ቅድመ- ታሪክ
አዲሱ ትዳር በንዝንዝ ተጀምሯል። ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ የሚሰሙት ጎረቤቶች የጥንዶቹን ጉዳይ የለመዱት ይመስላል። አባወራው ሚስቱን ከመሳደብ ባለፈ መደብደብና ማሰቃየቱን ቀጥሏል። ይህን የሚያዩ ብዙዎች ደግሞ በሚሆነው ሁሉ ያዝናሉ። ሰበብ ፈላጊው ሰው ባለቤቱን በየአጋጣሚው ለመወረፍ ጥቂት ምክንያት በቂው ነው። ሁሌ ጠብ ለማስነሳት ደግሞ ትንሸዋን ልጅ መነሻ ያደርጋል።
ልጅቷ ከአባወራው አትወለድም። እንደዛሬው የጠብ ምክንያት ሳትሆን በፊት ግን በእሱ ዘንድ የሚሰጣት ቦታ የተለየ ነበር። ይህ የሆነው ግን እናቷን አግብቶ ሚስቱ ከማድረጉ በፊት ነበር። ጥንዶቹ በአንድ ጎጆ ተጣምረው አብረው መኖር ሲጀምሩ ግን አባወራው ልጅቷ አስጠላችው። በእሷ እያመሃኘም እናቲቱን ማሰቃየት ያዘ። እንጀራ አባት መሆኑ ሲገባው ደግሞ የህጻንነት ለዛዋን ሰለቸ። በየሰበቡ እየተነኮሰም ያስከፋትና ያስለቅሳት ያዘ። ፍቅር የተነፈጋት ህጻን የእሱን ፊት እያየች ማደር ልምዷ ሆነ። በመሳቀቅና በፍራቻ መሀል ሆናም ልጅነቷን እንደዋዛ ገፋች።
ቆጣሪ አንባቢው አባወራ የቤቱ የገቢ ምንጭ እሱ ብቻ መሆኑ ያበሳጨው ይመስላል። ሁሌም ሚስቱን ከነልጇ የመያዙ ጉዳይም እንዳብከነከነው ነው። ጠዋት ለስራ ወጥቶ ማታ ሲገባ በስካር ናውዞ ነውና የእናትና ልጅ ስቃይ አይቀሬ ይሆናል። እንደውም አንዳንዴ ስለት እያወጣ ሚስቱን ያስፈራራል። ባስ ባለ ጊዜም በጩቤው አካሏን እየወጋና እያቆሰለ ያሰቃያታል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ዝምተኛዋ ሚስት ሚስጥሯን ለሌሎች አዋይታ አታውቅም። ከህግ ፊት ቀርባም ለበደሏ ፍትህን አትጠይቅም። የፊቷን መበለዝና የአይኖቿን ማበጥ አይተው ለሚጠይቋት ደግሞ ሁሌም ምላሽዋ አንድ ነው። ‹‹ በር መታኝ ›› ማለት ብቻ። እንዲህ መሆኑ ደግሞ ለሁሉ አድራጊው ባል አመችቶታል። ሚስቱን እያሰቃየና የእንጀራ ልጁን እያሳቀቀ የመኖሩን እውነት ያለ አንዳች ከልካይ ቀጥሎበታል።
ከአመታት በኋላ…
እነሆ! ይህ ታሪክ ካለፈ ጥቂት ዓመታት ተቆጠሩ። አሁን የዛን ጊዜዋ ህጻን በእድሜና በአካል ጎልብታ ክፉ ደጉን ለይታለች። የሁለቱ ባልና ሚስት ትዳርም እንደ ትናንቱ ሆኖ በልዩነት መጓዙን ይዟል። ጭቅጭቅና ግልፅ የሚባል በደል ያልተለየው ጎጆ እያደር የቤተሰቡን ቁጥር አክሏል። በላይ በላዩ የተወለዱት ልጆችም የወላጆቻቸውን ማንነት ሊለዩ ተገደዋል። ልጆቹ የአባታቸውን ሃይለኝነት የእናታቸውን ዝምታና ትዕግስተኝነት ያውቁታል።
ልጆቹ ሁሌም በአባታቸው ባህርይ እንደተፈተኑ ነው። ተናዳጁና ቁጡው አባወራ ለእነሱም ቢሆን ፊት አይሰጥም። ልጆቹ ከሌሎች በተለየ ሥርዓት ይዘው እንዲያድጉ ይፈልጋል። ከፍቅር ይልቅ ዱላ፣ ከፈገግታ በፊት ክፉ ፊት ማየት የለመዱት ልጆችም በአባታቸው ስሜትና ፍላጎት ብቻ ተመርተው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል።
የከፋ በደልና የአንድ ወገን አዛዥነት ባደላበት ጎጆ አሁንም ልጆች እየተወለዱነው። አንድ ሁለት እያለ ቁጥሩን ማበራከት የቀጠለው ቤተሰብም ታላቅን ከታናሽ እያስከተለ አስራ አንድ ልጆችን አፍርቷል።
አሁን የጥንዶቹ ትዳር በልጆች በረከት ታጅቧል። የቤተሰቡ ኑሮም ከቀድሞው በተለየ ተሻሽሏል። ዛሬም ግን ከዚህ ጎጆ ጣራ ስር የሚፈለገው ሰላም የለም። ያለፉት ዓመታትም በወይዘሮዋ ህይወት ክፉ አሻራዎችን ስለማሳረፋቸው ልጆችን ጨምሮ አካባቢው ሁሉ ያውቃል።
ሁለቱም ሁለት ጸጉር አውጥተው ‹‹አንቱ ›› መባል ቢጀምሩም ከአርባ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ትዳር ግን ፍቅርን እንደተራበ ቀጥሏል። ዛሬም አባወራው ከሚስታቸው ሰላም አያድሩም። አሁንም ከጭቅጭቅ አልፈው ወይዘሮዋን ለመደብደብ ያስባሉ። ይህ እውነትም እንደትናንቱ ብዙዎችን ያስገርማል። አንዳንዴ አብሯቸው የዘለቀው ቁጡነት ከልጆቻቸው እያጋጨ ያቀያይማቸዋል። ዛሬ ላይ ቆመው ‹‹እንደትናንቱ ልሁን›› ማለታቸውም በቤተሰቡ ዘንድ አልተወደደም።
እናታቸውን ከልብ የሚወዱት ልጆች የአባታቸውን ድርጊት አይደግፉም። ሰሚ ባያገኙም ፍራቻና አክብሮት ባለው ስሜት አባወራውን ሊቃወሙ ይሞክራሉ። ሰውዬው ግን አሁንም ቢሆን በሚስታቸው ላይ የክፋት በትራቸውን አልተውም። ምክንያት ፈልገው እጃቸውን ለቅጣት ያነሳሉ። ሲላቸው ልብሳቸውን አስወልቀው ይገርፏቿል። አንዳንዴም ቦታና ጊዜ ሳይመርጡ በጥፊ ይመቷቸዋል። ሚስት ግን ሁሉን በሆዳቸው ይዘው ትዕግስትን አማራጭ አድርገዋል። የሚሆነውን ሁሉ ልጆቹ እንዳያውቁ ሲሉም ይጠነቀቃሉ።
አባወራው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዱላቸው ምክንያት የቅናት ጉዳይ ሆኗል። ‹‹በሌላ ወንድ ጠርጥሬሻለሁ›› በሚል ሰበብ ነገር እያነሱ ለጠብ መጋበዝ ቀጥለዋል። ስለሚናገሩት ሁሉ እማኝና ማስረጃ ያጣቅሳሉ። የሚሉትንም ሚስታቸው አምነው እንዲቀበሏቸው ያስገድዳሉ።
በረጅም ዓመታት የትዳር ጉዞ አስራአንድ ልጆችን የሰጧቸው ወይዘሮ ከምንም በላይ ይህ አይነቱ ወሬ ይጎዳቸው ጀምሯል። እሳቸው ልጆች አሳድግ፣ ጎጆ አቀና ብለው ትዳራቸውን ስለመጠበቃቸው ያውቃሉ። ያለፉበት የመከራ መንገድ ደግሞ ከብዙዎቹ ያልተደበቀ እውነት ነው። ያን ሁሉ ችግር ተቋቁመው ዛሬ ላይ ሲደርሱም በፍጹም ታማኝነትና ጨዋነት ነበር።
ወይዘሮዋ አሁን አሁን ከባለቤታቸው የሚሰሙት ተደጋጋሚ ቃል ከእስከዛሬው ዱላና ስድብ በላይ ሆኖ እየሸነቆጣቸው ነው። ‹‹ውሽማሽ›› ሲሉ የሚደጋግሙት ንግግርም ጨዋነታቸውን እየሸረሸረ፤ ውስጣቸውን ይፈትን ይዟል። ይህን ከባድ ጉዳይ አዕምሯቸው እንደዋዛ ሊያልፈው አልፈቀደም። እንዲህ መባላቸው ከራሳቸው አልፎ የልጆቻውን ስሜት እንደሚጎዳ አምነዋል።
በልጅነት ዕድሜዋ ከእናቷ ጋር የስቃይ ገፈትን የቀመሰችው የወይዘሮዋ ልጅ አሁን ሁሉ ነገር ሰልችቷታል። እሷ ለቤቱ ትልቅና የመጀመሪያ ልጅ ብትሆንም ይህ ስሜት ግን አብሯት ዘልቆ አያውቅም። በትካዜ አድጋ በለቅሶ የኖረችው ወጣት ከዚህ በኋላ ለቀሪው ህይወቷ መወሰን እንዳለባት ቆርጣለች።
ወጣቷ ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ ያደረገችው ሙከራ በተሳካ ጊዜ አብዝታ ተደሰተች። ይህ አጋጣሚ የእሷን ህይወት ጨምሮ የእናቷን ኑሮ ለመለወጥ ምክንያት እንደሚሆን አልማምም ፈጣሪዋን አመሰገነች። ካሰበችው አገር ደርሳ ስራ ስትጀምር ያቀደችውን በማድረግ የመጀመሪያ ፍላጎቷን አሟላች። ወደ አገር ቤት የሚሄድ ሰው ስታገኝም ገንዘብ ልብስና ሽቶ እየላከች የእናቷን ምርቃት አገኘች።
ወጣቷ በሰው አገር ጠንክራ መስራቷን ቀጥላለች። ከአድማስ ማዶ ሆና የእናቷን ታሪክ የመለወጥ ዕቅዷም ከእሷ ጋር ነው። ሁሌም ግን የእናቷ ኑሮና የእንጀራ አባቷ ድርጊት ውል እያለ ያስጨንቃታል። የትናንቱን እያሰበችም በትካዜ ውላ ታድራለች። ለስጦታ ለእናቷ የምትልከውን ልብስ እንጀራ አባቷ እየተቀበለ እንደሚቀድና እንደሚያቃጥልባት ሰምታለች። ለድርጊቱ አዲስ ባትሆንም ወሬውን የሰማችው ግን በተለየ ኀዘን ነበር።
ወይዘሮዋ ከአባወራው የሚናፈስባቸውን ወሬ አሜን ብሎ የመቀበሉን ጉዳይ አላመነቡበትም። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ያለፉበትን የመከራ ሀይወት ሁሉ እያስታወሰ ከአንድ ውሳኔ አድርሷቸዋል። እስከዛሬ ህሊናቸውን ከአካላቸው ጎድተው ዓመታትን የዘለቁት ለልጆቻቸው ሲሉ እንደነበር ያውቃሉ። አሁን ግን በተለመደው መንገድ መቀጠሉን አልመረጡትም።
በባልና ሚስቱ መሀል ያደረው ቅራኔ እንደወትሮው በየሰበቡ ሳይፈታ ቀናትን አስቆጥሯል። ክፈተቱም መኮራረፍን አስከትሎና አልጋ አስለይቶ ገበታ በእኩል እንዳይቆርሱ አድርጓል። ይህ አይነቱ አውነት ሁሌም ለቤቱ አዲስ አይደለም። ሰሞኑን በወይዘሮዋ ህሊና የሚመላለሰው ጉዳይ ግን ከወትሮው የተለየ እየሆነ ነው።
አንድ ቀን ማመልከቻቸውን ይዘው ከፍርድ ቤት ደጃፍ የደረሱት ሴት የእስዛሬውን በደል አንስተው በምሬት ‹‹አቤት›› አሉ። ፍርድ ቤቱ። ሃሳባቸውን አድምጦ በሰጠው ቀነ ቀጠሮም ተጠሪውን አቅርቦ ጉዳዩን አሳወቀ። አባወራው በወቅቱ ከሚስታቸው የቀረበላቸውን የፍቺ ጥያቄ አላመኑበትም። ፍርድ ቤቱ ጋብቻው እንዳይፈርስ በሚል የሰጠውን የማሰቢያ ጊዜ ተቀብለው ጉዳዩን ለቤተዘመድ ጉባኤ ሲያሳውቁም ተስፋ ባለመቁረጥ ነበር።
ጥንዶቹ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ከቤተዘመድ ሊመክሩ ከሸንጎ ተቀመጡ። ይህኔ ሰውየው ሁሉን ረስተው ለመለሳለስ ሞከሩ። ወይዘሮዋ ግን ‹‹በይቅርብኝ›› ጽናት የያዙትን ሀሳብ አከረሩ። ከዚህ በኋላ ባልና ሚስቱ የደረሱበትን ይዘው በቀጠሮው ቀን ፍርድ ቤት ቀረቡ።
አሁን ዓመታትን የተጓዘው ትዳር ህልውና ተናግቷል። በፍርድ ቤቱና በወዳጅ ዘመድ ሽምግልና የተደረገው የእርቅ ሙከራም አልተሳካም። ፍርድ ቤቱ በሁለቱም ወገኖች ያለውን ሀሳብ አድምጦ በፍቺው ላይ ከመወሰኑ በፊት አባወራው ከቤት እንዲወጡና መኖሪያ እስኪያገኙም ወይዘሮዋ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ወጪያቸውን እንዲሽፍኑ ሲል ትዕዛዙን አሳለፈ።
ከዚህ በኋላ የባልና ሚስቱ መለያየት እውን ሆነ። እስከዛሬ የኖሩበት ቤት የግላቸው ባለመሆኑ ለንብረት ክፍፍል የሚያጨቃጭቃቸው ሰበብ አልነበረም። እንደተባለው አባወራው ቤት መፈለግ ሲጀምሩ ወይዘሮዋም የደረሰባቸውን የስም ማጥፋት እያሰቡ በትካዜ ሲብሰለሰሉ ከረሙ። ያሳለፉትን የመከራ ጊዜ እያስታወሱም ይዘውት በኖሩት የበደል ሸክም እንደ አዲስ ሆነው አዘኑ።
በነዚህ ቀናት መሀል ግን የአባወራው እግሮች በቤት ፍለጋ ብቻ አልተወሰኑም። ከአንድ ዓመት በፊት በአስር ሺህ ብር ገዘተው የያዙትን ሽጉጥ ከተቀመጠበት አንስተው የሚደርጉበትን ሲያቅዱ ቆዩ። አብሯቸው የኖረውን ባለፌሮ እጀታ ጩቤ ከጎናቸው ሽጠውም ራሳቸውን ሲወዘወዙና ጥርሳቸውን ሲነከሱ ከረሙ።
ወይዘሮዋ ሰውየው መሳሪያ ገዝተው መያዛቸውን ካወቁ ጀምሮ ስጋት ገብቷቸዋል። ይህን ለሚቀርቧቸው ሰዎች ባዋዩ ጊዜም በጎዉን ብቻ እንዲያስቡ ይመክሯቸዋል። እሳቸው ግን የባላቸውን አብሮ የኖረ ጭካኔ እያስታወሱ ይጨነቃሉ። አንዳንዴ ደግሞ ከክፉ ሀሳባቸው መለስ ብለው መልካሙን ብቻ ይመኛሉ። የአስራ አንድ ልጆች አባት እንዳደረጓቸው እያሰቡም ከእስከዛሬው የከፋ ድርጊት እንደማይፈጽሙባቸው ራሳቸውን ያሳምናሉ።
አንድ ቀን አባወራው ወይዘሮዋ በግቢው ከሚነግዱበት ሱቅ ደርሰው ልብሳቸውን እንዲሰጧቸው ጠየቁ። ይህ አጋጣሚም በሁለቱ መሀል የቆየውን ቅሬታ ቆስቁሶ ክፉ ደግ አነጋገራቸው። ይህኔ ሰውየው እንደተለመደው ዝተውና አስፈራተው ከስፍራው ራቁ። ከዚሀ በኋላ የስልሳስድስት ዓመቱ ሰው ሲያባብሉት የቆዩት የበቀል ስሜት አገረሸባቸው። ውስጣቸውም በክፉ ሀሳብ ሲጎሽ ከረመ።
የካቲት 6 ቀን 2007 ዓ.ም፤ ምሽት
ምሽቱ እየገፋ ነው። ሁሌም ሰአቱ ደርሶ የግቢው ሱቅ እስኪዘጋ ወይዘሮዋ ከስፍራው አረፍ ብለው ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ። የዛን ዕለትም ወደሱቁ ከማምራታቸው አስቀድሞ ከቤት ቆይተው የቤቱን ስራ ሲከውኑ አምሽተዋል። በተረፋቸው ጥቂት ጊዜም ከሱቁ ጎራ ብሎ የመቆየት ሀሳብ አላቸው።
በግቢው አንድ አቅጣጫ ቆም ብላ ስልክ የምታወራው ልጃቸው እሷ ካለችበት ፊትለፊት በሚገኘው የመጸዳጃ ቤት በኩል በድንገት ባትሪ በርቶ ሲጠፋ ተመለከተች። በዚህ ሰአት እንዲህ መሆኑ አስደንግጧታል። ማን ይህን ሊያደርግ እንደሚችልም መላልሳ አሰበች። መልስ አልነበራትም ። በዛው ፍጥነት እናቷ ከሱቅ ወጥተው ወደ ቤት ሲያመሩ ስታይ ግን ሁሉን ረስታ ወደ እሳአቸው አተኮረች።
አሁን አባወራው ካደፈጡበት ወጥተው ወደፊት መራመድ ጀምረዋል። ድንገት ወይዘሮዋን ማግኘታቸውም የልባቸውን ሃሳብ ሞልቶታል። በፍጥነት ከኋላቸው ደርሰው የያዙትን ሽጉጥ ከሚስታቸው ወገብ ላይ ደገኑት። ሴትዮዋ የነካቸውን እስኪያረጋግጡ ጊዜ አልሰጧቸውም። ወደኋላ ከመዞራቸው በፊት የተቀባበለውን ሸጉጥ አውጥተው ፊትለፊት ተኮሱ። በቅርበት ጥይቱ ያገኛቸው ወይዘሮ በደረታቸው ድፍት አሉ። ከልጆቻቸው መሀል ድንገት የደረሰው ወጣት የሚያየውን ማመን አልቻለም። በድንጋጤ እንደራደ በታላቅ ጩኸት ሊያስቆማቸው ሞከረ። ከንቱ ልፋት ነበር። ይህን ሲረዳ የእናቱን ስም እየጠራ በ‹‹ድረሱልኝ›› ድምጽ ተማጸነ።
ሰውየው የልጃቸውን ሁኔታ እንዳዩ ሁለተኛውን ጥይት ተኮሱ። የሽጉጡን አፈሙዝ ወደእሱ አዙረውም በፍጥነት እንዲንበረከክ አዘዙት። ጩኸትና የጥይት ድምጽ ሰምተው በስፍራው የደረሱ ጎረቤቶች የሆነውን ባዩ ጊዜ ሰውየውን ለመያዝ ተረባረቡ። ከሽጉጡ ጋር ያገኙትን ባለፌሮ ጩቤ ይዘውም ለአካባቢው ፖሊስ አስቸኳይ ጥሪ አደረሱ። የወይዘሮዋ ትንፋሽ አለመጥፋቱ ለሁሉም ተስፋ ሆኖ ለህክምና እርዳታ ወደሆስፒታል ተጣደፉ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹ፊናንስ›› ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሲደርስ ጥቃት አድራሹን በቁጥጥር ስር አውሎ የአይን እማኞችን ለጥያቄ ፈለገ። የዛን ምሽት ክፉ አጋጣሚ ለመላው ቤተሰብና ለአካባቢው ነዋሪዎች የማይረሳ ሆኖ ሰነበተ። ፖሊስ አባወራውን በቁጥጥር ስር አውሎ አውነታውን መመርመረ ጀመረ።
በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 906/04 የተከፈተው ፋይል የተጠርጣሪው ቃል አንድ በአንድ ተመዘገበበት። ክሱን የሚመረምረው ዋና ሳጂን ሲሳይ ተሾመ ከአካባቢው ከመላው ቤተሰብና ከግለሰቡ ያገኛቸውን መረጃዎች ሰንዶ በማስረጃነት አሰፈረ። በዕለቱ ወንጀል የተፈጸመበት EP 145080 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥም ከመሰል ጥይቶቹና ካርታው ጋር በኤግዚቢትነት ተመዘገበ። ባለፌሮው ጩቤም ለተጨማሪ ማሳያ በማስረጃነት ተያያዘ።
የወይዘሮዋ መጨረሻ
ዓመታትን በትዳር ተጋርተው አስራአንድ ልጆችን ከሰጧቸው ባለቤታቸው የጥይት አሩር ያረፈባቸው ወይዘሮ ህይወት ተርፏል።
ቁስልና የከፋውን ስቃይ መቋቋም ያቃታቸው ወይዘሮዋ ከመቼውም በላይ ተዳክመዋል። ሁሌም ዙሪያቸውን ከበው የሚላቀሱት ልጆቻቸው ተስፋ እየቆረጡ ነው። አንድ ቀን ግን ይህ ሁሉ ስቃይና የልጆቹ አጉል ተስፋ በድንገት ተቋረጠ። እናት መትርፍን እንደተመኙና አይናቸው እንደተንከራተተ እስትንፋሳቸው ቀጥ አለ። ለዓመታት የበደል ሸክምን ያዘለው አካል አሁን ከድካሙ ሊያርፍ ግድ ብሏል። የዝምተኛዋ እመቤት አንደበትም ከነሚስጥሩ ተሸብቧል። መከራና ስቃይ አስተናጋጁ አካል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እረፍትን ሽቶ አለምን ተሰናብቷል።
ውሳኔ
አቶ ቢልልኝ ደረሰ ለዓመታት በትዳር አብረዋቸው የቆዩትን ባለቤታቸውን ሆን ብለው በግፍ በመግደላቸውና ድርጊታቸው ከባድ የነፍስ ማጥፋት ወንጀል መሆኑ በመረጋገጡ ፍርድ ቤቱ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የሃያ ዓመት ጽኑአስራት እንዲቀጡ ሲል የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ወስኗል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 25/2011
መልካምስራ አፈወርቅ