ኢትዮጵያዊ የእጽዋት ሳይንቲስት ናቸው። በ2009 ዓ.ም የእንግሊዝ የሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ኪው ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸናፊም ነበሩ። በዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማትም አሸናፊዎች መካከል አንዱ ናቸው።
የኢትዮጵያን ብዝሀን ሕይወትን ለረዥም ጊዜ በማጥናትና በመመርመር ኅብረተሰቡም ሆነ አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደረጉ፤ የኢትዮጵያ ፍሎራ ፕሮጀክትን ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ ከ17 የአፍሪካና የአውሮፓ አገሮች የተወጣጡ የእጽዋት ተመራማሪዎችን የመሩ፣ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን የያዙ መጽሐፍትን የጻፉና በትልልቅ ጆርናሎች ያሳተሙ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
የአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሙያዊ ተቋማት አባል፤ የኢትዮጵያ ባዩሎጂካል ማህበረሰብ ሊቀመንበር፤ የታክሶኖሚክ ስተዲ ኦፍ ዘፍሎራ ተሮፒካል አፍሪካ ማህበር ዋና ጸሐፊ፤ የፕላንት ታክሶኖሚ ዓለም አቀፍ ማህበር ምክር ቤት አባል ናቸው። የመልቲ ዲስፕነሪ ኤክስፐርት ፓናል ፎር ዘ ኢንትሮግቨርመንታል ሳይንስ ፖሊሲ ፕላትፎርም ኦን ባዮዳይቨርሲቲ ኤንድ ኢኮ ሲስተም ሰርቪስ በምክትል ሊቀመንበርነት አገልግለዋል። የዛሬውን “የህይወት እንዲህ ናት” አምዳችን እንግዳ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው። ከእርሳቸው ጋር ያደረግነው ቆይታ እነሆ ብለናል።
ውልደትና ዕድገት
ሰኔ 21 ቀን 1960 ዓ.ም ከቡታጀራ ራቅ ብላ በምትገኘው ወሌንሹ ወረዳ ስሮ ቀበሌ በእነአቶ ደምሰው ቤት ፈንጠዝያ ያስከተለ ወንድ ልጅ ተወለደ። የዛሬው ሳይንቲስት የያኔው ህጻን እንደ እርግብ የዋህ ነበርና እናቱን ሲያጣ እንኳን አያለቅስም፤ በዚህ ጸባዩ ያሳደገው ጎረቤት ነበር።
ፕሮፌሰር አድገው ነብስ ሲያውቁ ግን የተለየ ባህሪ አወጡ። በምንም መልኩ የማይመስላቸውን አያደርጉም፤ ተቆጪም ናቸው። በዚያው ልክ ብቻቸውን ማንኛውንም ነገር ማድረግ አይፈልጉም። የቡድን ነገር ይመቻቸዋል። ይህ ደግሞ የእግር ኳስ ጨዋታን በሚገባ እንዲወዱ አድርጓቸዋል። የተከላካይ ቦታንም በመሸፈን ሰውነታቸው እስኪላላጥ ድረስ መጫወታቸውን ያስታውሳሉ።
እንግዳችን ሰብስቤ የሚለው ስም የወጣላቸ ውም በምክንያት ነው። እርሳቸው ከመወለዳቸው በፊት ሁለቱ አያቶቻቸው አይስማሙም ነበር። እናም ቤተሰቡ ተራርቆ ይኖራል። ይሁንና ሁለቱም አያቶች በማይጨው ጦርነት ላይ አረፉ። እርሳቸው ሲወለዱ ደግሞ አባታቸውና የእናታቸው ታላቅ ወንድም ጥብቅ ጓደኝነትን መሰረቱ። በዚህም ሰበሰብከን፤ አንድ አደረከን ሲሉ ሰብስቤ እንዳሏቸው ይናገራሉ።
‹‹ልጅነቴን ሳስታውስ የአካባቢው እናቶች እናት ሆነው አሳድገውኛል። እናቴ ገበያ ሲሄዱ የጓደኛዬን እናት ጡት ጠብቼ እውላለሁ።» ይላሉ። ይህ ደግሞ ለአካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላ እናቶች ያላቸው ክብር ከፍ እንዲል አድርጓቸዋል። በተለይ የጓደኛቸው እናት ከልጃቸው እኩል አድርገው በልጃቸው ስም “መሪ” ብለው ሲጠሯቸው ይበልጥ ለሁሉም ሰው ያላቸው ምልከታ እንዲልቅ አድርጓቸዋል።
ለእናታቸው የመጀመሪያ ለአባታቸው ሦስተኛ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ ከብት በማገድ፤ ለቤተሰቡ እንጨት በመልቀምና ለመስቀል ደግሞ የችቦ እና የማገዶ እንጨት በማዘጋጀት ያግዙ እንደነበር ይናገራሉ። ለአካባቢው ሰው መታዘዝና መላላክ እንደዋና ስራቸው ነበር። ከዚያ ውጪ ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ ነው። ይህም ውጤታማ አድርጓቸዋል።
ፕሮፌሰር ሰብስቤ የእጽዋት ሳይንስ ተመራማሪ እሆናለሁ ብለው አስበው እንደማያውቁ ነገር ግን በአካባቢያቸው የሚበቅሉ የእጽዋት ዝርያዎችን ለማወቅ እንደሚጥሩ ያነሳሉ። በተለይ ከሁለት ሰዎች ጋር በመሆን እያንዳንዱን የእጽዋት ዝርያና ጥቅም ለማወቅ ይጣጣሩ እንደነበር አጫውተውናል።
‹‹ልጅነቴ ሁልጊዜ አይረሳኝም። በተለይ የትልልቅ ሰዎች ምርቃት። ትንሽ ትልቁም ይመረቃል። ምርቃት የሚጀምሩት ከአገር ስለሆነ ያስደስተኛል። ለአገር የሚሰጠው ክብር ልዩ ነው። ዛሬ በተቃራኒው ሆኖ ከመንደር መጀመሩን ሳይ ያንጊዜን ቢያመጣው ያሰኘኛል። ኢትዮጵያን ከማንም ጋር እንዳላወዳድርም ያደረገኝ ያ ያደኩበት ማሕበረሰብ ባህል ነው›› ይላሉ።
እጽዋት ያሳደገው ትምህርት
ፊደል ቆጠራን የጀመሩት በአባታቸው አማካኝነት ነው። ከዚያም ቀላዲ ወደምትባል ቀበሌ ተልከው አባ ገብረእግዚአብሔር እግር ስር ቁጭ ብለው እስከ ዳዊት ድረስ ደግመዋል። ድቁና ለመቀበል የሚያበቃቸውን ትምህርት ቀስመዋል። ይሁንና ካህናቱ በአባቱ የትውልድ ቀዬ በወገራ ገብርኤል እንዲቀድሱ ቢፈልጉም አባት ግን በእንቢታቸው ጸኑ። ምክንያቱም የዘመናዊ ትምህርትን ጥቅም በእጅጉ ያውቁታል። ስለዚህ ከቄስ ትምህርቱ አስወጥተው በቀጥታ ወደ አንደኛ ክፍል ላኳቸው።
ፕሮፌሰር ሰብስቤ በቄስ ትምህርት ቤት መሰረታዊ የፊደል መቁጠር ብቻ አይደለም የተማርኩት፤ ግብረገብነትን፤ በቡድን መስራትን፤ የንባብ ፍቅርን፤ አንዱ ለአንዱ መምህር መሆንን አውቀውበታል። ከዚያ ቢወጡም ይህንን ባህሪ ይዘው ነው የቀጠሉት። ስለዚህም ሰዎችን ሳይንቁ የተሰጣቸውን መቀበል ስለሚወዱና ለማድረግም ስለሚጥሩ ጎበዝ ተማሪ ሆነዋል። 11ኛ ክፍል ድረስ እስኪደርሱም የደረጃ ተማሪ ነበሩ።
ቡታጀራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአንድ እስከ ስድስተኛ ነበር የተማሩት። ሰባትና ስምንትን ሲዊድኖች ባሰሩት ትምህርት ቤት ቀጠሉ። በዚህ ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩት 15 ብቻም እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ግን ሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ ውስጥ ምንም አይነት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ እነዚህ 15 ልጆች በዚያው የመማር እድል አልገጠማቸውም። ስለዚህም አካባቢያቸውን እንዲለቁ ግድ ሆነባቸውና ዘጠነኛ ክፍልን ለመከታተል ወደ ደብረዘይት አቀኑ። በአጼ ልብነድንግል ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 11ኛ ክፍል ተከታተሉ።
ይህ ጊዜ በጣም ከባድ እንደነበረ የሚያነሱት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ ከቤተሰብ ሥር ወጥቶ መልመድ በእጅጉ የተፈተኑበት እንደነበር ያስታውሳሉ። ለአምስት ተከራይተው በወር 20 ብር እየተላከላቸው በተራ ሻይ እያፈሉ እንደተማሩ አይረሱትም።“ ልምድ ቀስሜበታለሁ፤ በገንዘብ፤ በስራና ራስን በማስተዳደር ዙሪያ ማንም እንዳይችለኝና በሄድኩበት እንዳልፈተን ሆኜበታለሁ “ይላሉ። የአገልግል እንጀራንም ያዩት በዚያ ጊዜ እንደነበር ያነሳሉ።
እንግዳችን 12ተኛ ክፍልን ሳይማሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር በተቋቋመውና ለመምህርነት በቀጥታ ተመልምለው በሚገቡበት በዕደማርያም ትምህርት ቤት ነበር የገቡት። ከዓመት ቆይታ በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስን ተቀላቀሉ። እያስተማሩ ቆይተውም በዓመቱ ማለትም በ1977 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በስነህይወት ትምህርት አጠናቀቁ። ከዚያው ሳይለቁ በዘርፉ እያስተማሩ በቦታኒ የትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰሩ።
ቀጣዩ የትምህርት ክትትላቸው አገር ማዶ የሚያሻግራቸው ሆነ፤ በአፍሪካና አረቢያ እጽዋት ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር በማድረግ በሶስተኛ ዲግሪ ከሲውዲን አብሳላ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል። አገራቸው በመምጣትም የአስተ ማራቸውን ማህበረሰብ እያገለገሉ የተለያዩ አገራት ስልጠናንም ይወስዱ ነበር። በሚሰሯቸው የምርምር ስራዎች የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀበሉት ዶክተር ሰብስቤ፤ ሁልጊዜ የእውቀት ባለቤት ለመሆን የሚተጉ መሆናቸውን ይናገራሉ። ያነባሉ፣ይመራመራሉ፣ ይጽፋሉ፣ ዓለም አቀፍ ጆርናሎችን ያሳትማሉ፣ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እያማከሩና እያስተ ማሩ ይገኛሉ። ስልጠናዎችን በተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ ይወስዳሉ፤ ያሰለጥናሉ። በዚህም የብዙ ስልጠና ሰርተፍኬቶች ባለቤት ናቸው።
የእጽዋት ፍቅር
‹‹የገጠር ልጅ መሆኔ ከእጽዋት ጋር አቆራኝቶኛል። ይበልጥ ግን በእጽዋት ዙሪያ እንድ ሰራ ያደረገኝ ጋምቤላ እድገት በህብረት ዘመቻ በተጓዝኩበት ጊዜ ነው›› የሚሉት እንግዳችን፤ ጋምቤላ የህይወት ምዕራፋቸውን እንደቀየረው ይናገራሉ። በአካባቢያቸው ከሚያዩት ውጪ እጽዋት የተለዩ ናቸው ብለው አያስቡም ነበር። ሆኖም ጋምቤላ ሲሄዱ ሁሉም ነገር የማያውቁት እንደነበር ተረዱ። ስለዚህም የእጽዋት ፍቅር ነበራቸውና በሚገባ ለመረዳት ወደመጠየቁ ገቡ።
‹‹ያለ እጽዋት ውሃ አይኖርም፤ ምግብና መድሃኒትም እንዲሁ፤ መጠለያም ቢሆን ያለእነርሱ አይታሰብም። በዘርፉ የጠለቀ ምርምር እንዳደርግ ያነሳሳኝ የጋምቤላ መልከአ ምድርና እጽዋት ልዩ መሆን ነው። » ይህ ደግሞ በተለያዩ ስልጠናዎችና ሥራዎቻቸው ኢትዮጵያን ያካለለ ሥራ እንዲሰሩ አድርጓቸዋል። በሥራው ይበልጥ እንዲቀጥሉበት ያደረጋቸው አንድ መምህራቸው እንደነበር የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ የአራተኛ ዓመት ትምህርታቸውን ሲጀምሩ ባዩት ነገር ላይ ተንተርሰው እንዲሰሩ ሆነዋል። በዚያው የስነእጽዋቱ ፍቅር በውስጣቸው ሰርጿል። ሁለተኛም ሦስተኛም ዲግሪን ሲሰሩ ከዚያ ያልዘለሉት ለዚሁ እንደሆነ ይናገራሉ።
የአባታቸው የቅርብ ጓደኛ ከሆኑት አቶ ወልደሚካኤልና በአካባቢያቸው ስለ ዛፍና እጽዋት ጥቅም በሚገባ ከሚያውቁት አቶ መሃመድ ስለ እጽዋት ጥቅም በሚገባ የተረዱት ባለታሪኩ፤ ጋምቤላ ያለውን የእጽዋት ዝርያና ጥቅም ከአካባቢው አባቶች ልምድ ቀስመው በትምህርት አዳበሩት። ይህ ደግሞ በእጽዋት ሳይንስ ተመራማሪነታቸው የታወቁ ፣ በቦታኒክ ሳይንስ ምርምርና ጥናት ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ረድቷቸዋል።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲሰሩ የመናገሻ ደንን ያጠኑት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ኢትዮጵያ እጽዋት ጥናት ፕሮጀክት ውስጥ ተሳትፈው የኢትዮጵያን እጽዋት ዝርዝር የሚያሳይ ሥራ ሰርተዋል። በዚህም ከእጽዋት ሳይለዩ 30 ዓመታትን አሳልፈዋል። ይህ ደግሞ ለህይወቴ እጽዋት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነና ማህበረሰብን እንዴት መታደግ እንዳለብኝ ያሳየኝ ነው ይላሉ።
እጽዋትን መለየት አንድ ሳይንስ ነው። በፕሮጀክቱ ውስጥ ማሳለፍ መቻል ሌላ ነው። ምክንያቱም ሳይንሱ ሲታይ የኢትዮጵያ እያንዳንዱ ቦታ፤ ማህበረሰብና ባህሉ ይታያል። ሙሉ ኢትዮጵያዊ ለመሆንም ያስችላል። በእጽዋት ዙሪያ ተመራምሬ ጨርሼያለሁ የሚል አካል እንዳይኖርም ያደርጋል። ስለዚህም እኔም በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም ዙሪያ ያሉትን እጽዋት ቤተሰባቸውን አሁን ባለው ደረጃ እንዳውቅ ያደረገኝ ይህ ባህሪው ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የእጽዋት ዝርያና ቤተሰብ የማወቅ አቅማቸው የጎለበተው ሁኔታው ከልብ ኢትዮጵያዊ ስላደረጋቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
በዓለም ላይ እንሰትን፣ ጤፍን ምግብ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ ህብረተሰባችን እጽዋትን በተፈጥሮ ካሉበት ቦታ አንስቶ ወደ ቤት የማስገባት የደረጀ ባህል ባለቤት መሆኑን ያመላክታል። ህብረተሰቡ የጠነከረ ነባር እውቀትም ያለው እንደሆነ እንረዳለን። እናም የእጽዋት ተመራማሪ ሲኮን ጎን ለጎን ይህንን ማወቅ ያስችለናል። በአገሪቱ ውስጥ ብቻ የሚበቅሉ እጽዋት ሲለዩ ያንን ባህል እንድናመጣ ያደረገንና ህዝቡን እንድናድነው፤ ውስጡን እንድናውቀው ይሆናል። ስለዚህ እኔም በእጽዋት ፍቅር የተነደፍኩትና ከዚያ እንዳልወጣ ያገዘኝና ያስገደደኝ ይህ ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከመሬት በታች እንደዳሎል አይነት ጥልቀት ያለባቸው ቦታዎች ያሉባት፤ በከፍታም እንደራስ ዳሸን አይነት ተራራማ ቦታ የበዛባት ሀገር ነች። ይሄ ደግሞ ከመሬት በላይም ሆነ በታች በእጽዋት ሀብታም ሊያደርገን የሚችል የተፈጥሮ ጸጋ እንዲኖራት አድርጓታል። ከዚያ በተጨማሪ ከኡጋዴን እስከ ራስ ዳርጌ ሲታሰብ በዝናብ፣ በመሬት አቀማመጥና በአፈር ሁኔታ የተሻለ የእጽዋት ዝርያ ባለቤትም ነች። ይህ ደግሞ የብዝሀ እጽዋት ባለቤት መሆናችንን በሚገባ ያሳየናል። ይሁን እንጂ የመጠቀሙ ሁኔታ የሚያስደስት እንዳልሆነ ይናገራሉ።
አሁን ባለው ደረጃ በኢትዮጵያ ባሉት አካባቢዎች ሁሉ የሚበቅሉና በስፋት የሚገኙ እጽዋት የትኞቹ እንደሆኑ በመጽሐፍ መልክ ተጽፎ የሚገኝ ስለሆነ እርሱን መጠቀም ለህይወት እንደሚበጅ የማነሳውም ለእጽዋት ካለኝ ፍቅር አንጻር ነው። በስራዬ ሁሉ ውጤታማ ለመሆን ከሰዎች ጋር መስራትን የምፈልገው፤ ብዙ ተማሪዎቼ ከእኔ ልቀው እንዲወጡ የምሻው ከእጽዋት ባገኘሁት ልምድ ነው ይላሉ።
የጸና የሥራ ላይ ቆይታ
ብዙውን የሥራ ዘመናቸውን ያሳለፉት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይወጡ ነው። አሁንም በእዚያው እየሰሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ለሁለት ዓመታት ብቻ የጉለሌ እጽዋት ማዕከልን በዳይሬክተርነት አስተዳድረዋል። ከዚያ ውጪ የሥራ ዘመናቸው በሙሉ በማስተማር ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ደግሞ ጥሩና ተዋቂ ተመራማሪ አድርጓቸዋል። ባካሄዱት ሳይንሳዊ ምርምርም እጽዋት በሰዎች ሕይወት ላይ ያላቸውን ጥቅም ማሳየት ችለዋል። በተለይም በአገር በቀል እጽዋት ላይ ያዘጋጁት ሥራ ለየአካባቢው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።
በሥነ እጽዋት ምርምር ለዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት የበቁት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ እጽዋት መልክአ ምድራዊ ሥርጭት፣ ዓይነትና መጠንን በጥልቀት የሚፈትሽ ጥናት ሠርተዋል። ከዚያ በተጨማሪም በግላቸውና በጋራ ከሠሯቸው ከብዝሀ ሕይወት ጋር የተያያዙ የምርምር መጻሕፍት መካከል “Aloes and Other Lilies of Ethiopia and Eritrea”፣ “Aromatic Plants of Ethiopia”፣ “Atlas of the Potential Vegetation of Ethiopia”፣ “Ethiopian Orchids”፣ “Field Guide to Ethiopian Orchids” ይገኙበታል።
ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ እኤአ ከ1996 እስከ 2009 ድረስ በኢትዮጵያና በኤርትራ እጽዋት ላይ የተደረገን የ17 አገራት ተመራማሪዎችን ያሳተፈውን ፕሮጀክት በመምራት አገልግለዋል። በዚህ ሥራቸው ወቅት በተለይ በመጥፋት ላይ ያሉ እጽዋትን ከማሳወቅና ከመታደግ አኳያ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል። ስድስት ሺ የእጽዋት ዝርያዎችን በተደራጀ መልኩ በመሰነድና መረጃ በመስጠት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ከአፍሪካና አውሮፓ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በርካታ ውጤታማ ምርምሮችን ያደረጉ ናቸው።
“Evoiution in Afro alpine Environment ” በሚል በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሀገር በቀል ሰብሎች ዙሪያ ያደረጉት ምርምር በብዛት የሚጠቀስላቸው እንግዳችን፤ በግላቸውና ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር በመተባበር የኢትዮጵያና የአፍሪካ እጽዋትን በተመለከተም መጽሐፍ ጽፈዋል። የተለያዩ ጽሁፎችን በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ አሳተመዋል።
‹‹ስለ እጽዋት ግድ አለኝ›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ ለብዝሀ ሕይወት ልማት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ጭምር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ይናገራሉ። እጽዋቶች አሉን ማለት አንራብም፤ ሀኪም አያስፈልገንም፤ አንታመምም፤ አንራቆትም። ስለዚህ ትኩረት ለእነዚህ ሀብታችን ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
ሽልማት የአምናውን ብቻ እንኳን ብናነሳ ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው የሽልማት ድርጅት እነ ቻርለስ ዳሪዊን አይነት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የመሰረቱት ‹‹ፎሬን ሜንበር ኦፍ ዘሩያል ሶሳይቲ›› የሚባለው ድርጅት በአፍሪካ የመጀመሪያው አድርጎ የአባልነት ፊርማቸውን እንዲያኖሩ መርጧቸዋል። ከዚህ ሽልማት በኋላም የአፍሪካ የወደፊት ሳይንቲስቶችን የሚመለምል ቡድን ውስጥ ተካተው እንዲሰሩ ተመርጠዋል። ይሁንና ከበጎ ሰው ሽልማት የሚበልጥባቸው አንዳች ነገር እንደሌለ ይናገራሉ። ሽልማቱ የረካሁበት፤ የቀናሁበትና የበለጠ እንድሰራ አደራ የሰጠኝ ነው ይሉታል። ምክንያታቸው ደግሞ ሽልማቱ የአገራቸው ልጆች የሰጧቸውና አገራዊ ስሜትን የፈጠረባቸው ስለሆነ ነው።
‹‹ዓለም አቀፍ እውቅና ዓለም ላይ የሚቀር ነው። የትም ቢሄድ የምመሰገንበትና ይህንን ሰርቶልናል ሊባል የሚችልበት ነው። ከዚያ ውጪ የሚኖረው ዋጋ የለም። የእኔ የሆነውን ህብረተሰብ የማስተማር ሀይልም አይኖረውም። ማን እንደእናት እንደሚባለው ከቅርበቱ አንጻር ሲታይ የዓለም አቀፉ እውቅና ይርቅብኛል። የበጎ ሰው ሽልማት ግን የእኔ፣ የአገሬና የቤተሰብ ጉዳይ ስለሆነ ማንም አይተካውም።›› ይላሉ ስለ ሽልማቶቻቸው ሲያወሱ።
እጽዋት የመሰረተው ቤተሰብ
ከዛሬዋ ባለቤታቸው ጋር የተገናኙት ባለቤታቸው ተማሪ እርሳቸው ደግሞ ተማሪም ሰራተኛም በነበሩበት ወቅት ነበር። ቅመማ ቅመም ድርጅት ላይ መስራት ስትጀምር እርሳቸው ደግሞ የእጽዋት ምርምር ላይ ይሰራሉ። እናም ኬሚስቷ የዛሬዋ ባለቤታቸው እንዴት ከእጽዋት ቅመሞችን ማዘጋጀት እንደሚቻል ለመማር ወደእርሳቸው ትመላለሳለች። ፕሮፌሰሩ ደግሞ ከልባቸው የጠየቀቻቸውን ያደርጉላታል። በዚህም ቅርርባቸው ይጠነክርና ልባቸው ይሸነፋል። እናም ጊዜ ሳያጠፉ ይጠይቋታል።
እርሷም ብትሆን ልቧ ተቀብሏቸዋልና እሽታዋን ትንሽ ካንገራገረች በኋላ ቸረቻቸው። ፍቅር ጠነከረና ጋብቻው ተመስርቶ። 30 ዓመታትን ያለምንም ግጭት ዘለቀ። በእነ ፕሮፌሰር ቤት ያላደገ የሁለቱም ቤተሰብ የለም። ብዙዎችን አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል። ግን በቤት የሚቦርቅ ልጅ ሊታደሉ አልቻሉም። ያልተሞከረ ነገር የለም ያው አምላክ ካልፈቀደ አይሆንምና መቻሉ ግድ ሆኖባቸው ኑሯቸውን በፍቅር መምራቱን ቀጠሉ።
የልጅ አለመኖር አንድም ቀን አጣልቷቸው እንደማያውቅ የሚያነሱት እንግዳችን፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን ይላሉ። ቤተሰብም ሆነ ወዳጅ ዘመድ የልጅ ጥያቄ ሲያነሱባቸውም ሲፈቅድ ይሆናል ሲሉ ይመልሳሉ። ይህንን ማድረጋቸው ደግሞ የበለጠ እንዳበረታቸው አጫውተውናል።
‹‹ባለቤቴ ዛሬም እንደአዲስ ፍቅረኛዬ ናት። ፍቅር የያዘኝ ጊዜ እንዳየኋት ዛሬም እሳሳላታለሁ። ስበላም ስጠጣም ለእርሷ ነግሬ ነው። ከጓደኛም ጋር የማመሽ ከሆነ ለእርሷ መናገር ግዴታዬ እንደሆነ አስባለሁ። እርሷም እንደእኔ ይሰማታል። ስለዚህ ልጅ ባይኖረንም በፍቅራችን ጸንተን 30 ዓመታትን አሳልፈናል›› ይላሉ። ለዚህ መሰረቱ ደግሞ እርሳቸው ፕሮፌሰር እርሷ ደግሞ ዶክተር መሆናቸው ነው። የፕሮፌሰርና የእውቋ ኬሚስት ዶክተር ንግስት አስፋው ቅርርብ በቤት ውስጥም እንዳለ ነው። ለዚህም ማሳያው በሙያቸው አገርን ለማገልገል በተግባር ከሚሰሩት ውጪ በመጽሐፍ ሰንደው ለማስተማር የሚችሉበትን ‹‹መአዛማ ዘይት የሚሰጡ እጽዋት በኢትዮጵያ›› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትመው ለንባብ ማብቃታቸው ነው።
መልዕክተ ሰብስቤ
‹‹ሰዎች ስለእኔ ሲናገሩ አገሩን የሚወድና ለአገሩ የሚሰራ ቢሉኝ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም እኔ አገሬን የማየው እንደራሴ ነው። ብዙ ሀብት ያለባት ግን ባግባቡ ሀብቷን ያላየንባት መሆኗ ያሳዝነኛል። ስለዚህም የአገሬ ልጅ በማንኛውም ቦታ ልቆ እንዲወጣ እሻለሁ። ብቸኛ አፍሪካዊ ነህ ተብዬ የአባልነት ሽልማት ሲበረከትልኝ እንኳን ለምን የሚል ነገር ተፈጥሮብኛል። በቅርቡ የአፍሪካ የወደፊት ሳይንቲስቶችን ለመምረጥ ስታጭና የተሳተፉትን ስመለከት ኢትዮጵያ የለችም። ስለዚህ አስተባባሪውን ጠይቄ ጥያቄው ለአገሪቱ እንዲመጣም አድርጊያለሁ። ይህን ያልኩት ደግሞ ታሪኬን ለመዘርዘር ሳይሆን ሁላችንም በሰፈር ሳይሆን በአገር ከዚያም አልፈን በአህጉርና በዓለም ደረጃ ከፍ ማለትን እንዳለብን ለማስገንዘብ ስለምፈልግ ነው›› ይላሉ።
‹‹ለእኔ ሰፈር ሳይሆን ኢትዮጵያ ሲባልም ይጠብብኛል። ምክንያቱም እኛ ተምሳሌትነታችን ለዓለምም ጭምር መሆን አለበት። ስለዚህ ጠባብነት ከአዕምሯችን ተወግዱ ምሳሌነታችን ለዓለም ብርሃን መሆንን እንመኝ›› ሲሉ የሚመክሩት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ ለህብረተሰቡም ሆነ ለአገር በሚደረገው ሥራ ላይ ማንኛውም ዜጋ ሰፈሬ ሳይል መሳተፍና ያለውን እውቀት ማጋራት አለበት። ምክንያቱም አገር ሲያድግ ሰፈርም ሆነ ግለሰብ አብሮ ከፍ ይላል። ስለዚህም ሰዎች ቢሆኑ የምመኘው ለአገራቸው የሚቆጥቡት እውቀት የሌላቸው እንዲሆኑ ነው። ‹‹እኔ ለአገሬ እስከህይወት መስዋዕትነት ብጠየቅ አደርጋለሁ። ለአገሬ የምቆጥበው ምንም አይነት እውቀት እንዲኖረኝም አልፈልግም። ምክንያቱም ሳካፍል አገኛለሁ፤ አድጋለሁ፤ እደሰታለሁም። ›› ይላሉ።
ዛሬ በጎ ነገር አድራጊ መሆን ያስፈልጋል። ምክንያቱም የሰማይ ቤት ባይሳካ በምድሩ ደግነት ይልቃል። መማሪያ የመሆንንን አቅምም ይፈጥራል። እናም ኢትዮጵያ የጎደላት ነገር የለምና የሌላትን ለመሙላት መጣጣር ላይ መስራት ይገባል። መተጋገዝና መከባበራችንን ማስፋት፤ የእኔ የሚለውን የጽንፈኛ አመለካከታችንን ማጥፋትና በህብረት ማደግን ብቻ ማንገብ አለብን። አገራችን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር መበልጸጊያ እንደምትሆን ማመን ይኖርብናል ብለዋል።
ትውልድ ትውልድን በጎ ነገር በማስተማር መገንባት አለበት፤ ወደ ስድስት ሺ የእጽዋት ዝርያዎች በኢትዮጵያ አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አስር በመቶ የሚሆኑት በብቸኝነት ይገኛሉ እና ይህንን ብርቅዬነታችንን ልንጠብቀው ይገባል ሲሉ ይመክራሉ። እኛም ከምክሩ እናትርፍ በማለት በዚህ ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው