የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት የሃገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ ማቀላጠፍንና ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ እንዲሁም ጂቡቲ የሚደረገውን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ማሳደግን በዋናነት ታሳቢ በማድረግ የተገነባ ነው። ከጥር ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
የባቡር ትራንስፖርቱ ላለፈው አንድ አመት ከስድስት ወር የወጪና ገቢ ምርቶችን ሲያጓጉዝ፤ መንገደኞችንም ሲያመላልስ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዴ በስርቆት ሌላ ጊዜ ደግሞ በአደጋ እየተፈነ ነው።
የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማህበር ወቅታዊ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል፣ እያጋጠሙት ያሉትን ችግሮች በምን መልኩ እየፈታ እንደሆነና በቀጣይ ለማከናወን በያዛቸው እቅዶች ዙሪያ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሰርካ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ የወጪና ገቢ ምርቶችን የማጓጓዝ አቅሙን ለማሳደግ ምን እየሰራ ነው?
ኢ/ር ጥላሁን ሰርካ፡- ሃገሪቱ 14 ሚሊዮን ቶን የሚጠጉ ምርቶችን ከውጪ ሀገራት ስታስገባ 3 ሚሊዮን የሚሆኑትን ምርቶች ደግሞ ወደውጪ ሀገራት ትልካለች። ባቡሩ ስራውን ሲጀምር ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡና ከሃገር ውጪ ከሚወጡ ምርቶች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነውን የማጓጓዝ ድርሻ ነበረው። ይህንን ስራውንም ከሞጆ ጅቡቲ ወደብ በሚደረግ በአንድ የባቡር ምልልስ ነው ጀመረው።
ከአንድ አመት ከስድስት ወር የሙከራ ጊዜ በኋላ የደህንነት ሁኔታዎችን በማስተካከልና ምልልሱን በሁለት ባቡር በማድረግ አቅሙን የማሳደግ ስራ ተሰርቷል። እስካሁን ወደሀገር ውስጥ ያስገባቸውና ወደ ውጪ ሃገር የላካቸው ምርቶች እንዳሉ ሆኖ 70 ሺ ቶን ለግብርናው ዘርፍ የሚውል ኬሚካል ማዳበሪያ ወደሃገር ውስጥ አስገብቷል። በቁጥ ቁጥ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ብረታብረት፣ መኪናና ሌሎችንም ምርቶች አጓጉዟል።
ማህበሩ የነዳጅ ማመለሻ ፉርጎ ቢኖረውም ሃዲዱን ከአዋሽ ዲፖ ጋር የሚያገናኝ መስመር ባለመኖሩ እስካሁን ነዳጅ ማጓጓዝ ውስጥ አልገባም። በቀጣይም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ስንዴ ያጓጉዛል። የወጪና ገቢ ምርቶችን 40 በመቶ የማጓጓዝ ድርሻ ለመሸፈንም ምልልሱን በአራት ባቡር ለማድረግ የሚያስችል ስራ ይሰራል። ይህንንም ለማሳካት እ.ኤ.አ በ2020 እቅድ ተይዟል።
አዲስ ዘመን፡- የህዝብ ትራንስፖርት አገልግ ሎት አቅሙን ለማሳደግስ ምን እየተከናወነ ነው?
ኢ/ር ጥላሁን ሰርካ፡- ለአለም አቀፍ የትራንስፖርት ጉዞ ባቡሩ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በጎዶሎ ቀናት ከለቡ እንዲነሳ፤ በሙሉ ቀናት ደግሞ ከጂቡቲ እንዲመጣ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅትም ፉርጎዎቹ በአማካይ 500 ሰዎችን ብቻ እያጓጓዙ ናቸው። ያሉት ሰላሳ የመንገደኛ ፉርጎዎች አገልግሎት ላይ ቢውሉ ኖሮ በአንድ ጊዜ ሁለት ሺ ሰዎችን ማስተናገድ ይችል ነበር።
እስካሁን ባለው የመንገደኞች ጉዞ አፈፃፀም ከለቡ ድሬዳዋና ከድሬዳዋ ጅቡቲ የሚሄደው የመንገደኛ ብዛት ተመሳሳይ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ደግሞ አክሲዮን ማህበሩን ትርፋማ አያደርገውም። በሁለት ቀን አንዴ ባቡሩን ወደ ጅቡቲ መላክ አዋጭ ባለመሆኑ የጉዞ መስመሩን ለሁለት በመክፈል ከለቡ ድሬዳዋና ከድሬዳዋ ጂቡቲ በየቀኑ እንዲሆንና ይህም ከመጪው ህዳር ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የአክሲዮን ማህበሩ አስተዳደር ወስኗል። መንገደኞችን ከጉዞ መዳረሻቸው ላይ ለማንሳትም አውቶብሶችን ለመከራየት ከፐብሊክ ሰርቪስና ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበራት ጋር ለመስራትም እቅድ ተይዟል።
አዲስ ዘመን፡- ባቡሩ በስርቆቶችና አደጋዎች እየተፈተነ ነው ይባላል። ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ችግር እየተፈታ ነው?
ኢ/ር ጥላሁን ሰርካ፡- በባቡሩ ላይ እየተፈጸመ ያለው ስርቆት ከአክሲዮን ማህበሩ በላይ እየሆኑ መጥቷል። ባቡሩ በሚያልፍባቸው ቦታዎች ሁሉ የየአካባቢው ሻለቃዎች ተመድበው ጥበቃ የሚያደርጉ ቢሆንም፣ አብዛኛው ስርቆት በሌሊት የሚፈፀም ከመሆኑ አኳያ በተለይም የባቡር ሃዲዱን በሚገባ ከስርቆት መከላከል አልተቻለም።
የየቀኑ ጉዞ ከመካሄዱ በፊት አስቀድሞ ምርመራ በሚያደርግ አነስተኛ ባቡር አማካኝነት በሃዲዱ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በማየትና አስፈላጊውን ጥገና በማካሄድ የባቡሩን ደህንነት ለመጠበቅ ተሰርቷል። አክሲዮን ማህበሩ በየአካባቢው ቁጥጥር እንዲያደርጉ የቀጠራቸው የቅኝት ሰራተኞችም ለባቡሩ ደህንነት የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በጭነት መጓጓዣ ባቡር ላይ በቅርቡ የተከሰተው አደጋ መንስኤ ጎርፍ ነው። ይህም ከውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒሰቴር በተውጣጣው የባለሞያዎች አጥኚ ቡድን ተረጋግጧል። በወቅቱ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የጎርፍ መከላከያው በመሰበሩ አንድ ኪሎሜትር የሚሆነውን ሃዲድ ሙሉ በሙሉ ጠርጎ ውስዶታል።
የባቡር ግንባታውን ያከናወኑት የቻይና ሲቪል ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን /CCECC/ እና የቻይና ባቡር ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /CREC/ የጎርፍ መከላከያ ለመቶ አመት እንዲያገለግል ታስቦ ቢሆንም፣ ከሚጠበቀው በላይ ዝናብ በመጣሉ ሳቢያ ነው አደጋው የተከሰተው።
በአደጋው ጉዳት የደረሰበትን የጎርፍ መከላከያ መልሶ ለመገንባት ከኮርፖሬሽኑ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል፤ የጎርፍ መከላከያውን ዲዛይን በመከለስም ከቀድሞው በተሻለ እየተገነባ ነው፤ በሀዲዱ ላይም ለደረሰው ጉዳት የመልሶ ጥገና እየተደረገ ይገኛል፤ በሁለት ሎኮሞቲቮችና በአስራ ዘጠኝ ተሳቢ ፉርጎዎች ላይ የደረሰው ኪሳራም በኢንሹራንስ የሚሸፈን ይሆናል።
የባቡር አደጋው በመነሻ ጊዜ ውስጥ መድረሱ ሁሉንም ያስደነገጠ ቢሆንም፣ ከዚህ በኋላ ግን በደህንነት ርምጃዎች፣ በኦፕሬሽንና በፍጥነት ማሽከርከር ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያውያን የባቡር አሽከርካሪዎችና ሌሎች ባለሞያዎች ግንዛቤ እንዲወስዱ ትምህርት ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ምን ለማከናወን ታቅዷል?
ኢ/ር ጥላሁን ሰርካ፡- 110 ከሚሆኑ ነዳጅ አመላላሽ ፉርጎዎች ውስጥ ሶስቱን ለነዳጅ ማመላለሻ እንዲሆኑ በማድረግ ስራ የሚጀምሩ ይሆናል። ሁለት መቶ የሚሆኑ ኮንቲነር ጫኝ ፉርጎዎች በቻይናውያን ተመርተው እዛው የሚገኙ አሉ። ፉርጎዎቹ ወደሃገር ውስጥ በቀጣይ ሲገቡም በአራት ጎታቾች /ሎኮሞቲቭ/ እቃዎችን ያመላልሳሉ። አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚያጓጉዙ አስር ፉርጎዎችም ገበያውን በማየት የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል። በተመሳሳይም ያሉትን ፉርጎዎች በማሻሻልና የገበያውን ሁኔታ በማየት የቁም እንስሳትም ይጓጓዙባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ለትብብርዎ ከልብ እናመሰግናለን!!
ኢ/ር ጥላሁን ሰርካ፡- እኔም አመሰግናለሁ!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2012
አስናቀ ፀጋዬ