ዮሐንስ ብሩክ የ14 ዓመት ታዳጊ ነው:: ዕድሜውን በማየት ብቻ የትኛው የሚነገር ታሪክ እዚህ አምድ ላይ ጣለው ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል:: ታዳጊው ዕድሜው መቁጠር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አያሌ መከራዎችን ቆጥሯል:: ዮሐንስ ስላሳለፈው ውጣ ውረድ ሲናገር “እናትና አባቴ በመለያየታቸው ምክንያት አባቴ ሌላ ሚስት አግብቶ ከእነርሱ ጋር እኖር ነበር:: ቤት ውስጥ ከእርሷ ጋር መስማማት ስላልቻልኩ ትምህርቴን ተረጋግቼ ለመከታተል እቸገር ነበር:: በኋላም አባቴ ከእኔ እርሷን ስለመረጠ ቤቱን ለቀው አብረው ሄዱ:: ያን ጊዜ ብቻዬን ስለቀረሁ መሄጃ አጣሁ::” ይላል::
ብቻውን የቀረው ዮሐንስ መቦረቂያ ግቢው ፣ ማረፊያ ሳሎኑና የሞቀ መኝተው ጎዳና ሆነ:: ማንም በሚመላለስበት ጎዳና ማንም ሳይኖረው ኖሯል:: የሁሉም በሆነ ጎዳና የሁሉም ሳይሆን ብዙ ነገሮች ሆኗል:: በጎዳና ህይወቱ ስለተጋፈጠው ከባድ ችግር ብትጠይቁት የሌሊቱን ብርድ ፣ የጸሐዩን ንዳድ ፣ የጉልበተኞችን ዱላና ንጥቂያ አሊያም የክረምቱን ዝናብና ጎርፍ አያስታውስም:: እነዚህን ሁሉ ተጋፍጦ አሸንፏቸዋል:: ደጋግሞ የተሸነፈለት አንድ ነገር ግን አለ:: ርሃብ !
እርቦት ሲያለቅስ ፖሊሶች መንገድ ላይ አግኝተውት ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ስለወሰዱት በ2011 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ወደ ዘውዲቱ መሸሻ የህጻናትና ቤተሰብ በጎ አድራጎት ድርጅት የመግባት ዕድል ገጥሞት ተረጋግቶ ያቋረጠውን ትምህርት መቀጠል ቻለ:: ህንጻዎችን ስመለከት ደስ እሰኛለሁ የሚለው ዮሐንስ የራሱን ንድፍ ነድፎ ህንጻዎችን የመገንባት ሀሳብ አለው:: የወደፊት ህልሙም የሥነ – ሕንፃ ባለሙያ (አርክቴክት) መሆን ነው::
አሁን ዮሐንስ ሕልሙን ማሳካት የሚችልበትን ወርቃማ ዕድል አግኝቷል:: በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ቢሮ በኩል ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 14 ለሆነ የደረጃ ተማሪዎች ናይጄሪያ ውስጥ በሚገኘው ሮሽ ፋውንዴሽን አፍሪካ ኮሌጅ ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በተሰጠ ዕድል ከተመረጡት አምስት የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል:: በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በመጣው እድል ተጠቃሚ የሆኑት ተማሪዎች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ያላቸውና በስነ ምግባራቸውም ምስጉን ሲሆኑ የተመረጡት ከአራት የህጻናት ማሳደጊያ ተቋማት ነው::
ሌላኛዋ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ ተዋበች ረዳ የምትኖረው ቀጨኔ ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ነው:: ተቋሙን የተቀላቀለችው በ2004 ዓ.ም ሲሆን፤ የምትኖረው አክስቷ ጋር ነበር:: ስለኋላ ታሪኳና አሁን ስላገኘችው ዕድል ስትገልጽ “ትምህርት ስለማታስተምረኝ አክስቴን አልወዳትም ነበር:: ሁለት ልጆችዋ ትምህርት ቤት ውለው ሲመጡ እኔ ግን ህጻን ልጇን መያዝ ነበር ስራዬ:: አንድ ቀን አክስቴ ጋር እንግዶች መጥተው ሲወጡ እነርሱን እከታተላለሁ ብዬ ወጥቼ በዚያው ጠፋሁ::
ከዚያም ፖሊስ አግኝቶኝ ወደ ቀጨኔ ህጻናት ማሳደጊያ አመጣኝ:: መጀመሪያ ወደ ቀጨኔ ማዕከል ስመጣ በጣም ፈርቼ ነበር ከገባሁ በኋላ ግን ደስተኛ ሆኛለሁ:: ትምህርት ስጀምርም ስድስተኛ ክፍል አስክደርስ ድረስ የደረጃ ተማሪ መሆን ችያለሁ:: ከጓደኞቼ በመለየቴ ብከፋም ከሚሊየኖች መካከል ይህን ዕድል በማግኘቴ የወደፊት መስመሬን ሳስብ በጣም እደሰታለሁ:: ወደፊት ጠበቃ መሆን እፈልጋለሁ:: ብዙ ሰዎች በሀሰት ስለሚከሰሱ ለእነርሱ ጥብቅና መቆም እፈልጋለሁ:: ይህን ዕድል ለፈጠረልን ለቀዳማዊት ጽህፈት ቤት በጣም ትልቅ ምስጋና ላቀርብላቸው እወዳለሁ::” ትላለች::
ከሰላም የህጻናት መንደር ዕድሉን ያገኘችው ነፊሳ ሀቢብ መጀመሪያ ከእናትና አባቷ ጋር ትኖር ነበር:: በኋላ ግን ልጅ እንድትይዝላት ለአክስቷ ተሰጠች:: አክስቷ ስለማትስማማና ስለምትደበድባት አንድ ዕለት ከአክስቷ ቤት ወጥታ ጠፋች:: በመንገድ ላይም ፖሊሶች አግኝተዋት ወደ ቀጨኔ ህጻናት ማሳደጊያ ወስደዋት ኬጂ ገብታ ትምህርቷን ቀጠለች:: ሁለተኛ ክፍል ስትደርስም ወደ ሰላም የህጻናት ማሳደጊያ ተዘዋወረች:: ስለቤተሰቦቿ ሁኔታ ስትገልጽ “ቤተሰቦቼ በህይወት ስለመኖራቸው አላውቅም ይኖሩ የነበሩት ግን ደምቢዶሎ ነው::” ትላለች::
አራተኛዋ ተማሪ ኢየሩስ አላምረውም እናትና አባቷን እንደማታውቅ ትናገራለች:: “ከህጻንነቴ ጀምሮ የማውቀው አሳዳጊዬን ነው:: እርሷ ደግሞ ብዙ በደል ታደርስብኝና ትደበድበኝ ስለነበር ጎረቤቶች ለፖሊስ ተናግረው ወደ ቀጨኔ እጻናት ማሳደጊያ ገባሁ” ትላለች:: የአፀደ ሕፃናት ትምህርቷን ስትጀምር 1ኛ በመውጣት እስከ 6ኛ ከፍል ድረስ በትምህርቷ ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ በተደጋጋሚ ተሸላሚ መሆን ችላለች:: ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሴት አውሮፕላን አብራሪዎች ስለሌሉ ወደፊት ፓይለት መሆን እፈልጋለሁ›› የምትለው ኢየሩስ ‹‹እንዲህ አይነት ዕድል ይገጥመኛል ብዬ አስቤ አላውቅም:: ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽን በማግኘቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል›› ትላለች::
አቤል ሰለሞን ‹‹ ከእናትና አባቴ ጋር እኖር ነብር:: እናቴ ስትሞት ግን ክበበ ጸሐይ የህጻናት ማሳደጊያ ገባሁ:: በዚያ አምስት ዓመታትን ከቆየሁ በዃላ አድጋችኋል ተብለን ከኮልፌ ህጻናት ማሳደጊያ ተዘዋወርን:: ወደፊት የልብ ሀኪም ሆኜ በልብ ህመም እየተሰቃዩ ያሉትን ህጻናት ማዳን እፈልጋለሁ›› ይላል::
አቶ አስቻለሁ በዙ ‹‹ ሰላም የህጻናት መንደር ዕድሉን በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን:: ለሌሎችም ልጆቻችን መነቃቃትን የሚፈጥር ነው:: መንግስት ለካ ያየናል ወደሚል እሳቤ ውስጥ እያስገባን ነው:: ይህ ስራ በስፋት ቢሰራ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል:: እነዚህ ልጆች ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምንክንያቶች ያጡና ከቤተሰቦቻቸው በሰራተኝነትና እናሳድጋለን በሚል ከየክልሉ መጥተው በደረሰባቸው ችግር ምክንያት ወደተቋም የገቡ ናቸው:: ተመልካች እንዳላቸው ፤ አጋዥ እንዳላቸው ፤ ወገን እንዳላቸው እንዲረዱ የሚያደርግ አጋጣሚ ስለሆነ ተጠናክሮ ቢቀጥል ልጆቹ ተጠቃሚ ይሆናሉ›› ብለዋል::
ወይዘሮ ሀብታም ነጋሽ የቀጨኔ ሴት ህጻናት ጊዜያዊ ማቆያና ማቋቋሚያ ተቋም ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው ‹‹ እነዚህ ልጆች የሁላችንም ልጆች ናቸው:: ይህን ዕድል አግኝተው ለተሻለ የትምህርት ዕድል ወደ ውጭ አገር በማምራታቸው እጅግ በጣም ደስተኞች ነን:: በተቋማችንም ዝግጅት አዘጋጅተን ሽኝት አድርገንላቸዋል:: እንደዚህ አይነት ዕድል የሚገኘው ከፍ ያለ ጥረት ተደርጎ ነውና የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤትና ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ላደረጉት ጥረት ትልቅ አክብሮትና ምስጋና አለን›› ሲሉ ይናገራሉ::
ሮሽ ፋውንዴሽን አፍሪካ ኮሌጅ ከዚህ ቀደም የተቀበላቸውን 10 ኢትዮጵያዊ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ሲሆን ሁለተኛ እድል ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የተሰጠው ከዚህ በፊት የሄዱት ተማሪዎች ጎበዝና ውጤታማ በመሆናቸው ነው::
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2012
የትናየት ፈሩ