• ማቋቋሚያ አዋጁን ያሻሽላል
• የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መቶ በመቶ ለማስቆም ይሰራል
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የተቋቋሙበትን አዋጅ ለማሻሻል በመቶ ቀናት ዕቅዱ ይዞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባሶ እንደገለጹት፤ በመቶ ቀናት ዕቅድ ውስጥ ከተያዙት ጉዳዮች መካከል መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበትን አዋጅ ማሻሻል አንዱ ነው፡፡ ይህን ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻልም በአዋጁ ውስጥ አሉ የተባሉ ችግሮችን በማጥናት ማሻሻያዎች ተደርገው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ከዚሁ አዋጅ የሚቀዱ የተለያዩ መመሪያዎችና ደንቦችም በርካታ ማሻሻያዎችን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነዚህ መመሪ ያዎችና ደንቦች የተወሰኑት በተቋሙ የሚጸድቁ ሲሆን ሌሎቹ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚጸድቁ ናቸው።
መመሪያና ደንቦቹን ለማሻሻልም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ባደረገው ዝግጅት የተለያዩ የማስተካከያ ርምጃዎች ተወስደዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣በዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መቶ በመቶ ለማስቆም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ከተሰሩት ሥራዎች መካከል፣ ማንኛውም ታራሚ ማረሚያ ቤት ከደረሰ በኋላ ምንም ዓይነት የህግ ጥሰት እንዳይፈጸምበት፤ የምርመራ ሥራ በተቋም ውስጥ እንዳይካሄድ፤ ከተቋሙ ውጭ የሆነ ማንኛውም አካል ወደ ማረሚያ ቤት ውስጥ እንዳይገባ፤ ታራሚው ማረሚያ ቤት ግቢ ከረገጠ በኋላ ነጻ ሆኖ እንዲቆይ፤ እንዲሁም ከፍርድ ቤት ችሎት ውጭ የትም ቦታ እንዳይወሰድ የሚያደርጉ ሥራዎች በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸው ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ መሻሻል የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ተጠንቷል ያሉት አቶ ጀማል፣በጥናቱ ከተለዩት ችግሮች መካከልም የምግብ አቅርቦት፤ የጤናና የትራንስፖርት አቅርቦት በሰፊው ችግር ታይቶባቸዋል ፣እነዚህንና መሰል ችግሮች ለመቅረፍ በመቶ ቀናት ዕቅድ ውስጥ በዋናነት ተይዘው እየተሰራባቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2011
ፍሬህይወት አወቀ