ባህርዳር፡- የአማራ ክልል ተወላጅ ባለሀብቶች በክልሉ ሁለት ዞኖች ላይ የሚገኙ 12 የዳስ ትምህርት ቤቶችን በዘመናዊ ሕንፃ ሊተኳቸው መሆኑን አስታወቁ፡፡
የክልሉ ተወላጅ ባለሀብቶች ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከአቶ ጥሩነህ ተመስገንና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር የዳስ ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የወሰኑት፡፡ ትምህርት ቤቶች የሚገኙት በሰሜን ጎንደርና በዋግ ብሔረሰብ ዞኖች ሲሆን ባለሀብቶቹም የሚሰሯቸውን ትምህርት ቤቶች በዕጣ ተከፋ ፍለዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ እንዳስረዱት በዳስ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሕፃናት ዝናብ ሲመጣ ከሚማሩበት ወጥተው ሰፈር እየተጠለሉ፤ ዝናቡ ሲያባራ ደግሞ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡ የሚማሩበት ሰሌዳ የላቸውም፡፡ በክልሉ ዘጠኝ ሺ አስራ ሦስት ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ ከደረጃ በታች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በስብሰባው የተሳተፉት አቶ ይበሉ አስቼዋ የተባሉ ባለሀብት ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው የአማራ ክልል ተወላጅ መሆኑን አንስተው እንደነዚህ ዓይነት ጀግና ተማሪዎችን ለማፍራት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ኩራት እንጂ ኪሳራ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ በላይነህ ክንዴ የተባሉ ባለሀብት እንዳሉት የዳስ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል መድረኩ ተገቢ ነው ብሎ የክልላችን መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ተገቢና ወቅታዊ ነው፡፡ መንግሥትና ባለሀብቱ ተቀራርበው መስራት አለባቸው፡፡ ከተባበርን ችግሮች ሁሉ ይቀላሉ፡፡ እናም በዳስ የሚማሩ ተማሪዎቻችንን መታደግ አለብን ብለዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል ወደ ክልሉ የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው አማራ ቢቀየም እንኳን ‹‹ቢራ አልጠጣም ይላል እንጂ›› ፋብሪካ አያቃጥልም፡፡ ስለዚህ አማራ ክልል ቢቀየምም ፋብሪካ አያቃጥልም በማለት ወደ ክልሉ የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር ጨምሯል፡፡ እናንተም ትምህርት ቤት መገንባት ብቻ ሳይሆን መዋዕለነዋያችሁን ለልማት ለማዋል ብትመጡ በደስታ እንቀበላችኋለን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህም ባደረጉት ንግግር ዛሬ የጠራናችሁ በዳስ የሚማሩ ልጆቻችንን ከዳስ አውጥተን በተሻለ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ለማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም የዳስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ያሳያችሁት ርብርብ የሚደነቅ ነው፡፡ ክልላችንም ይኮራባችኋል፡፡
በኢንቨስትመንቱ ዘርፍም ተመሳሳይ ርብርብ በማድረግ ክልሉን ብሎን ሀገራችንን እንድትለማ ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ገንብቶ አስረክቦናል፡፡ ክልሉ ይህን አርአያ ተከትሎ የሚመጣ የባለሀብትም ሆነ የምሁር ድርቅ የለበትም ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 26/2011
አበረ አዳሙ