ፀጉር ተፈጥሯዊ ቀለሙን የሚይዘው በሰውነታችን ውስጥ በሚገኘው “ሜላሚን” የተሰኘ ኬሚካል ሳቢያ ሲሆን የኬሚካል መጠኑ መጨመርም ሆነ መቀነስ በፀጉራችን ተፈጥሯዊ መልክ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል:: ዕድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ የኬሚካል መጠኑ እየቀነሰ የሚመጣ ሲሆን በዚህም ምክንያት አዲስ የሚበቅለው ፀጉራችን ቀለም አልባ ሆኖ እንዲያድግ ያደርገዋል፡፡
በዕድሜ መሸምገል የተነሳ የሚመጣውን የፀጉር መሸበት ለማጥፋት በተለይ የከተማ ነዋሪዎች የፀጉር ቀለም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸው ይነገራል። በአገራችን በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ባይኖሩም፣ በአሜሪካ ኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት፤ 68 በመቶ የሚሆኑት ሴት አሜሪካውያን የፀረ- ሽበት ቀለም ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡
ታይም መፅሄት ያወጣው አንድ ዘገባም፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ የፊልምና የሙዚቃ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ዝነኞች የፀረ-ሽበት ቀለም ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
Boomgril.com የተሰኘው በሴቶች ጤናና ውበት አጠባበቅ ላይ አተኩሮ የሚሰራው ድረ- ገፅ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአሜሪካ የሴኔት አባላት ከሆኑና ዕድሜያቸው ከ46- 74 ዓመት ከሆናቸው ሴቶች መካከል የፀረ ሽበት ቀለም ተጠቃሚ ያልሆነ አንድም ሰው አልተገኘም። በፀረ ሽበት ቀለሞች አጠቃቀም ላይ ሴቶች ከፍተኛ ድርሻ ቢኖራቸውም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወንዶችም የፀረ ሽበት ቀለሙ ተጠቃሚ መሆናቸውንና የተጠቃሚው ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ድረ-ገፁ አመልክቷል፡፡
በውስጠኛው የፀጉራችን ክፍል አልፎ ወደ ማዕከላዊው የፀጉራችን ክፍል የሚገባና በቀላሉ የማይለቅ፣ ለወራት እንደጠቆረ አሊያም እንደቀላ የሚዘልቅ የፀረ ሽበት ቀለም አለ፡፡
የፀረ ሽበት ቀለም ተጠቃሚው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ጥሩ ምልክት አይደለም የሚሉት የቆዳና የአባላዘር ስፔሻሊስቱ ዶክተር አብርሃም ተከተል፤ ለፀረ ሽበትም ሆነ ለፀጉር ማቅለሚያነት ታስበው የሚሰሩ የፀጉር ቀለሞች በውስጣቸው ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን መያዛቸውንና የእነዚህ ኬሚካሎች ተደጋግሞ ጥቅም ላይ መዋል በካንሰር የመያዝ ዕድልን እንደሚጨምር አመልክተዋል።
ቀደም ሲል በጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩት የፀጉር ቀለሞች ከሰልና ‹‹ታር›› የተባሉ ኬሚካሎችን የያዙ እንደነበሩ የሚናገሩት ዶክተር አብርሃም፤ በአሁኑ ወቅት የሚፈበረኩትና ጥቅም ላይ የሚውሉት በአብዛኛው ከፔትሮሊየም የሚሰሩና ሜቲክሲና ዲያሚይን የተባሉ ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን በውስጣቸው የያዙ ቀለሞች ናቸው ብለዋል። ምንም እንኳን እነዚህን ቀለማት አምራች የሆኑ አገራት ካንሰር አምጪ ኬሚካሎችን ለቀለም ምርቱ ግብዓትነት ከማዋል መቆጠባቸውን የሚገልፁ ቢሆንም ምርቶቹ ሙሉ በሙሉ ከካንሰር አምጪ ኬሚካሎች የፀዱ ለመሆናቸው ማረጋገጫ መስጠት አለመቻላቸውንም ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፀረ ሽበት ቀለሞች ተጠቃሚው ቁጥር በአገራችን እየጨመረ መምጣቱ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት የህክምና ባለሙያው፤ እነዚህ ሰዎች ቀለማቱን በሚጠቀሙ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባና አዘውትሮ ቀለሞቹን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባቸው ይመክራሉ ሲል አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም ማስነበቡ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011