በጥንቱ ዘመን የአባይ ወንዝ ዋናዋ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗና ባለቤትነቱዋ ታውቆ የግብጽ መሪዎች በየዓመቱ ለሚጎርፍላቸው ውሀ ይከፍሉ ነበር። ባሁኑ ጊዜ ግን በተለይ ግብጽ የአባይን ወንዝ እንደ ግል ንብረቷ በመቁጠር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ለመጠቀም የምታከናውነውን ጥረት መቃወም ብቻ ሳይሆን ማስፈራራትም ይቃጣታል።
እንደሚታወቀው በየድረ-ገጹ በስፋት ከሚቀርቡት ሐተታዎች፣ ትችቶችና አስተያየቶች ውስጥ ሰፊ ስፍራ ይዞ የሚገኘው አንደኛው አርእስት ኢትዮጵያ ውስጥ በመገንባት ስላለው ታላቅ የአባይ ግድብ ነው። ስለ ግድቡ የተንጸባረቁት የተለያዩ አስተያየቶች እንዳሉ ሆነው የአባይ ወንዝ ባለቤትነት የማን እንደሆነ ውሱን በሆነ መንገድ ተነካ እንጂ በጥልቀት በተከናወነ ምርመራና በዓለም-አቀፍ ሕግ በተመሠረተ አስተማማኝ ማስረጃ የተደገፈ ጽሑፍ አልቀረበም።
የዚች ጦማር ዓላማም ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር እንዲሁም ከሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር በምታከናውናቸው ውሎች ያሁኑንና የመጪውን ትውልድ ሁሉ መብት በሚጠብቅ ስልት መጠቀሟን እንድታረጋግጥ ተገቢውን ቅድመ-ዝግጅትና ጥንቃቄ እንድታደርግ ለማሳሰብ ነው። በዚህ አጋጣሚም ተሞክሮው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ስለሚመስለኝ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት የለሶቶ (Lesotho) መንግሥት የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በነበርኩበት ጊዜ ስለዛች ሀገር ወንዝ በዓለም ባንክ ድጋፍ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር እኔ ራሴ በመራሁት የልዑካን ቡድን ስለተከናወነው ድርድርና ስለ ተገኘው ውጤትም ባጭሩ እገልጻለሁ።
የአባይ ወንዝ በረከት፤
አባይ፤ ኢትዮጵያ ካሏት እጅግ ታላቅና አኩሪ የተፈጥሮ ሀብቶች አንዱ ነው። ከልዩ ልዩ ወንዞች የተጠራቀመው ወደ 80 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር (cubic metre) ውሃ በአባይ አማካኝነት እየተዥጎደጎደ ሱዳንንና ግብጽን እያለማ አቋርጦ ከሚተነው ውሃ ጭምር የተረፈው ሚዲቴሬኒያን ባሕር ይገባል። አባይ ከኢትዮጵያ ሰንቆ የሚጓዘው ውሃ ብቻ ሳይሆን ለም አፈር ጭምር ነው።
በአባይ ወንዝ በረከት የተጠቀመው ማን ነው?
አባይ (በእንግሊዝኛ Blue Nile) ከተሰኘው በዓለም በታሪክ ታዋቂ ከሆነው ወንዝ ዋናዎቹ ተጠቃሚዎች ሱዳንና ግብጽ ናቸው። ከሌሎች ሀገሮች ጭምር ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚፈሰው ውሃ ሲታሰብ ከኢትዮጵያ የሚዘልቀው የአባይ ወንዝ አስተዋጽኦ ከጠቅላላው የውሃ መጠን 86% እንደሆነ ይታወቃል። የሚያሳዝነው ከባድ ጉዳይ ግን የአባይ ወንዝ ዋናዋ ምንጭ የሆነችው፤ ኢትዮጵያ፣ ለብዙ ዘመናት ተጠቃሚ ሳትሆን መቅረቷ ነው። ይህን ሁኔታ ከባድ የሚያደርገው ባንድ በኩል አባይን የመሰለ አኩሪ የውሃ ሀብት እያላት ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት በመደጋገም ረሀብና እልቂት የተፈራረቀባት ሀገርመሆኗ ነው።
ለመሆኑ የአባይ ወንዝ ባለቤት ማን ነው?
ዶር ሚንጋ ነጋሽ፣ ዶር ሰይድ ሀሰንና ዶር ማሞ ሙጬ በቅርቡ ባበረከቱት “Misplaced Opposition to the Grand Ethiopian Renaissance Dam” በተሰኘው ጽሑፋቸው፤ ከታዋቂው ከሪቻርድ ፓንከርስት (Richard Pankhurst) በመጥቀስ በጥንቱ ቱርኮች ግብጽን በሚገዙበት ዘመን የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ መሆኑ ታውቆ፤ 50,000 (ሃምሳ ሺ) የወርቅ መሀለቅ (gold coins) ለሀገራችን በየዓመቱ ይከፍሉ እንደ ነበር ታውቋል።
ከላይ እንደተጠቀሰው፤ ምንም እንኳ ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚነጉደው የአባይ ወንዝ ምንጭ ኢትዮጵያ ብትሆንም፤ በቅርቡ ዘመን የታየው ሁኔታ ለጊዜው ተጠቃሚ የሆኑት ሀገሮች እያንጸባረቁት የቆየው ተጨባጭ ሁኔታ ባለቤትነቱ የእነሱ እንደ ሆነ ዓይነት ነው። ከላይ የተጠቀሱት ምሁራን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችባቸው ውሎች፤ (ሀ) እ.አ.አ በ1929 በእንግሊዝና በግብጽ መሀል በተፈጸመው ውል 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለግብጽ፤ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለሱዳን እንዲመደብ፤ በኋላ ደግሞ (ለ) በ1959 በግብጽና በሱዳን መሀል በተከናወነው ውል 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ለግብጽ፣ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለሱዳን ተመድቧል። የሚያስገርመው፤ ዋናዋ የውሃው ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ መብት ምንም ዋጋ አልተሰጠውም።
በአሁኑም ጊዜ ተከስቶ ያለው ሁኔታ፤ ግብጽ “የአባይ ስጦታ” (“Gift of the Nile”) መሆኗን ስለምታውቅ በተለይ በቅርቡ ዘመን የለመደችውን ልቅ የሆነ በአባይ ወንዝ የመጠቀም ችሮታ ያለገደብ እንድትቀጥል መብቷ እንደሆነ እያስመሰለች ኢትዮጵያ በመብቷ ከተጠቀመች እርምጃ የሚያስከትል መሆኑን በመጠቆም የማስፈራራት ስልት እያናፈሰች፤ በሌላ በኩል የዚህ ዓይነት አጉል ዘዴ የማያዋጣ መሆኑን ግንዛቤ ያለው በሚመስል ሥርዓት ለመደራደር ፈቃደኛነት ታሳያለች ። ኢትዮጵያውያን መብታቸውን ለማስከበር በቁርጠኛነት ስለወሰኑ ማንም ሊገድባቸው እንደማይችል ግብጽም ብትገነዘብ መልካም ነው።
በወንዟ ሀብት የመጠቀም የለሶቶ (Lesotho) ተሞክሮ፤
በመግቢያው እንደ ገለጽኩት፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ለሶቶ (Lesotho) ሀገር እ.አ.አ በ1972-78 አገልግዬ ነበር። ለአራት አመቶች በፖስታ፣ ቴሌኮሙኒኬሽንና ሲቪል አቭዬሽን ዋና ዲይሬክተርነት የሠራሁ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመቶች ደግሞ የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በመሆን ሰርቻለሁ። የሥራ ሚኒስቴሩም የሚያጠቃልላቸው አገልግሎቶች የመንግሥት ሕንጻዎችና መንገዶች ግንባታዎችና ጥገናዎች፣ የውሃ ልማትና አቅርቦት፣ የኤሌክትሪክሲቲ አገልግሎትና የትራንስፖርት አገልግሎት ነበሩ።
ለሶቶ፤ ደቡብ አፍሪካ መሀል የምትገኝ አንድ ትንሽ ሀገር ናት። ትንሽ ብትሆንም እንደ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብት በረከት ያላት ሀገር ናት። እኔ ለሶቶ በነበርኩበት ጊዜ የለሶቶ ወንዝ የሚፈሰው ለደቡብ አፍሪካ ለልማትና ሌላም ጥቅም እንጂ ወደምትፈልገው አቅጣጫ ስላልነበር፤ አስፈላጊው የማስተካከል ተግባር ተከናውኖ ሙሉ ተጠቃሚ እንድትሆን በለሶቶና በደቡብ አፍሪካ ድርድር ተጀምሮ ነበር። በዚህም ምክንያት በለሶቶው የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነት ተግባሬ በድርድሩ ተካፍዬ ነበር።
ከዚሁ በተለይ የማስታውሰው እ.አ.አ. በ1977 በኔ መሪነት ኬፕታውን (Cape Town) በመጓዝ የለሶቶ ባለሥልጣኖችና ከዓለም ባንክም ተወካይ የተገኘበት ልዑካን ከደቡብ አፍሪካ የሚመለከታቸው ባለሥልጣኖች ጋር ተደራድረን ነበር። የድርድሩ ጭብጥም ለሶቶ በውሃ ሀብቷ (ለኤሌክትሪክ ኃይል ማፍለቂያ ጭምር) የመጠቀም መብቷ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ለደቡብ አፍሪካ ለሚፈሰው ውሃ ለሶቶ ተገቢው ክፍያ እንዲከናወንላት ለማድረግ ነበር።
ያ ሁሉ ድርድር ውጤቱ አምሮ፤ የለሶቶን ተራራ በመሸንቆር የወንዙን ፍሰት አቅጣጫ በማስለወጥ ለደቡብ አፍሪካ የሚያስፈልገው ውሃ በሚገባ እንዲቀርብ ለማድረግ ከቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሆነበት ሥራ ተጠናቆ ባሁኑ ጊዜ ለሶቶ በያመቱ በአማካኝ $50 ሚሊዮን በደቡብ አፍሪካ እየተከፈላት ነው።
ለሶቶ ብሔራዊ መብቷንና ጥቅሟን ከላይ እንደተገለጸው ማስከበር ከቻለች ኢትዮጵያም ተመሳሳይ እድል እንዲገጥማት ብርቱ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ::
ማጠቃለያ፤
አባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ታላቅ የተፈጥሮ ሀብት ነው። ኢትዮጵያ የሱዳንንና የግብጽን ተገቢ መብት እያከበረች የራሷንም ጥቅም መጠበቅና ማስከበር ይኖርባታል። ለዚህም በወንዝ ውሃ አጠቃቀም መርሆ፤ ሥልትና እቅድ ባለሙያዎች በመታገዝ ዝርዝር ጥናቶች በማከናወን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚከናወነው ድርድር የኢትዮጵያን የዘለቄታ ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ማረጋገጥና ስለ ሂደቱም ግልጽነትና ቁጥጥር የሰፈነበት እንዲሆን፤ የአባይ ወንዝ ዋናው ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሙሉ ግንዛቤ እንዲኖረውና ሙሉ መብቱ እንዲጠበቅ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን አመራር ሥልጣን ተረክበው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ ክቡር ዶር/ አብይ አሕመድ ወደ ካርቱምና ካይሮ ተጉዘው ከአመራሮቹ ጋር ቅንነት የተላበሱ ውይይቶች ያከናወኑ በመሆኑ የአባይ ወንዝንም ብሔራዊ እሴትነት ጉዳይ አጥብቀው በመያዝ የኢትዮጵያ መብት እንዲከበር ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስዱ ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ