“የፖለቲካ አስተሳሰብ ሁሉ ግብ ህዝብን ማስደሰት ነው፤ ህዝብን ማስደሰት ካልቻለ ግን ፖለቲከኛው ከስፍራው ራሱን ማግለል አለበት። ” ጃዋሃርላል ኔህሩ ነበሩ፤ ይህንን ያሉት። ኔህሩ፣ የመጀመሪያው የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ናቸው። ይህ አስተሳሰብ የመነጨው ከሁሉም ቤተ-እምነት ይመስለኛል። አንድ መሪ፣ በፍቅርና ማግባባት አንድን ደርጅት መምራት ካልቻልኩ በዚህ ስፍራ ምን አደርጋለሁ፤ ማለት ይገባዋል። እውነት ነው፤ ተፈርቼ ልኖር እችላለሁ፤ ተከብሬ ግን አይደለም። ፍርሃት የሚፈጥረው ክብር አሳሳች ነው፤ ነፋስ ሲገባው እንደሚበተን ጉም ነው፤ ማለት ነው ያለበት። መሪን የሰው ደስታ ጉዳይ ካላስጨነቀው ሰማያትም ቅር ይላቸዋል።
ተመሪዎችም ከዚህ ፍቅር ሲቀዱና በዚህ መንፈስ ውስጥ ሲያልፉ ትርጉም ያለው የመሪና ተመሪ ግንኙነት ውስጥ ያልፋሉ፤ ሲመሩ ይታዘዛሉ፤ ምድሪቱም የሰላምና የደስታ ፅጌ ያብብባታል። የተከበረ መሪ፣ የተከበረ ራዕዩን ህያው የሚያደርግበት የህዝብ ልብ አቅምና ሜዳ ይጠብቀዋል። የሚፈሩት መሪ ደግሞ ባይገፉትም እንደሚንገዳገድ ሰካራም የአመራር ዥዋዥዌ ውስጥ ወድቆ ለህዝብ ሰላም ጠንቅ ለሀገር ግንባታ ኪሳራ ይሆናል። የሚወደድ መሪ የሚደብቀው የሌለው መሪ፣ ህዝቡ ስህተቱን ይሳሳቱለታል እንጂ በስህተቱ አይሳለቁበትም። እንሆንለታን እንጂ ይሆናል፤ እንበረታለን እንጂ ይበረታል፤ አይባልበትም ። ይፀለይለታል እንጂ አይፀልዩበትም።
የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ በሥነ- ምግባር ደረጃ ሊከተላቸው የሚገቡ መሰረታዊ ነገሮች አሉት፤ ብዬ አምናለሁ። በዚህ የከበረ ሃሳብ ውስጥ፣ ሌላውን መውደድ ወይም በምክንያትም ቢሆን ጨርሶ አለመጥላት፣ አለማደም፣ ለኪዳን ታማኝ መሆን፣ ቸርነት፣ ሌሎችን ከሥጋት መጠበቅና በበጎ መተባበርን የመሳሰሉ ባህሪያትን የያዘ እውነት ነው።
ለመጨመር ቢያስፈልግ ደግሞ፤ “በሌላው ላይ እንዲደረግ የማልወደውና፣ እኔም በሌላው ላይ ልፈፅመው የማይገባኝ ሐሜት አለ፤ አድልዎ አለ፤ ጥላቻ አለ፤ ፍርሃት፤ ክህደት፣ ጭካኔ፤ የመብት ጥሰት፤ ማግለል፤ ማንቋሸሽ፣ ኢ-ፍትሐዊነት አለ ። ”
የሰው ልጅ ወደዚህ ምድር የመጣለትን የምስጋናና የመልካምነት ህይወት የሚያውከው ዋናው መንስዔ ጥላቻ ነው። ጥላቻ የቅናት ታናሽ ወንድም የጭካኔ ወላጅ አባት የፍርሃት ጥንስስ ነው። አንድ ሰው ሌላውን ለመጥላት እርሱ ከጠላው ሰው የሚለይበትን አንዳች ነገር ማየት በቂው ነው።
በሌላ በኩል፣ ሰው የተወለደበትን ዘር፣ ሥራውን፣ ዜግነቱን፣ ውበቱን፣ የትምክህቱ ምክንያት አድርጎ ከተንጠባረረ ሳይነግድ ያተረፈ፣ ሳይደክም ባገኘው ነገር የሚንጠራራ ግብዝና በሰው አዝመራ የሚዘንጥ ገመሬ ዝንጀሮ ሆኗል፤ ማለት ነው።
በቢሮ ውስጥ ባለ የአሠሪና ሠራተኛ ወይም የአለቃና ምንዝር ግንኙነት ውስጥ፣ መሪው ሲያነጥስ መሐረብ ልሁንልህ፤ አለቃው ሲያዝን “እኔ ላልቅስልህ”፣ ሲቆጣ “እኔ ልናደድልህ” የሚል ሰው የሰብዕና ጉድለት ያለውና መልካምነት የጎደለው ነው፤ ስለዚህ እውነተኛ ማንነታችንን ሳንደብቅ መግለጽ፣ እኛንም ነፃ ያወጣናል ብዬ አስባለሁ። ካለበለዚያ ትርፉ ስቃይ ነው።
ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር በነገሰበት ከመቀበል ይልቅ መስጠት በሰፈነበት በዚያ ስፍራ መቻቻል ብቻ አይደለም ሃይልና ራስ መግዛት ዋነኞቹ መሳሪያዎች ሆነው ታገኙዋቸዋላችሁ። አንዳንድ ሰው አንዱ ለቻለው ለሌላኛው ተብሰክሳኪ፣ አንዱ ለተሸከመው ሌላኛው አለክላኪ ሆኖ ይገኛል።
እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ወደድኩ። በፍቅር ተዋድደው ይኖሩ የነበሩ ባልና ሚስት በትዳራቸው ላይ እያሉ፣ በሂደት ሚስት ውብ የሆነው ቆዳዋ ደራሽ በሚመስል በሽታ መጠቃት ጀመረ። ይህም ሆኖ ባል ባህሪውን አልለወጠም። ጎረቤቶቿ እንጂ።
እርሱ ደግሞ ለሥራ በወጣበት የመኪና አደጋ ያጋጥመውና ዓይኑ ይታመማል፤ ዓይነ-ስውርም ይሆናል። ሁለቱም ርዕስ በርዕሳቸው እየተረዳዱ ህይወትን ይገፏት ጀመረ። ከጥቂት ዓመታት በኋላም ሚስት ትሞታለች።
ጎረቤታቸው የነበረ አንድ ሰው በመንገድ ያገኘውና፤ መቼም መቻል ነው፤ መጽናናት ይገባሃል፤ ነገር ግን እንደ እርሷ የሚመራህ ሰው አሁን ከየት ታገኛለህ፤ ጊዜው የጥድፊያ ነው፤ በዚያ ላይ ልጆችህ ለእገዛ አልደረሱልህ፤ ለመብላት እንጂ ለመሥራት አይመጥኑም እያለ የመከራውን ስፋት ይደረድርለት ገባ። ሚስትህ መቼም ምቹ ረዳትህ ነበረች፤ ሲል የእጦቱን ስፋትና ጥልቀት ያብራራለታል፤ ካጣው ይልቅ ያሳጣው ደስ ያለው ይመስል፤ ይናገረዋል። ሰውየውም ሌላ ረዳት አያስፈልገኝም፤ ምክንያቱም ሚስቴ በህይወት በነበረች ጊዜ ሁሉ፣ ዓይነ ስውር አልነበርኩም፤ ሚስቴ ግን በደረሰባት ህመም ትሸማቀቅ ስለነበረ ጉድለትሽን አላየሁም፤ ለማለት የተጠቀምኩበት ዘዴ ነው፤ ሲል ይመልስለታል።
ሁላችንም የምንወደውን ሰው ጉድለት የማናይበትን እምነት መፍጠር ከአፍቃሪ ልብ የሚጠበቅ ቸርነት ነው። የዚህ ሰውዬ ብልሃት አስቸጋሪ ቢመስልም ለአፍቃሪ የሚከፈልን የከበረ ዋጋ ያሳየናል። ለልዩነት የታወረ ልብ ስንል፤ በዘር የማናዳላ፣ በቀለም የማንሸማቀቅ፤ በህመም የማንከዳ፣ በንብረት የማንጎዳ፣ ራሳችንን የማንቆልልና የማንቀባረር መሆን ይጠበቅብናል፤ ማለት ነው።
ይቅርታን በኑሮ ደረጃ ባለመክፈል የምናይ፣ ያደረና የከረመ የጠነዛና የሻገተ በደል እየቆሰቆስን የማንራገም፤ አንቺ እኮ እንዲህና እንዲያ እንዳደረግሽኝ የምረሳ ይመስልሻልን ? የምንል፤ ሌሊቱ እንዳይነጋ የክረምቱ ጉም ጨለማ እንዳይገፍፍ የምንፈልግ ምስኪኖች መሆን የለብንም። ስለዚህ ይህንን መሰል የጥላቻ አጥር በመገርሰስና በቤት ውስጥ እንዳይኖር በማድረግ፣ በሀገር ደረጃም በምንሠራበት መ/ቤትም ለፈውስ ምክንያት እንሁን።
ህፃን እንኳን ቢሆን ሰው የበደልና የክፋትን ጥግ የመረዳት አዕምሯዊ ብቃት አለው። ስለዚህ በተቻለን መጠን፣ በልጆቻችንም ፊት ቢሆን በሌሎች ላይ በበደል ስሜት አንነሳሳ። ለልጁ የምናወርሰው ያልተገባ ክፉ ቂም ውርስ ይኖራልና ፤ በጥብቅ ልናስብበት ይገባል።
በትምህርት ቤት ሳለሁ የማውቀው በጣም ተደባዳቢና ስለት ነገር ከኪሱ የማያጣ ልጅ ነበረ። ልጁ፣ ድብድብ ከመውደዱ የተነሳ ፊቱ ከመዥጎርጎሩ ሌላ በማንኛውም ሰዓት ለመደባደብ የማያመነታና የቀረው ነገር የሌለ ነው፤ የሚመስለው። እንዲያውም ያስቸገራቸውን የገዛ ወንድማቸውን በእርሱ ያስደበደቡ ሴቶች ተማሪዎች እንዳሉ እንሰማ ነበር፤ አስቂኝ ቢመስልም ነገሩ።
እና ከዕለቶች በአንዱ ቀን ጫወታ ተነሳና፤ ( “መሶ” ነው የምንለው። ) መሶ ለምንድነው እንዲህ “ፀብ ያለሽ በዳቦ” የሆንከው ? ለምንድነው በትንሹም በትልቁም ዱላ የሚያምርህ ? ብዬ ጠየቅሁት።
ሳያቅማማ የመለሰልኝ፤ እንዲህ ሲል ነው። ልጅ ሆኜ እናቴን አባቴ በስለት ወግቶ ሲገድላት በዓይኔ አይቻለሁ። ህፃን ስለነበርኩና አቅም ስላልነበረኝ ያንን ብድር መመለስ አልቻልኩም። አባቴ በኋላ እስር ቤት ገብቶ ይሙት ይኑር አላውቅም ፤ አለኝ። እናስ? ስለው ፤ እያንዳንዱን ቡጢ ሰው ላይ ሳሳርፍ ለእናቴ የተበቀልኩ፣ ዱላው ሲያርፍብኝ ደግሞ የእናቴን ህመም የተጋራሁ ነው፤ የሚመስለኝ፡ ሲል መለሰልኝ።
የቂም ውርስ ይሉሃል ይኸው ነው። በዚያን ወቅት የመለስኩለትን ነገር አላስታውሰውም፤ አሁን ግን ሳስበው ከቤት የተነሳው የቂም ቋሳ እንዴት ሥነ-ልቡናዊና ማህበራዊ ቀውስ እንደፈጠረ ማጤን አያቅትም ።
ከዚህ ይልቅ ለፀብ ልባችሁ የደከመ፤ ለፍቅር የበረታ መሆን ብልህነትም ነው። ከሁሉም ከሁሉም ግን በደረሳችሁበት ስፍራ ሁሉ በልዩ ልዩ ምክንያት የሚተከለውን የጥላቻ አጥር መስበርና የተሰበረውንም የአጥር ፍራሽ ወደ መገናኛ ድልድይነት መቀየር የተገባ ነው።
ዛሬ ዛሬ ውጊያው በጥይት አረር፣ በሚሳይል ሮኬትና በቦንብ ድንጋይ፣ ከመለወጡ በፊት፣ የጥንቶቹ እሥራኤላውያን የሚታወቁበት ድንቅ ነገር ከጠላታቸው የሚወረወረውን ማናቸውንም ድንጋይ መከላከያ ካብ ይሠሩበት እንደነበር ታሪክ ያወሳቸዋል። እንዲሁም አንተ ከማንኛውም ክፉ የሚወረወርን የጥላቻ ድንጋይ የመለያያ አጥር ለመሥራት ሳይሆን፤ ህመሙ የሚፈጥረውን ክፋት ወደጎን በመተው ለድልድይነት ማዋል የትውልድ ካሳ ያስገኛል።
አዎ እደግመዋለሁ፤ ክፉዎች ባይኖሩ የደግነትን ዋጋ፣ የፍቅርን ፀጋ፣ የመልካምነትን ወርቅነት፣ የለጋስነትን ዕንቁነት ማጣጣምም አንችልም ነበረ፤ ይሁንናም ሆን ተብለው የሚዘሩ የጥላቻ ዘሮች በየትኛውም ደረጃ ከጠቀሜታቸው ጉዳታቸው፣ ከገንቢነታቸው አፍራሽነታቸው ስለሚያዘነብል ሁላችንም ለዚህ የምናደርገውን መዋጮ ትተን ለሀገር ፈውስ አበክረን እንሥራ።
ጥላቻ የሚያመነጨው ፍርሃትና ከእርሱም የሚመነጨው ጭካኔ ቤት ያፈርሳል፤ ማህበረሰብ ይበትናል፤ ወገን ያፈናቅላል፤ ሀገርን ያሳምማል። ስለዚህ ሐገሩ እንድትፈወስ የሚፈልግና ለዚህም ራሱን ያዘጋጀ ዜጋ ከቶውንም የጥላቻ ፈረስ ለመጋለብ አይኮለኩልም። የፀብ መዝሙር አያስዘምርም፤ የጥላቻን ጥጃም አያሳድግም፤ ጥላቻን ራሱን በመጥላት፣ የንፍገትን ሰንሰለት ፣ በመበጣጠስ መቆም ይገባዋል፤ ሰይፍን ያነሱ በሰይፋቸው ሲወድቁ፣ ስስታሞች አንድም ሲወድቁ፣ አለዚያም በስግብግብነታቸው ገመድ ሲታነቁ አይተናል ብለናልና፤ ለሀገር ፈውስ የጥላቻን አጥር በማፈራረስ፣ ቅንጣት በሚያህለው በጎነታችን ግዙፍ፣ የፍቅር ቤትና ሀገር እንገንባ። የተሰጠንን ትናንሽ የክፋት የቤት ሥራ ሐረግ እየመዘዝን በየተገኘው መድረክ ልንጠፋ ነው፤ “ወዮልን” ማለት እናብቃ!!
ለሁላችሁም መልካም የማሰብ የመናገርና የመስማት፤ ሳምንት ይሁንላችሁ!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ