ልጅነቱን እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ሲያሳልፍ በባህሪው ከሌሎች ይለይ ነበር። ረባሽነቱ፣ ተንኳሽነቱና ተደባዳቢነቱ ለብዙዎች ፈተና ሆኖ ቆይቷል። ያም ሆኖ በትምህርት ቤት ውሎ ቀለም ቆጠሮ ይመለሳል። ወላጆቹ የእሱን ተምሮ መለወጥ ይሹ ነበርና የሚያስፈልገውን ከማሟላት ወደ ኋላ አላሉም።
ቤተሰቦቹ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እስኪያጠናቅቅ ተስፋ አልቆረጡም። ከፍ ማለት ሲጀምር ግን አስቸጋሪነቱ ገባቸው። ይህ ዕድሜው እንደልጅነቱ ከጉያው ገብተው በቁንጥጫ የሚመዘልጉት አልሆነም። ይህ ጊዜ አርጩሜ አንስተው የሚስፈራሩበትም አልነበረም። ልጃቸውን ሲቆጡት ቀድሞ የሚቆጣበት፣ ሲመክሩትም ሊዘልፍ የሚነሳበት አስቸጋሪ የእሳት ጊዜ ሆነባቸው።
ማሙሸት እንደ ልጅነቱ ማሙሽ መሆኑ ቢቀር ከዛሬ ነገ ይመለሳል በሚል በትዕግስት ጠበቁት። ፍቅር እየመገቡና በዝምታ አያለፉም ሊታገሱት ሞከሩ። በእሱ ዘንድ ለውጥ አልነበረም።
ሰባተኛ ክፍልን አልፎ ወደ ስምንተኛ ሲሻገር ለቀጣይ ትምህርቱ አዲስ ለውጥ ቢኖረው ሲሉ በተስፋ ጠበቁት። እሱ ግን ይህን ጊዜ ለሌላ ባህሪይ ተጠቅሞ መንገዱን ቀየረ። ካልተገቡ ባልንጀሮች ውሎም በሱስ ባህሪያት ተጠመደ። ይህ ሁሉ ሲሆን ወላጆቹ ከመማሩ ውጭ የሚያውቁት አልነበረም።
ዓመቱ አልፎ ጓደኞቹ ዘጠነኛ ክፍል ሲገቡ ወላጆቹ የእሱንም አዲስ ምዕራፍ ጠብቀው ጥያቄ አቀረቡለት። በሰዓቱ ከልጃቸው የተሰጣቸው ምላሽ ግን በእጅጉ አሳዛኝ ሆነ። ማሙሸት ትምህርቱን ያቆመው ገና በጠዋቱ ነበር።
ከዚህ በኋላ በልጃቸው ተስፋ የቆረጡት ወላጆች ዳግም ላያስቡት አይናቸውን ከዓይኑ አነሱ። እንዲህ መሆኑ ደግሞ በአፍላ እድሜ ላይ ለቆመው ወጣት መንገዱን አቀናለት። በሱስ ባህሪያቱ ገፍቶም ካሻው ባልንጀሮቹ ውሎ አደረ።
የልጅነቱ አስቸጋሪ ባህሪይ ያገረሸበት ማሙሸት የወጣትነት ጊዜው በግልፍተኝነት ተሞላ። በየምክንያቱ ከብዙዎች እየተጋጨም በየፖሊስ ጣቢያው መካሰስ ልማዱ ሆነ። በዋሰ ተለቆ ቀናትን ቢያሳልፍም ተመልሶ ለድብድብ መጋበዙ አልቀረም። ሁሌም ተፈናጣሪ ጩቤ ከጎኑ የማይለየው ወጣት በነገርና በድብድብ መታወቅ መለያው ሆኖ ቆየ። እንዲህ መሆኑ ታላቅ ድፍረት እየሰጠውም በድርጊቱ ገፋበት። በጠብ የቀረቡትን ሁሉ በጩቤው እያስፈራራ መቆየትን እንደስሙ ተቀበለው።
ማሙሸት ከብዙዎች እየተጣለ ሲደበድ ብና ሲደበደብ ቆይቷል። ኮሽ ባለበት እየደረ ሰም ለቡድንና ግላዊ ጠብ ጊዜውን ሰጥቷል። የየዕለት ህይወቱ መልካም በሚባል መንገድ አልተጓዘም።
አንድ ቀን የሆነው ደግሞ ከሌሎቹ ቀናት የከፋ ሆነ። ሁሌም በግርግር መሀል የማይታጣው ማሙሸት እንደተለመደው ስለታም ጩቤውን ከጎኑ ሽጦ ከቤቱ ወጣ። ወቅቱ ምርጫ ዘጠና ሰባት የሚካሄድበት ጊዜ ነበርና በየምክንያቱ ተቃውሞና ግርግር የማይለያቸው አካባቢዎች በዝተው ነበር።
ማሙሸት በስፍራው ሲደርስ በድንገት አንድን ሰው ተመለከተ። ከእሱ ጋር ከዚህ ቀድሞ በነበረው ጠብ ቂም ይዞበት ቆይቷል። አሁን ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ያሻውን ማድረግ ፈልጓል። ለዚህ ሀሳቡ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንደማይኖር እርግጠኛ ነው።
ይህን እያሰበ ከራሱ መከረ። ውስጠቱ እንደተለመደው ‹‹አይዞህ›› ሲል አጀገነው። ጊዜ አላጣፋም። ጩቤውን እንደያዘ ቀረበው። ሰውዬው ከጎኑ ቆሞ የሚቁነጠነጠውን አጥቂ አላየውም። ይህ መሆኑ ለማሙሸት አመቺ ሆነለት። በስለቱ ጎኑን ደጋግሞ ወጋውና ከአካባቢው ተፈተለከ።
የከፋ ጉዳት የደረሰበት ሰው ደሙን እያዘራ ከመንገዱ ሲዘረር ለነፍስ ያሉ ሀኪም ዘንድ ሊያደርሱት ተጣደፉ። ድርጊቱን ያስተዋሉ እማኞችም ከህግ ዘንድ ቀርበው እውነታውን አጋለጡ። ማሙሸት ከፖሊስ የፍለጋ ትዕዛዝ እንደወጣበት ሲያውቅ ራሱን ደብቆ ቆየ። ከቀናት በኋላ ግን በቁጥጥር ስር ውሎ በህግ ጥላ አደረ።
ህይወት በማረሚያ
የማሙሸት የወንጀል ድርጊት በበቂ ማስረጃዎች ሲረጋገጥ ፍርድ ቤቱ ይገባዋል ያለውን የአስራ አንድ ዓመት ጽኑ አስራት በይኖበት ከማረሚያ ቤት ገባ። የዝዋይ ማረሚያ ቤት ቆይታው ለወጣቱ እስረኛ ጸጸትን ከቁጭት እያቀበለ ወራትን አስቆጠረው። እያደርም የሰራውን ሁሉ እያሰበ መብሰልሰል ጀመረ። ወጣትነቱን የሚከፍልባቸው የእስር ዓመታትን በቆጠራቸው ጊዜም በትካዜ አንገቱን ደፍቶ በንዴት ጥርሱን ነከሰ።
ይህ ሁሉ ቁጭት ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ›› ሲሆንበት በድንገት ቢፈታ እንዴት እንደሚለወጥ እያለመ ውስጡን በምኞት አሰከረ። ድርጊቱ በአስራ አንድ የእስር ዓመታት እንዲቆይ ግድ እንዲለው በገባው ጊዜም ከዕድሜው ላይ ሰባት ዓመታትን ቆንጥሮ ቀሪውን አንድ ሁለት ሲል መቁጠር ያዘ።
ሰባተኛውን ዓመት እንደጀመረ ግን ለታራሚዎች የሚሰጠውን የአመክሮ ዕድል ተጠቅሞ ከእስር ሊለቀቅ መሆኑን አወቀ። ይሄኔ ልቡ በደስታ ተሞልቶ የነገውን በጎነት አሰበው። ባለፈበት መንገድ ዳግም እንደማይጓዝ ወስኖም ከራሱ ተማማለ።
ከእስር ሲፈታ ያለፈውን እያሰበ መቆጨቱ አልቀረም። ተመልሶ ቤቱ ሲገባ እንደልጅነቱ በፍቅር የተቀበሉት ወላጆቹ የራሱን ቤት አዘጋጅተው ቆዩት። ከሰባት ዓመታት በኋላ ከሌሎች መቀላቀሉን ሲያስብ ደግሞ ሁሉን ረስቶ እድለኝነቱን አመሰገነ ።
ሌላ መንገድ
ዋል አደር ሲል ማሙሸት ከቤት መውጣትና የቀድሞ ባልንጀሮቹን መፈለግ ጀመረ። ይህ አጋጣሚም የቀድሞ ውሎውን አስታውሶ ከሱስ መንደር ሊቀላቅለው ግድ ሆነ። ይህ መሆኑ ድብቅ ማንነቱ አገርሽቶ ከብዙዎች እንዲላተም ምክንያት ሆነው።
አንድ ቀን በድንገት ባስነሳው ድንገቴ ጠብ ከሰዎች ተጋጭቶ ለእስር ተዳረገ። ጉዳዩ በቀላል እንደማይፈታ የተረዱ የቅርብ ሰዎች ግን ከጠበኞቹ በይቅርታ አስማምተው የክስ ፋይሉን አዘጉለት። ማሙሸት ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ራሱን ከጠብ አርቆ በሰላም ለመኖር ሞከረ። የሴት ጓደኛ ይዞም ጥላቻን በፍቅር ለመተካት ወሰነ። ወደ ዱባይ እየወጣም መነገድን አወቀ።
አሁን የትናንትናው ጠበኛ ወጣት በሌላ የህይወት መስመር ላይ ቆሟል። ያለፈውን ማንነት ሰርዞ በአዲስ መንገድ ለመራመድ የሚያደርገው ሙከራም የሚሳካለት መስሏል። በፍቅር ህይወት አብራው የዘለቀችው ጓደኛው ወደ አረብ አገር በሄደች ጊዜ በእሱ ዘንድ የነበረው ሽኝት ከሌሎች የተለየ ነበር። ቃሉን ጠብቆ እንደሚቆያት ሲነግራት በተለየ አመኔታና በማይሻር መሀላ ሆነ።
ማሙሸት የፍቅር ጓደኛውን ወደ ውጭ ከላከ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት በብቸኝነት ቆየ። በወላጆቹ ቤት በተዘጋጀለት ክፍል እየኖረም በስልክ አይዞሽ ባይነቱን ገለጸላት። ጓደኛው የእሱን የተስፋ ቃል በሰማች ጊዜ ውስጧ በበጎነት ተሞልቶ የነገን ህይወት አሰበች። የሚኖረውን አብሮነት አልማም ለትዳር ጎጆዋ ተዘጋጀች።
ማሙሸት ግን ከቃል የዘለለ ቁምነገርን በውስጡ ማሳደር አልቻለም፤የጥቂት ጊዚያት ብቸኝነቱን ሽሮ በሌላ ማንነት ለመታየት ጊዜ አልፈጀበትም። ሚስጥሩን ደብቆ ሌላ የፍቅር ጓደኛ አበጀ። ለአዲሷ ሴት የቀድሞ ፍቅረኛው እሱን ትታ ወደ ውጭ ሀገር መሄዷን አሳምኖም ለፍቅር ጠየቃት። ይህ ስሜት የእሷ ጭምር ነበርና ያለማንገራገር ጥያቄውን በእሽታ ተቀበለች።
ማሙሸትና አዲሷ ጓደኛው አብረው መታየት ጀምረዋል። እሱ ከሁለቱም ሳይለይ እንዴት መቀጠል እንዳለበት የገባው ይመስላል። ውጭ ያለችውን በትዝታ፣ ከጎኑ የምትገኘውን በናፍቆት እያየ መኖሩን አውቆበታል። ዛሬም ቢሆን ዙሪያ ገባውን የማያምነው ወጣት ሁሌም ከጎኑ የሚሽጠውን ተፈናጣሪ ጩቤ ከአጠገቡ ማራቅ አይፈልግም።
ወጣ ብሎ በሚዝናናባቸው ስፍራዎች ሁሉ የጎኑን ሚስጥር አየነካ ባሻገር መቃኘቱን ልምድ አድርጓል። ዛሬም ቢሆን ይህ ስለት የህይወቱ መከታ የሆነ ያህል ይሰማዋል። በተለይ ደግሞ ከሴቶች አጠገብ በሆነ ጊዜ ጩቤውን በተለየ ጥንቃቄ ይዳስሰዋል።
አሁን ወጣቱ በሁለት ካርታ መጫወቱ የተሳካለት ይመስላል። ከውጭ በሚላክለት ገንዘብ ራሱን እየጠበቀ ሌሎችን በፍቅር ይማርካል። በአፉ እየደለለና በአጉል ቃላት እያሳመነም የማይጨበጥ ተስፋን ይገነባል። ከእሱ ጋር በፍቅር የዘለቀችው የአገር ቤቷ ወጣት እሱ የሚላትን አምና ለመቀበል ጥርጣሬው አልነበራትም።
ከቀናት በአንዱ ቀን ወደ ውጭ አገር ለስራ የሄደችው ሴት በድንገት ወደ አገር ቤት መጥታ ከእሱ መኖሪያ ደረሰች። በወቅቱ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ካለችበት ቦታ ሲቀበላት ደስታዋ ወሰን አልነበረውም። ማሙሸት አብራው ያለችውን ሴት ገሸሽ ብሎ ከአረብ ሀገር ከመጣችው ጋር ፍቅሩን ቀጠለ። ይህችኛዋን ስልኳን እየዘጋና ምላሹን እየነፈገም እንደማያውቃት ሆኖ ዘለቀ።
የሆነውን ሁሉ አንድም ሳይቀር የሰማቸው ሴት በየቀኑ እየደወለች የሚላትን ለመስማት ናፈቀች። ‹‹ይመጣል›› በሚል ተስፋም ያለመታከት ቀናትን ጠበቀች። አንድ ቀን ደግሞ ጥቂት ጊዚያትን አብራው ያሳለፈቸው የቀድሞ ፍቅረኛው ቤተሰቦችዋን ለመጠየቅ ራቅ ካለ ስፍራ ተጓዘች።
ሰኔ 5 ቀን 2007 ምሽት
ይህ በሆነበት ምሽት ደግሞ በድንገት የማሙሸት የእጅ ስልክ ጮህ። ይህን ቁጥር ከዚህ ቀድሞ ደጋግሞ ቢያየውም እንደ ሁልጊዜው ለማንሳት ደፍሮ አያውቅም። አሁን ግን ብቻውን ስለሆነና ነጻነት ስለተሰማው ያለምንም መደናገጥ ሀሎ! ሲል ምላሽ ሰጠ።
ከመስመሩ ጫፍ የፍቅረኛዋን ድምጽ በድንገት የሰማቸው ሴት ከሰላምታዋ ቀጥሎ እያደረገ ስላለው እውነት አንድ በአንድ ነገረችው። እሷን ትቶ ከቀድሞ ፍቅረኛው ጋር አዲስ ህይወት መጀመሩን ሰምታም ከልብ ማዘኗን በዕንባ አሳወቀቸው። ይህን የሰማው ማሙሸት እውነቱን ከማስተባበሉ በፊት የት እንዳለች ጠይቆ በፍጥነት እንዲገናኙ ለመናት። እሱ እንዲህ ባላት ጊዜም ሰዓቱ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ከሰላሳ እያለ ነበር።
በተቀጣጠሩበት የዘሪሁን ህንጻ አካባቢ ሲገናኙ ጓደኛው አዝናና ተከፍታ ነበር። በማሙሸት ፊት ላይ ግን ከወትሮው የተለየ ገጽታ አልተነበበም። ተያይዘው ወደአንዱ መጠጥ ቤት እንደገቡ ደግሞ ለመጨቃጨቅ ፈጠኑ። ባለመተማመን ጊዚያትን የፈጁት ጥንዶች ጭቅጭቃቸውን በመጠጥ እያዋዙ ሰአቱን ባለመስማማት ገፉት።
ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ከሰላሳ ሲሆን ግን አስቀድመው በነገር የተጣመዱት ጥንዶች ራሳቸውን ለመጠጥ አስገዝተው በስካር ናወዙ። በዚህ መሀል አንድ ሀሳብ ተነሳ። አዳራቸውን እሷ ቤት አድርገው ቀሪውን ጊዜ አብረው ለያሳልፉ ተነጋገሩ። ሁለቱም ተስማምተው ጉዞ ወደ ቤት ሲጀመር ደቂቃዎቹ ወደ ስምንት ሰዓት እያመሩ ነበር። የውስጥ አስፓልቱን ተጠቅመው ወደ ካዛንቺስ ሲያመሩ ማሙሸት ለሽንት ከአንድ አጥር ጥግ ቆመ።
ሰውዬው
ማሙሸት ጉዳዩን አጠናቆ ወደ መንገዱ ሲመለስ ጓደኛውን ከአንድ ወንድ ጋር ስታወራ ተመለከታት። ዓይኑን ባለማመንም ምንድነው ሲል አምባረቀ። ይሄኔ ፈጠን ብላ ለክፏት እንደሆነ ዋሸቸው። ንዴቱ እንደጋለ እጇን እየጎተተ የእሱ ፍቅረኛ መሆኗን ለማስረዳት ሞከረ። ቀጠል አድርጎም እያንገላታና እየሰደበ ማንነቷን በሚያዋርድ ስድብ ይወርድባት ያዘ።
ከመንገድ ዳር የቆመው ሰው የማሙሸትን ሁኔታ ሲያስተውል ከድርጊቱ እንዲታቀብ ሊመክረው ሞከረ፡፡ በሴት ልጅ ላይ ያልተገባ ስድብና እንግልት መፈጸሙም መልካም እንዳልሆነ ገለጸለት። ይህን ሲሰማ ማሙሸት የእሱን ወቀሳ ከስድብ ቆጥሮ ድብቋን ተፈናጣሪ ጩቤ አወጣ። በፍጥነት ተጠግቶም ሆድና ጎኑን ደጋግሞ ወጋው። የጨለማው መንገደኛ ከአስፓልቱ እንደተዘረረ ማሙሸት እግሬ አውጭኝ ሲል ተፈተለከ።
የፖሊስ ምርመራ
ገና በማለዳው መረጃ ደርሶት ከስፍራው የተገኘው ፖሊስ አንድ ግለሰብ በስለት ተወግቶ ህይወቱ ማለፉን አረጋገጠ። አስከሬኑን አንስቶ በቂ መረጃዎችን ከያዘም በኋላ ተጠርጣሪዎችን ለማግኘት አሰሳውን ቀጠለ። በመርማሪ ፖሊስ ኢንስፔክተር ሲሳይ ተሾመ የሚመራው ቡድን በመዝገብ ቁጥር 936/07 ላይ በየቀኑ የሚገኘውን መረጃ እየመዘገበ ለተጨማሪ መረጃዎች ተንቀሳቀሰ። ከተጠርጣሪው ጋር አብራ ትኖራለች የተባለችውን የቀድሞ ፍቅረኛውን ይዞም ለምርመራ ከማረፊያ ቤት አቆየ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ማሙሸት ስለሰውየው ሁኔታ የሰማው አልነበረም። በርካቶች በጥርጣሬ ተይዘው ሲጠየቁም እሱ ለሁለት ወራት ዱባይ ቆይቷል። አገር ቤት ተመልሶ እውነታውን ሲረዳም ራሱን ቀይሮና አድራሻውን ለውጦ ሱሉልታ ተደብቋል። ጥቂት ቆይቶ ደግሞ በመተማ በኩል ወደሱዳን ለመሄድ ፓስፖርት አወጣ። ባሰበው ቀን መንገድ ለመጀመር ሲዘጋጅ ግን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ። ማሙሸት ተይዞ ሲጠየቅ ሟችን ከዚህ ቀድሞ በመልክም ሆነ በስም እንደማያውቀው ተናገረ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2012
መልካምስራ አፈወርቅ