– ጉቦ ሲቀበል የተያዘ የትራፊክ ፖሊስ የለም
አዲስ አበባ፡- በ2011 በጀት ዓመት ለትራፊክ ፖሊሶች ጉቦ ለመስጠት የሞከሩ 2954 አሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ፣አሽከርካሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ህግ በመተላለፍ ወንጀል ሲጠየቁ ለትራፊክ ፖሊስ አባላት የመማለጃ ገንዘብ ለመስጠት በመሞከራቸው ነው።እንደ ኮማንደር ፋሲካ አባባል ግለሰቦቹ ከሃምሳ እስከ ሁለት መቶ ብር ጉቦ ለመስጠት የሞከሩ ናቸው። ድርጊታቸው በበቂ ማስረጃ በመረጋገጡም ጉዳያቸው ለዓቃቤ ህግ ተላልፎ በክስ ሂደት ላይ ይገኛል።
እስካሁን ከአሽከርካሪዎች ገንዘብ ሲቀበሉ የተያዙ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ያለመኖራቸውን ያረጋገጡት ኮማንደር ፋሲካ ድርጊቱ ካለፈው ተመሳሳይ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸርም ቁጥሩ በ 5 በመቶ ያህል መጨመሩን ተናግረዋል። ጉቦ ለመስጠት ከሞከሩት አሽከርካሪዎች መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ኮድ 3 እና ኮድ 1 ተሽከርካሪዎች ናቸው። በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ጉቦ የመስጠት ወንጀል የመከላከል ኃላፊነቱ የፖሊስ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡም ሊሆን ይገባል ያሉት ኮማንደሩ ድርጊቱን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመቆጣጠርም ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የተቀናጀ አሰራርን ለመከወን ስለመታሰቡ ገልፀዋል።
ከመጪው 2012 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥርን ለመተግበር መንግሥት በጀት መድቦ ከማቀዱ ጋር ተያይዞም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የራሱን ድርሻ ለመወጣት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ኮማንደር ፋሲካ አክለው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
መልካምስራ አፈወርቅ