የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ የምርመራ ጥናቶችን አስተባብረዋል፡፡ እ.አ.አ በ2003 በጋምቤላ በአኝዋክ ሕዝብ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 424 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ በ2004 የአኝዋክ ጀስቲስ ካውንስልን አቋቁመዋል፡፡ የካውንስሉ ዓለም አቀፍ አድቮኬሲ ዳይሬክተር በመሆን ከተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመተባበር በአኝዋክ ሕዝብ ላይ የተጋፈጠው ችግር ትኩረት እንዲያገኝ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡
የሰብአዊ መብት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ይከበር ዘንድ ልክ እንደ አኝዋኮች ሌሎችም ተቋማዊ ድምፅ ኖሯቸው እንዲሰሙ ‹‹ሶሊዳሪቲ ሙቭመንት ፎር ኤ ኒው ኢትዮጵያ››ን መስርተዋል፡፡ በተቋሙ አማካኝነት በአካባቢ፣ በክልል፣ በሀገርና እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩነቶችን ማስታረቅ ላይ ያተኮሩ ዘመቻዎችን አከናውነዋል፡፡
‹‹ሂውማኒቲ ቢፎር ኢቲኒስቲ» እና «ኖ ዋን ኢዝ ፍሪ አንትል ኦል አር ፍሪ» በሚሉ መርሆች የዘር ክፍፍሎችን ለማስወገድ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ለሀገር ትልቅ ውለታን ውለዋል፡፡ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በዩኒቨርሲቲዎች ጭምር በመዘዋወር ሕዝብን አንድ ለማድረግ መልካም አመለካከትን የሚገነቡ ንግግሮችን በማድረግ ይታወቃሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ባሻገር በአፍሪካ የሰብአዊ መብት ፍትህና ተጠያቂነት የሰፈነበት ፖለቲካ እንዲኖር ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከአውሮፓ ፓርላማ፣ ከአሜሪካ ምክር ቤቶች እንዲሁም ከዓለም ባንክ ጋር ከ10 ዓመታት በላይ ሰርተዋል፡፡ በመሬት ወረራ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የሚፈናቀሉትን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠርና የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ዓለም አቀፍ ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡ እነዚህና ሌሎች ሥራዎቻቸው ‹‹ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዳያስፖራዎች›› በሚል ዘርፍ የ2011 ዓ.ም የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆን ችለዋል የዛሬው የሕይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን አቶ ኦቦንግ ሜቶ፡፡ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ እነሆ ለንባብ ብለናል፡፡
ሦስተኛው ልጅ
በአኝዋክ ብሔረሰብ ባህል ከአንድ እስከ ሦስት የሚወለድ ልጅ የራሱ የሆነ መጠሪያ ስም በመደበኛነት ይሰጠዋል። የተለየ ክብርም አለው። እናም እንግዳችንም ከእነዚህ መካከል አንዱ ናቸው። ምክንያቱም ለመጀመሪያው ኦሞድ ወይም ኤሞድ የሚል ስም የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህ ማለትም መንገድ፣ በኩር፣ በር ከፋች ሊሉት ሲፈልጉ ያወጡለት ነው። ሁለተኛውን ደግሞ ኡጁሉ ወይም ኤጅሉ ሲሉ ይጠሩታል።
ስያሜውም አጋዥ የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል። ብቻውን እንዳይሆን ወንድም ወይም እህት ሰጠው ለማለት ይጠቀሙበታል። በሦስተኛነት የተወለደውን ወንድ ልጅ ደግሞ ልክ እንደእንግዳችን ኦቦንግ የሚል መጠሪያ ያወጡለታል፤ይህም አብሮነት፣ ማሳረጊያ መሆኑን ሊነግሩበት ስለሚፈልጉ ይጠቀሙበታል። ከዚያ በኋላ ለሚወለድ ልጅ ግን ቤተሰቡ የፈለገውን ስም ነው የሚያወጣለት።
በብሔረሰቡ ባህል ሴቶቹ ሲሆኑ የመጀመሪያዎቹ ፊደላት ወደ ኤ ተቀይሮላቸው እንዲጠሩበት ይደረጋል። በዚህም ሁሉም በአንድ ዓይነት ስም የመጠራት ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ለአብነት እንግዳችንም 400 ሰው በያዘ መድረክ ላይ ከ40 በላይ የሚሆኑት መጠሪያ ስማቸው ኦቦንግ የሆኑ ሰዎች አጋጥሟቸው እንደሚያውቅ ያስታውሳሉ። እና በምን አንዱ ከአንዱ ይለያል ከተባለ መልሱ ቅጽል ስም ማውጣት ነው። ስለዚህም ባለታሪኩም እርሳቸው መሆናቸውን ሊለይ የሚችል ቅጽል ስም ነበራቸው። ኦቦንግ ቀጫጫው፤ መዝናኛ ቦታ የተወለደው ኦቦንግ ለማለት ሲፈልጉም ኦቦንግ ቱዌር ይሏቸው እንደነበር አጫውተውናል።
አቶ ኦቦንግ፤ ‹‹አሁን ሀብት ንብረት ሞልቶኝ ከኖርኩት ሕይወቴ ይልቅ ደስተኛ የነበርኩት በልጅነት ጊዜዬ ነው። የልጅነት ሕይወቴ ፍቅር የተማርኩበት፣ መወደድና መከባበርን የለመድኩበት፤ ታዛዥነትና ታማኝነትንም እንዲሁ ያወኩበት ነው። በተለይም ሰውን በሰውነቱ ብቻ የምወድበት መንገድን የተማርኩበት ስለነበር አብዝቼ እወደዋለሁ›› ይላሉ። ይህ ጊዜ መተኪያ አይገኝለትም ሲሉ ይናገራሉ። እናም ዛሬ በአገራችን ጎዳና ላይ የወደቁትን ልጆች ሲያዩ ልባቸው እንደሚሰበር ይናገራሉ። ይህንን ትውስታ ሲገልጹትም እንዲህ ነበር ያሉት።
‹‹እኔን የሰራኝ የአካባቢዬ ሰው ነው፤ እኔን የሰራኝ ቤተሰቤ ነው። በዚህም ለጎረቤቶቼ ከቤተሰቤ ያነሰ ቦታ የለኝም። ማንኪያዬን ይዤ እነርሱ ቤት እበላለሁ፤እጠጣለሁ። ጨዋታም ሲያምረኝ እንደዚያው ገደብ ሳይኖርብኝ እጫወታለሁ። የእነርሱም ልጆች እንዲሁ እንደኔ በእኛ ቤት ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት ከውስጤ እንዳጠፋ አድርጎታል›። ዛሬ ግን ለምን ልጆችን በየአካባቢው ማሳደግ ተሳነን፤ ለምንስ ጎዳና እንዲወድቁ ፈቀድን ስል መልስ እያገኘሁ አይደለም። ይልቁንም በጣም የምታመምበት ሀሳብ ሆኗል›› ይላሉ የእርሳቸውን ልጅነትና የዛሬውን የልጅ አስተዳደግ ሁኔታ ሲያነሱ።
የአቶ ኦቦንግ እናትና አባት እንዲሁም አያታቸው አልተማሩም። በግብርና ሙያ ላይ ተሰማርተው ነው ልጆችቸውን ያሳደጉት። ነገር ግን ሰውን በሰውነቱ እያዩ እንዲያድጉ በእጅጉ ረድተዋቸዋል። እንዴት ከሰዎች ጋር መኖር እንደሚችሉም አስተምረዋቸዋል። ይህ ደግሞ ለትናንቱ ታዳጊ ለዛሬው ጎልማሳ እንግዳችን መሠረት የጣለ እንደነበር በሚያከናውኗቸው ተግባራት መረዳት ይቻላል።
አቶ ኦቦንግ በልጅነታቸው ከተጫወቱት ጨዋ ታዎች ሁሉ ቢደገም የሚሉት ባህላዊ ጨዋታዎችን ነው። በተለይ በጋምቤላ ባህል የጦር ውርወራ የተለየ ትኩረት ይቸረዋልና ዱባ መሃል ላይ አድርገው በተቀረጸ ጦር መሳይ እንጨት ሲተከትኩት የተሻለ ተጨዋችነታቸውን ያስመሰክርላቸው እንደነበር አይረሱትም።
አቶ ኦቦንግ ልጅ ቢሆኑም ብዙ ጊዜ ውሏቸው ከትልልቅ ሰዎች ጋር ነው። በዚህም የተጣሉ ልጆችን ያስታርቃሉ። መጣላትንም በፍጹም አይወዱም። እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ ሴት ልጅ መትታቸው አፀፋውን ባለመመለሳቸው ፈሪ የሚል ቅጽል ስም ወጥቶላቸው ነበር። ልጅነታቸውን ሲያስቡት የሚወዱበት ምክንያት በጋምቤላ ማህበረሰብ ዘንድ የነበረው መተሳሰብ፤ በህብረት መብላት፤ በአንድነት ለሁሉ ነገር መነሳት እንደሆነ ያነሳሉ።
‹‹በቀለምህ ምክንያት ብዙ ችግሮች ይመጡብሃል። አንተ ግን ሰውን በሰውነቱ ብቻ እንጂ በቀለሙ አይተህ እንዳትለይ። ራስህንም ቢሆን ከማንም አሳንሰህ ማየት የለብህም። እኩል እንደሆንክም አስብ። እውቀት የሌለውና ያልተማረ መኖሪያው ጭለማ ነው። በእውቀቱ የተጠቀመና እውቀቱን ያጎለበተ ወይም የተማረ ደግሞ ሁሌ ብርሃን ውስጥ ይኖራል። ስለዚህም አንተም ሁሌ በብርሃን ለመመላለስ ከፈለክ በትምህርትህ ጎበዝና አስተዋይ ልጅ መሆን አለብህ›› የሚለው የአያታቸው ምክር ከአዕምሯቸው አይጠፋም። አቶ ኦቦንግ በልጅነታቸው በትክክል ምን መሆን እንደሚፈልጉ ባያውቁትም በጣም ትልቅ የሥራ መስክ ላይ ተሰማርተው እንደሚሰሩ ግን በሚያደርጓቸው ተግባራት ይገምቱ እንደነበር ይናገራሉ። አንዳንዴ ደግሞ የገበሬ ልጅ ስለነበሩ በጣም ጥሩ ገበሬ መሆንን ይፈልጉ እንደነበርም ያነሳሉ።
በሰው አገር
አቶ ኦቦንግ፤ በ16 ዓመታቸው ነበር አገራቸውን ትተው ትምህርትን ፍለጋ ወደ አሜሪካ የነጎዱት። ስለዚህም ግማሹን የልጅነት ጊዜያቸውን በዚያ አሳልፈዋል። በዚህም በጥቁርነታቸው ብዙ ፈተና ገጥሟቸዋል። በተለይ ጓደኛ ፍለጋ ያደረጉት ትግል በጣሙን የፈተናቸው እንደነበር አይረሱትም። ምክንያቱም እርሳቸው የለመዱት አብሮ መብላት፣ መጠጣትና መጫወት ነው። እዚያ ደግሞ ሁሉ ነገር ለግል ነው። እናም ብቸኝነት ውስጣቸውን ያስጨንቃቸው ጀመር። በዚህም ለምን መጣሁ አሰኝቷቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ። እናም አንድ ቀን ቆራጥና ወሳኝ መሆን እንዳለባቸው አምነው ጓደኛ ለመፈለግ ተነሱ። አንዱ ልጅ ላይም ሙጭጭ አሉበትና ጓደኛ እንዲሆናቸው ጠየቁት።
እርሱ ግን እንደእርሳቸው ዓይነት ጥቁር ጓደኛ ኖሮት እንደማያውቅ ነግሯቸው ጓደኛ መሆን የሚችለው ጓደኞቹ ከፈቀዱለት መሆኑንም አስረዳቸው። ማስጨነቃቸው ሲበረታበት ግን መጀመሪያ ጓደኞቹን ጠየቃቸው። እነርሱም ‹‹ከእርሱ ጋር ጓደኛ ከሆንክ ከእኛ ጋር መሆን አትችልም›› አሉት። ግን ልጁ ሊተዋቸው አልወደደም። ስለዚህ ጓደኞቹን ትቶ እርሳቸውን ጓደኛ አደረጋቸው።
ጓደኝነታቸው ጠንክሮም ስለነበር እረፍት ላይ ቤተሰቡን እንዲያስተዋውቃቸው ጠየቁት። እርሱ ግን ፈራ። ለእናቱም ታይቶ የማይታወቅ ጥቁር ጓደኛ አለኝ ይዤው ልምጣ ሲል አስፈቀደ። በብዙ ትግልም ተፈቀደለትና በደስታ ቅዳሜና እሁድን አብረው አሳለፉ። ከዚያ ግን ጥቁረታቸው ውበት ሆኗቸው ለየት ያሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም ጓደኛ ሲመረጥባቸው የነበሩት ወደ መራጭነት ገቡ።
በአንድ ጊዜ ከስድስት ወደ አስር
እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ በዚያው በገጠራማዋ የትውልድ ቀያቸው ነበር ትምህርታቸውን የተከታ ተሉት። ምንም እንኳን ቤተሰቦቸቻው ያልተማሩ ቢሆኑም ለትምህርት ልዩ ፍቅር ነበራቸውና ያበረቷ ቸዋል። በዚህም ታዳጊው ኦቦንግም በትምህርታቸው ጎበዝ ነበሩ። ግን ጋምቤላ በትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት እንዲሁም በመምህራንና መሰል ጉዳዮች ላይ ያለው ትኩረት አናሳ ነውና በብዙ ትግል ውስጥ ነው ይህንን ጊዜያቸውን ያሳለፉት። ሆኖም ባለታሪኩ ይህንን አውቀው ባህር ማዶ ተሻግረው የሚማሩ ሁለት ወንድሞቻቸው ነበሩና እርሳቸውም ከስድስት በኋላ በዚያው እንዲቀጥሉ ስላልፈለጉ ወሰዷቸው።
የሌሎች ልጆች ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው የፈሩትም የስድስተኛ ክፍሉ ተማሪ ኦቦንግ፤ ጓዛቸውን ጠቅልለው ቤተሰቦቻቸውን ትተው ወደ አሜሪካ አመሩ። በዚያም እንደደረሱ የመግቢያ ፈተና ወሰዱና በቀጥታ አስረኛ ክፍልን ተቀላቀሉ። ለዚህ ደግሞ ብርታት የነበራቸው እንግሊዝኛ በሚገባ መቻላቸው እንደነበር ይናገራሉ።
እርሳቸው በሚማሩበት ወቅት ከጋምቤላ ውስጥ በትምህርት ዲፕሎማ ያለው ሰው 20 እንደማይሞላ የሚናገሩት አቶ ኦቦንግ፤ የጋምቤላ ተማሪ በብዙ ነገር ተበድሎ የቆየ መሆኑን ያነሳሉ። በተለይም በኢህአዴግ ዘመን «አናሳ ክልል» በሚል ተፈርጆ ብዙ ችግሮች አጋጥመውትም ነበር ይላሉ። የመማሪያ ክፍሎች፣ የቤተሰብ ሁኔታና የመንግሥት ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠው ግምት እጅግ የሚያሳዝን ነው።
ስለዚህም በአገራቸው ከመማር ይልቅ አሜሪካን የመረጡት ለዚህ እንደሆነ ይናገራሉ። በአሜሪካም ደረጃውን ጠብቀው እስከ 12ኛ ክፍል ዘለቁ። ይህ ከተጠናቀቀ በኋላ በዚያው ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ አጠኑ። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር የሕግ ትምህርት ቤት ተመዝግበው እያሉ የአገር ጉዳይ ገጠማቸውና ጋምቤላን ነፃ ለማውጣት ወደ ትግል ገቡ። በዚህም ሳይቀጥሉበት ቀሩ። እናም ትምህርት ያበቃው የመጀመሪያ ዲግሪ ላይ እንደነበር ያነሳሉ።
ትግል ለሰብአዊ መብት
ሁለት ዋና ጉዳዮች ወደዚህ ትግል አስገብተውኛል። የመጀመሪያው የጋምቤላ ልጆች ፈቃዳቸው ሳይ ጠየቅ በቀጥታ ታፍሰው ወደ ብሔራዊ ውትድርና መወሰዳቸው ነው። በተለይ ረጃጅሞቹ ልጆች ተምረው ራሳቸውን መለወጥ አይፈቀድላቸውም። ሲደበደቡና መብታቸውን ሲጠይቁም የሚሰማቸው አይኖርም። ትምህርት ቤት እንኳን ለምን ይህንን አልሰራችሁም ተብሎ መደብደቡ እጅግ የከፋና ዘግናኝ ነበር። ለምን ይሄ በእኛ ላይ ይሆናል የሚለው የልጅነት ጥያቄዬ መልስ ማግኘት ስላለበት ለሰብአዊ መብት ትግል ተነሳሁ ።
ሌላው ከዛሬ 22ዓመት በፊት የተከሰተው አጋ ጣሚ መሆኑ ይጠቅሳሉ። ይኸውም የእናታቸው እህት ስለታመሙ አዲስ አበባ አምጥተው እንዲያሳክሟቸውና ተንከባካቢ ቀጥረውላቸው እንዲመለሱ የእናታቸው እህት ልጅ አዘዛቻቸው። ከዚያም ቤት ተከራይተው ዕቃ በአይሱዙ ጭነው ለማስገባት በዝግጅት ላይ እያሉ አከራይዋ ድንገት ተከሰተች። ስታያቸውም ጋምቤላዊ መሆናቸውን ተረዳች።
ወዲያውም ደላላውን ጠርታ ‹‹ለእኛ ሰው አከራይ አልኩህ እንጂ ለዚህ ነው›› ብላ ተቆጣችው። ወዲያውም ገንዘቡን አምጥታ እንዲለቁ አደረገች። ይህ ደግሞ በጣሙን ልባቸውን ሰበረው። ‹‹እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም፤ የእኛ ማለት ምን ማለት ነው›› እያሉም ራሳቸውን እንዲጠይቁ አደረጋቸው። ከእርሳቸው አልፎ ባህር ማዶ ተሻግሮ ሳይቀር ያዘዛቸውንም ልጅ አስቀየመው።
ሌላ ቦታ ፈልገው ቢያስቀምጧቸውም ለምን ግን ከውስጣቸው ሳይጠፋ ግማሹን የልጅነት ጊዜ ወዳሳለፉበት አሜሪካ ተጓዙ። ለብዙ ጊዜም ከሌሎች የትውልድ ቀያቸው ነዋሪዎች ጋር የተስማማ ሀሳብ ያዙ። ሆኖም አንድ ቀን ግን ይህንን ስሜታቸውን በሰው አገር መልካም አስተሳሰብ ባለው አንድ የታክሲ ሹፌር ተቀየረ። የግለሰቦች ምልከታ ብዙዎችን እንደሚያርቅም አመላከታቸው።
እናም እውነትም እነዚህ አገር እንዲጠላ የሚያደርጉ ሰዎች መታረም ያለባቸው በእኛ ነው እንዲሉ አስቻላቸው። የአያታቸው ምክርም ታከለበትና ወደ ሰብዓዊ መብት ሙግቱ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው አጫውተውናል። ሌላው ለዚህ ትግል መሠረቱ 430 የጋምቤላ ልጆች አልቀው ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጣና መብት እንዲከበር በተለያየ መንገዶች ቅስቀሳ ቢደረግም የተገኘው ሰው በጣም ትንሽ መሆኑ ትግላቸው እንዳይገደብ ማድረጉን ያነሳሉ።
ስኬት
‹‹ሰው ከፋፍሎ፤ ገድሎ የተሸለመ የለም። በጎ ተግባር ግን አድርጎ ሰው ባይሸልመው እንኳን ህሊናው ሽልማትን ይሰጠዋል›› ብለው የሚያምኑት አቶ ኦቦንግ፤ ድርጅታቸው ብሔር ወይም ዘር ሳንቆጥር ሰው በመሆናቸው ብቻ ከ21 ሀገር በላይ በመሄድ ያግዛል። በዚህም ብዙ ኢትዮጵያውያን ተጠቅመዋል። ስለዚህም ይህ ስኬቴ ነው ይላሉ። በተለይም በበጎሰው ሽልማት ያዩት የፊት ገጽታ ምን ያህል ስኬታማ ሥራ እንደሰሩ ያሳያቸው መሆኑን ያነሳሉ።
‹‹ሁላችንም እርስ በርስ አልተረዳዳንም የመርሃ ግብሩ ታዳሚዎች እኔ የማላውቃቸው ናቸው። ግን ዘርና ሃይማኖት ሳይገድባቸው ስሜ ሲጠራ መዝለላቸው ተወዳጅነቴን አሳይቶኛል። በዚህ ትልቅ ክብርም ሞራልን እና የቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት ያተጋኛልና ስኬታማ ነኝ›› ሲሉም አጫውተውናል። እውቀት እና ገንዘብ ይዞ የተወለደ ሰው የለም። ስለዚህም ባመንበት ሙያ እችላለሁ በማለት ሌላ ሰው እንዲከተለን ካደረግን ስኬታማ ነን ይላሉ። ‹‹በሽልማቱ ወቅት የኢትዮጵያን አበባ ተመልክቻለሁ። ሳይሰሰት የሚሰጥ የፍቅርና የደስታ ልገሳን የሚያደርግ ቤተሰቤንም እንዳየሁ ተሰምቶኛል። እናም ይህንን ትልቅ ጸጋ የማስጠበቅ ኃላፊነት የእኔ እንድል የጠቆመኝ ነው›› ይላሉ።
ሀገርን ያቆየ መንግሥት ሳይሆን ሕዝቦች እርስ በእርስ የነበረው ትስስር ቡና ስንጠጣ የነበረን ቅርበት ነው የሚሉት እንግዳችን፤ በበጎ ሰው ሽልማት ሥራዬን ስላየሁት ተደስቼበታለሁ። ሕዝቡ አሁንም አንድ እንደሆነ፣ ሰዎችን እንደሚወድ አስገንዝቦኛል። የዛሬ ዓመት በዚህ ቀን ከ16 ዓመት በኋላ ስመጣ ትውልዱን ከመቅረጽ አንጻር ከ12 በላይ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ ተማሪዎች እርስ በእርስ እንዲዋዳዱ እና እንዲተጋገዙ ማድረግ ስችል ያየሁት ፈተና እንደማይደገምም አውቄያለሁ። እናም ይህ ስኬት በእኔ መሰል ሰዎች የተከናወነ በመሆኑ እንዲያስደስተኝ ሆኗል።
ሽልማቱ የአምባሳደርነት ማዕረግን አቀናጅቶኛልና የበለጠ እንድሰራ ያተጋኝ። ስኬታማ ነኝ እላለሁ የሚሉት ባለታሪክ፤ ‹‹እኛ ስንፈጠር በስህተት አይደለም፤ ፈጣሪ ለአንድ አላማ አስቦን ነው እንጂ። ግን የተፈጠርንበትን አላማ አልፈልግም ብለን ወደ ጎን በመተው በሰዎች እየተመራን የማይፈለጉ ሀሳቦችን እናራምዳለን። የራሳችንን ማንነት ለቀንም ሰዎች በመሩን ብቻ እንጓዛለን።
ይህ ደግሞ እኛ ሳንሆን እነሱን እንድንሆንና የእነርሱን መጥፎ ሕይወት እንድንኖርላቸው ያደርገናል። ነገር ግን ገበሬው የሚያጭደው የዘራውን ብቻ ሳይሆን ያልዘራውንም መልካም ነገር እንዲሆን ማድረግ የግለሰቡ ግዴታ ነው። ስለሆነም የበለጠ ለስኬቴ ለመስራት መጀመሪያ ልክ እንደችግኝ ስብዕናን፣ ፍቅርን መትከል ያስፈልጋልና ይህንን አደርጋለሁ። ስኬት በቃኝ ማለትንም አልፈልግም።›› ሲሉ አጫውተውናል።
እኔ በአደኩበት አካባቢ ቤተሰብ ልጁን ማሳደግ ካልቻለ መንግሥት ይወስዳቸዋል። እዚህ ግን ማንም አያያቸውም። ይልቁንም በር ላይ እንኳን እንዲያድሩ አይፈቀድላቸውም። ያባርራቸዋል። ይህ ደግሞ መጥፎ ዘር እንድናጭድ ያደርገናል። ምክንያቱም እነዚህ ልጆች ነገ አገር ገዢ ይሆናሉ። በእንደነዚህ ዓይነት የሚመራ አገር ደግሞ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ቀላል ነው። እናም ፍሬያችንን መንከባከቡ ከዛሬ መጀመር አለበትና ስኬታማ መሆኔን ለማረጋገጥ በዚህ ላይ አጥብቄ እሰራለሁም ብለውናል።
ጋምቤላ ለምለም መሆኗ ሰዎች ሁሉ በደስታ እንዲኖሩባት ታደርጋለች። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየች እንዳልሆነች እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት አቶ ኦቦንግ፤ በሰው አገር ሳሉ ውጪዎች የምትመገቡት እንኳን የሌላችሁ ናችሁ ይላሉ። ትከፋፈላላችሁ ይሉናልም። እኔ ይህንን አልረዳውም። ምክንያቱም ሳልበላ አድሬ አላውቅም። በአንድነት መብላትን እያየሁ ነው ያደኩት። ስለዚህም ኢትዮጵያዊነት በእያንዳንዱ ማህበረሰብና የልጅ አስተዳደግ ሁኔታ የተሰራ ነውና ብዙ ጋምቤላዎች በውጭ አገር ስንገናኝ ለአገራቸው ብዙ ፍቅር ሳይኖራቸው ሲቀር ያ ስሜት እኔ ላይ የለም። በዚህም ሁሌ ለአገሬ እንድል ሆኛለሁ፤ ይህም ስኬቴ ነው ይላሉ።
የግለሰቦች ጥቅም ፍለጋና የቤተሰብ የአስተዳደግ ክፍተት ይህንን አመጣው ብዬ ስለማምን ለአገራችን መቆም እንዳለብን ለማሳመን ጥሬያለሁ። በዚህም የሕዝቡ አመለካከት በትንሹም ቢሆን በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ለውጥ እንዲያሳዩ አድርጌያለሁ። ለአብነት እኔ በጎ ተብዬ መሸለሜ ከጋምቤላ በጎዎች አሉ የሚለው አስተሳሰብ እንዲመጣ አድርጓል። የእኛ አይደሉም ያሉት ሁሉ ጋምቤላም የኢትዮጵያ እንደሆነ እንዲያምኑ በር ከፍቷል። ይህም ከስኬት ውስጥ የሚጠቃለል መሆኑን ይናገራሉ። አሜሪካ ሳለሁ ብዙዎች ስለ አገራችን መብት እንደምታገል እያወቁ መጥተዋል። በዚህም እናመሰግናለን የሚሉኝ ብዙ ናቸው። ይህም ለእኔ ስኬቴ ነው።
ሽልማት
የእንግዳችን ሽልማት የሚጀምረው ከተማሩበት ትምህርት ቤት ነው። ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ሙሉ ፕሮፋይላቸው በስክሪን ተደርጎ ተማሪዎች እንዲማሩባቸው ይቀመጣል። እርሳቸውም ይህ ሽልማት ካላቸው መካከል አንዱ ናቸው። ሌላው ሽልማታቸው በካናዳ በሚያደርጓቸው የሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴ የቡድኑ አባላት በተለያየ ጊዜ ስጦታ አበርክቶላቸዋል።
ሲት የተባለ ድርጅት በአሜሪካ አገር እንደአገርቤቱ የበጎሰው የሽልማት ድርጅት ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው ከሚላቸው መካከል አንዱ አድርጎ ሽልማት አበርክቶላቸዋል። በተመሳሳይ የተለያየ አሜሪካ ኦርጋናይዜሽኖችም እንዲሁም በሚያደርጓቸው የበጎ እንቅስቃሴዎች በተለያየ ጊዜ ሽልማት ሰጥተዋቸዋል።
በሴቶች መብት ተሟጋችነታቸውም ከአሜሪካ የሴቶች መብት ተሟጋች አባላት ሽልማትን ተቀብለዋል። ከዚያም አልፎ ለጋምቤላ ባደረጉት የልማትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው ሽልማትን አግኝተዋል። ከዚህ በላይ ከተለያዩ አካላትም የአገኟቸው ለቁጥር የሚያዳግቱ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል። ግን ከሁሉ የሚልቅብኝ በሰው አገር ሆኜ ብሰራም ሥራህ ትልቅ ቦታ ያለው ነው ብሎ በአገር ውስጥ የሸለመኝ የበጎ ሰው ሽልማት ነው ሲሉ ይናገራሉ።
የሕይወት ፍልስፍና
‹‹እኔ የምኖረው ለምክንያት ነው፤ ስለተሰጠኝና እንድሰራበት ስለተፈቀደልኝም ነው። የተሰጠኝ ነገር ገደብ አለበትና ያንን በጊዜው አድርጌ ማለፍ እፈልጋለሁ።›› የሚል እምነት ያላቸው አቶ ኦቦንግ፤ በቆምኩበት ጊዜ ጥሩ ማድረግ ብቻ የሕይወት ፍልስፍናዬ አድርጌ እኖራለሁ ይላሉ። ምክንያቱም ዛሬ ቆሜ ነገ ላልቆም እችላለሁ። ታምሜ የምወድቅበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለው ስለሚያምኑ ነው።
በዚህ ጊዜ ከሞትኩ ደግሞ ማንም ሊያስታውሰኝ አይችልም። ስለዚህ ለአሁን አሁን መኖር እንዳለብኝ አምናለሁ ባይ ናቸው። ለበጎ መኖር ሥራዬ ማድረግም የዕለት ከዕለት ተግባሬ ሊሆን ይገባል የሕይወት ፍልስፍናቸው ነው። ለዚህም ነው መጀመሪያ የተነሱበትን ዓላማ ትተው አገራዊ ድርጅትን በመመስረት መስራት የጀመሩት።
መጀመሪያ ጋምቤላ ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲን፤ ከዚያ አኝዋክ ጅስቲስ የተሰኘ ድርጅት አቋቁሞው ሲሰሩ ነበር። ከዚያም የአገሪቱ ችግር በቀላሉ የሚቀረፍ አለመሆኑን ሲረዱ ለአዲስቷ ኢትዮጵያ የጋራ እንቅስቃሴ የተሰኘ ድርጅት መሠረቱ። ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ግን አንድም የፖለቲካ ድርጅት አባል ሆነው አይደለም። ለአገር ተቆርቋሪነታቸው አስገድዷቸው እንጂ። የፖለቲካ አባል ያልሆኑት ለኢትዮጵያ ለውጥ በትክክል ይሰራል ብዬ የማምነው ድርጅት ባለመኖሩ ነው። ወይ ለጥቅም አለያም ለብሔር ብቻ የተዋቀሩና ለዚያ የሚታገሉ በመሆናቸው አልገቡበትም።
ቤተሰብ
ለ16 ዓመታት አብረው ኖረዋል። ሁለት ልጆችንም አፍርተዋል። ግን ዜግነቷ ፈረንሳዊት ነች። ይሁንና ለአገራቸው ሰብዓዊ መብት በመሟገት ላይ እያሉ ኑራቸውን መምራት አልቻሉም። ንብረታቸው ሁሉ እየተሸጠ ለሰብዓዊ መብት ሙግት ይውላል። እናም አንድ ቀን ምን እናድርግ በሚል ተመካከሩ። እርሳቸውም ምርጫሽን አከብራለሁ አሉ። እኔና አንቺ ብንለያይ ቤተሰብ ነው የሚበተነው።
ይህ ሥራ ቢቆም ደግሞ አገርነው ስለዚህ እንደፈለገሽ ወስኝ አሏት። እርሷም ሥራውን እንደማያቆሙት ስለገባት እነርሱ ቢፋቱ የሚሻል እንደሆነ አስቀመጠች። ይሁንና ዛሬ ድረስ በጣም የሚዋደዱ ጓደኛሞች እንደሆኑ ይናገራሉ። ልጆቻቸውም አድገው በትምህርት ላይ ናቸው።
ከዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ በድንገት በትውልድ ቀያቸው የሚያውቋትን የስድስተኛ ክፍል የትምህርት ቤት ጓደኛቸውን በሥራ አጋጣሚ አገኟት። ፍቅረኛ እንዳላትና እንደሌላት ተጠያየቁ ሁለቱም ያላገቡ ስለነበሩ የትዳር አጋር እንዲሆኑ ተስማሙ። ተጋብተው ዛሬ በደስታ እያሳለፉ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው