መንግሥት በዚህ ዓመት ከሚያከናውናቸው ዓበይት ተግባራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ የሚጠበቀውን አገራዊ እድገት ከማረጋገጥ አኳያ ዓመቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራት በተጠናከረ ደረጃ የሚከናወኑበት እንደሚሆን፤ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው እንዳመለከቱት፤ ለሚጠበቀው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሠረት ተደርጎ የሚሰራባቸው ጉዳዮች ዋና ዋና ዓላማዎች ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም የማክሮ ኢኮኖሚውን ጤንነት መጠበቅ፤ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግ፤ እንዲሁም ለዜጎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ናቸው። እነዚህን ዓላማዎቹን ለማሳካትም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማስተካከል፣ የኢኮኖሚ መዋቅሮችን ማሻሻል እና የኢኮኖሚ ዘርፍ ማሻሻያ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡
በኢኮኖሚው ዘርፍ ማሻሻያ ትኩረት ከሚደረግባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል ደግሞ ቀዳሚው የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በግብርና መስክ ባለፈው ዓመት ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ ነው።
በዚህ ረገድ የ2010/2011 ዓ.ም ምርት ዘመን የሰብል ምርትን 406 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ፤ 316 ሚሊዮን ኩንታል (የዕቅዱን 78 በመቶ) ማድረስ ተችሏል። ይህም በ2009/2010 ዓ.ም ከተመረተው 267 ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲነፃፀር የአራት ነጥብ 29 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የእርሻ ግብአቶችን በሚፈለገው መጠንና ወቅት ማቅረብ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በክልሎች ፍላጎት መሠረት ለ2011/12 ምርት ዘመን የሚያስፈልግ አንድ ነጥብ 27 ሚሊዮን ቶን የኬሚካል ማዳበሪያ የውጭ ግዥ በማከናወን ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ደርሷል።
በግብርናው ዘርፍ የ2011/12 በጀት ዓመት ዋናዎቹ የትኩረት መስኮች መካከል የገበያ መር ግብርና (የሰብልና እንስሳት) ልማት ማስፋፋት፤ የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ አቅርቦትና ግብይትን ማጠናከር፤ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶች በተለይም የስንዴ ምርትን በሀገር ውስጥ መተካት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የስንዴን ምርታማነት ከማሳደግና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ከመተካት አኳያ የመስኖ ልማት ሥራ አንዱ ሲሆን፤ ሰፋፊ የመስኖ ልማት ሥራ የሚከናወንበት ዓመት ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ይሄን መነሻ አድርገን ያነጋገርናቸው በግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ዳንኤል ዴንታሞ እንደተናገሩት፤ በ2011 ዓ.ም በአብዛኛው በአነስተኛ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ እስከ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል፡፡ ይሄንኑ እንደመነሻ እርሾ በመውሰድም በ2012 ዓ.ም ሰፊ የመስኖ ልማት ሥራ ለማከናወን እቅድ የተያዘ ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ ወደ ሦስት ሺ ሄክታር የሚጠጋ በአርሶ አደሩና በእርሻ ምርምር ተቋማት የተያዘን መሬት በማልማት በሄክታር በአማካይ እስከ 40 ኩንታል ምርት መገኘቱ በመስኖ ልማት ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚቻል የታየበት ነበር፡፡
በመሆኑም በዚህ ዓመት በመንግሥት በኩል ለመስኖ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ነው፡፡ በተለይ በቆላማ አካባቢዎች ላይ ስንዴን በማምረት ከውጭ የሚገባ ስንዴን ለማስቀረት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም ግብርና ሚኒስቴር፣ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ ግብርና ምርምር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እየሰሩ ሲሆን፤ በተለይም የአዋሽና ዋቤ ሸበሌ ወንዞችን ተከትሎ ባሉ የአፋርና የሶማሌ ክክሎች እንዲሁም በደቡብ ክልልም በኦሞ አካባቢ በበጋው ወራት ብቻ እስከ 50ሺ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን ለማልማት እየተሰራ ነው፡፡
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፤ ለበጋው ዘር የማሳ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ሲሆን፤ ለመስኖ የተዘጋጀው የስንዴ ዘር ደግሞ ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ መከናወን ስላለበት የዘር ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል በግብዓትና ዘር አቅርቦት ሂደት የሚሰማሩ ባለሙያዎችና ባለድርሻዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተከናውኖ ዘር ለመጀመር ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ ይህም ለተያዘው ግብ መሳካት የራሱ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ ለውጤታማነቱም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከተሰራና በምርምር ከታገዘም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ከሚከናወን የመስኖ ልማት በተሻለ በሄክታር ቢያንስ እስከ 40 ኩንታል ምርት እንደሚገኝም ታሳቢ በመደረጉ፤ ከእርሻ ዝግጅት እስከ ዘር ሂደት ላለው ሥራም የሜካናይዜሽን የእርሻ ዘዴም ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡
በመሆኑም በበጋው ወቅት ለሚከናወነው ስንዴን በመስኖ የማልማት የተያዘውን እቅድ ከማሳካት አኳያ ጥጥ ተለቅሞ የተነሳባቸው ማሳዎች፤ የሸንኮራ እርሻ ያለባቸው ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ሸንኮራ ወደማልማት ሥራ ባልተገባባቸው ቦታዎች፤ እንዲሁም በአርሶ አደርና አርብቶ አደሩ የተያዙ ሰፋፊ የሆኑ ውሃ ገብ መሬቶች የመስኖ ሥራው አካል ይሆናሉ፡፡ ለዚህም ወንዞችን በመጥለፍ (በመቀልበስ) እንዲሁም በውሃ ፓምፖች መጠቀመም ጭምር ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡ ሥራውም በበጋው ከሚከናወነው የ50 ሺ ሄክታር የሚቆም ሳይሆን፤ የቀደመውን ልምድ በማቀናጀት እና በበጋው የሚታየውን መልካምና ፈታኝ ሁኔታ በመቀመር በመንግሥት፣ በባለሀብቱ፣ በአርሶ አደሩና በሌሎች ባለድርሻዎች የላቀ ተሳትፎ እየተደረገበት ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚከናወንም ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012
ወንድወሰን ሽመልስ