ይህቺ ምድር በሳይንስና ምርምር ዘርፍ እጅግ የተሳካላቸው ኢትዮጵያውያንን አለምን አጀብ! ያሰኙ ሀበሾችን አፍርታለች። ቁጥራቸው ቢያንስም በአለም መድረክ የሀገራቸውን ስም ከፍ አድርገው ያስጠሩ፤ ምጡቅ በሆነ አዕምሮአቸው አለምን ያቀኑ ኢትዮጵያውያን፤ ከፍተኛ በጎ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ሊህቃን ስራቸው የሰው ልጆችን ስልጣኔ አቅርቧል። ለነበረባቸው ዘርፈ ብዙ ችግር በምርምር መፍትሄ አግኝተዋል።
የ“ራስ ወርቅ…” ሆነና ነገሩ ስራቸውን ማድመቅ ተግባራቸውን ማወደስ ላይ ብዙም ልምድ የለንም። የደረሱበትን ታላቅ ምርምርና የፈጠራ ስራ ማስተዋወቁ ላይ እጅግም ነን። ከኛ ይልቅ ሌላው ስለነሱ ብዙ ይልላቸዋል። አውቀናቸው ስራቸውን በማስተዋወቅ ላይ ብንሰንፍም ከምናውቀው በላይ ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ገና ብላቴና ነበር። ያውም የአራት አመት ህፃን፤ ግን ደግሞ የተመለከተውን ነገር እንደሌሎች የእድሜ እኩዮቹ አይቶ የማያልፍ፤ ሰምቶ ችላ የማይል ህፃን ነበር። የፊደል ቅርፅ መለየት በሚጀመርበት፤ የቀለም ቆጠራ “ሀ” በሚባልበት እድሜ ላይ ነገሮችን አጢኖ “ምነድነው?” ብሎ ጠይቆ ከማወቅ ባለፈ “እንዴት ሆነ?” ብሎ የተመለከተውን መመርመር፤ “ለምን?” ሆነ ብሎ ምክንያቱን ማሰብ አልተለመደም። ይህ ህፃን ግን በዚህ እድሜው ምርምር የጀመረ፣የተመለከተውንና ያየውን ማለፍ የማይወድ ነበርና ከጥያቄ ከፍ ባለ ድርጊት ለማወቅ መማሰን ጀመረ።
ፍጥረታት ምድር ላይ እየዳሁ፤ ወፎች ከፍ ብለው መብረር እንዴት ቻሉ? በብላቴናው አዕምሮ ውስጥ ለተፈጠረው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ጠፋ። በግል ጥረት መልስ ማግኘት ፈለገ። ስለምላሹ ሁሌ ማሰብ አዘወተረ። “ውስጧ በምን ስሪት ቢታነፅ፤ ተፈጥሮዋ ምን ቢሆን ነው?” ብሎ መመራመር ጀመረ። ብሩህ የሆነ የልጅነት አዕምሮው በአካባቢው ያሉ ነገሮችን የማጥናትና ምንነታቸውን የማወቅ ጉጉት ፈጠረበት።
አንድ ቀን በአጋጣሚ የሞተች ወፍ አግኝቶ አንገቷን በመቁረጥ ውስጧ ያለውን የተለየ ማሽን(ለሱ በወቅቱ የተጠቀመበት ቃል ነው) ለመብረር ያስቻላት አቅም ምን እንደሆነ በመመርመር ላይ ሳለ ወላጅ እናት ትመለከታለች። በድንጋጤ ምን እያደረገ እንደሆነ በጩኸት ትጠይቃለች። እናቱን ያየው ህፃን “እናቴ ይሄ ወፍ እንዴት ሊበር እንደቻለ ሆዱ ውስጥ ያለው ማሽን ምን እንደሆነ እያየሁ ነው።” በማለት ጥያቄዋን መለሰ ።
ልጇ የወፍ ሆድ ቀድዶ በእጆቹ ሲነካካ የተመለከተችው እናት በድንጋጤ እሪታዋን ታቀልጠዋለች። የጩኸቷ ምክንያት ደግሞ “ልጄ ተለክፏል፤ አዕምሮው ተነክቶብኛል” የሚል ነበር። ባዩት ነገር የተደናገጡት እናት ከቤተሰብ ጋር በብዙ መከሩ በመጨረሻም ለልጃቸው መዳኛ ብለው የመረጡት ፀበል ነበረና እሱን ሞከሩ።
እናት ልጃቸውን ወደተለያዩ የእምነት ቦታዎች ወስደው ፀበል በማስጠመቅ ታመመ ያሉት ልጃቸው ፈውስ ያገኝ ዘንድ መፍትሄ ፈለጉ። ልጁ ግን በአንፃሩ ተባብሶበት ጉዳዮችን መመርመሩን ቀጠለ። የያዘው ክፉ መንፈስ ሳይሆን ክፉ ጉዳዮችን ከሰዎች ላይ የሚያስወግድ ምጡቅ አዕምሮና ብሩህ ሃሳብ ነበርና እያደር መልካምነቱን እናቱም ቤተሰቦቹም ተረዱት።
ገና አስር አመት ሳይሞላው አንዲት ዝንብ ይዞ ክንፍዋን እየገነጣጠለ መብረር ትችላለች? አትችልም? እያለ ሲመራመር ያዩትና ስለ ልጁ ይበልጥ የተረዱት አያቱ ድጋፋቸውን መስጠት ጀመሩ፤ የልጅ ልጃቸውን ሁኔታ ተረድተው ነበረና አበረታቱት። “ወደፊት ጎበዝ ተመራማሪ ይወጣሀል ጎበዝ ልጄ!” ብለው አሞካሹት።
ይህ ብላቴና ዛሬ ላይ ተግባሩ ልቆ አለም ካፈራቻቸው ውድ ሳይንቲስቶች መሀል ይጠቀሳል። ፕሮፌሰር ይልማ ጥላሁን፤ (ከዚህ በኋላ አንቱ እላቸዋለሁ)በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለበርካታ አመታት የምርምር ስራዎችን በመስራት የሰውና የእንስሳት በሽታዎችን ለማከምና በክትባት መከላከል የሚያስችሉ መድኃኒቶችን በመቀመም አለም አቀፍ እውቅናን አትርፈዋል። እኚህ ስማቸው የናኘ፤ ተግባራቸው የጎላ ሳይንቲስት አለም በስስት የሚመለከታቸና ከርሳቸውም ብዙ ያተረፈ ለመሆኑ የምርምር ውጤቶቻቸው ይመሰክራሉ።
የደስታ በሽታ ከብቶችን በመፍጀት በምስራቅ አፍሪካ፤ ብሎም በሀገራችን ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሎ እንደነበር ድርሳናት ይናገራሉ። በተለይም፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ እልቂት አስከትሎ ለነበረው የደስታ በሽታ ክትባትና ፈውስ የሚሆን መድኃኒት ለመጀመሪያ ጊዜ በምርምር በማግኘት በሀገራችንና በመላው አለም የከብቶችን እልቂት ታድገዋል።
ፕሮፌሰር ይልማ ጥላሁን፤ ይህን እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ከብቶች ያረገፈውን በሽታና የከብት እልቂት ተብሎ ይታወስ የነበረውን ጊዜ ታሪክ ሆኖ እንዲቀር ያደረጉ ታላቅ ሳይንቲስት ናቸው። ለዚህ የሀገርና ለአለም ትኩሳት ለነበረውና እንስሳትን ለፈጀው በሽታ መድኃኒት በመፍጠር ብቻ አላበቁም። የሰዎችን እና የእንስሳትን ጤና የሚጎዳውን የፈንጣጣ በሽታ ክትባትና መድኃኒት በተሻሻለና ቀላል በሆነ መንገድ በማዘጋጀት ህክምናው ቀላል እንዲሆን አድርገዋል።
ፕሮፌሰር ይልማ ጥላሁን በበዛ ግኝታቸው አለም የሚነጋገርባቸው፤ በህክምናው ሳይንስ አንቱ የተባሉ፤ ተማሪዎቻቸውን ስኬታማ ያደረጉ ታላቅ ምሁር ናቸው።እኚህ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት በአሁኑ ሰዓት የሀገራቸው ብሎም የአፍሪካን ወጣቶች በሳይንስና በምርምር ትልቅ የሚያደርጋቸውን አቅም ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
በዚህም በልዩ ልዩ የአፍሪካ ሀገሮች ላይ የምርምር ቤተ ሙከራዎችን በመክፈትና ወጣቶችን በማስተማር ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ። በሚሰሩበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባደረጉት የላቀ ምርምር ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ከሌሎች ሙያተኞች ጋር በመሆን ያቋቋሙት ቤተ ሙከራ በአለም ቀዳሚ ከሚባሉ የምርምር ቤተ ሙከራዎች አንዱ መሆንም ችሏል። ከአለም አቀፍ የጤና ምርምር ተቋማትና መንግስታት ጋር የተለየዩ የምርምር ስራዎች በመስራት አስደናቂ ውጤቶችና ከፍተኛ ተቀባይነትንም ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ።
ፕሮፌሰር ይልማ ከቻይና መንግስት ጋር በመተባበር በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ የተባለ የምርምር ማዕከል ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ይናገራሉ። እኚህ በምርምር ስራቸው አለምን ያስደመሙ ሰው ለሀገራችን ሳይንስና ተክኖሎጂ እድገት ወጣቶችን በዘርፉ ማብቃት ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ። የባለ ብዙ ራዕዩንና ታላቁን ምሁር ስራዎች በወፍ በረር የቃኘንበት ፅሁፍ ይህንን ይመስላል።ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መስከረም 30/2012
ተገኝ ብሩ