– ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ
አዲስ አበባ፡- የደቡብ ክልል ምክር ቤት አቶ ርስቱ ይርዳውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ። የ2012 የክልሉ መንግሥት 40 ቢሊዮን 56ሚሊዮን 938ሺ826 በጀት አጸደቀ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 5ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 9ኛ ጉባኤው አቶ ርስቱ ይርዳውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በማድረግ ነው የሾመው።
አቶ ርስቱ ይርዳው ከዚህ ቀደም ከወረዳ ጀምሮ ከጉራጌ ዞን አስተዳዳሪነት እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ሰርተዋል። በአሁኑ ወቅትም የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ።
በተያያዘ ዜናም የደቡብ ክልል ምክር ቤት የክልሉ መንግሥት የ2012 በጀት አፀድቋል። በዚሁ መሠረት የክልሉ መንግሥት በጀት 40 ቢሊዮን 56 ሚሊዮን 938 ሺ 826 ብር ሆኖ የፀደቀ ሲሆን፥ የዘንድሮ በጀት ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር የ5 ነጥብ 59 ከመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል። በበጀቱ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ጭማሪ እንደተደረገላቸው ተገልጿል።
በክልል ማዕከል መደበኛ ወጪን ጨምሮ ለካፒታልና ለተለያዩ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራሞች እንዲውል ከበጀቱ 20 በመቶው የተመደበ ሲሆን፥ የዞን፣ ልዩ ወረዳና ከተማ አስተዳደር እርከኖች ደግሞ 29 ቢሊዮን 24 ሚሊዮን 101 ሺ 645 ብር ተመድቧል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሄለን ደበበ ጉባኤውን ሲከፍቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ምክር ቤቱ ጉባኤውን አለማድረጉ የሚያሳዝን ቢሆንም የዜጎች ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ የነበረ መሆኑን በመጥቀስ ይቅርታ ጠይቀዋል።
አሁን ከተፈጠረው ችግር በላይ አርቆ በማሰብ የሕዝብ ዘላቂ ሰላምና ጥቅም የሚረጋገጥበት ሁኔታ ላይ መሥራት ከምክር ቤቱ አባላት ይጠበቃል ብለዋል። አሁን ችግር የሆነው ገደብ የለሽ ዘረኝነት እልባት ሊሰጠው እንደሚገባም አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሄለን ደበበ ተናግረዋል።
በክልሉ በተፈጠረው ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን ለማቋቋም ኢትዮጵያውያን ላሳዩት ርብርብ ማመስገናቸውን ጠቅሶ ፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 26/2011