ሀይቲ በካሪቢያን ባህር ውስጥ ከሚገኙ ደሴቶች አንዷ ስትሆን 27.7 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋትና 10.8 ሚሊየን ህዝብ ያላት አገር ናት። አብዛኞቹ ህዝቦቿም ከደቡብ አሜሪካ የፈለሱ እንደሆነ ይነገራል። የነፃ ገበያ ኦኮኖሚን የምትከተለው ይህች አገር የነፍስ ወከፍ ገቢዋም 1800 የሜሪካ ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። አገሪቷ በአሜሪካ አህጉራት ከሚገኙ አገራትም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። ህዝቦቿም በድህነት፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በደካማ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የጤና ችግር በመንግስታቸው ላይ ምሬት ያሰማሉ።
ሰሞኑንም ይህንኑ መነሻ በማድረግ አብዛኞቹ የአገሪቱ ዜጎች ከፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ ሰንብተዋል። በዚህም የሰው ህይወት እስከመጥፋት ደርሷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልዑካን ቡድንም ችግሩን ለመፍታት ጥረት ቢጀምርም እስካሁን ስኬታማ አልሆነም። በዚህ የተነሳ ውጥረቱ አሁንም ቀጥሏል። በዚህ ዙሪያ ሰሞኑን አልጀዚራ ይዞ የወጣውን ዘገባም እንደሚከተለው አቅርበናል።
እንደመነሻ
ለወራት የዘለቀው የሀይቲ የተቃውሞ ሰልፎች ሁሉም ቦታ እየተዳረሰ ይገኛል። ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ እያደገ የመጣው የነዳጅ እና የምግብ እጥረት ህዝቡ አደባባይ እንዲወጣ አድርጎታል። ሰልፈኞቹ በአሜሪካ እየተደገፈ የሚገኘውን የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ጆቬኔል ሞሲ ከስልጣን እንዲለቅ ጥያቄ አቅርበዋል። ቀውሱ የተጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን የደሴቲቱን ህዝብ በተደጋጋሚ እያጠቃ የሚገኘው የተፈጥሮ አደጋ ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ አድርጎታል። ሀሪኬን የተባው አውሎ ነፋስ ቤትን፣ የምግብ ምርትን፣ የኑሮ ሁኔታዎችን እና መሰረተ ልማቶችን አፍርሷል። በተጨማሪም አውሎ ንፋሱ የሀይቅ ውሃዎች ወደ ደረቃማ መሬት እንዲለወጡ አድርጓል።
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሀይቲ ስላለው ሙስና እና ስለ አስተዳደራዊ ችግሮች ዘገባ ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ የአየር ንብረቱ ለውጥ በፈጠረው አሰቃቂ ቀውስ ምክንያት ያለው ችግር በጣም እየከፋ ይገኛል። የቅኝ ተገዥነት፣ የኒዮሊበራሊዝምና የአየር ንብረት ለውጥ ተደማምረው ችግሩን አባብሰውታል። በእርግጥ አሁን በሀይቲ ውስጥ እየተከናወነ ያለው ነገር እጅግ በጣም ከባድ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ደሴቷ ሙሉ ለሙሉ ልትጠፋ እንደምትችል በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት እያስገነዘቡ ይገኛሉ።
የፔትሮ ካርቤ እና የነዳጅ ቀውስ
እ.ኤ.አ 2006 ጥር ወር ሀይቲ የቬንዝዌላ አንድነት ትብብር ፕሮግራም ወይም ፔትሮ ካርቤን ከተቀላቀለች በኋላ የነዳጅ ዘይት በቅናሽ ዋጋ ማስገባት ጀመረች። ሀገሪቱ በቀን 60 ሺ በርሜሎችን በቅናሽ ዋጋ ስትገዛ ግማሽ ዋጋውን በ25 ዓመታት ውስጥ ለመክፈል በመስማማት ነው። ክፍያው በገንዘብ ከሆነ አንድ በመቶ ወለድ ለመቁረጥ በገንዘብ ካልሆነ ደግሞ ሀይቲ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች በነፃ ለቬንዝዌላ ለመስጠት ስምምነት ተደርጓል። ይህ ሁኔታ ለመሠረተ ልማት እና ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተነሳሽነት ለመፍጠር እንዲያስችል ሀብቶችን ለማሰባሰብ እና የግብርና ምርትን ለማሳደግ ታስቦ የተከናወነ ነው። ይሁን እንጂ ከፍተኛ ሙስና በመንሰራፋቱ መንግስት ያገኘውን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችዶላሮ እንዲባክኑ አደረገ። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ቬንዝዌላ እዳዎቹን ለመሰብሰብ ዝግጅት ጀመረች።
የቬንዝዌላ ኢኮኖሚ እየተዳከመ ሲመጣ ለሀይቲ ትሰጥ የነበረውን የነዳጅ ማጓጓዝ ስራ እአአ 2018 መጋቢት ወር ላይ አቆመች። በሀይቲ ቀውሱ የተከሰተው የኃይል አቅርቦት ድጎማዎችን ለማቆም መንግሥት ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ሐምሌ ወር ባደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት ነበር:: ይህም የነዳጅ ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ እንዲጨምር አድርጓል። ውሳኔው አገሪቱ ዕዳዋን እንድትከፍል የሚያግዘውን የ96 ሚሊዮን ዶላር የብድር እቅድን ከያዘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጫና ተደርጎበት ነበር::
እንዲሁም የነዳጅ ድጎማዎችን እንዲያቋርጡ ጥሪ ያቀረቡት የቡድን 20 አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ናቸው። በተጨማሪም እርምጃው በ2030 የፓሪስ ስምምነት መሠረት የሀይቲ የጋዝ ልቀትን በ31 በመቶ ለመቀነስ የገባችውን ፖሊሲ አንፀባርቋል። በፔትሮሊ ካርቤ ፕሮግራም አውጪው በኩል የነዳጅ አቅርቦቱ መቆራረጡ ደግሞ የሀይቲ መንግስት ወደ አለም ገበያ እንዲሄድ በተለይም በአሜሪካን የተመሠረተውና የኃይል አቅራቢ ከሆነው ኖሚየም ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ጋር እንዲዋዋሉ አስገድዷል። መንግሥት ከፍተኛ እዳ ውስጥ እየገባ በመምጣቱ በአሁኑ ጊዜ የነዳጅ አቅራቢዎች ወደ 130 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ አለበት።
የነዳጅ ድጎማዎች ቀውስ
የሀይቲ መንግስት ድጎማዎችን ለመቀነስ በዓለም አቀፍ ግፊት በመሸነፍ የውጭ አጀንዳዎችን በማስተናገዱ የገዛ ወገኖቹን ህልውና አደጋ ላይ ጥሏል። አገሪቱ ከዓለም አቀፉ የግሪን ሃውስ ጋዝ ልቀት ዜሮ ነጥብ ዜሮ ሁለት ከመቶ የሚሆነውን ታመርታለች። እናም የአየር ልቀት ቁጥጥር ለማድረግ ህዝቧ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። የነዳጅ ድጎማዎች ከሀይቲ አጠቃላይ አገራዊ ምርት/ጂዲፒ ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ ብቻ ሲሆን መንግስት በድህነት የተያዙ ዜጎችን መደገፍ የሚችልበት አንዱ መንገድ ነበር:: እ.ኤ.አ. በ2010 ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እና በየዓመቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ከሚያስከትለው መዘዝም ጋር እየታገሉ ይገኛሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አውሎ ነፋሱ ካስከተለው ችግር በኋላ ብዙ ማህበረሰቦች የኃይል አቅርቦት ከመጠቀም ተቆራርጠዋል:: የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት ነዳጅ በጣም አስፈላጊ ነበር። የአገሪቱ ኢኮኖሚም መውደቅ ምክንያት አብዛኛዎቹ ሰዎች መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ተቀጥረው እንዲሰሩ አድርጓል። በእርግጥ እነዚህ የኃይል ድጎማዎች በቀን ሁለት ነጥብ 41 ዶላር በመመደብ ስድስት ሚሊዮን ለሚበልጡ ድሃ የሀይቲ ዜጎች ድጋፍ ይሰጥ ነበር።
እ.ኤ.አ. ከ2018 አጋማሽ ጀምሮ ቀውሱ ደረጃ በደረጃ እየተባባሰ በመምጣቱ በቅርቡ በመንግስት ላይ የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲባባሱ አድርጓል። ዛሬ ሀይቲን ለሚጎበኝ ማንኛውም ሰው የለውጥ እርምጃዎች እና የነፃ ገበያ አማራጮች በአገሪቱ የተከሰቱትን የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች፣ የመንግስት መዳከም፣ የለጋሽ አገራት ሙስና እና በጭራሽ ማለቂያ የሌለው የዕዳ ቀውስ መፍታት እንደማይችሉ ይረዳል።
ከተከሰተው ነዳጅ ችግር ለመላቀቅ ጥረት ቢያደርጉም ለአየር ንብረት ለውጡ በጣም የተጋለጡ ከሦስቱ ሀገሮች መካከል በመሆናቸው ከአየር ንብረት ለውጡ እያዳከማቸው ይገኛል። ለሚደረጉት ማንኛውም እንቅስቃሴዎች አለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በተደረገ ጥናት መሠረት ሀገሪቱ እንደ አረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ ያሉ ዓለም አቀፍ እርዳታዎችን በመጠቀም የተመደበላቸውን ፋይናንስ ለማግኘት እየታገሉ ይገኛሉ። የቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች እና አንድ ላይ የተቀመጡ መመዘኛዎች መንግሥት እነዚህን ሀብቶች ለማዳረስ ፈጽሞ የማይቻል አድርጎበታል።
ይህ አገሪቱ የአየር ንብረት የመቋቋም አቅሟን ለመገንባት ፈተና ሆኖባታል። አሁን በተፈጥሮ አደጋ በሚከሰት እያንዳንዱ አደጋ ውጤቱን ለመቆጣጠር በአጭር ጊዜ እፎይታ ላይ መድረስ አለበት። ከአየር ንብረት ለውጥ በፊት ቅኝ ግዛት ተመሳሳይ አደጋ አድርሶ ነበር። የሀይቲ ቀውስ የቅኝ ገዥነት፣ የኒዮሊቤሊያሊዝም እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተቀመጠው ስትራቴጂ ብልሹነት ያመጣው ውጤት ነው። በእያንዳንዱ ድርቅ እና አውሎ ነፋስ በሚከሰትበት ወቅት እየተባባሰ የመጣው የአካባቢ ብክለት እንዲሁም መሬትና ጫካዎች መውደም የሀይቲ የፈረንሣይ ቅኝ ተገዥነት ታሪክ ያስታውሳል:: ይህም የሀገሪቱን ኋላ ቀርነትና ድህነት እንዲባባስ አድርጎታል።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሀይቲ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች በኋላ በአሜሪካ ተጽዕኖ ውስጥ ወድቃለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እራሷ ነጻ ማውጣት አልቻለችም። አሜሪካ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል አገሪቷን ከተቆጣጠረች በኋላ ደጋግማ በአገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች:: ነገር ግን የተቃውሞ ሰልፈኞቹ የሚጠይቁት አገሪቱን እየመራ የሚገኘው ፕሬዚዳንት መውረድ እንዳለበት ነው።
የሀይቲ ህዝብ ፖለቲከኞቻቸውን በኃላፊነት እንዲይዙ እና ሙስናን እንዲዋጉ እያገዛቸው ቢሆንም፣ አሜሪካ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸውን የኒዮሊቤራል ፖሊሲዎችን በሀገሪቱ ላይ እየጫነች ትገኛለች። አሜሪካ የሀይቲ ኢኮኖሚን በተመለከተ ያላት አመለካከት በዋነኝነት ትኩረት ሰጥታዋለች። አገሪቱ በአሜሪካ እና በካናዳ ኮርፖሬሽኖች የሚለገስ 20 ቢሊዮን ዶላር ተቀማጭ ገንዘብ አላት።
ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ መፈለግ
በአሁን ወቅት ዓለም በሀይቲ ለሚከናወነው ነገር ትኩረት መስጠት የጀመረበት ጊዜ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የኒውክለራላዊ እና የኒዮ-ግሎባላዊ ፖሊሲዎች የዓለም ኢኮኖሚ የሚቆጣጠሩበት ጊዜና የቀረው የዓለም ቀውስ ውስጥ እንደሚገባ በመረዳታቸው ነው። ሀይቲዎች አሁን በአሜሪካን የተመሰቃቀለው ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ በአገሪቱ ያለውን ችግር ከአየር ንብረትና ከኋላ ቀርነት ጋር ተደማምሮ እያባባሰው መጥቷል ብለው ያምናሉ። ህዝቡ በራሱ እንቅስቃሴ ተቃውሞዎችን እያሰማ ይገኛል። የአገሪቱ ምሁራን ሀሳቦቻቸውን በግልፅ እያወጡ አይደለም በዚህም የአገሪቱ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር ይገኛል።
እስካሁን ድረስ የዓለም የአየር ንብረት እንቅስቃሴ በሀይቲ ውስጥ ምን እየሆነ እንዳለ ሙሉ በሙሉ ችላ ብሎት ነበር። ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ስምምነት እንዲመሰረት ጥሪ ማድረጉ የሚያስመሰግን ቢሆንም፣ እንደ ሀይቲ ያሉ ቦታዎችን የሚያጠቃልል ቀጣይ የአየር ንብረት እንቅስቃሴ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በእርግጥ ይህ አዲስ ስምምነት ከሆነ ለሀይቲ የሚበጀውን እናውቃለን የሚለውን አባባል መከተል አይችሉም። መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመገንዘብ መሰራት ከተቻለ ሌሎች አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት ለውጥ ሊመጣ ይችላል።
ወደ አዲስ የኃይል ስርዓት ሽግግር ሊሳካ የሚችለው ዓለም አቀፉ አገራት አሁንም ያለውን ኃይል እና የአየር ንብረት ፍትህ አስፈላጊነት ከተገነዘበ ብቻ ነው። የአየር ንብረት እርምጃ አዲስ እና ቀጣይነት ያለው የተለየ ሁኔታን ሊያመጣ የሚችለው ኤጀንሲውን እና የታዳጊ አገራት እና የአገሬው ተወላጅ እንቅስቃሴዎችን ዕውቀት ከተገነዘበ እና በዚህ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ብቻ ነው።
በሀይቲ ውስጥ አብዛኛውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው የሚያሟሉበት ዝቅተኛ የስራ መደብ ያላቸው ዜጎች አሉ። የህዝቡ ብዛትና የስራ ፍላጎቱ የተጣጣሙ አይደሉም። የአገሪቱ መንግስት በተቃውሞ ሰልፎች ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ እና የተጠያቂነት ሂደት ማመቻቸት አለበት። አገሪቱ ወሳኝና የማንም ጣልቃ ገብነት የሌለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያስፈልጋታል። እንቅስቃሴው ከሙስና የፀዳ በማድረግ እና ኢኮኖሚውን ከውጭ ንግድ እንቅስቃሴ በማላቀቅ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ማሸጋገር አለባቸው። ሀይቲያን እራሳቸው የአየር ንብረት መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት ቀጣይ ስራቸው ሊሆን ይገባል። ዘገባው የአልጀዚራ ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
መርድ ክፍሉ