የባህረ ሰላጤዋ ሃገር ኳታር ከነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት ማህበር (ኦፔክ) ራሷን ለማግለል መወሰኗን ሰሞኑን አስታውቃለች። ማህበሩን ከ57 ዓመት በፊት የተቀላቀለችው ኳታር ለመልቀቅ ከመወሰኗ ጀርባ ያለው ምክንያትም በርካታ የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞችንና መገናኛ ብዙሃንን እያነጋገረ ይገኛል።
የዓለማችንን 82 በመቶ የነዳጅ ፍላጎት የሚያሟላው (ኦፔክ) ሳዑዲ አረቢያ፤ ሊቢያ፣ኢራን፣ ኩዌት፣ ናይጄሪያ፣አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ኮንጎ፣ ኢኳዶር፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን፣ ኢራቅና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችን በአባልነት ይዟል።
ከሌሎች አባል ሃገራት ጋር ስትነጻጸር ታዲያ ኳታር አነስተኛ የነዳጅ ምርት አምራች ናት። የአቅርቦት ሚናዋም በቀን 600ሺ በርሜል ሲሆን፣ ይህም አባል አገራት ከሚያቀርቡት ሁለት በመቶ ማለት ነው። ሳውዲ አረቢያ በአንፃሩ አስር ሚሊዮን በርሜል በቀን ታቀርባለች። ይህም የዓለም አቀፉ የነዳጅ አቅርቦት በሳውዲ ትከሻ ላይ ስለመሆኑ ምስከር ይስጣል።
የኳታር ማህበሩን የመልቅቅ ውሳኔ ምክንያት ሲነሳም የነዳጅ ላኪ ሃገራት ማህበርን በበላይነት የምትመራው ሳዑዲ አረቢያ ቀድማ ትጠቀሳለች። የሪያድ መንግሥት በነዳጅ አቅርቦት ብልጫ በማህበሩ ውስጥ ያለው ተፅእኖ መግዘፍና ማህበሩን በፈለገው መልኩ የመዘወሩ ፍላጎትም ኳታርን ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ከቆየችበት ኦፔክ ለመውጣት እንድትሻ አስግድዷታል የሚሉም አሉ።
ምንም እንኳ ከኳታር ውሳኔ ጀርባ የተለያዩ አስተያየቶች በተለይም ፖለቲካዊ አንድምታዎች ቢሰጡም፤ አገሪቱ በአንፃሩ በኢነርጂ ሚኒስትሯ ሳድ አል ካቢ በኩል«እኛ በነዳጅ ዘርፉ ብዙ አቅም የለንም፤ ይልቅስ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አለን፤ ይህ እንደመሆኑም በጋዝ ምርት ላይ ማተኮር እንፈልጋልን፤ ማህበሩን ለመሰናበት የመሻታችን ምክንያትም ይሄው ነው፤ ከውሳኔው ጀርባም አንዳችም ፖለቲካ እንድምታ የለም ስትል አስታውቀዋል።
እ.ኤ.አ1961 ኳታር ኦፔክን ስትቀላቀል ብቸኛው የኃይል አማራጯ ነዳጅ እንደነበርና ይሄውም በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ውስጥ ሁነኛ አቅም እንደነበር በመግለጽ ፤አሁን የማህበሩ ሁለንተናዊ አቅምና የአባል አገራቱን ፍላጎት የማስጠበቅ ሚናው እንደቀደሞው አለመሆኑ ይገለጻል፡፡ይህም ኳታር አቋሟን እንድትቀይር አድርጓታል የሚሉ ወገኖች አሉ።
ሽብረተኝነትን ትደግፋለች በሚል ላለፉት 18 ወራት ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ በሌሎች የጎረቤት አገሮች ተገልላ መቆየቷ ከዚህ ውሳኔ አድርሷታል የሚሉ እንዳሉም መረጃዎች ያመለክታሉ።
የገልፍ አገራት በዓለም አቀፉ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ላይ ስላላቸው ሚና በሚዳስሰው መፅሐፋቸው የሚታወቁት ዶክተር ክርስቲያን ሪችስን በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ ባሰፈሩት ትንታኔ፤ ውሳኔው የኃይል አቅርቦት ሚዛንን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመውስድና የሳውዲ አረቢያን የተባበሩት ዓረብ ኤመሬትስን፤ ባህሬንና የግብፅን ተፅእኖ ስትራቴጂያዊ በሆነ መልኩ ለመመከት የታቀደ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
በእርግጥ ላለፉት 18 ወራት በሳውዲ ዓረቢያ ቀማሪነት ከጎረቤቶቿ ጋር የተቃቀረችው ኳታር፣ሪያድ መንግሥት ጋር ክፉኛ ተፋጣለች። መገለሏን ተከትሎ የደረሰባት የኢኮኖሚ ጫና በከባድ ሁኔታ ዕድገቷን ፈትኖታል። ይህን ተከትሎም ከባላንጣዋ ሳውዲዓረቢያ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተቀራርባ መሥራትን እንደማትፈልግ ግልጽ ነው።
አገሪቱ ኦፔክን ለመልቀቋ ምክንያት ተብለው ከሚቀርቡ አጀንዳዎች መካከል ከሪያድ መንግሥት ጋር የገባችው ፍጥጫ አንዱና ጎልቶ የወጣው ቢሆንም ፣ ይህ ግን ለውሳኔዋ ዋነኛና በቂ ምክንያት አይሆንም ሲሉ የሚያስረዱ ፀሐፍት ቁጥርም ጥቂት እንዳልሆነ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙና በአሜሪካ ብራውን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጄፍ ኮልጋን ዋሽንግተን ፖስት ላይ ባሰፈሩት ሐተታ፤ ቁርሾና ሽኩቻ ማህበሩን ለመልቀቅ በቂና አሳማኝ ምክንያት አለመሆኑን አስረድተዋል።
«ኢራቅና ኢራን 1980ዎቹ ለስምንት ዓመታት ተዋግተዋል። ይሁንና አንዳቸውም ቢሆኑ ከማህበሩ ራሳቸውን አላገለሉም›› ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ኳታርም ራሷን ያገለለችው ከሳውዲ ጋር ስለተኳረፈች እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ የኦፔክ ዓለም አቀፍ ሚና ያን ያህል አለመሆኑን ጠንቅቃ በመረዳቷ መሆኑን በመጥቀስ፣ የፖለቲካ አቅሙ እንደ 1970 ዎቹ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ገዝፎ ስላልታየት ነው ይላሉ።
የኳታር ከማህበሩ ሯሷን ለማግለል የደረሰችበት ውሳኔ ዋና ምክንያት በሚገባ ባለየበት ሁኔታ፣ባሳለፍነው ሳምንት የነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት ማህበር (ኦፔክ) ስብሰባ ለሁለት ቀናት ማካሄዷ ይታወሳል፡፡ በኦፔኩ ዋና መስሪያ ቤት ቬና በተካሄደው ጉባኤም አባል አገራትና ሩሲያን ጨምሮ ነዳጅ አምራችና ላኪ አስር አገራት ከዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦቱ በቀን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በርሜሉን ለመቀነስ ተስማምተዋል።
ከቀናት በፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሳዑዲ አረቢያና ሩሲያ ምርታቸውን እንዲጨምሩ ጥያቄ ማቅርባቸው ቢታወስም የኦፔክ አባል አገራት በአንፃሩ በየቀኑ ስምንት መቶ ሺ በርሜል፤ ሌሎች እንደ ሩሲያ ያሉ ነዳጅ አምራች አገራት ደግሞ አራት መቶ ሺ በርሜል ለመቀነስ ወስነዋል። ይህ ውሳኔያቸውም በቅርቡ የተከሰተውን የነዳጅ ዋጋ ግሽበት መቀነስንና ቅጥ ያጣ ምርትን ከማቅረብ ለመቆጠብን ታሳቢ ያደረገ እንጂ፣ሌላ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንድምታ እንደሌለው አስታውቀዋል።
በእርግጥም የኦፔክ ዋነኛ ግብ አገራቱን ማስተባበር፤ ፍላጎታችውን ማስጠበቅና ከነዳጅ ሀብታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢ ጥቅም እንዲቋደሱ ማስቻል ነው። ይሁንና የነዳጅ ገበያው የማህበሩ አባል አገራት ከምዕራባዊያን ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ውስጥ የራሱን ፖለቲካ እንድምታ ያነገበ ሆኖ ቆይቷል።
በተለይ እ.ኤ.አ1973 በእሥራኤል፣ በሶሪያና በግብፅ መካከል በነበረው ጦርነት የማህበሩ አባል አገራት ከእሥራኤል ጎን ለወገኑ ምዕራባውያን አገራት የነዳጅ አቅርቦት በማቋረጥ ማህበሩ ሌላ ያልተገለጠ የትብብር ገፅ እንዳለው አሳይቷል።
አሁን ማህበሩ በ1970 ዎቹ እንደነበረው ዓይነት የፖለቲካ አቅሙ ግዙፍ ባይሆንም፣ አሜሪካና ሌሎች አገራት ግን ከኳታርም ሆነ ከጉባኤው ውሳኔ ጀርባ አንዳች የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ መቀመሩን ይጠርጥራሉ። አባል ባትሆንም፤ ከኦፔክ አባል ሃገራት ቀጥሎ ትልቋ ነዳጅ አምራች የሆነችው ሩሲያ በነዳጅ አቅርቦት ቅነሳው ቀመርና ውሳኔ መሳተፏም ጉዳዩን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲላበስ ፍንጭ መስጠቱም ተጠቁሟል።
ከዚህም በተጓዳኝ የዋሽንግተን መንግሥት ከጋዜጠኛው ጀማል ካሾጊ ግድያ ጋር በተያያዘ በሳውዲዓረቢያ ላይ ፊቱን ማጥቆሩን ተከትሎ የሪያዱ መንግሥት የሰጠው የመልስ ምት ነው የሚሉም በርክተዋል። ከግድያው ጋር በተያያዘ የትራምፕ መንግሥት በሪያድ ላይ አንዳች ማዕቀብ ለመጣል እንዳያስብ የሚያስጠነቅቅ ቀይ መብራት መሆኑን የሚያስረዱ ተንታኞችም ጥቂት አይደሉም። የያዩ ፋይናንስ ዘገባም፤ የሳውዲ ተግባር ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለመገዳደር ሁነኛ እርምጃ ነው ሲል ገልጿል።
ከሁሉም በላይ ከኒውክሌር ባለቤትነትና የማስወንጨፍ ሙከራ ጋር ተያይዞ የዋሽንግተን መንግሥት በኢራን ላይ የጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ያበገናትና ከሳውዲ አረቢያ ጋር አስፍሪ ፍጥጫ ውስጥ የምትገኘው ሌላኛዋ የኦፔክ አባል አገር ኢራን፤ የጉባኤውን ውሳኔ በደስታ መቀበሏ የፖለቲካ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃኑን ምልከታ አስቀይሯል።
ኢራን ከሁለቱ አገራት በተለይ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በገጠመችው ፍልሚያ ከጉባኤው አስቀድሞ የነዳጅ ቅነሳውን ውጥን አትቀበለውም ተብሎ መገመቱን ዘገባዎች ቢጠቁሙም፣ ይህ ግን ስህተት ሆኖ ታይቷል። ፕሬዚዳንት ሃሳን ሩሃኒም በጉዳዩ ከመስማማት ባለፈ ውሳኔው ለአሜሪካ መንግሥት የጣልቃ ገብነት ፖሊሲ ከባድ ውድቀት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
«ምንም እንኳን አሜሪካ በኦፔክ ጉዳዮች እጇን ለማስገባት ሌት ተቀን ብትዳክርና ሚዛናዊነቱንም ለማዛባት የተቻላትን ጉድጓድ ብትቆፍርም ምስጋና ለአባላቱ ጠንካራ አቋምና ተግባር እቅዷ መክኖ ቀርቷል» ሲሉ ተሰምተዋል።
ይህ የአባል አገራቱ የትብብር ውሳኔ ግን ከትራምፕ አስተዳደር ፍላጎት ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም ሆኖ መገኘቱ የነዳጅ ፖለቲካውን ጡዘት እንዳከረረው ዘገባዎች ያመለክታሉ። ሁኔታው በርካታ ወገኖች ቀጣዮቹ እርምጃዎች እና ውጤቱስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ እያሉ እንዲጠበቁት አስገድዷል።
የብሎንበርግ ግራንት ስሚዝ በአንፃሩ ፤ኦፔክና አጋሮቹ ከአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ጀምሮ ለስድስት ወራት ያህል የዓለም የነዳጅ ገበያውን ሚዛን ለማስጠበቅ የሚያስችላቸውን እርምጃ ለመውሰድ መወሳናቸውን ጠቅሶ፣ ፍላጎታቸውን ዳር ለማድረስ ግን ከፊታቸው ብዙ ሥራዎች እንዳሉ አትቷል። ባለሙያዎችን ዋቢ በማድረግም በነዳጅ ዋጋው ላይ ተጨባጭና ፈጣን ለውጥ ለማምጣት የምርት ቅነሳው ውሳኔ ብቻውን በቂ አለመሆኑን አመላክቷል። ውሳኔውንም እያደር በሁሉ መልኩ ለገዘፈው የአሜሪካው ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያ ሼል የገና ስጦታ ብሎታል።
ምንም እንኳን ከቀጣዩ ወር መጀመሪያ አንስቶ ተግባራዊ የሚሆነው የነዳጅ አምራችና ላኪ ሃገራት ማህበር (ኦፔክ) አባልት ውጥንና ድምር ውጤት የተለያዩ አስተያየቶች ቢሰነዘሩበትም ገና ከወዲሁ በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱም እርግጥ ሆኗል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011
ታምራት ተስፋዬ