የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ12 ሚሊየን ብር ያስገናባውን የሀዋሳ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከል አስመረቀ።
የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ለፋና ብሮድ ካስቲንግ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የሀዋሳ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ግንባታ ተናቅቆ ታህሳስ 6፣ 2011 ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ማዕከሉ ከመስከረም 21 ቀን 2011 ጀምሮ የሙከራ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፥ ከመስከርም ወር 21 እስከ ህዳር 21ቀን 2011 ዓ.ም ብቻ 22 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 315 ቶን ያህል ቡና ምርትን በስኬት ማገበያየት መቻሉን ምርት ገበያው አስታውቋል።
1 ሺህ 380 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ማዕከሉ ለግንባታው 12 ሚሊየን ያህል ብር ወጭ የተደረገበት ሲሆን፥ 7 ነጥብ 76 ሚሊን ብሩ በኢትዮጵያ ምርት ገበያና ቀሪው 4 ነጥብ 87 ሚለየን ብር ከአውሮፓ ህብርት መሸፈኑም ገልጿል።
90 ደንበኞችን በአንዴ የሚያስተናግደው ማዕከሉ 40 የኤሌክትሮኒክስ ማገበያያ ኮምፒዩተሮች የተገጠሙለት ነውም ብሏል።
የዘመናዊ የግብይት ስርዓትን ለማስፈንና ተደራሽነቱን ለማስፋፋት አየሰራ የሚገኘው የምርት ገበያው ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ዘዴ ከተሸጋገረ 3ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።
ይህ የግብይት ዘዴ ለምርት ገበያው ታማአኒነት፣ ግልጽነትና ቅልጥፍናን ከመጨመሩ በላይ የመረጃ አያያዙን የተሻሻለ አድርጓል ተብሏል።
አሰራሩ አሁን ላይ ግብይት ከሚፈጸምባቸው ምርቶች በተጨማሪ ሌሎች ምርቶችን ለማገብያየት ሰፊ እድል የፈጠረ ሲሆን፥ በሚቀጥሉት ወራት ሌሎች 3 የምርት ዓይነቶችን ወደዚሁ ግብይት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ምርት ገበያው በመግለጫው አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ደንበኞች አንድን የምርት ግብይት ለማከናወን በርካታ ሰዓታት ይፈጅባቸው የነበረ ሲሆን፥ አዲሱ አሰራር ሰዓትን ከመቆጠብ በተጨማሪ በሂደቱ ይፈጠሩ የነበሩ ስህተቶችን ለመቀነስ ያስቻለ ነው።
በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት 10 ነጥብ 5 ቢሊየን ዋጋ ያላቸው 186 ሺህ 390 ቶን ያህል ምርት በኤሌክትሮኒክስ ግብይት አገልግሎት መፈጸሙም ነው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያስታወቀው።
ግብይቱ ቀደም ሲል በዋናው የምርት ገበያ ብቻ ይከናወን የነበረ ሲሆን፥ አሁን ላይ በሁመራ፣ ጎንደር፣ አዳማ፣ ጅማ ከተሞች የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑም ተገልጿል።