ከእለታት አንድ ቀን ብር ቸግሮኝ
የማዘርን ቦርሳ ፈልጌ አጣሁኝ
ተናደድኩኝና ሀሳቤን ለውጬ
እቃ ልሸጥ ወሰንኩ ከጓዳ አውጥቼ
የሚሸጠውን እቃ ሳወጣጣ ሳለሁ
ድንገት ድስት ስር አስር ብር አገኘሁ
በደስታ ብዛት እጆቼን እየሳምኩ ከቤቴ ስወጣ
ደጓ ማዘርዬ አየችኝ አፍጥጣ
‹‹መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ›› የምትለውን ስንኝ እየደጋገምን ወደ ትምህርት ቤት ማልደን የምንሄድበት ሁኔታ አሁንም ድረስ በአይነ ህሊናዬ ይታየኛል። መስከረም ወር የሁሉም ነገር የመጀመሪያ ነች በተለይ ለተማሪዎች ከነበሩበት ክፍል አንድ ጨምረው ስለሚመጡ ደስታና ፍርሃት ይቀላቀልባቸዋል። ምክንያቱም አዲስ ክፍል ሲገባ ሊከብድ ይችላል፣ አስተማሪዎቹ ሀይለኛ ሊሆኑ ይችላሉ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ናቸው።
እኔ የትምህርት መክፈትን ተከትሎ ከማይረሱኝ ሁነቶች መካከል በተለይ የደብተር መሰረቅና መነጠቅ ከፍተኛውን ድርሻ መያዙ ነው። እርግጥ ነው፤ ትምህርት ቤት ውስጥ እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ ታሪክ አለው። እኛም በትምህርት ቤት ያሳለፍናቸውን አንዳንድ አይረሴ ሁነቶችን እያስታወስን እናውጋ።
አይ የኔ ነገር ከላይ ያስቀመጥኩት ግጥም እንዴትና በምን ምክንያት እንደተፃፈ አላጫወትኳችሁም። መቼም ሌባ ነበርክ ብላችሁ አትፈርዱብኝም አይደል! ያው የዛሬ ጭውውታችን በትምህርት መክፈቻ ቀን ላይ ስላሉት ገጠመኝም አደል! መልካም! አሁን ልቀጥል። ከላይ ያሰፈርኳት ያላለቀች ግጥም ካንተ ጋር ምን አገናኘው ካላችሁ በትምህርት መክፈቻ ቀን የተከሰተች አስደንጋጭ ሁነት ናት።
እህ ብላችሁ አድምጡኝ! ሰባተኛ ክፍል በገባሁበት ዓመት ኃይሌ ገብረ ስላሴ ሲድኒ ኦሎምፒክን አሸንፎ ስሙ የገነነበት ወቅት በመሆኑ እሱን ለማስታወስ ምስሉ ደብተር ላይ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር። አባቴም አገር ወዳድና ጀግና የሚያደንቅ በመሆኑ ስድስት የካቲት ደብተርና ሁለት የኃይሌ ምስል ያለበት ደብተር ገዛልኝ። የየካቲት ደብተሮቹን በጋዜጣና በላስቲክ ስሸፍን የኃይሌ ምስል ያለበትን ደብተሮች ግን በላስቲክ ብቻ ሸፍኜ አዘጋጀሁ።
የትምህርት መጀመሪያ ቀን ላይ እንደምታውቁት የደንብ ልብስ አይለበስም፤ ቦርሳም አይያዝም። እኔም ወደ ትምህርት ቤት እንደፈለኩ የሚያደርገኝን ልብሶች አድርጌ፣ ሸበጥ ጫማዬን ተጫምቼ እና ሁለት የኃይሌ ምስል ያለባቸውን ደብተሮች ይዤ ሄድኩኝ። የምማርበት ክፍል እንደደረስኩም ተሸቀዳድሜ ቦታ ያስኩኝ። እንደምታውቁት መንግስት ትምህርት ቤት አንድ ክፍል ውስጥ ለ80 ሆኖ መማር የግድ ነበር።
በዚህም በመጀመሪያ የትምህርት ቀን ክፍል ውስጥ የቦታ ነገር በጣም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተረዱልኝ። ቀድሞ መጥቶ ቦታ ያልያዘ ተማሪ የተሰባበረ ወንበር ላይ ተቀምጦ ዓመቱን ማሳለፍ ግድ ይለዋል። ይሄ እሽቅድድም ተለምዶ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሲገባም ቀድሞ ዶርም በመግባት ጥሩ መተኛ ፍራሽ መረጣ ውስጥ እንደሚገባ አትርሱልኝ።
እኔ ሲፈጥረኝም አንድ ቦታ ተረጋግቶ መቀመጥ አይሆንልኝምና የያዝኩት ቦታ ላይ ደብተሬን ማስቀመጫው ስር ከትቼ ከጓደኞቼ ጋር ልጫወት ወጣሁ። የመጀመሪያ ቀን እንደመሆኑ መምህራን ክፍል አልገቡም። ከልጆች ጋር ሳር ለሳር ስሯሯጥና ጭቃ ስወራወር ልቤ ጥፍት እስኪል ኳስ ስራገጥ ሰዓቱ ደርሶ ኖሮ ደብተሬን ላመጣ ክፍል ገባሁ። ግን ያየሁትን ማመን ነበር ያቃተኝ፤ ምክንያቱም የሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ምስል ያለበትና በላስቲክ ተጠንቅቄ የሸፈንኩት፣ ከቤት ስወጣም ሁለት ሶስቴ በጥንቃቄ እንድይዘው የተነገረኝ ደብተር ከቦታው የለም።
በጣም ተደናገጥኩ! አባቴ ማታ ከስራ ሲመጣ ‹‹ዛሬ ምን ተማራችሁ ደብተርህን አምጣ›› ብሎ ይጠይቀኛል። አማራጭ ስላልነበረኝ ምንም እንዳልተፈጠረ ወደቤቴ ሄድኩ። እቤት እንደደረስኩ ለታላቅ ወንድሜ እየተቅለሰለስኩ ደብተሬ መጥፋቱን ነገርኩት። ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ‹‹ታድያ አንተም ትሰርቃለሃ›› ብሎ አበረታታኝ። የማታውን የአባቴን ጥያቄ በመላ አልፌ ጠዋት እንዴት አድርጌ ደብተር እንደምሰርቅ ሳሰላስል አደርኩ።
ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ስሄድም ባዶ እጄን ነበር። ወደ ቅጥር ግቢው እንደገባሁም ጓደኞቼን ሰብስቤ በቀጥታ ያመራነው ደብተር ልናገኝበት ወደምንችለው አራተኛና አምስተኛ ክፍል መደዳ ነበር። በእለቱም አስር ያህል ደብተሮች የሰበሰብን ቢሆንም እኔ የተሰረኩትን አይነት የሃይሌ ምስል ያለበት ደብተር ግን ማግኘት አልተቻለም። ደብተሩን ለመግዛት ደግሞ ገንዘብ ያስፈልጋል ነገር ግን ቤተሰብ እንዳሁኑ የኪስ ገንዘብ አይሰጥም ነበር። ያለኝ የመጨረሻ አማራጭ ከቤት በሆነ መንገድ ገንዘብ መውሰድ ብቻ ሆነ፤ እናም ለደብተሮቹ የሚሆን አስር ብር ልሰርቅ ስል እጅ ከፍንጅ ተያዝኩ፤ የተገረፍኩትን ግን አትጠይቁኝ። የግርፊያ ያበቃኝን ሁኔታ ለማስታወስም ከላይ የተቀመጠውን ግጥም ጻፍኩ።
ሌላኛው በትምህርት መክፈቻ ወቅት ያጋጠመኝ ትንሽ ለየት ይላል። ወቅቱ የሚሊኒየም ዓመት የተበሰረበት ጊዜ በመሆኑ ትምህርት ቤት የገባነው በጉጉት ነበር። በመጀመሪዋ የትምህርት ቀን ከጓደኞቼ ጋር ውይይት ተብላ በምትጠራው ታክሲ ተሳፍረን መጓዝ ይዘናል። ትይዩ በመቀመጣችን ከጓደኞቼ ጋር በክረምት ስላሳለፍነው እረፍት ሞቅ ያለ ጨዋታ ውስጥ ለመግባት ጊዜ አልፈጀንም። የወሬውን አቅጣጫም አንዲት ሰፈራችን የምትገኝ ልጅ ላይ አደረግን። ከጓደኞቼ ጋር ስለ ልጅትዋ ክርክር ውስጥ ገባን፤ በወሬያችን መደማመጥ ባለመኖሩም የሌሎች ተሳፋሪዎችን ቀልብ ለመሳብ ቻልን።
ከተሳፈሩት ሰዎች መካከል በትምህርት ቤታችን የሂሳብ መምህር ከጥግ መቀመጡን አላስተዋልንም ነበር። እርሱ ግን በአንክሮ እኛንም ወሬያችንንም ሲከታል ቆይቶ መውረጃችን ሲደርስ ቀድሞን ከአካባቢው ተሰወረ። ‹‹አይመጣምን ትተሸ ይመጣልን ፍሪ›› የሚለው አባባል በተግባር ያየሁት ያኔ ነው። የመጀመሪያ ቀን እንደመሆኑ መምህራችን በየክፍላችን እየገቡ እየተዋወቁን ስለ ባህሪያቸውና ውጤት አያያዛቸው ሰፊ ማብራሪያ እየሰጡ ይወጣሉ። ካልተሳሳትኩ ሶስተኛው ክፍለ ጊዜ ላይ ይመስለኛል አብሮን የመጣው መምህር ወደ ክፍላችን ገባ፤ ክፍል ውስጥ ሲንጎራደድ ቆይቶም እኔ አጠገብ ሲደርስ ትኩር ብሎ አይቶኝ ሲያበቃ ሰሌዳው ፊት ለፊት እንድቆም አዘዘኝ።
ያዘዘኝን ካደረኩ በኋላም ታክሲ ውስጥ ሳወራት የነበረውን እያንዳንዱን ጉዳይ በአስተማሪው ጠያቂነት እንድናገር ተገደድኩ። ዝብዘባዬን እንደጨረስኩም አስተማሪው ምክር ይሁን ስድብ ባልገባኝ ቃላት ያለሁበትን ቦታ እስክስት ተቆጣኝ ፤ አልበቃ ብሎትም የመጀመሪያውን የእሱን ፈተና ጥሩ ውጤት ካላመጣሁ የመጀመሪያውን ሴሚስተር ውጤት አልተሟላም (incomplete) እንደሚለኝ ቁጣ በተቀላቀለበት ሁኔታ ነገረኝ። በመጀመሪያው የትምህርት ቀኔ በእንዲህ አስደንጋጭ ሁኔታ የጀመርኩበትን ሁኔታ እስካሁንም በደንብ አስታውሰዋለሁ። ይህን ያህል ካወጋኋችሁ እናንተም የትምህርት መክፈቻ ዕለት ገጠመኞቻችሁን እያሰታወሳችሁ በትዝታ ኮምኩሙ… እኔ ለዛሬ አበቃሁ።
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2012
መርድ ክፍሉ