አዲስ አበባ፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመው የተሸሸጉ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተርና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ አቶ ኦባንግ ሜቶ ተናገሩ፡፡
አቶ ኦባንግ ሜቶ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሰሞኑን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አስመልክቶ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ባስተላለፉት ዶክመንተሪ የታየው እውነታ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ ቢሆንም ለእኔ ግን አዲስ አይደለም ብለዋል፡፡ እኔና ጓደኞቼ ስለሰብዓዊ መብት ጥሰት ስንሞግት መንግሥት ጸረ ልማትና አሸባሪዎች ናቸው ይለን ነበር፤ ዛሬ ግን አሸባሪው ማን እንደነበረ የኢትዮጵያ ህዝብ ተገንዝቧል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመው የተሸሸጉትንም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለህግ እንዲቀርቡ የበኩላችንን ድርሻ እናበረክታለን በማለት አስረድተዋል፡፡
አቶ ኦባንግ ድርጅታቸው የሰብዓዊ ምብት ጥሰት ፈጽመው የተሸሸጉ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆምም ያሳወቁ ሲሆን፤ በዚህም ‹‹ሰርቆ መንደላቀቅ ወንጀል ሰርቶ መደበቅ አይቻልም›› በሚል ሰሞኑን መንግሥት ያወጣውን መግለጫ በመደገፍ ወንጀለኞች የትም ቢሸሸጉ በሰብዓዊ መብት ጥሠት ላይ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ፍርድ እንዲያገኙ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ወንጀለኞቹ በሀገር ውስጥም ይሁን በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዓይን ስለማይሰወሩ እያንዳንዱ ዜጋ መረጃ በመስጠት ትብብር ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
እንደ አቶ ኦባንግ ገለጻ፤ በአገሪቱ ባልተለመደ መልክ ይፈጸም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዜጎች ላይ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ያስከተለ፤ የህዝብን አንገት ያስደፋና የሀገሪቱንም ገጽታ ያበላሸ ነው፡፡ ‹‹አሁን ኢትዮጵያን ብርሃን ያጎናጸፋት ለውጥ በብዙ መስዋትነት የመጣ ስለመሆኑ በመገናኛ ብዙሃን ያየነው የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ሰቆቃ ምስክር መሆን ይችላል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ያላገኙትን የተሰወሩ፣ የተገደሉና መሰል ጥቃት የተፈጸመ ባቸውን ደግሞ ቤቱ ይቁጠራቸው›› ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ኦባንግ አባባል፤ እውነትና ንጋት አንድ ናቸው፡፡ እውነት ብርሃን ነው፡፡ ብርሃን ሲመጣ ጨለማ ቦታውን ይለቃል፡፡ እነዚህ በደልና ሰቆቃን በገዛ ወገናቸው ላይ የፈጸሙ ወንጀለኞች የጨለማ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ምድር የፈነጠቀው ብርሃን ዳግም በጨለማ እንዳይዋጥ ለውጡን እንደዓይናችን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል፡፡ ወንጀለኞችም በሠሩት ሥራ በህግ መጠየቅ አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2011
በኢያሱ መሰለ