሚናውን እንዲወጣ ግብርናው ሊዘምን፤ ከማምረትም ወደ ገበያ ተኮር የኤክስቴንሽን ሥራ ሊሸጋገር ያስፈልጋል። ግብርናው ሊዘምን ካስፈለገ ደግሞ አንደኛ፣ ምርታማነትን በማሳደግ ትርፍ ማምረት፤ ሁለተኛ፣ የተመረተው ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ የግብይት ስርዓቱን ማዘመን የግድ ይሆናል። በዚህ ሂደትም አርሶ አደሩ፣ ወጣቱና ባለሃብቱ ከምርት እስከ ግብይት ባለው ሂደት እንዴት ተቀናጅተው ይስሩ የሚለው ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
እንደ ዶክተር ኢያሱ ገለጻ፤ ግብርናው አትራፊ ዘርፍ ነው። ይህ አትራፊ ዘርፍ ደግሞ በአግባቡ ካልተመራና ካልተሰራበት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይችልም። ይህ ደግሞ በሰብል ልማቱ ብቻ ሳይሆን በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማቱም የሚገለጽ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ልማቱ ረገድ ሰፊ አቅምና እድል አላት። የገበያ ፍላጎቱም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል። በመሆኑም ይሄ ፍላጎትና አቅርቦት የሚጣጣምበትን እድል መፍጠር፤ አምራቹም አገርም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይገባል።
ለዚህ ደግሞ ከእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ጀምሮ የመኖ ልማት፣ የእንስሳቱ የጤና አገልግሎት፣ ምርታማነት ላይ በትኩረት የሚሰራ ሲሆን፤ ዝርያን ከማሻሻል ጀምሮ ምርታማነቱን በብዛትም በጥራትም ከማሳደግ በተጓዳኝ የገበያ ሰንሰለቱ ዘመናዊ እንዲሆንና ሕገወጥ ንግድና ደላላን ለማስወገድ ሰፊ ጥረት ይደረጋል። ለዚህ ደግሞ ከሜካናይዜሽን የመኖ ልማት ሥራ ጀምሮ እስከ ክላስተር የእንስሳት ልማት (የዶሮ፣ የዓሳ፣ የሥጋና የወተት፣ ወዘተ ልማት ክላስተርን በመፍጠር) አርሶ አደሩና ወጣቱ እየተቀናጀ እንዲሰራ በማድረግ ከባለሃብቱ ጋር በቀጥታ ግብይቱን እንዲፈጽም የሚደረግበት አግባብ ይፈጠራል።
ይሄም ሰፋፊ መሬት የሚፈልግ መሆኑን በመገንዘብ የሚሰራ ሲሆን፤ ምርታማነቱን ማሳደጉ ብቻ ሳይሆን ሕገወጥነትን ከመከላከል አኳያ በኮማንድ ፖስት እየተሰራ ይገኛል። ሆኖም ሥራው የህብረተሰቡን ሰፊ ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ለዘርፉ የምርት እድገትና ውጤታማ የገበያ ሥርዓት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። መንግሥትም ምርታማነቱን ከማሳደግ፣ የገበያ ሥርዓቱ እንዲሻሻል ከማድረግ፣ ባለሃብቱን በስፋት እንዲሳተፍ ከማድረግና ከመደገፍ፤ የወጣቱ የሥራ መፍጠሪያና ገቢ ማግኛ እንዲሆን ከማድረግ፣ ገበያ ተኮር ምርት የሚያመርት አርሶ አደር ከመፍጠርና በተለይም ምርትና ገበያን ከማገናኘት አኳያ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2012
ወንድወሰን ሽመልስ