ሀገራት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን በማስመዘገብ ድህነትን ለመቅረፍና የብልጽግና ማማን ለመቆናጠጥ ያዋጣናል የሚሉትን የኢኮኖሚ አማራጭ ይከተላሉ። ከዚህ አንጻር ሀገራችን ኢትዮጵያም ኢኮኖሚዋን በፍጥነት በማሳደግ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ ከነዚህ አማራጮችም ውስጥ ለውጭ ኢንቨስትመንት የተሰጠው ትኩረት ዋነኛው ነው፡፡
ይሁን አንጂ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየተገበረች ያለችው በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ መሠረት ያደረገ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጥገኝነትን ያስከትላል የሚል ትችትም ይቀርብበታል፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ግን የውጭ ኢንቨስትመንቱ አስፈላጊነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ቁጥጥር እየተደረገበት በአግባቡ ካልተያዘ ጎጂ ጎኑ አይሎ ስጋት መሆኑ እንደማይቀርም ይገልጻሉ፡፡
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚገልጹት የውጭ ኢንቨስትመንት ከልማት ግብዓት አንዱ በመሆኑ ለእድገት መሰረታዊ ጉዳይ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ገና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቀርቶ የበለፀጉ ሀገራትም የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በሀገራቸው ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹም ይገልፃሉ፡፡ የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ረገድም አሜሪካ ቀዳሚ ስፍራ መያዟን ማስረጃዎችን በማጣቀስ ያብራራሉ፡፡
በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች የሰዎች የዕለት ተዕለት ገቢ አነስተኛ በመሆኑ በቁጠባ የሚገኘው ገቢ አነስተኛ ነው፡፡ይህ ደግሞ ለተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሚናው ያነሰ ስለሚሆን ወጪዎችን መሸፈኛ ካፒታልን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ግድ ይላቸዋል፡፡
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የገንዘብ፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማስገኘትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ድርሻው ጉልህ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ፍሬዘር፤ ይሁንና የውጭ ኢንቨስተሮች መሳተፍ ያለባቸው ከፍተኛ የእውቀትና የገንዘብ አቅም በሚጠይቁና በሀገር ውስጥ ሊሸፈኑ በማይችል ዘርፎች ላይ ነው ይላሉ፡፡መሬቱና የሰው ሀብቱ የሀገር በመሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ ኢኮኖሚን ማሳደግ ይገባል፡፡በዚህ መልኩ ከተከናወነ ኢኮኖሚው እያደገ፣ ፍላጎትና አቅርቦት እየተጣጣመ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እየጨመረ፣ ቴከኖሎጂን የማላመድና እውቀትንም የማስረጽ አቅም ይፈጠራል፡፡
የውጭ ኢንቨስትመንት ጥቅሙ ከፍተኛ ቢሆንም በጥንቃቄ ካልተያዘ ግን ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጎ ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነም ምሁሩ ይጠቁማሉ፡፡ የኢኮኖሚ ጥገኝነት ወይም ቅኝ ግዛትነት የሚፈጠረው የውጭ ባለሀብቶች ያለገደብ እንዲሰሩ መንገድ ተከፍቶላቸው በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አቅም ሊሸፈኑ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ሲሰማሩና ለሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል መፍጠር ሲኖርባቸው የራሳቸውን ሰው የሚያሰሩ ሲሆን እንደሆነም አብራርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሚያገኙትን ትርፍ ወደ ሌላ ሲያሸጋግሩ ስጋት ይፈጠራል በማለት የደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ የነጭ የበላይነት የሰፈነበትን ታሪክም አቶ ፍሬዘር ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በሀገራቱ ከነጮች መሬት ነጥቆ ለዜጎች የመስጠት ደረጃ ላይ የተደረሰበትንም አጋጣሚ ወደ ኋላ መለስ ብለው አስታውሰዋል፡፡
በግላቸው የምጣኔ ሀብት ላይ በማማከር የሚሰሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር በየነ ታደሰ እንዳስረዱት የውጭ ኢንቨስተሮች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ባለው እርከን ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ሲጠበቅባቸው የሰው ኃይልን የሚቀንስ ቴክኖሎጂ የተጠቀሙ እንደሆነና የሠራተኛውን መብት ጥሰው ሲገኙ አላግባብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ በሲሚንቶ ማምረት ላይ የተሰማራው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር ያለው አቅም አነስተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ሀገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመፍታት የውጭ ባለሀብቶች ገንዘብ ይዘው እንዲመጡና ወደሥራ ከገቡም በኋላ ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ይጠበቃል፡፡ ብዙዎቹ የውጭ ኢንቨስተሮች ጥቂት ገንዘብ ይዘው በመምጣት ከኢትዮጵያ ልማት እና ኮሜርሻል ባንኮች ብድር በመውሰድ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ አካሄዱ የሀገሪቷን ችግር የሚፈታ ሳይሆን ባለሃብቶችን ነው ተጠቃሚ የሚያደርገው፡፡ ለአብነትም በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣በቤንሻንጉል ክልሎች በእርሻ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በአበባ እርሻ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ብድራቸውን ሳይከፍሉ የጠፉበት ሁኔታ መታየቱን ይናገራሉ፡፡
ባለሀብቶቹ እነርሱ በሚመቻቸው መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ተጽእኖ ስለሚፈጥሩና መንግሥትም ከችግሩ አኳያ ለቀቅ ስለሚያደርግ ምርታቸውን በምን ያህል ዋጋ እንደሸጡና ገቢያቸውንም ለማወቅ ያዳግታል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ደግሞ ሀገሪቷ መጠቀም የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ ያደርጋል፡፡ ባለሀብቶቹ መጠበቅ ያለበትን ደን በመመንጠር ለአካባቢ ብክለት ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት የሚሰሩት ሥራም የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ መንገድ እንደሚከፍት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችንም በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዶክተር በየነ ማብራሪያ የኢንቨስትመንት፣ የንግድ እና የታክስ ስርዓቱ ለእነርሱ በሚመች መንገድ ተፈጻሚ እንዲሆን ተጽዕኖ በማሳደር፣ እንዲሁም በፖለቲካው ውስጥም ጣልቃ በመግባት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመደገፍና አስፈጻሚዎችን በገንዘብ በማማለል የኢንቨስትመንት ዘርፉን በሚመቻቸው መንገድ ለማንቀሳቀስ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ገበያውን እንዲቆጣጠሩ እድል ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳም አቅማቸው አነስተኛ የሆኑትን ባለሀብቶች እንቅስቃሴ ያቀጭጫል፡፡ በዚህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ይጎዳሉ፡፡ የሀገሪቷን የኢንቨስትመንት ዓላማም ያስታል፡፡
የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ስለ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ስለ ውጭ ምንዛሪ ግኝትና ስለአካባቢ ጥበቃ በአጠቃላይ በኢንቨስትመንት ፖሊሲው ላይ በባለሙያ በተደገፈ አሰራር ግልጽ የሆነ ስምምነት መኖር አለበት፡ ፡ስምምነቱ ግልጽ ካልሆነ በህግ ለመጠየቅ አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ በዲፕሎማሲ ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡
የውጭ ኢንቨስትመንት በጥንቃቄ ካልተያዘ፣ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ካልተደረገበት የሀብት ብክነት ያስከትላል፣አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ከተገባም ባለሀብቶቹ ሀገራቸውን ወክለው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከየሀገሮቻቸው ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያሻክረው ይችላል፡፡
ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን የውጭ ኢንቨስትመንትን ማስቀረት እንደማይቻል የሚገልጹት ሌላው በግላቸው በማማከር ሥራ ላይ ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ጌታቸው ሚናስ የንግድና የኢንቨስትመንት ፖሊሲው የሀገርን ጥቅም የሚያስከብር ካልሆነ ፣የቁጥጥርና ክትትል ስርዓቱም ደካማ ከሆነ ጥገኝነቱ እንደሚኖር ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በጥምር የሚሰሩበትን አማራጭ መፍጠር፣ ስርዓት ተከትለው የማይሰሩ የውጭ ኢንቨስተሮች ችግሩ ስር ሳይሰድ ተከታትሎ መፍትሄ በመስጠት ስጋቱን ለማስቀረት ይረዳል፡፡ የውጭ ኢንቨስተር የሚያመርተውን ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ ከሆነ ግን አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
እንደ ምጣኔ ባለሙያዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብትን ያላማከለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም ሆነ የውጭ ባለሀብቱ እንደፈለገ እንዲንቀሳቀስ በር ተከፍቶለት ገበያውን ከተቆጣጠረው የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን ብቻ ሳይሆን ገበሬውንም ከዕርሻው እስከማፈናቀል ሊያደርስ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቷ ኢኮኖሚዋን በምትፈልገው መንገድ እንዳታሳድግ እንቅፋት ይፈጥራል፡፡
ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተያዘው ግብ እንደሚያሳየው በ2012 መጨረሻ ኢንቨስትመንት (የግልና የመንግሥት) ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚኖረው ድርሻ 41.3 በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል በያዝነው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የወጪ ንግድ ገቢ አገልግሎትን ጨምሮ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ከፍተኛ ዕመርታ በማሳየት በ2007 ከነበረበት 9.7 በመቶ በ2012 ወደ 20.6 በመቶ እንደሚያድግና የገቢ ንግድ ወጪ አገልግሎትን ጨምሮ ደግሞ በ2007 ከነበረበት 27.1 በመቶ በ2012 ወደ 32.3 በመቶ ከፍ እንደሚልም ይጠበቃል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በቀሪው የእቅድ ዘመኑ ክፍተቶችን መለየትና የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ ከመንግሥት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 12/2011
ለምለም መንግሥቱ