1ሳይንስ የእድገት ዋንኛ ማሳያና ማፍጠኛ የብልፅግ ጣሪያ መቃረቢያ መንገድ ነው። ሳይንስ ቀርቦ የማይለውጠው ተሳክቶ የማያስተካክለው ጉዳይ ማግኘት ይከብዳል። የምርምር ሥራ ችግርን መፍቻ ዋንኛ ተግባርና ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለምርምር ሥራዎች የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ ለመስራት ዋንኛ ምክንያትም ይሄው ነው። እንደሀገር ምርምር የፈጠራ ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሰራ ማለት የሀገሪ መፃኢ እድል የተቃና መሆኑን ማመላከቻ ሊሆን ይችላል።
ለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ለፈጠራና ምርምር ብሎም ለፈጣሪዎቹና ለተመራማሪዎቹ ምስጋና ይድረስና የሰው ልጆች በዘመን ሂደት የአኗኗር ዘይቤያቸው ተቀይሮ፤ ከዘመን ጋር ዘምነው፤ ከወቅቱ ጋር ተቀይረው ታላቅ ለውጥ ላይ ይገኛሉ። በጥናትና ምርምር መስክ በየጊዜው የሚገኙ የፈጠራ ሥራዎች ለሰው ልጅ ጤና መጠበቅ እና የተሻለ መሆን ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። በዚህም የተሻሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል። ከሰው ልጅ ጤና በላይ አሳሳቢ ጉዳይ በምድር ላይ የለምና ዛሬ ላይ በህክምናው ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ የምርምር ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በጤናው ዘርፍ በሀገር ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ሰፊ ሥራዎች በጥናትና ምርምር መታገዛቸው ውጤቱ የተሻለ እንዲሆን ያደርገዋል። በተለይ ሀገር በቀል የሆኑ ምርምርና ጥናቶች በችግሩ መነሻና አውድ ላይ የተመሰረቱ ስለሚሆኑ ለሚፈጠሩ የጤና ችግሮች ትክክለኛ መፍትሄ ሊያስገኙ የሚችሉ ናቸው።
ወጣቶች በጤና ሳይንስ መስክ ስኬታማ የሆኑ ሥራዎችን በመስራት ትልቅ እመርታ በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ። በዚህም አገራዊ፤ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎች በመስራት የስኬትን በር ማንኳኳት የጀመሩ ወጣቶችን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል። በጤና ዘርፍ ምርምሮችን በማድረግ ስኬታማ የሆነና በብዙ መድረኮች ሽልማትና እውቅናን ያተረፈች ወጣት የምርምር ሥራዋን በተመለከተ አነጋግረን በወፍ በረር ማስቃኘት ወደድን፤
ምህረት ይልማ ትባላለች። የባዮ ሜዲካል ኢንጂነርና የህክምና መሳሪያዎች ዲዛይነር ናት። በአሁኑ ወቅት በጅማ ዩኒቨርሲቲ በህክምና መሳሪያዎች ላይ ሁለተኛ ዲግሪዋን በመማር ላይ ትገኛለች። እንዲሁም የኤም ዋይ ሄልዝ ኢኖቬሽን መስራችና ባለቤት ናት። የፈጠራ ባለሙያና በምርምር ሥራዎቿ ታላላቅ ግኝቶችን ያበረከተች ትጉህ እና ታታሪ ወጣትም ናት።
የምርምር ሥራው መነሻ
ያኔ የሁለተኛ ዓመት የጅማ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ሜዲካል ኢንጅነሪንግ ተማሪ ነበረች። ለእረፍት ቤተሰብ ዘንድ በሄደችበት እናቷን ወደጤና ተቋም ለምርመራ ይዛ ትሔዳለች። እናቷ ሐኪም እስኪያያቸው የምርመራ ክፍሉ ኮሪደር ላይ ቆማ በመጠበቅ ላይ ሳለች ከጤና ተቋሙ አንደኛው ክፍል አንድ ድምጽ ትሰማለች።
ለሰማችው ድምፅ ምንነት ምላሽ ለማግኘት ወደሰማችበት አቅጣጫ ታመራለች። የእናትነት አንጀታቸው አልችል ብሎ የሚያነቡ የሞተ ህፃን ልጃቸውን እያዩ በሀዘን የሚወራጩ እናት፤ ሀዘን ተጭኗቸው እህ እያሉ የሚያለቅሱትን የህፃኑን አባት ትመለከታለች። ይህን አይታ ማለፍ ያልፈቀደችው ምህረት የጤና ባለሙያዎቹን ቀርባ ስለ ጉዳዩ ትጠይቃለች።
ልጁ የሞተው ህፃኑን ሊያድን የሚችል መሳሪያ ባለመገኘቱ እዚያ ቢኖርም ሊሰራ ባለመቻሉ እንደሆነ ስትረዳ እጅግ አዘነች። እናቷን ወደ ቤት ሸኝታ እዚያው የህክምና አገልግሎት መስጫ ሆስፒታል ውስጥ “አለ ግን አገልግሎት አይሰጥም። ” የተባለውን መሳሪያ ለማየት ትጠይቃለች። በመቀጠልም፤ የሆስፒታሉን አስተዳደር አናግራ ማስተካከል እንደምትችልና መሳሪያውን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ፍላጎት እንዳላት አስረድታ ፍቃድ ታገኛለች።
ሆስፒታሉ ውስጥ እያሉ ጥቅም መስጠት ያልቻሉ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በማስወጣት በወቅቱ ባገኘችው ውስንና ስለ መሳሪያው ባላት እውቀት ፈታ አስተካክላ ለአገልግሎት እንዲውል ማድረግ ቻለች። በዚህም የተደነቁት የሆስፒታሉ ሠራተኞች በመሳሪያው ሥራ ማቆም ይከሰት የነበረውን ሞት ማስቀረት በመቻሉ በእንባ የታገዘ ምስጋና ይቸሯታል።
እዚያው ለሁለት ወራት ቆይታ የህክምና መሳሪያዎቹን በማስተካከል ለራስዋም አዳዲስ እውቀቶችን በመቅሰም በመስኩ የተሻለ ግንዛቤን ማግኘት ቻለች። በዚህ አጋጣሚ አሳስቧት የነበረው የህክምና መሳሪያዎች አጠቃቀም ችግርና ዕጥረት ለመፍታት የበኩሏን ለማድረግና በዚህ ምርምሮችና ጥናቶችን ማድረግ ጀመረች።
የፈጠራ ሥራዋ ምንነት ፡-
የፈጠራ ባለሙያዋ ምህረት የ2011 ተሸላሚ የሆነችባቸው የፈጠራ ሥራዎች በቁጥር ሁለት ናቸው። አንደኛው የቲቢ (የሳንባ ነቀርሳ) ባክቴሪያ ከአየር ላይ ሰብስቦ የሚገድል መሳሪያ ሲሆን፤ የቲቢ ባክቴሪያ ባለበት ክፍል ውስጥ እና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ የሚደረግና በአካባቢው ላይ ያለን የቲቢ ባክቴሪያ በመሰብሰብ ወደ ሌላ ሰው እንዳይተላለፍ የሚከላከል ነው።
ሌላኛው የፈጠራ ሥራዋ፤ ዘርፈ ብዙ የህፃናት ጤና መመርመሪያ መሳሪያ ነው። ይህም ህፃናት በአንድ መሳሪያ ብቻ የሙቀት መጠናቸውን፣ የደም ግፊት መጠናቸው፣ የአተነፋፈስ ሥርዓታቸውንና መሰል የጤና ሁኔታቸውን በማየት መከታተል የሚያስችል መሳሪያ ነው።
በፈጠራ ሥራው የተገኘ እውቅናና ሽልማት
የተመራማሪ ምህረት ይልማ የፈጠራ ሥራ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ2011 የፈጠራና የምርምር ሥራ ውድድር ላይ በልዩ ሁኔታ በመመረጥ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘላት ሲሆን፤ ከሀገር ውስጥና ከዓለም አቀር የጤና ተቋማት የተለያዩ እውቅናና የምስክር ወረቀቶችን አግኝታባቸዋለች። ከሀገር አልፋ በባህር ማዶ ጥሪ ቀርቦላት ሥራዎቿን የማስተዋወቅ እድል የገጠማት ወጣት ምህረት በአሜሪካ መንግሥት ጥሪ ቀርቦላት አሜሪካ ድረስ በመሄድ ሥራዎቿን የማቅረብና ለሥራዋ የሚጠቅማትን ስልጠና የማግኘት እድልም ገጥሟታል።
በምርምር ሥራው የገጠመ ችግር፡-
የምርምር ሥራ መስሪያ ቁሳቁስ አለማግኘት፣ የፈጠራና ምርምር ሥራ ማድረጊያ ቦታ ማጣት፣ ምርምሩ ታምኖበት ወደ ሥራ ተገብቶ ምርት ለማስጀመር የሚያስችል ገንዘብ አለመገኘት በተመራማሪዋ የተነሱ የምርምር ሥራና ውጤት አስቸጋሪ ፈተናዎች ናቸው። ለዚህም መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባም ጠቁማለች።
ቀጣይ እቅድ ፡-
በቀጣይ በሳይንስና ምርምር መስክ ጠንክራ በመስራት ሌሎች አዳዲስ የህክምና ቁሳቁሶችን ለማበርከት በዝግጅት ላይ መሆኗን የምትናገረው ትጉህዋ ተመራማሪ ምህረት በሶስት የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ላይ ጥናት አድርጋ የዲዛይን ሥራ በመስራት ላይ እንደምትገኝ ገልፃለች።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2012
ተገኝ ብሩ