ዘመን ተሻጋሪው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አነስታይን ከታላላቅ ግኝቶቹ ከአንጻራዊ እይታ፣ ለአቶሚክ ቦንብ መገኘት ፈር ቀዳጅ ከሆነው ቀመርና ከሌሎች ፈጠራዎቹ እኩል የሚታወሱለት ድንቃ ድንቅ አባባሎች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጠቀስለት” ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ ፤ ችግር መፍታት አይቻልም። “ የሚለው ነው። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከኢህአዴግ ቤት የሚሰማው መልካም “ ዜና “ ይህን የአነስታይንን ዘመን ተሻጋሪ አባባል እና “ቁሞ ቀር “ርዕዮት ጠል የሆነውን የብሌየርን ምክረ ሀሳብ ምርኩዝ ያደረገ ይመስላል። የለውጥ ኃይሉ ዘመኑንም ትውልዱንም የሚዋጅ የመደመር ፅንሰ ሀሳብን ባወጀ በአጭር ጊዜ ይሄን ፅንሰ ሀሳብ ይመጥናል ያለውን አደረጃጀትና አሰራር ይዞ እንደሚመጣ ካበሰረ ወዲህ በመደበኛም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያው ቀዳሚ መነጋገሪያ ሆኗል።
ገዥው ፓርቲ ኦፊሴላዊ በሆነ አግባብ የውህደት ጊዜ ሰሌዳውንም ሆነ ዝርዝር አፈጻጸም ባይገልፅም “ኢህአዴግ “ ከግንባርነት ወደ ውህድ አንድ ፓርቲነት እያመራ መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው። በተለይ አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ደኢህዴን እንዲሁም አምስቱ አጋር ፓርቲዎች ማለትም ጋሕአዴን፣ አብዴፓ፣ ቤጉሕዴፓ፣ ሶህዴፓና ሀብሊ የውህደቱ ዋልታና ማገር እንደሚሆኑ ተሰምቷል። ተቸካዩ፣ ቁሞ ቀሩ ትህነግ/ ህወሀት ግን ከመማፀኛ ከተማው ሆኖ ውህደቱን እንደማይቀበል ከዚያም አልፎ በብርቱ እንደሚቃወመው በደም ፍላት ሀኒታዬን እየሸለለ ነው። ሆኖም ይህ መደመር፣ መዋሀድ፣ መሻገር፣ ለውጥ፣ ፍቅር፣ ወዘተ . ጠልነት የትግራይን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት የማይወክል መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይችላል።
የመደመር ፅንሰ ሀሳብ የማዕዘን ድንጋዮች ማለትም መሰብሰብ፣ ማከማቸትና ማካበት ከቀዳማዊ ኢህአዴግ አሰራርና አደረጃጀት ጋር ጀርባና ሆድ ናቸው። በእነዚህ የመደመር አላባውያን ስር በውስጠ ታዋቂነት ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ሌሎች ሰብዓዊ እሴቶች አንዳሉ ይታመናል። በተለይ በቀዳማዊ ኢህአዴግ የ28 አመታት አሰራርና አደረጃጀት ፍትሐዊነት፣ እኩልነት፣ ነፃነትና ዴሞክራሲያዊነት ደሮ ማታዎች ነበሩ። ህወሀት ኢህአዴግን ጠፍጥፎ የሰራው ለእሱ በሚያመቸው መንገድ ነው። ግንባሩን በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወለፈንዲ ኀልዮት ጠርንፎ እራሱን ዘላለማዊ መንበር ላይ ማቆየት። ይህ መሰሪና ራስ ወዳድ ህልሙ በፀጥታና በደህንነት መዋቅሮች ታግዞ ለአመታት እውን አድርጎ አቆይቶታል። በአጋር ድርጅቶች አይደለም በራሱ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ዴሞክራሲያዊ ግንኙነት፣ አሰራር፣ አደረጃጀት አልነበረም። እስከ ለውጡ ዋዜማ ድረስ የግንባሩ አባል ድርጅቶች በህወሀት ፈላጭ ቆራጭነት እና በሞግዚት የሚመሩ ከመሆናቸው ባሻገር 5 ሚሊዮን ሕዝብ እወክላለሁ የሚለው ህወሀት ከእሱ ከ5 እስከ 10 እጥፍ ሕዝብ ከሚወክሉ አባል ድርጅቶች ጋር በግንባሩ እኩል ውክልና ነበረው። ከዚህ በላይ ህወሀት በግንባሩ ውስጥ ፍፁም የበላይነት እንደነበረው ፀሐይ የሞቀው ጥሬ ሀቅ ነው።
ከሀገሪቱ ግማሽና ከዚያ በላይ የሚሆነውን መልክዓ ምድር የሚወክሉ አምስት ክልሎችን ገዥ ፓርቲዎች በአምሳሉ ጠፍጥፎ ከመስራቱ ባሻገር በእሱ ቀጥታ የዕዝ ሰንሰለት ወይም ጥርነፋ ስር በማድረግ ለጥ ቀጥ አድርጎ መግዛቱ ሳያንስ ለእሱ ፍፁማዊ አምባገነንነት እንዲመቸው በአጋርነት ስም 2ኛ ዜጋ አድርጓቸው ኖሯል። እነዚህ አጋር ፓርቲዎች በሀገሪቱም ሆነ በሞግዚትነት በሚያስተዳድሮአቸው ክልሎች መፃኢ እድል የመምከርና የመወሰን መብት አልነበራቸውም። ግንባር ታክቲካዊ፣ ጊዜአዊ የጋራ አላማን ለማሳካት ማለትም ፖለቲካዊ ሕብረትን እውን ለማድረግ የሚቀየስ ጊዜአዊ ስልት እንደሆነ ቢታወቅም ህወሀት ግን ስልጣን ላይ የሚያቆየው ብቸኛ ስትራቴጂ ስለነበር በአለማችን የፖለቲካ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔት ከ30 አመታት በላይ የሙጥኝ ብሎት መኖሩ ሳያንስ ይህን ግትር አቋሙን ወደ መቃብር ይዞት ለመውረድ የወሰነ ይመስላል። ለዚህ ነው አንድ ጊዜ የኢህአዴግ መስመር፣ ሕብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ሌላ ጊዜ ሕገ መንግስታዊ የፌዴራል ስርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል እያለ የሚያላዝነው።
ሆኖም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ጅማሬ ማብሰሪያ ላይ “የኢትዮጵያን ሕልውና እና ብልፅግና ጉዞ የሚያቆም ምንም ኃይል የለም !!!” ካሉ በኋላ በማስከተል “ዶሮዋ የእንቁላሉ ባለቤት ብትሆንም ሰብሮ ጠብሶ ከመብላት ግን ልታግደን አትችልም። “ ያሉት። ዶሮዋ ማንን እንደምትወክል እንቁላሎቹና የፍርፍሩ ተመጋቢ እነማን እንደሆኑ እንቆቅልሽ እንድትፈቱት ለእናንተ ትቸዋለሁ ። እንግዲህ እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል የሚለው በመማፀኛ ከተማው መሽጎ የሚገኘው የህወሀት ተቸካይ ቡድን ዜጎችን 1ኛ ፣ 2ኛ ፣ 3ኛና 4ኛ ፣ …ዜጋ የሚያደርገው ኢፍትሐዊ ፣ ኢዴሞክራሲያዊ፣ አድሎአዊ ፣ አምባገነናዊ ፣ ወዘተ . የነበረው ኢህአዴግ በውህደት ወደ አንድ ፓርቲ እንዳይለወጥ እየተቃወመ ያለው ፍትሐዊ ያልነበረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሙን እንዳያጣ እንጂ ውህደቱ በእውነት ጨፍላቂ ይሆናል ከሚል ስጋት አለመሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
እንግዲህ የለውጥ ኃይሉ ግንባሩ ሲከተለው የነበረ አሰራርም ሆነ አደረጃጀት ፍትሐዊም ዴሞክራሲያዊም ካለመሆኑ ባሻገር ግንኙነቱ በእኩልነት መርህ ላይ ያልተመሰረተ ስለነበር ይህን የሚያስተካክል አሰራርና አደረጃጀት ለማስፈን የሚያግዝ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዳር እስከ ዳር በእኩልነት፣ በፍትሐዊነት የሚያሳትፍ ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑ እየተገለፀ ነው። ፓርቲ ተመሳሳይ ሀሳብና አመለካከት ያላቸው ሰዎች ፖለቲካዊ ስልጣን ለመያዝ ብለው የሚመሰርቱት ድርጅት መሆኑን ስናስብ ግንባሩ ወደ ፓርቲነት ለመለወጥ መወሰኑ በራሱ ትልቅ እመርታ ቢሆንም የመጨረሻ ግቡ እንዳይደል እሙን ነው። ይህን በእርግጠኝነት የማወሳው የለውጥ ኃይሉ የትውልዱን ድምፅ፣ ጥሪ አድምጦታል በሚል እምነት ነው። ከሁሉም በላይ አዲስና ተግባራዊ እይታን የግድ የሚያደርገው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘውት የመጡት የመደመር ፍልስፍና ነው። በታላቁ መፅሐፍ የማቲዎስ ወንጌል 9 ÷ 17 ላይ “ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም። ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል። ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።” እንደሚለው አዲሱን የወይን ጠጅ መደመርን በአረጀው አቁማዳ በኢህአዴግ የሚያኖር የለምና አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲሱ ፓርቲ ማኖር የግድ ያደርገዋል። ስለ አዲሱ ፓርቲ ስያሜም አንድ ስም ተደጋግሞ በማህበራዊና በአንዳንድ መደበኛ ሚዲያዎች እየተዘዋወረ እየተወሳ ነው። እሱም ፦ የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ ( ኢብፓ ) የሚል ነው። ከስያሜው በመነሳት ፓርቲው ማንኛውንም በብልፅግና የሚያምን ኢትዮጵያውያንን በአንድ ድንኳን የሚያሰባስብ ስለመሆኑ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
ለቀደሙት 50 አመታት በተለይ ካለፉት 28 ተከታታይ አመታት ወዲህ ልዩነት፣ ማንነት አውራጃዊነት ላይ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሊባል በሚችል ሁኔታ በመሰራቱ ለጊዜው የተዘራው እንክርዳድ እስኪታረም ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት ላይሆን ይችላል። ስለሆነም እንክርዳዱን ከመንቀል ጎን ለጎን አማራጭ አሰባሳቢዎችን ማማተር የግድ ይሆናል። አሁን እጃችን ላይ ከቀሩት አሰባሳቢ ኢትዮጵያዊ ማንነት ኢኮኖሚው ቀዳሚ ነው ። ኢኮኖሚው ያለ ምንም ልዩነት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድ ጥላ ስር የማሰባሰብ አቅም አለው ። የስራ ዕድል መጥበብ፣ የዋጋ ግሽበት ፣ የኑሮ ውድነት ፣ የመሰረታዊ ሸቀጦች ዕጥረት፣ ድህነት ፣ ኋላቀርነት ፣ ወዘተ . የሀገሪቱን ዜጎች ያለ ልዩነት ቀስፈው የያዙ ኢኮኖሚያዊ የጎን ውጋቶች ናቸው። እነዚህ ውጋቶች የኦሮሞውም፣ የአማራውም፣ የትግራዊም፣ የሶማሌውም፣ የሀድያውም፣ የአዲስ አበቤውም፣ ወዘተ . ሕመሞች ናቸው። በተለይ የወጣቶች ለሆነችው ሀገራችን የኢኮኖሚ ጉዳይ ታክቲካዊም ስትራቴጂያዊም ስልት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ስለሆነም ኢህአዴግ ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ የሚያደርገው ሽግግር በእርግጥ “ብልፅግና “ን የአዲሱ ፓርቲ አስኳል አድርጎ የሚመጣ ከሆነ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት የሚያሰባስብ ማንነት ስለሆነ ይበል የሚያሰኝ ነው።
እንደ ማሳሰቢያ
በታላቁ መፅሐፍ የአብራም ስም ወደ አብርሃም፣ ሦራ ወደ ሣራ፣ ያዕቆብ ወደ እስራኤል፣ ሰሎሞን ወደ ይዲድያ፣ ጳስኮር ወደ ማጎርሚሳቢብ፣ ዮሐንስ ወደ ቦአኔርጌስ፣ ስምኦን ወደ ኬፋ፣ ወዘተ . ሲቀየር አሮጌው ማንነታቸው አብሮ በአዲስ ተቀይሯል። ኢህአዴግም ስያሜውን ወደ ኢብፓ ሆነ ወደ ሌላ ሲቀይር አሮጌውን ማንነቱን ማለትም ኢዴሞክራሲያዊነትን፣ ኢፍትሐዊነትን፣ አግላይ ነቱን፣ ጨፍላቂነቱን፣ አህዳዊነት፣ ወዘተ. በአዲስ ማንነት ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል።
የውህደቱ መንገድ አልጋ በአልጋ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። በተለይ ህወሀት ውህደቱን ከጥንስሱ ጀምሮ ሲቃወመው የቆየ ቢሆንም ሰሞኑን ግን 24/7 እያመነዠከው ይገኛል። ሆን ብሎ የክልሉን ሕዝብ እያደናገረ ለእገታው እያመቻቸ ከመሆኑ ባሻገር ምንደኞቹንና ጭፍራዎቹን በዚህ ዙሪያ ለማሰባሰብ ነጋሪት እየጎሰመ ነው። ይህን የእፉኝት ተግባር ያለ ልዩነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘው ቢገባም የለውጥ ኃይሉ ግን ቸልታውን የበዛ ትዕግስቱን ቀነስ አድርጎ በሚከተሉት ስትራቴጂዎች ላይ ሊሰራ ይገባል።
1ኛ. ውህደቱ ለትግራይ ሕዝብ ሊያመልጥ የማይገባ ዕድል እንጂ ስጋት አለመሆኑን በማስገንዘብ “እወክለዋለሁ” በሚለው ድርጅት ላይ ጫና ማሳደር እንዲችል ምቹ መደላድል መፍጠር። ለዚህ የፌዴራል መንግስት በክልሉ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ለዓረና ትግራይ፣ ለየትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሆነ ለሌሎች የክልል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ በማድረግ አማራጭ ሆነው እንዲወጡ ማገዝ ይጠበቅበታል።
2ኛ . ይህ ቡድን ምን ያህል እኩይ እንደሆነ ከሞላ ጎደል ሁሉም ዜጋ ግንዛቤ ያለው ቢሆንም የጆሴፍ ጎብልስ ደቀ መዝሙር ስለሆነ ዛሬም “ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል።” በሚል ስሁት ፕሮፓጋንዳ የሚነዛው ሀሰተኛ ፣ የተዛባና የተሳሳተ መረጃ አደገኛ መሆኑን በመገንዘብ የመመከቱና ሴራውን የማጋለጥ ስራ በተቀናጀ አግባብ ሊመራ ይገባል ። እዚህ ላይ አበው፣ እመው ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ያሉትን ያጤኑአል።
3ኛ . ይህ ቡድን ለስልጣኑ፣ ለጥቅሙ ሲል ምንም ከማድረግ አይመለስምና የፌዴራል መንግስትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግ ጎን ለጎን ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ለሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና ለአለም አቀፍ እንዲሁ ለቀጣናዊና አህጉራዊ ተቋማት ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ ማብራሪያ የመስጠቱ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ኤምባሲዎቻችንና ቆንስላዎቻችንም ይህን ተልዕኮ ደርበው ይወስዳሉ ተብሎ ይታመናል።
“… የኢትዮጵያን ብልፅግና ምንም ኃይል አያቆመውም !!! … “
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )