በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያለፉት ሦስት አመታት አፈጻጸም ኢንዱስትሪው ማደጉን የግብርናው እድገት መቀነሱን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሰሞኑን ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኢንዱስትሪው ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ያበረከተው ድርሻ ከ15 በመቶ ወደ 26 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ይህ እድገት የመጣው በኮንስትራክሽንና መሰል ንኡስ ዘርፎች አማካይነት ነው፡፡
ለኢንዱስትሪው እድገት የኮንስትራክሽን ዘርፉ እድገትና መስፋፋት ፣የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እየተስፋፋ መምጣትና መዘመን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡
በእቅድ ዘመኑ ያለፉት ሶስት አመታት ኢንዱስትሪው ማደጉ ፣ሀገሪቱ ዘርፉን በማሳደግ የኢኮኖሚውን ሽግግር እውን ለማድረግ የያዘችው ራዕይ በመልካም የስኬት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል፡፡ኢንዱስትሪው በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመንም እድገት ማስመዝገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን የተመዘገበው እድገት ኢንዱስትሪው በጠንካራ መሰረት ላይ እየቆመ መሆኑን አመላካች ነው፡፡
እድገቱ ሀገሪቱ ባለፉት ሶስት አመታት በተለይ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚያስፈልጉ እንደ ብረት የመሳሰሉትን ግብአቶች ከውጭ ለማስገባት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ባጋጠመበት እና የኮንስትራክሽን ስራዎች በተቀዛቀዙበት ወቅት የተመዘገበ እንደ መሆኑ ዘርፉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ እድገት የሚያስመዘግብ ጠንካራ ዘርፍ ለመሆን መብቃቱንም ያሳያል፡፡
በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን ከታቀደውና ከተጠበቀው አንፃር የተመዘገበው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ዝቅተኛ ቢሆንም፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተመዘገበው እድገት ሳቢያ ከግብርና ዘርፍ ግብርና ወደ አልሆኑ ዘርፎች የመዋቅር ሽግግር መታየቱ ይታወሳል፡፡ያለፉት ሦስት አመታት የዘርፉ እድገትም የመዋቅር ሽግግሩ እንደሚቀጥል የሚጠቁም ነው፡፡
ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ከተመዘገበው እድገት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረከተው እንደ መጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን ሁሉ አሁንም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እድገት መቀጠሉ አኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ለሚደረገው ጥረት ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡
የኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ዘላቂና የሚጠበቅበትን ያህል እንደሚሆን በዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባሮች ማረጋገጫ ናቸው፡፡በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መጠነ ሰፊ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ይህም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ባለፉት አመታት ያጋጠሙት ፈተናዎች ፈተና ሆነው እንደማይቀጥሉ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ባለፉት ሶስት አመታት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ፣ በባለሀብቶች ምልመላ ፣በሰራተኞች ስልጠናና በመሳሰሉት የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች አዝመራ የሚሰበሰበው ከዚህ በኋላ ባሉት አመታት እንደመሆኑ የኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ከእስከ አሁኑም በላይ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ይቻላል፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ እንደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ተግባሮች ሲታዩም እድገቱ ይበልጥ መሰረት በመያዝ እንደሚቀጥል መተንበይ የሚያስችልም ነው፡፡
የእድገቱን ቀጣይነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በመንግስት በኩል ሊከናወኑ የታቀዱ ተግባሮችን አጠናክሮ መቀጠል፣ በእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ፣በገበያ እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግኝት ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከእስከ አሁኑም በላይ ለመሳብ መስራትን ፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ሚና ማሳደግን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡
በተለይ በለጋው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አለም አቀፍ ታዋቂ ኩባንያዎችን በመሳብ በኩል እየተከናወነ ያለውን ተግባር ባለሀብቶች አምራቾች ብቻም ሳይሆኑ ገበያም እንደመሆናቸው ይህን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡
ኩባንያዎቹ ለዜጎች ያስገኙት የስራ እድ ፣ ያሸጋገሩት እውቀትና ቴክኖሎጂ በቀላሉ ሊታወቅ የሚችል ቢሆንም ከውጭ ምንዛሬ ግኝት አንጻር ግን መረጃዎችን ማግኘት አደጋች ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች አኳያ ለጊዜው የተባለ ባይኖርም ለውጭ ገበያ ለማምረት ፈቃድ ወስደው በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሀገር ውስጥ ገበያው አማለለን እያሉ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያውሉበት ሁኔታ እንዳይጋባባቸው በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን በመላክ የሚያስገኙትን የውጭ ምንዛሬ በመከታተል ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሬ ግኝት የያዘችው እቅድ እንዲሳካ መስራት ያስፈልጋል፡፡
ለኢንዱስትሪ ልማት እየወጣ ያለው ሀብት ዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ የሚያደርግ እንዲሆን መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እና ሀገሪቱን ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ከእስከ አሁኑም በላይ በኢንዱስትሪው ላይ መስራት ያስፈልጋልና የተመዘገውን እድገት ዘላቂ ማድረግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011