የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ በሥነ- ምግባር ደረጃ ሊከተላቸው የሚገቡ አንድ ወይም ሁለት መሰረታዊ ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። ከሁሉም የቀደመው ግን ፣ “በራስህ እንዲደረግ የማትወደውን በሌሎች ላይ አታድርግ” የሚለው ነው። በዚህ የከበረ ሃሳብ ውስጥ፣ ሌላውን በተግባር መውደድ ወይም ቢያንስ ቢያንስ አለመጥላት፣ በሌላው ላይ አለማሴር ፣ ለቃልህ ታማኝ መሆን፣ አለመሰሰት፣ ለተጎዳ ሰው መድረስ፣ ሌሎችን ከአደጋ መጠበቅና በማንኛውም ሁኔታ ክፋትን በሌሎች ላይ አለመጫንን የመሰለ ጥቅል ፅንሰ-ሐሳብ የያዘ እውነት ነው።
ሌሎቹን ዝርዝር ሐሳቦች አለማንሳት ይሻላል ፤ ምክንያቱም ዝርዝሮቹ አያባሩምና ። ለማከል ያህል ግን ሌላው ላይ እንዲደረግ የማልወደውና፣ እኔም በሌላው ላይ ልፈጽመው የማይገባኝ ሐሜት አለ፤ አድልዎ አለ፤ ጥላቻ አለ፤ ፍርሃት ፤ ክህደት ጭካኔ ፤ ማስራብ ፤ ማግለል ፤ ማንቋሸሽ፣ ኢ-ፍትሐዊነት አለ፤ ምን ቅጡ ይዘረዘራል ።
እዚህ ላይ ታዲያ ይህንን ርዕሰ ነገር ለምን አነሳኸው የሚል ሰው ካለ የርዕሱ መጠቅለያ ነገር እርሱ ስለሆነ ነው። ስለዚህ እስካሁን በጉጉት ለምትጠብቁኝ “ምን ጠላህ” ካላችሁኝ ፣ በእኛ ሐገር ምድሩን እያወከው ያለውን ክፉ የዘር ጥላቻ ጠላሁ።
የሰው ልጅ ወደዚህ ምድር የመጣለትን የምስጋናና የመልካምነት ህይወት የሚያውከው መግፍኤ ነገር ፣ መንስዔ ጥላቻን ነው የጠላሁት። ጥላቻ የቅናት ታናሽ ወንድም ነው። አንድ ሰው ሌላውን ለመጥላት እርሱ ከጠላው ሰው የሚለይበትን አንዳች ነገር ማየት በቂው ነው።
በሩዋንዳ የእርስ በእርስ እልቂት ውስጥ አጫጭሮቹና አፍንጫ ሰፊዎቹ ሁቱዎች ረዣዥሞቹንና አፍንጫ ሰልካካዎቹን ቱትሲዎች ከእኛ ወገን አይደሉም ብለው ለመጥላት አንደኛው ምክንያታቸው ቁመታቸው ነበር ቢባል አጀብ ማሰኘቱ አይቀርም። ሰው ልጥላ ካለ ምክንያትም አይፈልግም ፤ ለመውደድ ግን የሆነ አንዳች ሰበብ ይፈልጋል ። ከነብሒሉም “ፍቅር እንጂ የሚቸግረን ጥላቻማ አፍንጫችን ሥር ነው “ ይልሃል ፤ የሀገሬ ሰው።
አንድ ሰው ወደዚህ ምድር ከዚህ ቤተሰብ ልወለድ ብሎ አልመጣም፤ አይመጣምም። በተለመደው አባባል አመልክቶ አልተወለደም፤ ስለዚህ አመልክቶም አይሞትም፤ ድንገት በተፈቀደላቸው የሆነ ቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰብ ውስጥ ተወልዶ የሆነ ቋንቋን በለመደበት ማህበረሰብና ቤተሰብ ውስጥ አድጎ ያልፋል እንጂ፣ በምክርና በስምምነት ኦሮሞ፣ አማራ ፣ ወላይታ ወይም ዳሰነች ሆኜ ልወለድ ብሎ አይመጣም።
በተባለው ቤተሰብ ውስጥ ተወልዶ እንኳን የወላጆቹን ቋንቋ ሳይለምድ የሚቀር አለ። ቋንቋ በተወልዶ ቢሆን ኖሮ እኛም የመጣንባቸውን ቋንቋዎች ተናጋሪዎች ሆነን ነበር፣ የምንቀረው። የሥነ-ቋንቋ ምሁራን፣ አንዱ የቋንቋ ባህሪ ብለው የሚሉትም “ቋንቋን እንለምደዋለን ፤ወይም እንማረዋለን”፣ እንጂ አንወለደውም። አንድ ኦሮሞ ቻይና ውስጥ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ የሚናገረው ኦሮሚፋ ሳይሆን ማንዳሪን ነው። (ማንዳሪን የቻይና ኦፊሴላዊ የሥራ ቋንቋ መሆኑን ያጤኗል)
ስለዚህ “ምንጠላህ?” ካላችሁኝ የተወለደበትን ዘር ፣ የትምክህቱ ምክንያት አድርጎ የሚንጠባረር፣ በመልኩና ቁንጅናው፣ በአፍንጫ ሰልካካነቱ ወይም በጥርሷ ትክል ማማር በቁመቷ ሎጋነት ወይም በቆዳዋ ንጣት፣ የምትኩራራና የምትመካ ሰው ካየሁ ባልነገዱበት አትርፈው እንደሚቀናጡ ሰዎች አስቤያቸው እቆጣለሁ። እርሱ፣ ባላዋጣበት መንቀባረር አፍራለሁ፤ እርሷ ባልነገደችበት አተረፍኩ በማለቷ አዝናለሁ፤ ስለዚህ ትምክህቱን እጠላዋለሁ!!
ሌላ ምን ጠላሁ መሰላችሁ? አለቃውን ከጀርባ እያማ ድንገት “ሰውየው” ሲከሰት ፣ ተደናግጦ የተናገረው የሚጠፋበት፣ የጀመረው የሚቋረጥበት፣ አካሉ አልታዘዝ የሚለው ፣ ዓይኖቹን ማሳረፊያ የሚያጣ ሰው፤ አለቃው ሲያነጥስ መሐረብ ልሁንልህ፤ አለቃው ስለበላ እኔ ላግሳልህ የሚል ሰው ካየሁ እጠላለሁ።
በአኗኗራችን ስልት ውስጥ በጎና መጥፎ ልማዶች አሉን ፤ ብዙዎቹን በጎ ልማዶች ማለትም እንደ ርህራሄ፣ ለጋስነት፣ ቅንነት፣ ትዕግስት ፣ ራስን መግዛት ፣ አፍቃሪነት ፣ የዋህነትና ይቅርባይነት ያሉትን ማጎልበት ለምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ህይወታችን ስምረት ተገቢዎች ናቸው። በአንጻሩ፣ ጭካኔን፣ ንፍገትን፣ ምቀኝነትን፣ ቁጠኛነትን፣ ትዕቢትን፤ ማንአህሎኝነትን፣ በዋልፈሰስነትን፣ ጥላቻንና ቂመኛነትን ከሥራቸው ማድረቅ ፣ ከምንጫቸው ማድረቅ የተገባ ነው።
ስለዚህ ልናወድሳቸው የሚገቡን የአስተሳሰብ ወርቆች ያሉንን ያህል ልናወግዝና ልንጠላቸው ፣ ከላያችን ላይ እንዲነሱ ልንታገላቸው የሚገቡን ባህሪየ አስተሳሰቦች አሉን።
ምን ጠላህ ያላችሁኝን ፣ ጥቅል ሃሳብ ስተረትረው፤ የሰው ልጅ በሌላው ወገኑ ላይ አደጋ ደርሶበት ሳለ ከመርዳትና ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ለሚፈስሰው ደሙ ትርጉም ሳይሰጡ፣ ካሜራቸውን አውጥተው ምስል የሚቀርፁ ሰዎች ማየት አስጠላኝ ። ትሰሙ እንደሆነ ታቀቡ፤ ጽሁፉን እያነበባችሁ ካላችሁም ይህንንም ፎቶ አንሱና ጋዜጣውን ሊያገኙ የማይችሉ ሰዎችን በማስነበብ የማሳሰቢያው አካል ሁኑ። ይህንን ርህራሄ አልባ ህይወት ከየት እንደተማራችሁትም ራሳችሁን እንድትጠይቁ ጠይቃችኋለሁ።
እንድትረዱት የወደደና የፈለገ ሰው፣ ደጃችሁ ላይ መጥቶ ፣ ልመናን ያህል ክብረ-ነክ ነገር እያደረገ ሣለ ፤ መከልከል ዐመብታችሁ ቢሆንም ከክልከላችሁ በላይ የልመናውን እርግጠኛነት መለካትና፣ ስባትና ቅላት ሽንጥና ዳሌ እያወጣችሁለት በእርሱ ላይ መሳለቅን ምን አመጣው ? ማንስ በሌላው ወገናችሁ ላይ የመሳለቅንም ሆነ የማኪያኬስ ስልጣን ሰጣችሁና ትዛበቱበታላችሁ። አንድ ሰው እኮ ወደ ልመና ሲወጣ ከይሉኝታው በላይ፣ ከእምነቱም በላይ ሆኖበት ነው፤ ፊታችሁ የቆመው፤ አለቀ። ይህንን ሁሉን ክብሩን የጣለ ሰው፣ የሚያንጓጥጥና ባያከብረውም ዝም የማይል ሰው ሳይ እናደዳለሁ ባህሪውንም እጠላለሁ!!
የሰዎችን ልባዊ አመጣጥ ለመገንዘብ ሳትችሉ ገጽታቸውን በማየት ብቻ ለፍርድ የምትቸኩሉ፣ በይመስላል ብይን ሰጥታችሁ እንዲህ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፤ የምትሉ ፈራጆች ሆይ! እናንተን በፍርድ ወንበር ላይ ማን አስቀመጣችሁና፣ “እንትን “ የሆነው እኮ በዚህ ምክንያት ነው፤ እንዲህ የተፈጸመው በዚያኛው ሃጢያት ነው፣ ለማለት ማንና ምን ድፍረት ሰጣችሁ? በወንድማችሁ ወይም በእህታችሁ ላይ ድንገት ተነስታችሁ የምትሰጡትስ ማጠቃለያስ ተገቢ ነው፤ ትላላችሁን?
እንበልና ፣ አንዲት የ11ኛ፣ ክፍል ተማሪ ፣ ድንገት አርግዛ ተገኘች እንበል። የዕድሜዋን ትንሽነት፣ ያጋጠማትን ቅድመ-ትዳር ፈተናና ክፉ እንቅፋት ከማየትና የችግሯ መፍቻ ቁልፍ ከመሆን ይልቅ፣ ስትንቀዠቀዥ ያጋጠማት የክፉ ሥራዋ ውጤት ነው፤ የእጇን ነው ያገኘችው ፤ “ይበላት!“ ብሎ ፍርድን ምን አመጣው? ብዙ ፈራጆች እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ በቤታቸው፣ በዘመዳቸው ፣ በእህታቸው ላይ ሲደርስ ድምጽ ላለማሰማት የሚደፍሩትን ያህል በጎረቤት ልጅ፣ በትምህርት ቤትና በአካባቢ ሲያጋጥም ለፍርድ ይጣደፋሉ። እህቴ ብትሆንስ? አክስቴ ቢገጥማትስ ? ኧረ ወንድሜ፣ የጦሷ ምክንያት ሆኖ እንደሆንስ ብለው፣ ለመጠየቅ አይደፍሩም።
ቀስ ብለው ሁኔታውን ቢያጤኑት እኮ፣ ልጅቱ ሁኔታው የገጠማት ተገድዳ በመደፈር ይሆናል። ወይም ዘመናዊ የመከላከያ ሥርዓትን ካለማወቅ በመነጨ የአንዲት ቀንና ቅጽበት ስህተት ይሆናል፤ ወይም ቤተኛ በሚባል የቅርብ ሰው ጥቃት ተፈጽሞባት ይሆናል ፤ ይባስ ብሎም በቤተሰብ መካከል በተፈጠረ ነውርም ያጋጠማት ክፉ ክስተት ሊሆን ይችላል፤ ከፍርጃ ይልቅ ለዘብ ብሎ ማጤን መመርመርና ተገቢውን የማረሚያ እርምጃ መውሰድ አስተዋይነት ነው። ከዚህ ባነሰ ቅጽበት፣ ልጅቱን “ዓይንሽን ላፈር” ብሎ ከምድሩ የቤተዘመድ ባህረ-መዝገብ ፍቆ፣ ከሰማያትም የእግዚአብሔር መንግስት ንስሐ በሚያርቅ ብያኔ ላይ መጣል ክፉ ደምዳሚነት ነውና ያስጠላኛል።
ሌላው ሰው በሰጠው፣ ሌላው ባደረገው ለጋስነት ቀንቶ ማን መሆኑን ቢያውቅ አያደርግለትም ነበር፤ ማን መሆኗን ጠንቅቆ ቢረዳ የማይገባትን እንዳደረገላት ቢያውቅ ያዝናል፤ በማለት ለሰጭው ያዘነ በመምሰል የሌላውን ለጋስነት ስህተት ለመጠቆም የሚያዝን የምቀኝነት ባህሪን ጠላሁ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ቢመረመሩ ይዘው የሚጠይቁ ተርፏቸው የለንም የሚሉ፣ ጠግበው የሰው ገንዘብ ስለሆነ ሳያቋርጡ የሚጠጡ ሽንቁር ጋኖች ናቸው። ራሳቸው አለማድረጋቸው አንድ ነገር ሆኖ፣ ሌላው በሰጠው የሚብሰከሰኩ የሰው ስጦታ ጭራቆች ናቸው።
“ምን ጠላህ?” አላችሁኝ አይደል፣ አንዱ በበደለ ተበዳይ በደሉን ረስቶ በዳይን ይቅር በማለቱ ለይቅርታው ባትና ላት አውጥተውለት በስልጣኑ ፈርቶት እንጂ፣ ገንዘብ ስላለው ተለማምጦ እንጂ፣ በዕውቀቱ አካብዶት እንጂ እርሱ ማን ስለሆነ ነው ይቅርታ የሚጠየቀው ብለው ይቅርታን በኑሮ ደረጃ ለመክፈል የሚቃጣቸው የጥላቻ ነገስታት የጨለማ ልኡላንን ጠላሁ። ሰው ሲጣላ ዘና የሚሉትን፣ ሲታረቅ ዓይናቸው ደም የሚለብሰውን የአጋንንት ድቤ ደብዳቢዎች ፣ “ይድፋውና በአጭር ያስቀረው “ ባይ ሟርተኞች ጠላሁ። አላወቁም እንጂ የእነርሱ ዛቻና ሟርት ጠልፎ የሚጥለው እነርሱኑ እንጂ እርቅና ፍቅር አውራጆቹን አይደለም።
ደግሞ፣ “ምን ጠላህ?” አትሉኝም፤ ካላችሁኝ፣ የደረሰበትን እንደደረሰለት ቆጥሮ ፣ መገፋቱን ከፍ እንደማለት አይቶ፣ የተዘጋጁበትን እንደተዘጋጁለት መዝኖ በየዋህነት ወደጠሉትና ወደጣሉት ዘንድ ሄዶ ምንም እንዳልከፋው የሚያደርገውን መልካምነት “ ገልቱነት “ ነው ብለው፣ ከሞኝ ተራ አሰልፈውት በክፋታቸው የሚቀጥሉት አንገላቾች ክፉኛ ጠላሁ።
ማንም ሰው ፣ ለራሱ ሲሆን የማያውቀው በነፍሱ ሲመጣ የማይገነዘበው ክስተት የለም ። ምንም እንኳን የደረሰበት ግፊት ኃያል ቢሆንምና የተተወ መስሎ ቢሰማውም፣ ጥቃቱን አፍኖ መተውን ጨፍኖ በትዕግስት ሲጓዝ አልገባውም ብለው ጫናቸውን ሲጨምሩበትና ቀንበራቸው ሲያከብዱበት ሳይ በሥራቸው ጠላኋቸው።
የሰጠውን ትንሽ አጋኖ ፣ የጎደለበትን ብጫቂ አደንድኖ እንደተበደለ እያወራ በዳዮቹን እንደሚበቀል ያለሃፍረት የሚናገርና በየደረሰበት ምን ያህል ትልቅ እንደሆነና ብዙ እንዳለው፣ የሚደሰኩር በብዙ ጉራ ትንሽ አድራጊን ምስኪን ጠላሁ።
አንዳንድ ደግሞ ግብዝ፤ አለላችሁ በቤቱ ውስጥ ምንም ሳይኖር ብዙ እያወራ፣ በጭንቅላቱ ምንም ሳይይዝ እየደፈራ ( እየደበላለቀ) ከሰው ያገኛትን ትናንሽ ዕውቀት በየተገኘው አጋጣሚ እየወነጨፈ፣ “ተለማማጭ አልማጭ ፣ የጎረቤቷን ድልህ አሟጣጭ” የሆነ ደፋር ጠላሁ። በየትኛውም ድግስ ላይ ባትጠሯቸውም አሉ፤ በየትኛውም ትዕይንት ላይ ግንባር ቀደም ሰልፈኛ ናቸው፤ ግን ስለተገኙበት ነገር የሚያውቁት አንድም ጥቂት ነው፤ ካለዚያም ምንም ነው።
ሌሎች ደግሞ አሉ ። ፈርጅ የለሾች! በተነሳው ርእሰ-ነገር ላይ አስተያየት ለመስጠት የማያመነቱ፣ “ከጳጳሱ ቄሱ” የሆኑ፣ ከኢኮኖሚስቱ በላይ ስለኢኮኖሚው መዋለል ስለገንዘብ ግሽበትና መዋቅር፣ አስተያየት የሚሰጡ፣ ከፍልስፍናው ምሁር በላይ ስለፍልስፍና የሚደሰኩሩ፣ ከሶሻል ሳይንቲስቱ በላይ ስለማህበረሰብ ፈርጅና ታሪክ ልተንትን የሚሉ፣ ከፖለቲከኞቹ በላይ ፖለቲካ ከእኔ በላይ ላሳር የሚሉና ስለስውር መንግስት የሚያስወሩ፣ ከገበያው ባለሙያ በላይ ስለገበያው ውጣውረድ የሚናገሩና እንደመተንበይ የሚቃጣቸው፣ ሁሉን አወቅነት የተጣባቸውን ራሳቸውን የማይገዙ ሰዎች ጠላሁ።
“ምን ጠላህ “በሉኝ፤ የሚጥል ሃሳብ መክረው፣ ስትወድቅ “እኔ እንደዚህ አላልኩህም፤ አልተረዳኸኝም ነበር” ብለው የሚክዱ ዋላዮች ፣ በእግርህ ሥር የሙዝ ልጣጭ ጥለው ስትንጋለል የሚስቁ ሰዎችን ሳይ ግብራቸውን ክፉኛ፣ ጠላሁ። ለመነሳትህ አስመስለው ለውድቀትህ አዋጥተው ጨለማ ውስጥ ጥለውህ የሚሄዱ ክፉዎችን ክፋት ጠላሁ!!
እንደ ደፋር አዳፍረውህ፤ ገፋፍተውህና አለንልህ፣ አይዞህ ብለው ወደ ፍጥጫው መድረክ እንድትወጣ ካደረጉህ በኋላ ዞር ስትል የምታጣቸውን ተንሸራታቾች ጠላሁ፤ በሬ በኩርኩም ከሚገድል ሰው ጋር ተጣልተው “እንዴት ዝም ብለህ ታየኛለህ“፣ ብለው ነገራቸውን እንድትዋጋላቸው የሚጋብዙህንና፣ ለመዳንህ ሳይሆን ለመሰበርህ ብለው ብረትን በአርጩሜ እንድትመክት የሚገፉህን አቅመ-ቢሶች ጠላሁ። እግረ መንገዴንም በገዛ ጸባቸው ገላጋይ የሚሆኑ ፈሪዎችንም ጠላሁ።
አሉ ደግሞ፣ የተውከውን አንስተው፣ የረሳኸውን ክፉ አስታውሰው ህመምህን መልሰህ እንድትታመም፤ ሃፍረትህን እንድትሸማቀቅ፣ በነውርህ እንድታቀረቅር፣ ከጊዜ ተበድረው ከዘመን አሮጌ አንፏቀው፣ የጣልከውን መዝዘው አምጥተው፣ የሚጥሉብህን አዛኝ ቅቤ አንጓቾች ጠላሁ።
ከሰራኸው ደግ ይልቅ በደግነትህ ውስጥ ክፋትን የሚመዝዙ፣ ቀናነትህን በጥርጣሬ የሚመርዙ፣ “ይኸንን ያደረገው ለዚህ ነው” ብለው፣ የራሳቸውን ምክንያትና ውጤት ሰጥተው፣ ላይጠቅማቸው ስምህን መሬት ለመሬት ለመጎተት ተኝተው የማያድሩ የድሁር አስተሳሰብ ፌንጣዎችን ጠላሁ።
ታዲያ ከሁሉም ከሁሉም “የሚያስጠሉት ክፉ ነገሮች” እንኳን ኖሩልኝ; እነርሱ ባይኖሩ የደግነቴን ዋጋ ፣ የፍቅርን ፀጋ፣ የመልካምነትን ወርቅነት ፣ የለጋስነትን ዕንቁነት አላጣጥመውም ነበረ፤ እናም እንኳንም ያስጠሉኝ ነገሮች ኖሩልኝ።
በአጠቃላይ የሚጠላው ሐሳቡ ፣ የሚጠላው ክፉ ምግባሩ እንጂ አሳቢውና ተግባሪው አይደለም ። እኔም ስጠላ የጠላሁት ከላይ ያልኳችሁን የንፍገት ሰንሰለት ፣ የሐሜትን ስለት፣ የቅናትና ምቀኝነትን ጭራቅ፣ የጭካኔን ፍትወት፤ የቂመኛነትን መጋዝ፣ የትዕቢትን ጉልበት፣ የበዋል- ፈሰስነትን ዝቅጠት እና የማንአህሎኝነትን ቅብጠት እንጂ አድራጊውን አይደለም። ከቶውንም በምድራችን ላይ በትእቢት የተነሱ ሲወድቁ፣ ምቀኞች በቅናት ሲንገራበዱ፣ ሐሜተኞች መግቢያ አጥተው ሲደናበሩ፣ ጨካኞች በሰይፋቸው ሲሰየፉ፣ ስስታሞች አንድም ሲወድቁ አለዚያም ሲታነቁ አይተናል። ስለዚህ ለመልካምነት እንነሳና በትንሹ መልካምነት ለዘላለም እንወሳ!!
ለሁላችሁም የመልካምነት ሳምንት ይሁንላችሁ!!
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ