አዲስ አበባ፡- የሕገ ወጥ ደላሎች ሰንሰለት መርዘም የሽንኩርት ዋጋ ከምንጊዜውም በላይ እንዲወጣና ሸማቹ እንዲማረር እያደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በምሥራቅ ሸዋ ቦራ ወረዳ በማሊማ ቀበሌ ነዋሪና ሽንኩርት አምራች የሆነው ወጣት አማኑኤል ለማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፀው፤ ሕገ ወጥ ደላሎች መበራከታቸው የሽንኩርት ዋጋ ከምንጊዜውም በላይ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ ምርቱ ከአምራቹ እስከ ሕጋዊ ነጋዴዎች ለመድረስ ቢያንስ ሦስት ደላሎችን ያልፋል፡፡
እያንዳንዳቸው ደላሎች በመኪና (በቢያጆ) ከአራት እስከ ስድስት ሺ ብር ጭማሪ ያደርጋሉ፡፡ ይህ የደላሎች ሰንሰለት በመንግሥት ሕጋዊ እርምጃ ካልተወሰደበትና በቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቹ የሚደርስበት አሠራር ካልተዘረጋ የምርት ችግር ባይኖርም የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል፡፡
እንደ አማኑኤል ገለፃ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ገበሬው በጅምላ ከ12 እስከ 15 ብር በመሸጥ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ነጋዴዎች በችርቻሮ እስከ 30 ብር እየሸጡ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከአምራቹና ከሸማቹ ይልቅ ነጋዴዎችና ሕገ ወጥ ደላሎች ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከሕገ ወጥ ደላሎች ባሻገር የሽንኩርት በሽታ መከሰቱ ካለፈው ዓመት ያነሰ ምርት እንዲኖር እና እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ ሽንኩርት ከተለመደው በላይ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ብዙ ሰዎች አዲስ ዓመትን አስበው ሽንኩርት በመትከላቸው በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ምርት እየደረሰ መሆኑን ገልጾ በቀጣይ ወራት ሽንኩርት እንደሚቀንስ አመላካች ነገሮች መኖራቸውን ተናግሯል፡፡
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያ ድርጅት ኢንስፔክተርና ሬጉላቶሪ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ካሳሁን ሙላት በበኩላቸው እንደገለፁት፣ የንግድ ሰንሰለቱን በመጣስ በርካታ ደላሎች በገበያ ሥርዓቱ እየገቡ የንግድ ሥርዓቱ እንዲበላሽ ምክንያት ሆነዋል፡፡ እንዲሁም ነጋዴዎች በመመሳጠር ምርትን በማከማቸት አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት አድርገዋል፡፡ መንግሥት ይህ ችግር እንዳለ በመገንዘብ እርምጃ ከመውሰድ በዘለለ በተለይ ሽንኩርት ከአምራቹ በቀጥታ ለሸማቹ የሚደርስበትን አሠራር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 26/2011
ሞገስ ፀጋዬ