አዲስ አበባ፡- መጪው የ2012 ዓ.ም በሀገሪቱ የተለያዩ ኩነቶች የሚከናወኑበት በመሆኑ ከዚያ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የትምህርት መስተጓጎል እንዲሁም አላስፈላጊ ሁከቶች እንዳይከሰት ጠንካራ ሥራ መሰራቱን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሰላማዊ እና የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በተለየ ሁኔታ መዘጋጀታቸውን አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ገልጸዋል፡፡
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ግጭቶች፣ ሁከቶች እና ሞት ትልቅ ትምህርት ሰጥተው ስላለፉ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይደገሙ ጠንካራ ሥራ ተሰርቷል፡፡
ዶክተር ሳሙኤል እንዳሉት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ያደርግልኛል ያለውን ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡ ሰነዱ በአገሪቱ ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ጋር ውይይት የተደረገበት ሲሆን እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ኃላፊ ነት፣ መብትና ግዴታን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች ወደየተመደቡበት ተቋም ሲሄዱ በሰነዱ ዙሪያ እንደሚወያዩበት የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ተማሪዎች መብት እና ግዴታቸውን የሚያውቁበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
«ተማሪዎችም ሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማንኛውም ፀረ ሰላም ኃይል ሃሳብ ማስፈጸሚያ አይደሉም» ያሉት ዶክተር ሳሙኤል ተማሪዎች ለትምህርት እንደሄዱ ሁሉ ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለውና ዓላማቸውን አሳክተው መውጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ እና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር የሺመቤት ቦጋለ እንዳሉት፣ ባለፈው ዓመት በተማሪዎች መካከል አለመግባባትና የተለያዩ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ትምህርት ለአንድ ሳምንት ያክል መስተጓጎሉን ጠቅሰው ይህንን መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ማህበረሰቡ እንዴት እና በምን ሁኔታ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በግልጽ የሚያሳይ ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን ሰላማዊ እና የተረጋጋ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ተማሪዎቹ ወደከተማዋ ሲገቡ ጀምሮ አቀበባል በማድረግ እና ከገቡም በኋላ ተማሪዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ውይይት ለማድረግ ተቋማቸው ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀል፡፡
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ ግብዓት በማሟላት ከአገልግሎት ጋር የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች ከአካባቢው ማህበረሰቡ ጋር በመሆን ደማቅ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ በሰላማዊ መማር ማስተማሩ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ ከሚገኙ ሱቆች ጋርም በተለየ መልኩ ለመወያየት እቅድ መያዛቸውን ገልጸው የከተማዋ ወጣቶች እንዲሁም ማህበረሰቡ የውይይቱ አካል እንደሚሆኑም አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 26/2011
አብርሀም ተወልደ