መርማሪ ፖሊስ በጋዜጠኛ ፍጹም የሽጥላ ላይ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ውድቅ በማድረግ የቀሩ ስራዎችን ለመስራት የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።
ፖሊስ ከጋዜጠኛ ፍጹም የሽጥላ ጋር በተያያዘ ቀድሞ ተፈቅዶለት በነበረው 7 ቀን ያከናወናቸውን ስራዎች ለችሎቱ አቅርቧል።
በዚህም ከቀድሞ መስሪያ ቤቷ ማስረጃ ማሰባሰቡን፣ ዘጋቢ ፊልም ለማሳየት ከሜቴክ ስፖንሰር የተደረገችበትን የውል ሰነድ ማሰባሰቡን፣ በአሜሪካ የ30 ቀን ቆይታዋ ከሜቴክ የወሰደችውን ከ200 ሺህ ብር በላይ የውሎ አበል እንድታወራርድ መጠየቋን የሚያሳይ ሰነድ ማግኘቱን፣ በሜቴክ ስፖንሰር ተደርጎ አሜሪካ የታየውን ዘጋቢ ፊልም እንዲሰጠው መጠየቁን አስረድቷል።
ከዚህ ባለፈም ከሜቴክ እንድታወራርድ ተብሎ በተሰጣት ሰነድ ላይ የምስክር ቃል የመቀበል እንዲሁም የተጠየቀችውን ገንዘብ ማወራረድ አለማወራረዷን የሰነድ ማስረጃ የማሰባሰብ ስራ እንደሚቀረው በመጥቀስ፥ ይህን ለማከናወን ችሎቱ ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቅድልን ሲልም ጠይቋል።
ችሎቱ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ በእስር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ታሳቢ ባደረገና ባገናዘበ መልኩ ስራውን በትጋት እየሰራ አለመሆኑንና፥ ሜቴክ ጋዜጠኛ ፍጹም እንድታወራረድ የጠየቀበትን ሰነድ አግኝቶ ሳለ ምስክር እቀበላለሁ ማለቱ አግባብ አይደለም ብሏል።
እሰራለሁ ያለውን ስራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ መፍቀዱ ተገቢ ሆኖ ስላገኘው፥ ከታህሳስ 5 ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ለታህሳ 12 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በተያያዘ ዜና ፖሊስ ከቀድሞው የህብረት ማኑፋክቸሪንግ ስራ አስኪያጅ ጋር በመመሳጠር ከገቢዋ በላይ ሃብት አፍርታለች ብሎ በጠረጠራት ትዕግስት ታደሰ ላይ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ያከናወነውን ስራም ለችሎቱ አቅርቧል።
ተጠርጣሪዋ በተጠቀሰው ተቋም ሰራተኛ እንደነበረች የሚያሳይ ሰነድ ማግኘቱን፣ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ያላለቀና ስላብ የተሞላ ባለሁለት ወለል መኖሪያ ቤት ህንጻ በ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ገዝታ በ400 ሺህ እንደተገዛ በማስመሰል የተዘጋጀ የውል ሰነድ ማግኘቱን፣ 300 ሺህ ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስሟ መግባቱንና ገንዘቡን ያስገባውን አካል ማንነት እያጣራሁ ነው ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ለ40/60 መኖሪያ ቤት ከ200 ሺህ ብር በላይ መቆጠቧን መረጃ ደርሶት እንዲረጋገጥ ደብዳቤ መጻፉን፣ ቀድሞ የተገዛውንና ያላለቀውን ባለ ሁለት ወለል ህንጻ ወደ ባለ ሶስት ወለል በማሳደግ ፊኒሺንጉ ማለቁንና ለዚህ የወጣውን ተጨማሪ ገንዘብ ምንጭ እያጣራ መሆኑን በመጥቀስ ይህን ለማከናወን ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።
ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው አልተከናወኑም የተባሉ ስራዎች ከዚህ ቀደም የቀረቡና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ በመሆናቸው ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በማለት ተቃውመዋል።
የግራ ቀኙን የተመለከተው ችሎቱ ከታህሳስ 5 ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ፈቅዷል።
መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በተጨማሪም 1 ሺህ 480 ትራክተሮችን ደልሎ ሜቴክ ያለጨረታ እንዲገዛ በሚል የተጠረጠረው አቶ ቸርነት ዳና፥ ከቻይና ኩባንያ ወደ አካውንቱ 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ያዘዋወረበትን ሰነድ ማግኘቱን ለችሎቱ ገልጿል።
ጉዳዩን ለማጣራትም ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀ ሲሆን፥ ችሎቱም ከታህሳስ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ የ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ችሎቱ በከሰዓቱ ውሎው የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውና የእርሳቸው ወንድምና በኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ የኤን ጂ ፒ ኦ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ዳኘውን ጉዳይ ይመለከታል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።