የጋዜጠኝነት ሙያ በዘመናችን ከሙያነት ይልቅ ወደ ተልዕኮነት አመዝኗል በሚባልበት በዚህ ወቅት ባደጉና በበለፀጉ አገራት ጭምር ጋዜጠኞች ሲታሠሩና ሲገደሉ መስማት የተለመደ ነው። በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ አገራት በፖለቲካ፤ ሙስናና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ጋዜጠኞች በመንግሥታት እጃቸው ሲጠመዘዝ፤ ሲታሠሩና ዕጣ ፋንታቸው ሞት ሲሆን መመልከት ብርቅ አይደለም። በቅርቡ እንኳን በቱርክ በሚገኘው የሳውዲ ዓረቢያ ኤምባሲ እንደተገደለ የተነገረው የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ትኩረት በመሳብ የዓለማችን አጀንዳ እስከ መሆን ደርሷል።
እንደ አገር ከተቋቋመች ገና በጣት የሚቆጠሩ ዓመታትን ያሳለፈችው ወጣቷ አገር ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከጋዜጠኝነት ሥራ ጋር በተያያዘ አደጋው እጅግ የከፋ እየሆነ መምጣቱን አልጄዚራ ሰሞኑን ያወጣው ሐተታ ያመለክታል። በዚህች አገር በፖለቲካ፤ ሙስናና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ጋዜጠኞች ህይወታቸው በአደጋ የተከበበ መሆኑን ዘገባው ያትታል።
የሰላሳ ሦስት ዓመቱ ደቡብ ሱዳናዊ ሬይ ኦኬች በዚህች አገር የጋዜጠኝነት ሥራውን በማከናወን ብዙ ችግሮች የደረሱበት ባለሙያ ነው። ኦኬች በዚሁ ሥራ ላይ እያለ ከአንዴም አራት ጊዜ ለእስር እንደተዳረገ ይናገራል። ከመታሰር በዘለለም ጋዜጠኝነት ምን እንደሆነ ፍንጭ እንኳን በሌላቸው የፀጥታ አካላት ድብደባ እንደደረሰበትም ያብራራል። ይህም እንደሌሎቹ የሙያ አጋሮቹ ወደ ፊት በጋዜጠኝነት ሙያ አገሩን ለማገልገል ያለውን ተስፋ እንዳጨለመበት ይናገራል።
እ.ኤ.አ 2011 ላይ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተለይታ ነፃነቷን ባወጀችበት ወቅት ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ እንደገባ የሚናገረው ኦኬች በተለይም አገሪቱ ነፃነቷን በቅጡ እንኳን ሳታጣጥም ወደ ዕርስ በዕርስ ጦርነት በመግባቷ ሙያውን አዳጋች እንዳደረገው ያስረዳል። «የዕርስ በዕርስ ጦርነቱ እንደተጀመረ ነገሮች እጅግ አስቸጋሪ እየሆኑ መጡ፤ የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆኑም በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ተዟዙሮ የጋዜጠኝነትን ሥራ ማከናወን አደጋው የከፋ እየሆነ መጣ» በማለት ሁኔታውን ያስረዳል።
የኦኬች ባልደረባ የሆነው ሌላኛው ደቡብ ሱዳናዊ ጋዜጠኛ ፒተር ሞይ እ.ኤ.አ 2015 ላይ መገደሉን ተከትሎም በአገሪቱ የጋዜጠኝነት ሙያ አደጋ ውስጥ መግባቱን ያብራራል። ኦኬች ከሟቹ ጋዜጠኛ ጋር አብሮ በሚሠራበት ወቅት በጥይት ተመቶ ህይወቱ ሲያልፍ መመልከቱን ይናገራል። «ፒተር ሞይ ከመገደሉ አስራ አምስት ደቂቃ በፊት አነጋግሮኝ ነበር፤ በወቅቱ እንደፈራና ከዚህ በኋላ በፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ለመሥራት ፍላጎት እንደሌለው ነግሮኝ ነበር» በማለት የተፈጠረውን ያስታውሳል። ፒተር ሞይ የተገደለው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በአገሪቱ ጋዜጠኞች ላይ ዛቻ አዘል አስተያየት ከሰጡ ከቀናት በኋላ ነበር።
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ ከ2011 ወዲህ በደቡብ ሱዳን ቢያንስ አስር ጋዜጠኞች ተገድለዋል። ይህም ደቡብ ሱዳንን በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ከመቶ ሰማንያ አገራት መቶ አርባ አራተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። በዘንድሮው ዓመት ግን ደረጃዋ በአንድ መሻሻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህንን አስመልክቶ በደቡብ ሱዳን ሰብአዊ መብት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው የጋዜጠኞች ቡድን መሪ የሆነችው ላውራ ቤን በአገሪቱ የጋዜጠኝነት ሙያ ነፃነት ዙሪያ ትንሽ ለውጥ ቢኖርም ጋዜጠኞች አሁንም ድረስ በፀጥታ ጉዳይ ኃላፊዎች ማስፈራሪያ እንደሚደርሳቸው ትናገራለች።
በደቡብ ሱዳን በእንግሊዘኛ ቋንቋ በየዕለቱ እየታተመ ለንባብ በሚበቃውና ገለልተኛ እንደሆነ በሚነገረው ጁባ ሞኒተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና ኒሚሪያኖ በቅርቡ እንደተናገረችው ባለፉት ዓመታት የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋዜጠኝነትን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት በጋዜጣው ላይ የሚያደርጉት መጠን ያለፈ ግምገማ አሳሳቢ ነበር። በአገሪቱ ካቶሊክ ሬድዮ ኔትወርክ ጋዜጠኛ የሆነችው የሃያ ዘጠኝ ዓመቷ ማውራ አጃክ ጋዜጠኞች ካሜራቸውን ሲጠቀሙ እንደጦር መሣሪያ የሚመለከቱ ባለሥልጣናት ሪፖርተሮችን እንደጠላት የመመልከት አባዜ እንዳለባቸው ታስረዳለች።
ይህች ጋዜጠኛ በአገሪቱ ከተለያዩ ሰዎች ላይ መረጃ መቀበልና ቃለ መጠይቅ ማድረግ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነም ትናገራለች። « ሰዎች አሁንም ድረስ ስለዕርስ በዕርስ ጦርነቱ መናገር አይፈልጉም፤ ሌላው ይቅርና ቀላል ጥያቄዎችን ለመመለስ እንኳን ፍርሃት አለባቸው፤ ምክንያቱም ቃለመጠይቅ መስጠታቸው ፖለቲካ ውስጥ ሳይፈልጉ እንደሚያስገባቸውና ለእስር እንደሚዳርጋቸው ይሰጋሉ» በማለትም የጋዜጠኝነት ሙያ በዚህች አገር ምን ያህል ፈተና ውስጥ እንደገባ ታብራራለች። ይህም የጋዜጠኝነትን ሙያ ፈታኝ ከማድረጉ ባሻገር ሙያውን ትቶ ወደ ሌላ ነገር ለማተኮር አስገድዷታል።
በደቡብ ሱዳን ጋዜጠኝነት ሌላም ፈተና አለበት። በዚህ አገር ጋዜጠኝነት ጥሩ ክፍያ የሚያስገኝ ሙያ አይደለም። አብዛኞቹ የአገሪቱ ጋዜጠኞች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ማስተዳደር የሚችል ገቢ ከሞያው አያገኙም። ከዚህ ጎን ለጎን ከሚያገኙት በቂ ያልሆነ ክፍያ ላይ ለሙያው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን የመግዛትና ዜናዎችን ለመሥራት ወደ ተለያየ ሥፍራ ሲጓዙ የትራንስፖርት ወጪን የመሸፈን ግዴታ አለባቸው። ይህም ሙያውን እየወደዱትም ቢሆን ሳይፈልጉ እንዲርቁት እያደረጋቸው ይገኛል።
አጃክ ይህንን በማስረጃ አስደግፋ ስትናገር በወር አንድ መቶ ሃያ ዶላር ብቻ እንደሚከፈላት ታስቀምጣለች። ይህም ክፍያ የስድስት ዓመት ሴት ልጇን ለማሳደግ በቂ ስላልሆነላት ከደቡብ ሱዳን ውጭ የሚገኙ እናቷ ጋር ለማቆየት ተገዳለች። ይህ ክፍያ ለሁለት ዓመታትም ልጇን ርቃ እንድትቆይ አድርጓታል። ክፍያው ራሷንም ለማኖር በቂ ባለመሆኑ ለሌሎች የውጭ አገር መገናኛ ብዙኃን ጽሑፎችን በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ግዴታ ውስጥ ከቷታል።
በደቡብ ሱዳን ባለው የትምህርት ጥራት ችግርና የፀጥታ ጉዳይ ምክንያት ልጆችን ወደ ጎረቤት አገራት በተለይም ወደ ሱዳንና ዩጋንዳ መላክ የተለመደ በመሆኑ አጃክ የወሰደችው ውሣኔ ለጊዜውም ቢሆን ትክክል መሆኑን ታስረዳለች። ኦኬች የተባለውም ጋዜጠኛ በዚሁ ችግር ምክንያት ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱን ከደቡብ ሱዳን ውጭ የላከ ቢሆንም በሥራው ላይ በተጋረጠው አደጋ ምክንያት ሙያውን ትቶ ቤተሰቦቹን ለመቀላቀል ወስኗል። አጃክ ግን ሥራዋን የመልቀቅም፣ ከደቡብ ሱዳን የመውጣትም፣ ዕቅድ እንደሌላት ትናገራለች። «የእኔ ዕጣ ፋንታ እዚህ ነው፤ ለአገሬና ለወገኔ ጥሩ ነገር የመሥራት ግዴታ አለብኝ፤ ቀጣዩ ትውልድ ሊከተለው የሚገባ ነገር መሥራት እፈልጋለሁ፤ በየቀኑ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ» በማለትም ለሙያውና ለአገሯ ሕዝብ ማገልገልን መርጣ ጁባ ለመቆየት ቆርጣለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2011
ቦጋለ አበበ