ይኸ ዘገባ ሰሞኑን ቢቢሲ አማርኛ የሰራው ነው። “ባለፉት ሰባት ወራት ለሥራ ወደ ሊባኖስ ካቀኑ ኢትዮጵያውያን መካከል ሰላሳ አራቱ በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸውን እንዳጡ በሊባኖስ ያሉ የኢትዮጵያውያንና ሌሎች የበጎ አድራጎት ማህበራት ይፋ አደረጉ” ይላል።
“ለኢትዮጵያውያኑ ህይወት መጥፋት እንደምክንያት የሚጠቀሰው በአሰሪዎቻቸው በሚፈጸምባቸው አሰቃቂ ግፍና ጥቃት ሳቢያ ራሳቸውን በማጥፋት እንዲሁም ካሉበት ኢሰብዓዊ የስቃይ ኑሮ ለማምለጥ በሚያደርጉት ትግልና ጥረት እንደሆነም ተገልጿል።
ይህ ይፋ የሆነው በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየገጠማቸው ያለውን አስከፊ ችግር በተመለከተ “መንግሥት የኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ሞትና ስቃይን ለማስቆም” አፋጣኝ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድ በጠየቁበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ላይ ነው።…”
እንዲህና መሰል ጥቃቶች በየዕለቱ የሚሰሙ ግን ብዙም ትኩረት ያልሰጠናቸው ናቸው። የሥራ ስምሪቱ በአብዛኛው በሕገወጥ መንገድ የተካሄደ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ከታወቀው ይልቅ ያልታወቁ ችግሮችም በባሰ ደረጃ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። እ.ኤ.አ በ2015 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን በኩል እንደወጣ የሚነገርለት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሪፖርት እንዲህ ይላል።
“ኢትዮጵያ ለግዳጅ ሥራ እና ለወሲብ ንግድ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተዳረጉ ወንዶች፣ሴቶች እና ሕፃናት መነሻ፤ በተወሰነ ደረጃም መዳረሻ አገር ናት። ከኢትዮጵያ የገጠር አካባቢዎች የሚወጡ ወጣት ሴቶች፤ በአገሪቱ ውስጥ በቤት ሠራተኝነት እና፣ አልፎ አልፎም፣ በሴተኛ አዳሪነት ይበዘበዛሉ፤ ወጣት ወንዶች ደግሞ በባህላዊ ሽመና፣ በእረኝነት፣በጥበቃ እና በጎዳና ላይ ንግድ በግዳጅ እንዲሠሩ ይደረጋሉ። አዲስ አበባ የሚገኘው ዋና የገበያ ማዕከል ከአፍሪካ ቀዳሚው የወሲብ ንግድ ቤቶች መገኛ ሲሆን ዕድሜያቸው እስከ 8 ዓመት የሚሆኑ ልጃገረዶች በነዚህ ቤቶች በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተዋል።
ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች ከኢትዮጵያ ውጪም በተለይ ጂቡቲ፣ደቡብ ሱዳን እና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ በቤት ሠራተኝነት እና በሴተኛ አዳሪነት እንዲሰሩ ይገደዳሉ፤ ኢትዮጵያውያን ወጣት ወንዶች ደግሞ ጂቡቲ ውስጥ በሱቅ ሰራተኝነት፣ በተላላኪነት፣ በቤት ሰራተኝነት፣ በስርቆት እና የጎዳና ልመና ላይ እንዲሰሩ ይገደዳሉ። ወጣት ወንዶች ከኢትዮጵያ ገጠር አካባቢዎች የተሻለ ሕይወት እንደሚገጥማቸው ቃል እየተገባላቸው በስፋት ይመለመላሉ። ለዚህም ምክንያቱ በመካከለኛው ምሥራቅ ር ካሽ ጉልበት ስለ ሚፈለግ ነው።
ባለሥልጣናት በህጋዊ መንገድ በቀን እስከ 1 ሺ 500 የሚሆኑት እንደሚወጡ ሪፖርት አድርገዋል። በርካታ ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሲሰደዱ ጂቡቲ፣ ግብጽ፣ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ኬንያን እንደመሸጋገሪያ ይጠቀማሉ። ከነዚህ አንዳንዶቹ ሊሄዱ ካሰቡበት አገር ሳይደርሱ እንደመሸጋገሪያነት ባረፉበት አገር ተይዘው ለብዝበዛ፣ለእስራት፣ለግዳጅ ሥራ እና ለመታገት ይዳረጋሉ። በደቡብ ኢትዮጵያ አድርጎ ወደ ደቡብ አፍሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚጋዙ፤እንዲሁም ቀይ ባህርን በጀልባ አቋርጠው የመን ሊገቡ ሲሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚሞቱ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች ቁጥር እያደገ መጥቷል። ከነዚህ አብዛኛዎቹ በህገወጥ ስደት ወደነዚህ ማዳረሻዎች ሲያቀኑ ለህገወጥ ዝውውር ይዳረጋሉ።
ወጣት ሴቶች በመካከለኛ ምሥራቅ ፣ በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ለቤት ሠራተኝነት ይዳረጋሉ። በመካከለኛው ምሥራቅ በቤት ሠራተኝነት የተሰማሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት፣ ደመወዝ ክልከላ፣ የእንቅልፍ መነፈግ፣ የፓስፖርት መያዝ፣ በቤት ውስጥ መታገት እና ግድያን ጨምሮ አስከፊ ጥቃቶች ይደርሱባቸዋል። ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሥራ ፍለጋ ሲሰደዱ ወይም በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚበዘብዟቸው ቀጣሪዎች ለማምለጥ ሲሉ አንዳንዴ የህገወጥ የወሲብ ንግድ ሰለባ ይሆናሉ።
በቂ የሙያ ክህሎት ሳይኖራቸው ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ የባህረ-ሰላጤው አገሮች እና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ወንዶች አንዳንዶቹ በእነዚህ አገራት ለግዳጅ የጉልበት ሥራ ይዳረጋሉ። በወረዳ ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት ጉቦ ተቀብለው በወረዳ በሚሰጡ የመታወቂያ ወረቀቶች ላይ የህፃናትን ዕድሜ እንደሚቀይሩ፤ህፃናት ያለወላጅ ፈቃድ ፓስፖርት እንዲወጣላቸውና ህገወጥ ሥራ ላይ ለመሰማራት ሀገር ለቀው እንዲወጡ እንደሚያደርጉ ሪፖርቶች አመልክተዋል። ”
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ዓይነቱ ስር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ አንድ አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱ ከሰሞኑ ተሰምቷል። በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እየተረቀቀ የሚገኘው ረቂቅ ሕግ ይዘት እነሆ በአጭሩ ቀርቧል።
በሰዎች የመነገድ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ህገ-ወጥ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ይዘት በአጭሩ
በሰዎች የመነገድ ወንጀል በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም የብዝበዛ ወንጀል ሲሆን፣ በዜጎች ላይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚፈጸም ድርጊት ነው። ይህ ወንጀል በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ሲሆን አስከፊም ነው።
ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል የአገርን ድንበር ከሚፈቀደው ሥርዓት ውጭ በሆነ መልኩ ማቋረጥ እንዲሁም በአገር ውስጥ መቆየትን የሚመለከት ወንጀል ሲሆን በዋናነት የሚፈጸም የአንድ አገርን የኤሚግሬሽን ህግን በመጣስ ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እነዚህ የወንጀል ተግባራት በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች እና በተናጠል የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች የሚፈጸሙ እና በዓመት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸው፣ በሰው ልጆች ስቃይና ደም ከፍተኛ ጥቅም የሚታፈስባቸው አደገኛ ወንጀሎች ናቸው።
ዜጎቻችን በውጭ አገር ለብዝበዛ እንዲጋለጡ ከሚያደርጉ ምክንያቶቹ ውስጥ አንዱ ለተሻለ ሥራ ፍለጋ የሚያደርጉት ጥረት ነው። የተሻለ ሥራ ፍለጋ ወይም ሥራ ፍለጋ ገፊ ምክንያት ሆኖ ዜጎች ወደ ሌላ አገር እንዲፈልሱ ሲያደርግ ይህንን ተጋላጭነት በመጠቀም ለሥራ ወደ ውጭ አገር የመላኩን ተግባር በህገ ወጥ መንገድ የሚያከናውኑ ተዋናዮች ተፈጥረዋል::
ረቂቅ አዋጁ “በሰዎች የመነገድ፣ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና ህገ-ወጥ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ ረቂቅ አዋጅ የሚል ስያሜ የተሰጠው ከላይ እንደተጠቀሰው ሶስቱ ወንጀሎች ተያያዥ በመሆናቸው ነው።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ያወጣውን በሰዎች መነገድ በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት እና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባት ለመከላከል የወጡትን ፕሮቶኮሎች እንደቅደም ተከተላቸው በአዋጅ ቁጥር 737/1999 እና 736/1999 የማስፈፀም ስልጣኑን ለቀድሞው ፍትህ ሚኒስቴር ለአሁን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 መሰረት ሰጥታለች።
ኢትዮጵያ እነዚህን ፕሮቶኮሎች ከማጽደቋ በፊት በኢፌዴሪ ወንጀል ህግ በቂ ባይባልም ወንጀል በማድረግ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማድረግ ተሞክሯል። ፕሮቶኮሎቹን ካጸደቀች በኋላም የተጣጣመ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ አዋጅ ቁጥር 909/2007ን አውጥታለች። ሆኖም ከችግሩ ስፋት፣ ጥልቀት እና ውስብስብነት አንጻር እነዚህ የህግ ማዕቀፎች በሚፈለገው ደረጃ ምላሽ መስጠት የሚችሉ አልሆኑም።
ስለሆነም ይህንን ረቂቅ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶችን ስንመለከት በሰዎች የመነገድ ወንጀል በተለይም የሴቶችና ሕጻናት ዝውውር፣ ሰዎችን በሕገ- ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የነበረው የህግ ማዕቀፍ ክፍተት ያለበት እና ችግሩን በሚፈለገው ደረጃ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ባለመሆኑ፤የህግ ማዕቀፉ ክፍተት መኖር እና የተጠናከረ አፈጻጸም ባለመኖሩ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደዱ እና እየተባባሱ፣ ዜጎችን ለአስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ እንግልትና ግፍ እየዳረገ መሆኑን በመረዳትና ችግሩን ለመፍታት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ የህግ ሥርዓቱ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የተጣጣመ፣ ነባር ህጎች የነበረባቸውን ክፍተቶች የሚያስተካክል እና አፈጻጸሙ የተሳለጠ መሆን እንዲችል ስርዓት የሚፈጥር የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ ነው።
በተጨማሪም በወንጀሉ ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች ጥበቃ፣ እንክብካቤና መልሶ ማቋቋም ሊደረግለት እንደሚገባ በመገንዘብ እና ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዕድሜያቸውን፣ ጾታቸውንና ልዩ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ የተለየ ጥበቃ፣ እንክብካቤና ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ መሆኑና ለዚህም ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ በመሆኑ፣ እና ወንጀሎቹን በአገር አቀፍ ደረጃ መከላከል እና መቆጣጠር የሚያስፈልግ በመሆኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያስተባብር እና አፈጻጸሙን የሚከታተል አካል ግልጽ ኃላፊነት እና ተግባር መስጠት ያስፈልጋል።
ይህን አካል በህግ በማደራጀት ወንጀሉን መከላከል እና መቆጣጠር እንዲችል ወጥ የሆነ ሥርዓት እንዲፈጠር በህግ አስፈላጊው ሥርዓት መፍጠር ከማስፈለጉ በተጨማሪ እነዚህ ወንጀሎች ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች ያላቸው በመሆኑ ቀጥታ ወንጀሎቹ እንዳይፈጸሙ መከላከሉ እና ወንጀል ፈጻሚዎችን በመቅጣት መቆጣጠር የሚቻል አይሆንም። ስለዚህ ገፊ ምክንያቶች ሊቀረፉ የሚችሉበትን ስርዓት በመፍጠር የወንጀል መከላከሉ ሂደት ወንጀሉ ከመጀመሩ ወይም ከመጠንሰሱ በፊት መግታት ያስፈልጋል። ይህም የአገር ውስጥ መፈናቀልን፣ ፍልሰትን እና የሥራ ዕድል ፈጠራ የተመለከቱ የፖሊሲ፣ የህግ እና የስትራቴጂ ማዕቀፎች ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንጻር እርስ በርሱ ሊመጋገብ በሚችል መልኩ ማውጣት እንዲቻል ሥርዓት መፍጠር በማስፈለጉ አዋጁ ተዘጋጅቷል።
ረቂቅ አዋጁ በሰባት ክፍል የተደራጀ እና 58 ድንጋጌዎችን የያዘ ነው።
በውስጡ ስለ ብዝበዛ፣ በሰዎች የመነገድ ወንጀል፣ በሌሎች የዝሙት አዳሪነት መጠቀም፣በህገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገር፣ህገ-ወጥ የውጭ አገር የስራ ስምሪት፣ወንጀል አለማሳወቅ፣ ማስረጃ ማጥፋት፣ ንብረት መሰወር እና የድርጅት ተጠያቂነት፣ የወንጀል መከላከል፣ ምርመራ እና ንብረት መውረስ፣የተጎጂ ጥበቃ፣ መልሶ ማቋቋም እና ካሳ፣ ፈንድ መቋቋም ፣ስለብሔራዊ ምክር ቤት፣ የተቋማት ሚና እና ትብብር የተቋማት ሚና ዓለም አቀፍ ትብብርና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን አካቷል።
እንደመውጫ
የተመድ ሪፖርት መፍትሄ ያለውንም ሰፊ ሀሳብ አንስቷል። በኢትዮጵያ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም የሚረዱ የመፍትሄ ሐሳቦች መካከል ሕገወጥ ቅጥር ፈጻሚዎችን መቅጣት በሚቻልበት መልኩ የሥራ ቅጥር አዋጁን ማሻሻል እንደሚገባ ያስቀምጣል። እንዲሁም በውጭ አገራት ሥራ የሚያስቀጥሩ ኤጀንሲዎች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር ማጥበቅ፤የቅጥር ውሎችን የሚያፀድቁ ኃላፊዎችን ግንዛቤ ለማሳደግ መደበኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሥልጠና ሥርዓት መዘርጋት ወይም ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን መቆጣጠር፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ለተዘረዘሩ ለወሲብ ንግድና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች የተቀመጡትን ቅጣቶች ማክበድ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 597 እና 635ን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ግልፅ ትርጉም ባካተተና ወንድ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ራሱን በቻለ አንቀጽ በሕጉ እንዲሸፈኑ በሚያደርግ መልኩ ማሻሻል ያስፈልጋል ይላል።
እንዲሁም ቅጣቶችን በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ላይ ከሚጣሉ ቅጣቶች ጋር እንዲጣጣሙ በሚያደርግ መልኩ ማሻሻል፤ በመላ ሀገሪቱ የፖሊስን የወንጀል ምርመራ አቅም ማጎልበት በአገር ውስጥ የሚፈፀመውን ህገወጥ የሕጻናት ዝውውር ወንጀል ፈጻሚዎችን (ባለስልጣናትን ጭምር) ለሕግ ማቅረብ፤በጉልበት ብዝበዛ እና በወሲብ ንግድ ዓላማ የሚካሄዱ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን ለመቅጣት የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን አንቀጾች 596፣597 እና 635 ይበልጥ በተግባር ላይ ማዋል ይገባል።
ብሔራዊ መታወቂያዎች እና ፓስፖርቶች በሚሰጡበት ወቅት የሚከናወነውን የማጣራት ሥራ በማሻሻል ሕጻናት አጭበርብረው እነዚህን ሰነዶች እንዳላገኙ ማረጋገጥ፤በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚተዳደሩ የሰለባዎች መጠለያዎች ያልተቋረጠ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጀት መመደብን ጨምሮ ከስደት ለሚመለሱ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ደረጃ ለማሳደግ ከአገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ መሥራት ተገቢ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ውስጥ የሠራተኞች ጉዳይ አታሼዎችን መመደብ እንዲቻል አስፈላጊውን በጀት መያዝ፤ በውጭ አገራት ለሚሾሙ ዲፕሎማቶች እና የሥራ ቅጥር ውሎችን ሕጋዊነት ለሚያረጋግጡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ የሥራ ኃላፊዎች ስለ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መደበኛ ሥልጠናዎች መስጠት ይገባል። በውጭ አገራት ተቀጥረው ለመስራት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ከለላ መስጠት፤ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና ሌሎች አገራት ለሚጓዙ ስደተኛ ሠራተኞች በሚሰጠው የቅድመ ጉዞ ሥልጠና ውስጥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና የሠራተኛ መብትን የሚመለከት መረጃ ማካተት ያስፈልጋል። ”
ከእነዚህ ወሳኝ የመፍትሔ ሀሳቦች አንጻር አዲሱ “በሰዎች የመነገድ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ህገ-ወጥ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ” ምን አቅም ይኖረው ይሆን የሚለው ጥያቄ በሒደት የሚታይ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012