ድንገት ያቃጨለው የእጅ ስልኩ ከነበረበት ሀሳብ ፈጥኖ አባነነው። ቆም ብሎ ወደ ኪሱ ገባና ሞባይሉን አወጣ። ደዋዩ የቅርብ ጓደኛው ነበር። ሰውዬው ከሰላምታ በፊት ቀጥታ ወደ ጉዳዩ ገባና ያለፋታ ያወራ ጀመር። ሃይሉ ከጓደኛው አንደበት የሚሰማውን እውነት አምኖ መቀበል ቸግሮታል። ግንባሩን ቋጠር፣ ፈታ እያደረገ የሚናገረውን ሁሉ በትኩረት አዳመጠው።
ሃይሉ የጓደኛውን ስልክ ከዘጋ በኋላ በድንጋጤ ተውጦ በሀሳብ ሰመጠ። የቀኝ እጁን ጭብጥ ከግራ መዳፉ አያጋጨም በንዴት ሲብከነከን ቆየ። አሁንም የሰማውን በቀላሉ አምኖ መቀበል ቸግሮታል።
በአዕምሮው ለሚመልሰው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት በሀሳብ መባከኑ ብቻ አልበቃውም። ወደኪሱ የመለሰውን ሞባይል በፍጥነት አውጥቶ ወደታላቅ ወንድሙ ደወለ። ወንድሙ የሚለውን አንድ በአንድ አዳመጠው። እሱ በቅርብ እንደሌለ ነግሮትም በሰላም ወደቤቱ እንዲገባና ትዕግስተኛ እንዲሆን አስጠነቀቀው።
ሃይሉ የወንድሙን ስልክ ከዘጋ በኋላ ወደሚስቱ ለመደወል ቁጥሮቹን በድጋሚ ነካ። ስልኩን ፈጥና ያነሳችው ሚስት የሚለውን ካደመጠች በኋላ ቤት እንደሌለችና ጉዳዩን ግን ከሌሎች እንደሰማች ነገረችው።
ሃይሉ ባለቤቱ ከቤት ያለመኖሯን ሲያውቅ ጥቂት ለመረጋጋት ሞከረ። ከአንድ ጥግ አረፍ ብሎም ከዓመት በፊት ከታናሽ ወንድሙ ጋር ስለተፈጠረው ጠብና ችግር ማብሰልሰል ጀመረ።
ወንድሙ የዛኔ ከሚስቱና ከእሱ ጋራ በነበረው ያለመግባባት ተከሶ የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶበት እንደነበር ያውቃል። ከደቂቃዎች በፊት ጓደኛው እንደነገረው ግን አንድ ዓመቱን እንኳን በወጉ ሳይደፍን በዛሬው ቀን ከእስር ተፈቷል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? አሁንም ሃይሉ ያልተመለሰለት ጥያቄ ሆኖ ወደቀድሞው ሁኔታ በሀሳብ ነጎደ።
አንድ ዓመት ወደኋላ
በርከት ብለው የተወለዱት እህትና ወንድሞች በየአጋጣሚው ለመገናኘት ምክንያታቸው ብዙ ነው። ከቤቱ የመጀመሪያ ልጅ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረሰ በህይወት ቆይተው የራሳቸውን ኑሮ መምራታቸው ብዙዎችን ያስገርማል። ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ግን በሃይሉና በታናሽ ወንድሙ በቀለ መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።
ወንድማማቾቹ በየምክንያቱ በተጋጩ ጊዜ ደግሞ ጠባቸው የግል ሆኖ አያውቅም። ሁሌም የሃይሉ ሚስትና ወንድ ልጁ በቀለን ለማጥቃት እንደተዘጋጁ ነው። በጋራ በሚኖሩበት ግቢ የሚገኘውን የቀበሌ ቤት ‹‹በይገባኛል›› ሲሟገቱበት ቆይተዋል። ጉዳዩ ያለመፍትሄ ቀጥሎ መቀያየም ማስከተሉም የጎሪጥ እያተያዩ በክፉ ያፈላልጋቸው ይዟል።
ጠብ በተነሳ ቁጥር የአባወራው ሀይሉ ሚስትና ወንድ ልጁ በቀለን ለማጥቃት ሰበብ እንደፈለጉ ነው። እንደውም አንድ ጊዜ ልጅዬው በግርግር መሐል ገብቶ የአጎቱን ጥርስ አውልቋል። በቀለም ከዚህ በኋላ በቤተሰቡ ላይ አምርሮ ቀን ሲጠብቅላቸው ቆይቷል።
በቤተሰቡ መሐል አሁንም በክፉ ዓይኖች መተያየቱ ቀጥሏል። ሀይሉ ከሚስትና ከልጁ ጋር ሆኖ ወንድሙን ለማጥቃት ያስባል። በቀለም ቢሆን ቂምና ጥላቻን ይዞ አመቺ ጊዜን እየጠበቀ ነው። ወንድሙ ከአንድም ሦስት ሆኖ ያደረሰበትን ጥቃት ፈጽሞ ሊረሳው አልቻለም። በተለይም ሚስቱ ሁሌም ከልጇ ጋር በማበር ‹‹ትፈጽምብኛለች›› የሚለውን ደባ እንደዋዛ ማለፍ አልተቻለውም።
ባልና ሚስቱን ጨምሮ ወንዱ ልጃቸው በቀለን በዓይነ ቁራኛ መጠበቅ ከጀመሩ ቆይተዋል። ሁሌም ሸንጎ የማያጣው ቤተሰብ በየጊዜው ጠብና ክስ እያስተናገደ ነው። በቀለ የቤተሰቡን በእሱ ላይ ማበር እያሰበ በነገር ይብከነከናል። እነሱ እንደማይተኙለት ሲያውቅም ባያቸው ቁጥር ጥርሱን ይነክሳል።
ከዕለታት በአንዱቀን
በሀይሉ ቤተሰብና በበቀለ መሐል ያለው ቅራኔ ብሶበታል። ለማስማማት የሞከሩም ችግሩ በቀላሉ እንደማይፈታ ሲረዱ ገሸሽ ብለዋል:: አንድ ቀን የተፈጠረው አጋጣሚ ግን ከሁሉም ቀናት የባሰ ክስተትን አስተናገደ።
በዚህ ቀን የወንድሙ ሚስትና በቀለ በተለየ ንግግር ጠባቸውን ጀመሩ። በቀለም በጭቅጭቃቸው መሐል የጥርሱን ጉዳት አንስቶና ብሶቱን በምሬትና በስድብ ቀላቅሎ በንዴት ጦፈ። ይህን ያየቸው ሴት በሁኔታው እያፌዘች ተሳለቀችበት። ጥርሱ ብቻ ሳይሆን አንገቱም ጭምር እንደሚቆረጥ እየነገረችም ዛተችበት።
ይህኔ በቀለ ንዴቱ ጨምሮ ሰውነቱ ጋለ። ያለፈው ሳያንሰ ሌላ ተንኮል እየታቀደበት መሆኑ ሲገባውም በእጅጉ በሸቀ። የሁለቱ ግጭት እንደወትሮው በጭቅጭቅ ብቻ አልተቋጨም። ገና ጠብ ሲነሳ ንዴት የቀደመው በቀለ በእነሱ የደረሰበትን በደል ሁሉ እያሰበ እጆቹን ሰነዘረ። ይህን ያየቸው እማወራም በድርጊቱ ተናዳ አፀፋውን ለመመለስ ሞከረች። በቀለ ይህን ለማስተናገድ ትዕግስት አልነበረውም። በድንገት ያገኘውን የፌሮ ብረት አንስቶ ከእግሯ ላይ አሳረፈው።
የዛን ለታው ጠብ እንደወትሮው በቀላሉ አልተቋጨም። በብረት የተመታችው ሴትም በጩኸትና በስድብ ብቻ አልተመለሰችም:: ጉዳቷን በማስረጃ ይዛ ክስ መሰረተችበት። ጉዳዩን በቀላል ያላየው ሕግም ድርጊቱን በምስክር አረጋግጦ ለተበዳይዋ ፍትህን በየነ።
በቀለ በወንድሙ ሚስት ላይ በፈፀመው የድብደባ ወንጀል ማስረጃ ተቆጥሮበት ጥፋተኛነቱ ተረጋገጠ። ፍርድ ቤቱም ‹‹ይገባዋል›› ያለውን የሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወራት እስር አሳለፈበት።
በቀለ የሁለት ዓመት እስሩን በማረሚያ ቤት እንደጀመረ ለጊዜውም ቢሆን ግቢው ሰላም ውሎ ማደር ጀመረ። እንደቀድሞው ጠብና ግርግር ባለማስተናገዱም ሰላም የሰፈነበት መስሎ ታየ። በቀለ ግን ካለበት ሆኖ ክፉ ዜናዎችን እየሰማ ነበር። ባልና ሚስቱ በየቀኑ ስለሱ የሚሉትን ሁሉ የሚነግሩት በረከቱ። እሱም ከስንቅ ጋር የሚቀበለውን አሉባልታ እየሰማ በንዴት መጦፍ ጀመረ።
የበቀለ ወሬ አመላላሾች ባልና ሚስቱ ከእስር ሲፈታ እንደማይለቁት መስማታቸውን አረጋግጠው ነግረውታል። እሱም ቢሆን ዛቻውን በቀላሉ ሰምቶ አልተወውም። የሚችለውን ሁሉ ማስፈራራት እየላከ እንደማይሸነፍ ሲያሳውቃቸው ቆይቷል። ሁሉንም የሚያውቁ አንዳንዶች ግን የሀይሉ ቤተሰቦች ድርጊትና ባልተገባው ዛቻቸው አዝነዋል። እሱ በእስር ላይ እያለ ዛቻና ማስፈራራት አግባብ እንዳልሆነ ሊነግሯቸው ሞክረዋል።
በርከት ያለው ቤተሰብ መሀል የተፈጠረው ያለመግባባት ሌሎች እህትና ወንድሞቻቸውንም ማሳዘኑ አልቀረም። መግባባት ሲቻል መጣለት፣ መታረቅ ሲገባም መካሰስና መታሰር በመፈጠሩ በሁሉም ዘንድ ቅያሜን አስከትሏል።
ከእስር መፈታት
በቀለ በፈፀመው ስህተት እስር ተወስኖበት ማረሚያ ቤት ከገባ አስራ አንድ ወራት ተቆጥረዋል። ሁሌም ቢሆን የመታሰሩን ጉዳይ ሲያስበው ውስጡ በንዴት እየጋመ በቁጭት ይበግናል። ከጥቂት ጊዚያት ወዲህ ግን ውስጡ በሌላ ዕቅድ ተይዟል። የተወሰነበትን የእስር ቅጣት ለማቅለል ‹‹ይግባኝ›› መጠየቅን እያሰበ ነው።
እሱ ያሰበው ተሳክቶለት ከእስር ከተፈታ ህይወቱን በአዲስ ለመጀመር ያስባል:: ከጠብና ከጭቅጭቅ ርቆ ሰላማዊ ህይወትን መቀጠል ግድ ስለመሆኑም የእስር ቆይታው በሚገባ አስተምሮታል።
በቀለ ያሰበውን ዕቅድ በሙከራ ተራምዶበት ይግባኙን በማመልከቻ ጠየቀ። የማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎችም እስከዛሬ በነበረው ቆይታ ያሳየውን በጎ ሥነ ምግባር ከግምት አስገብተው ሕጉ በሚፈቅደው አሠራር ከእስር እንዲለቀቅ ፈቀዱለት። በቀለ ይህን ሲያረጋገጥ ልቡ በደስታ ተሞላ።
ጓዙን ሽክፎ ከማረሚያ ቤቱ ሲወጣ አዲስ ተስፋ ታየው፤ መለስ ብሎ ደግሞ የሚገባበትን ግቢና የሚኖርበትን ቤት አሰበ። በዚህ መሀል ልቡ ተረበሸ:: ወንድሙና ሚስቱ ከልጃቸው ጋር ተባብረው ያደረጉትን ውል ቢልበት ውስጡ በነገር ጎሸ። ይህን እያሰበም ወደሰፈሩ አቀና።
የበቀለን ከእስር መፈታት ያዩ በመልካም ምኞት እየሳሙ ተቀበሉት:: አንዳንዶችም በአጭር ጊዜ በመለቀቁ ተገርመው ተንሾካሾኩ። ከሀይሉ ጓደኞች አንዱ ደግሞ የእጅ ስልኩን አንስቶ የወንድሙን መፈታት ከታላቅ ሥጋት ጋር አሳወቀው።
ሀይሉ ወሬው ሲደርሰው የጓደኛው ሥጋት ተጋብቶበት በድንጋጤ ክው እንዳለ ቆየ። የወንድሙን የሁለት ዓመት እስር ሲጠብቅ ዓመት ባልሞላ ጊዜ መለቀቁን አስቦም ንዴትና ቁጭት ተሰማው። ጥቂት ቆይቶ ስልክ እየደወለ ለሚመለከታቸው ሁሉ የሰማውን አሳወቀ።
ታላቅ ወንድማቸው የበቀለን ከእስር መፈታት ከሀይሉ በሰማ ጊዜም በነገሮች ሁሉ እንዲጠነቀቅ ምክሩን ለገሰው። ከእናቱ ልጅ ጋር መጣላት እንደማይበጀው ነግሮም ሊገስፀው ሞከረ። በቀለ ግን ምክሩን ሊቀበል አልወደደም። ስልኩን ዘግቶ ለባለቤቱ በመደወል ሁኔታውን በበጎ እንዳታየው አስጠነቀቃት።
ጉዞ ወደቤት
በቀለ በቢጫ ፌስታል የቋጠረውን ጓዙን እንደያዘ ወደ መኖሪያው ሲያመራ አንድ የሰፈሩ ልጅ ዕቃውን ተቀብሎ ወደቤቱ አስገባው። አንዳንድ የሰፈሩ ሰዎች በበቀለ መፈታት ተደስተውም ‹‹እንኳን ለቤትህ አበቃህ›› እያሉ ተቀበሉት። የቅርብ የሚባሉትም ወሬውን ተቀባብለው ለመንደሩ አዳረሱት።
በቀለ በግቢው ከሚገኝ የእህቱ ቤት ጥቂት አረፍ ብሎ ወደ መኖሪያው አመራ። በስፍራው ሲደርሰ ግን ቤቱን እንደነበረ አላገኘውም። ቁልፉ መሰበሩንና ክፍሉ መበርበሩን ሲያውቅ ዓይኖቹን ወደ ወንድሙ ቤት ልኮ በትዝብት ቃኘ።
ሁኔታውን ያስተዋለው ሀይሉ የበቀለ አስተያየት ገብቶታል። ዓይን ለዓይን እንደተጋጠሙ ነገር ፈለገው። ይህኔ በቀለ ቤቱ ለምን እንደተሰበረ ጠየቀ። ሀይሉ ለምላሹ ማብራራት አልፈለገም። ልክ እንደቀድሞው እጁን ጨብጦ ተጠጋው። በጭቅጭቃቸው መሀል አለመግባባቱ ባሰ። ንግግራቸው ተካሮም አንገት ለአንገት ተያያዙ።
ሀይሉ እየደጋገመ ወንድሙ ከቤት እንዲወጣ እያስጠነቀቀው ነው። በቀለም ‹‹በሕግ አምላክ›› እያለ መማፀኑን ቀጥሏል። ሀይሉ እሱን ጨፍጭፎ መልሶ ወደ እስር እንደሚያስገባው እየዛተ ነው። ባሻገር የታሰረው ውሻ ደግሞ በሁለቱ ግብግብ ተረብሾ ግቢውን በጩኸት ማወክ ጀምሯል። ወንድማማቾቹ በእልህ ተያይዘው መደባደባቸውን ቀጥለዋል። ገላጋይ በሌለበት መካረር የጀመረው ጠብ መልኩን ሲቀይር ታስሮ የነበረው ውሻ ከገመዱ በጥሶ መሀላቸው ገባ። ይህኔ ሀይሉ ከወደቀበት ሆኖ በዓይኑ አንዳች ነገርን ፈለገ።
በቀለ ከውሻው ለማምለጥ ወደመሬት ዝቅ እንዳለ ወደውጭ ለመሮጥ ተንደረደረ፤ ሀይሉ በአጋጣሚ በእጁ የገባውን ወፍራም አጣና ይዞ ከኋላው ደረሰበት፤ አላመለጠውም፤ በያዘው ዱላ አናት አናቱን ደጋግሞ እየመታ ከመሬት ጣለው።
አቅም ያጣው በቀለ የሚወርድበትን የዱላ መዓት መቋቋም አልቻለም። ከወንድሙ በድጋሚ ያረፈበት ከባድ ቦክስም ፊቱን በደም አጥቦ በጀርባው ዘረረው። ይህን ሲያይ ሀይሉ በፍጥነት የግቢውን በር ዘግቶ ወደቤቱ ተመለሰ። የእጅ ስልኩን አውጥቶም ለታላቅ ወንድሙ ደውሎ የሆነውን ሁሉ ነገረው። በንግግሩ መሀልም እየደጋገመ ‹‹ጣልነው፣ ከሸከሽነው›› ሲል ተሰማ።
ታላቅ ወንድም በስልክ የሰማውን ባለማመን እየሮጠ ወደ ግቢው ደረሰ። ሀይሉ እግሩ ተጎድቶ እየደማ መሆኑን ሲያውቅም ለማሳከም ወደክሊኒክ ወሰደው። ሃይሉ ቁስሉን ከታከመ በኋላ ወደ ቤት መመለስ አልፈለገም። ከእስር የተፈታው ወንድሙ ጥቃት እንዳደረሰበት ለመክሰስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራ። ፖሊስ ሀሳቡን ከተቀበለ በኋላ በወንድሙ ላይ ጥቃት በማድረስ ወንጀል እንደሚፈልገው ነግሮ በቁጥጥር ስር አዋለው።
በቀለ ጉዳት እንደደረሰበት ያዩ የሰፈሩ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያ አደረሱት። በዕለቱ የነበሩት የህክምና ባለሙያዎች ጉዳቱ ከአቅም በላይ መሆኑን ጠቅሰው ወደሌላ ሆስፒታል ላኩት። በሆስፒታሉ ቀናትን ያስቆጠረው በቀለ እንደምንም አንደበቱን ከፍቶ ወንድሙ ያደረገውን በሙሉ እንደተናገረ ትንፋሹ ቀጥ አለች።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ወንድም በወንድሙ ላይ የፈፀመውን የወንጀል ድርጊት በማስረጃ አረጋግጦ ምርመራውን አጠናቋል:: የህክምና ምርመራው ተጎጂው በሰው እጅ እንደተደበደበና የጉዳት መጠኑን ጠቅሶ ማስረጃውን ልኳል። በበቂ ምስክሮችና በአስተማማኝ መረጃዎች ማስረጃዎቹን የሰነደው ፖሊስ በረዳት ሳጂን አዲስ መቻል መርማሪነት በመዝገብ ቁጥር 392/09 ያጠናከረውን ሰነድ ለዓቃቤ ሕግ አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2012
መልካምስራ አፈወርቅ