በአፍሪካ የዲሞክራሲ ባህል በሚገባ ካለመገንባቱ ጋር በተያያዘ የዲሞክራሲ ስርአት ምንድነው የሚለውን በመረዳት ረገድ በዜጎች ዘንድ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው። በአህጉሪቱ ስልጣን በዲሞክራሲዊ መንገድ ከማግኘት ይልቅ ሃይልን መሰረት በማድረግ እጅ ጠምዝዞ ወንበር መቆናጠጥ ተለምዷል።
አህጉሪቱ አለም አቀፍ መስፈርት ያላማላ ምርጫ ተካሂዶ ይቅርና ትክክለኛ ምርጫ ተደርጎ የተሸነፈ ተወዳዳሪ ሽንፈቱን በጸጋ የማይቀበልባት ናት። ሽንፈቱን በጸጋ የማይቀበል ተፎካካሪ ፓርቲ አሸናፊውን ፓርቲ አጭበርብሯል ብሎ ደጋፊዎችን ወደ ጎዳና ይዞ መውጣትም ተለምዷል።በሁሉም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መተማመን፣መከባበር፣መግባባት አይስተዋልም፤እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነ የሚሉ፤እልህና ግትርነት የሚያጠቃቸው አልፎ ተርፎም ስለሀገር የማይጨነቁ ጎልተው የሚስተዋልበትም ሁኔታ አለ።
ይህ ምስል የማይገልጻቸው ጥቂት የአፍሪካ ሀገሮች ግን አሉ። ከእነዚህም መካከል ቤኒንን አንዷ ናት። ውጥንቅጥ በሚጎላበት የምእራብ አፍሪካ ቀጠና ዴሞክራሲ በአርአያነት የሚታይባት ቤኒን፣ የዲሞክራሲን ልእልና በማክበር በፖለቲካ መረጋጋት ከጎረቤቶቿ በእጅጉ እንደምትገዝፍ በርካቶች ይስማማሉ። በሰፊ ፖለቲካ ምህዳር፣ በመገናኛ ብዙሃን ነፃነት፣ በሌሎችም የዲሞክራሲ መገለጫዎች ትሞገሳለች።
በሀገሪቱ ከአመት በፊት የተካሄደው ምርጫ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተስተዋለበት መሆኑ ለምስክርነቷ ይጠቀሳል። በዚህ ምርጫ 65 በመቶ ድምፅ በማግኘት ወደ ፕሬዚዳንትነት ስልጣን የመጡት ደግሞ ፓትሪክ ታሎን ናቸው።
ፓትሪክ ታሎን የፕሬዚዳንትነት ቦታውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ በስልጣን ዘመናቸው ዲሞክራሲን ለማስፈን፣ ፖለቲካዊ ምህዳሩን ይበልጥ ለማጎልበትና በተለይም የሙስናን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ተግተው እንደሚሰሩ ለህዝባቸው ቃል ገብተው ነበር።
ይሁንና ሰውየው መንበረ ስልጣኑን ከተቆናጠጡ ብዙም ሳይቆዩ ዲሞክራሲን እያደበዘዙ ነው፣ የተቀናቃኛቸውን ፓርቲ አባላት ዘብጥያ እያወረዱ፣ ታዋቂ የመገናኛ ብዙሀንን ሲዘጉም ተስተውለዋል›› በሚል ከየአቅጣጫው ትችት ሲሰነዘርባቸው ተስተውሏል።፡
በአገሪቱ ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር በተካሄደውና አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ባልተሳተፈበት የፓርላማ ምርጫ ለፕሬዚዳንቱ ቅርበት አላቸው የሚባሉ ሁለት ፓርቲዎች ለስልጣን መብቃታቸውን ተከትሎ ውጤቱ ያልተዋጠላቸው ወገኖች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።፡
ተቃውሞው እየተባባሰ መጥቶ ሕይወት እስከ መቅጠፍ መድረሱ ከቀውሱ ጀርባ የአገሪቱ መንግስት ስውር እጅ ይታየኛል በሚል እኤአ ከ2006 እስከ 2016 አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ቶማስ ቢኒ ያያን በቁም እስር እንዲቆዩ ሲል ትእዛዝ አሳልፎባቸዋል።
ይህ ግን በእሳት ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ ሆኗል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት መታሰር ያስቆጣቸው በርካታ ደጋፊዎቻቸውም በአገሪቱ ዋና ዋና አደባባዮች ወጥተው ተቃውሟቸውን ለማሰማት ጊዜን አላባከኑም።
ይህን ያስተዋሉት ፕሬዚዳንት ፓትሪክ ታሎንም ከምርጫው በኋላ በአገሪቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ፈር ለማስያዝ ስለፖለቲካ፣ ስለሀገር እድገትና ልማት ልንነጋገርና ልንወያይ ይገባል፣ ብሄራዊ መግባባት፤ ያስፈልገናል›› በሚል የፊት ለፊት ውይይት መድረክ አዘጋጅተዋል።
ከተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ለመነጋገር በተሰናዳው የብሄራዊ መግባባት መድረክም፣ ሁሉም የተቀዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም ሲቪል ማህበራት እንዲገኙ በሩ ወለል ተደርጎ መከፈቱም ታውቋል።
አንዳንዶች ፕሬዚዳንት ታሎን ይህን የማድረጋቸውን ምክንያት እያደር የተፋፋመው የህዝብ ቁጣና ተቃውሞ ስልጣናቸውን ሳይነቀንቅ ለማርገብ መሆኑን እየገለጹ ናቸው፤ፕሬዚዳንቱ ግን ‹‹ይህን የማደርገው የፖለቲካ ትርፍ ለማኘት አሊያም አኩራፊዎችን ለማባበል ሳይሆን በዲሞክራሲ ልእልና ችግሮቸን በውይይት መፍታት እንደሚቻል እምነት ስላለኝ›› ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በብሄራዊ መግባባቱ መድረክ ላይ ለተገኙት ተሳታፊዎች እወቁልኝ ባሉት በዚህ መልእክታቸው፣ የብሄራዊ መግባባት መድረኩ ትርፍ በአገሪቱ ዲሞክራሲዊ ምህዋር ላይ የተደቀኑ ለበርካታ ወገኖች ቅሬታ ማቅረብ አሊያም ተቃውሞ ምክንያት የሆኑ ደንቦችን ጨምሮ ሌሎች ማነቆዎችን ለማስወገድ መሆኑንም አስምረውበታል።
በብሄራዊ መግባባት መድረኩ የተጋበዙ ወገኖች ‹‹ጠሪ አክባሪ›› ነው ብለው የተገኙ ቢሆንም፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በአንጻሩ፣ የሰውየው ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በመድረኩ አለመገኘታቸውን አስነብቧል። በመድረኩ ያልተጋበዙ በርካታ ፓርቲዎችም የራሳቸውን መድረክ ‹‹የአፀፋ ውይይት›› በሚል በማዘጋጀት ፕሬዚዳንቱን መቃወም ምርጫቸው ማድረጋቸው ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2012
ታምራት ተስፋዬ