መጠራጠር፣ መለያየት፣ ክህደት፣ ሳይሰሩ ጥቅም ማግኘት፣ ቂም፣ ጥላቻ፣ ሴራ፣ አድመኝነትና አእምሮን አለመግዛት የሰው ልጆች የአእምሮ በሽታ መገለጫ ናቸው የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በኢትዮጵያም እነዚህ የባህሪ ጉድለቶች በፖለቲከኞችና በአክቲቪስቶች እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡ አስተሳሰቦቹና ድርጊቶቹ ከግለሰቦች ወደ ቡድኖች እየተሸጋገሩ በመሆናቸው የአብሮነት እሴት ገመዶችን እየበጣጠሱት እንደሆነ ያነ ሳሉ፡፡
«ቀደም ሲል የነበረው የኢትዮጵያውያን የጋራ የአብሮነት እሴት እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ ይህ ችግር ካልተፈታ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ጥላቻ፣ ቂም፣ ሴረኝነትና እርስ በእርስ መጠራጠር የጤነኝነት አእምሮ መልዕክት አይደለም» የሚሉት የሥነ አእምሮ ሕክምና ባለሙያ ዶክተር ታደሰ በዳሳ ባለፉት 27 ዓመታት በፖለቲከኞች በተሰበኩት የውሸት ትርክቶች የብዙ ወጣቶች አእምሮ እንደተበረዘ ይጠቅሳሉ፡፡ ምክንያቱም ልዩነት፣ ውሸትና ጥላቻ ሲራገብ በወጣቱ ዘንድ እውነት ይመስለዋል ባይ ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር ታደሰ ገለፃ የሚራገቡ ጥላቻዎች እየቆዩ ሲሄዱ በሰዎች መካከል እርስ በርስ አለመግባባትን ይፈጥራሉ፡፡ ይህም ወደ መጎዳዳት መሸጋገሩ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ታይተው የማይታወቁ ሰዎችን የማፈናቀል፣ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ መፈጸምና ጥላቻን የሚያንጸባርቁ ጸያፍ ስድቦች በማህበራዊ ሚዲያ የሚታዩ መሆኑ ሕዝብና ሕዝብን ከማራራቅ ውጪ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ይህ የአእምሮ ጤና ችግር አንዱ መገለጫ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የተቀላቀለና የተዋለደ ሕዝብ ቢሆንም በልዩነት ላይ ሆን ተብሎ ስለተሰራ ጫፍ የረገጠ ብሔረተኝነት የገነነበት ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተ ዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብና ድርጊት ከምክንያታዊና ጤነኛ አእምሮ ሰው የሚመነጭ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ቀውሱም ቀላል እንዳልሆነ ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት ታይቷል ነው ያሉት፡፡
«በአገራችን የአብሮነት ባህሎች፣ እሴቶች፣ ወጎችና ልምዶች በየጊዜው በተለያዩ ምክንያቶች እየተሸረሸሩ መጥተዋል፡፡ የአብሮነት መገለጫዎች እየጠፉ በአንጻሩ እኔነት መገለጫ ብቻ እየገነነ መምጣቱ ይታያል» የሚሉት በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሥነ ልቦና ባለሙያ መኮንን በለጠ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በአገራችን የግለሰቦች የፖለቲካ ቅራኔ ወደ ማህበረሰቡ እየተሸጋገረ በአገርና በሰዎች ላይ ቀውስ እያስከተለ ነው፡፡
«ጥላቻ፣ ማፈናቀል፣ መጨካከን፣ መሰዳደብ በይበልጥ የሚስተዋለው ፊደል ቆጠርን ባልን ሰዎች ጭምር መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ የመማር ትልቁ ፋይዳ ክፉና ደጉን መለየት ነው፡፡ የማወቅ ትልቁ ብቃት በራስ መተማመን ነው፣ የራስ መተማመን ትልቁ መገለጫ ማንኛውም ሰው ዘር፣ ሃይማኖት፣ ገንዘብ፣ የፖለቲካ አቋምና የእውቀት ደረጃ ሳትለይ በቀና ተቀብለህ መግባባትና ችግርም ካለ በውይይት መፍታት ነው» የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው የሰው ልጅ የሚማረው የሕዝቡን ስሜትና ፍላጎት በማድመጥና በመመልከት በበጎ ህሊና ተርጉሞ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ሥራ ለመስራት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአንጻሩ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው በተቃራኒው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ለእኛነት የሚያበቃ እኔነትን አላዳበርንም፣ መተባበር፣ መከባባርና መደማመጥ ጠፍቶ ራስ ወዳድነትን፣ እኔን ብቻ ስሙኝ ባይነትን ጎልቶ እየወጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ራስን መግዛት ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ሃይማኖት ተቋማት ድረስ ተሸርሽሯል፡፡ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ተቀናቃኞቻቸውን ካልተሳደቡ፣ ካላወረዱ፣ ጥላቻን ከአልሰበኩ የተናገሩ አይመስላቸው፤ ዋነኛው የጥፋት ተዋንያንም እነሱ ናቸው፡፡ ለሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት የማይፈጽሙት እኩይ ተግባር አይኖርም፡፡ ይህ ችግር የሥነ ልቦና ቀውስ ውጤት መሆኑን ነው የነገሩን፡፡
የአእምሮ ህመሙ ከግለሰብ ወደ ማህበረሰብ የሚሸጋገር መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ታደሰ በቡድን ደረጃ በስሜት የሚነዳ ጥላቻና ጸያፍና ዘግናኝ ድርጊት (ሞቨ አክሽን) አገርን ለከፋ ቀውስ፣ የማህበረሰቡን ሕይወት እስከማናጋት የሚደርስ አደጋ ያስከትላል፡፡ ጭፍን ጥላቻን፣ ሴረኝነትና አድመኝነት ውስጣቸው ባለ ግለሰቦች ላይም የአእምሮ ጤና ቀውስ እንደሚያስከትል ገልጸው ከዚህ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው ከአልተላቀቁ በራሳቸው አይተማመኑም፣ ጸጸት ውስጥ ይገባሉ፤ ራሳቸውን የማግለል የሥነ ልቦና ቀውስ የሚያጋጥማቸው መሆኑን ያብራሩት፡፡
የጥላቻና የሴረኞች ሃሳብ አራማጅ ግለሰቦች ማስፈጸሚያ የሚሆኑት በአብዛኛው ወጣቶች መሆናቸውን የገለፁት ዶክተር ታደሰ ወጣቶች የጥፋት ድርጊቱ ተካፋይ ላለመሆንም በአክቲቪስቶችም ሆነ በፖለቲከኞች የሚነዙ ሃሳቦችንና ትርክቶችን ከሕዝብ ጥቅምና ከአብሮነት አንጻር በመመርመርና በመመዘን የተሻለውን ሃሳብ መግዛት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን መልካም ስብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተው መሰራት እንዳለባቸውም ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ ዶክተር ታደሰ፡፡
ሴረኝነትን፣ ጥላቻን፣ ጭካኔንና መገፋፋትን በሚያቀነቅኑት ሰዎች ላይ የአእምሮ ጤና ጉድለት እንደሚያጋጥማቸው አመልክተው፣ እነዚህ ግለሰቦች ፍላጎታቸው ገደብ የለውም፡፡ እርስ በእርሱ የሚጣረስ ሃሳብና አቋም ያራምዳሉ፤ ማህበራዊ ሕይወታቸው፣ በእውቀት ደረጃቸው፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የተጣመመ ነው፡፡
ጨለምተኞች ናቸው፡፡ ልክ ጊዜ ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦንብ ስብዓና ነው ያላቸው፡፡ ምክንያቱም ይህን የሚያደርጉት ስሜታቸውን መግዛት ሲያቅታቸው፣ ሩቅ አሳቢና ሆደ ሰፊ ባለመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ባህሪያቸው አካላዊ ሆነ አእምሮዊ ጤናቸውን ሊጎዳው እንደሚችል ጥናቶች ያረጋግጣሉ ሲሉም ዶክተር ታደሰ ገልጸዋል፡፡
ጥላቻን፣ መለያየትን፣ ጭካኔንና አብሮነትን የሚጎዱ ድርጊቶች የሚፈጸሙ ግለሰቦች ሆኑ ቡድኖች የአእምሮ በሽተኛ ራሱ አመመኝ ብሎ ስለማይመጣ ነው እንጂ ታማሚዎች ናቸው ያሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው አቶ መኮንን በበኩላቸው ጫፍ የወጣ ፅንፈኝነት ልክ እንደ ሂትለርና ሞሶሎኒ መጨረሻቸው አያምርም ይላሉ፡፡ ከሞቱ በኋላም በመልካም አይነሱም፡፡ እናም ከወዲሁ ማህበረሰቡ የጥላቻ አቀንቃኞችንና ሴረኞችን ፊት ሊነሳቸው እንደሚገባ ነው ያመለከቱት፡፡
«መልካም መሆን ለራስ ነው» እንዲሉ ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶችና የአገር ሽማግሌዎች መልካም ሥነ ምግባር መገለጫ በሆኑት ቅንነት፣ ለጋስነትን፣ ሩህሩህነት፣ ተባባሪነት፣ አብሮነት፣ በፍቅርና በሰላም ልጆቹን ሊቀርጻቸው እንደሚገባ ምክር ሃሳባቸው ሰጥተዋል፡፡
ቀና አስተሳሰብ፣ ፍቅርንና አብሮ የመኖር ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦና እሴቶች በመደገፍ መልካም ጤንነት መጠበቅ ይቻላል፤ ቀና አስተሳሰብ መያዝ ረጅም ዕድሜና ጤናማ ሕይወት መምራት እንደሚያስችል ጥናቶች አመልክተው በአንጻሩ የእሳቤ፣ትውስታና ዕይታ መመረዝ አእምሮን የጤና ችግሮች ተጋላጭ ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 27/2011
ጌትነት ምህረቴ