ከሀገራችን በርካታ የባህል መገለጫ እሴቶች መካከል ተጠቃሽ የሆኑትን አሸንዳ፣ ሻደይ በዓላትን በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መዲና አዲስ አበባ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በድምቀትና በልዩ ድባብ ለማክበር የሚያስችል መርሐግብር መውጣቱ ሰሞኑን ተሰምቷል።
በየዓመቱ በተለይም በትግራይና አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን ልዩ ልዩ ባህላዊ ትውፊቶች የሚያጎሉት የሻደይና አሽንዳ በዓላት በአዲስ አበባ ደረጃ በተናጠልና በጋራ በያዝነው ወር ይከበራሉ:: የሻደይ በዓል ነሐሴ 19 ቀን 2011 ዓ.ም፣ የአሸንዳ በዓል ደግሞ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በመዲናችን በልዩ ድምቀት ለማክበር ታቅዷል::
በዓሉ በትግራይ እና በአማራ ክልሎችም እንደተለመደው በድምቀት የሚከበር ሲሆን የዘንድሮውን ለየት የሚደርገው በዓላቱን ‹‹የኢትዮጵያ የልጃገረዶች ጨዋታ›› በሚል ስያሜ በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ተስማምተው በጋራ እንቅስቃሴ የመጀመራቸው ጉዳይ ነው።
አሸንዳ- ሻደይ
አሸንድዬ – ሶለል
በዓላቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ የጾመ ፍልሰታ ፍጻሜን ተከትሎ ከነሐሴ 16 ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት መካከል የሚጠቀስ ነው።
አሸንዳ የሣር ዓይነት ሲሆን እንደነጭ ሽንኩርት ቅጠል ሰፊና ረጅም ተክል ነው። ይህ ተክል አሸንድየ ተብሎ ለሚታወቀው በዓል መነሻ ስምም ነው። አለቃ ታዬ በ1902 ዓ.ም መጽሐፋቸው በዓሉን አሽንድዩ ሳይሆን አሸንዳ በማለት የተክሉም የበዓሉም ስም መጠሪያ ያደርጉታል።
አሸንድየ፣ አሸንዳ፣ ሻዴይ እና ሶለል ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ 18 ቀን ድረስ (አንዳንድ መዛግብት እስከ ነሐሴ 21 ድረስ ይከበራል ይላሉ) በመላው ትግራይ፣ በዋግ፣ በላስታ፣ጎንደር አካባቢዎች የሚከበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጓሜ ያለው በዓል ነው።
የአሸንዳ በዓል ጥቂት በክረምት ወቅት ከሚበቅለው ቁመቱ ከ80 እስከ 90 ሳ.ሜ የሚሆን የአሸንዳ ተክል ስሙን የወረሰውና በአብዛኛው ልጃገረዶች አሸርጠው የሚጫወቱበት የአሸንዳ በዓል አከባበር በዋናነት ሴቶች በዕድሜ ደረጃቸው ተቧድነው የሚያከብሩት ትልቅ በዓል ሲሆን ወንዶችም ያጁቧቸዋል።
የአሸንዳ በዓል በትግራይ አሸንዳ በሚለው ስም በዋናነት የሚታወቅ ሲሆን ፣ በሰሜን ወሎ ቆቦ (ሶለል ይባላል)፣ በዋግ ኸምራ ሰቆጣ (ሻደይ)፣ በላስታ ላሊበላ (አሸንድዬ)፣ በአክሱም አካባቢ (ዓይነ ዋሪ) በመባል ይታወቃል። በዓሉ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ኤርትራ ጭምር እንደሚከበር ይነገራል።
አሸንዳ የዜማ ብቻ ሳይሆን የውበትም በዓል ነው። ሴቶች ለጨዋታው የሚያስፈልጉ አልባሳትና ጌጣጌጥ የማሟላት ቅድመ ዝግጅት ለበዓሉ ሁለት ሳምንት አካባቢ ሲቀረው ጀምሮ ያከናውናሉ። የአሸንዳ በዓል የፀጉር አሠራሩ ከአልባሶ እስከ ግልብጥ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ከደቃቅ እስከ ጉልህ ከሕፃን እስከ አዋቂ ተቆናጅተው ከቱባው ባህል ልብስ አንስቶ ከዘመናዊው ስፌት ከተገኙት ጃርሲ፣ ሽፎን ቀሚስ ጋር ተኩለው፣ ተውበው የሚታዩበትም ትልቅ በዓል ነው። ጌጣጌጡም ልዩ ነው፤ አንገት ላይ ከሚንጠለጠለው ሕንቆ፣ እግር ላይ እስከሚጠለቀው አልቦ ያካትታል። ጫማም በዋናነት ኮንጎ ይጫማሉ። ታድያ ይህን የታዘቡ አባቶቻችን የአሸንዳ ልጅ አይተህ አትታጭ እስከማለት ደርሰዋል።
የአሸንዳ በዓል የበዓሉ ኩነት ለከተማው ወይም ለአካባቢው እንግዳ ለሆነው ብቻ ሳይሆን በዚያው ከተማ የሚኖሩትን ጭምር ቀልብ ይገዛል። በዓሉ በፀጉር አሠራርና በአልባሳት፣ በመዋቢያ ቁሶችና በመጋጋጪያዎች ብቻ አይደለም የሚገለጠው፣ በዓሉን የሚያጎሉ የተለያዩ ዘፈኖች ይገኙበታል።
የአሸንዳ ልጃገረዶች ከሚዘፍኗቸው ዘፈኖች ለምሳሌ በጥቂቱ
‹‹መፀት መፀት
ኣሸንዳ ዕምባባ መፀት››
(መጣች መጣች፣ አሸንዳ አበባ መጣች)
‹‹አሸንዳ ናይ ዓሚ’የ
ናይ ዓሚ’የ››
ተጋነና ሎሚ’የ›› (አሸንዳ የዓምናዬ፣ የዓም ናዬ ተገናኘን ዘንድሮ) እና ሌሎችም በበዓሉ የሚዘ ፈኑ ዘፈኖች እየዘፈኑ ወንዶችም ሽልማቱንም ካልነፈግናቸው ‹‹ፈሰሰ ከም ማይ ነሓሰ›› (እንደ ነሐሴ ውኃ ፈሰሰ) በማለትም ያወድሱናል።
በሻደይ የወንዶች ሚና እና የፍቅር ክዋኔዎች
የሻደይ ጨዋታ ተምሳሌቱ ሃይማኖታዊ ነው። ሻደይ ለሴቶች የነፃነት ማብሰሪያም ነው፤ በነፃነት ከአቻዎቻቸው ጋር ይጫወታሉና። ለመሆኑ በሻደይ ጨዋታ የወንዶች ሚና ምንድን ነው? የዋግ ኽምራ ወጣት ወንዶች አብዛኛውን ጊዜ ከነሐሴ መጀመሪያ ቀናት ጀምሮ ክምክም ጎፈሪያቸውን የሚያስውብ ልዩ መዓዛ ያለው ቅባት ይቀባሉ። ቅባቱ ተፈጥሯዊ ነው፤ በተፈጥሯዊ ውበት ላይ የሚያርፍ የተፈጥሮ መዋቢያ።
በተለይም ‹ባጠቋ›› ተብሎ የሚጠራውን ዛፍ ግንዱ ላይ በድንጋይ በመቀጥቀጥ የሚወጣውን ፈሳሽ ነው ጎፈሪያቸውን የሚቀቡት። ቅቤ ወይም ሌላ ሰው ሠራሽ መዋቢያ አጥተው አይደለም ይህን የሚመርጡት፤ የ‹‹ባጠቋው›› መዓዛ በአካባቢው ወንዶች አገላለጽ ‹‹ከፈረንሳይ ሽቶዎች ሁሉ ስለሚልቅ›› እንጅ። ጥሩው መዓዛ ደግሞ ከውቡ አለባበስና የበዓል ድባብ ጋር ተዳምሮ ጨዋታው ለሚከወንበት አካባቢ ልዩ ድባብ ይፈጥርለታል። ምክንያቱ ደግሞ ተፈጥሯዊው ውብ መዓዛ ባልተበረዘው ባህል ላይ አርፎ ልዩ ገጽታ ስለሚሰጠው ነው።
ነሐሴ 16 ወደ ዋግኽምራ ጎራ ያለ ሰው ታዲያ በሻደይ ጨዋታ ውበት ብቻ ሳይሆን ዘመን ባልከለሰው አክብሮታቸው እና ፍቅራቸው ተደንቆ፣ በደግነታቸውም አክብሮቱን ገልጾ ይመለሳል። ወንዶች ነሐሴ 15 ላይ አንድ ቀዳሚ ሥራ አላቸው፤ ለልጃገረዶቹ የሻደይ ቅጠሉን መቁረጥ።
ቅጠሉን ማምጣቱ የወንዶች ሥራ ነው፤ የሚቆርጡትም በባዶ ሆዳቸው ነው፤ ቁርስ ሳይበሉ። ሻደዩን በሴቶቹ ወገብ ልክ በሚሆን ግምት በዛፎች ልጥ ያዘጋጁላቸዋል። የተዘጋጀውን ሻደይም ለልጃገረዶቹ በደስታ ይሰጧቸዋል። ‹‹ከዓመት ዓመት ያድርስህ!›› መባሉ የሚጀምረውም ያኔ ነው። ሴቶችም የተቀበሉትን ሻደይ በቀጥታ ወደቤታቸው ይዘውት አይገቡም፤ ይልቁንም ከቤታቸው ጓሮ ባለው ሳር የለበሰ ቦታ ላይ ያስ ቀምጡታል።
ነሐሴ 16 ላይ ወንዶቹ በጠዋቱ ተጠራርተው ወደ ቆላማው አካባቢ በመሄድ በኽምጣኛ ቋንቋ ‹‹ጊጤ›› የሚባለውን ወፍራም፣ ደንዳና እና በውስጡ ከፍተኛ ውኃ የሚይዝ ግንድ ይቆርጣሉ።
ከጊጤው ላይ የሚሰካ መፎካከሪያ ጦር ደግሞ ከዕጽዋት ሹል እያደረጉ ያዘጋጃሉ። ጊጤው ከእንጨት የተሠራው ጦር ሲያርፍበት በቀላሉ የሚበሳ ነው። ወንዶች እነዚህን ያዘጋጁና ሴቶቹ ለመንደርተኞቹ አማካኝ በሆነ ቦታ ‹‹ሻደይ!›› እያሉ ከሚጫወቱበት ቦታ ጦር እየመከቱ ጥንካሬያቸውን ይፈትናሉ። በትግል እና በንጥቂያ ውድድርም በልጃገረዶቹ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ይጥራሉ።
ሴቶቹ ሲጫወቱ ውለው ሲመሽ ወደየቤታቸው ይሄዳሉ፤ ሌላ አካል እንዳይተ ናኮላቸው ደግሞ ወንዶቹ መከታ ሁነው ይጠብቃሉ፤ ወደ ቤታቸውም ያደርሳሉ።
የሻደይ ጨዋታ ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 21 በዚህ መልኩ ሲከበር ሁሉም ውበቱን ተጠንቅቆ ይጠብቃል፤ ሳይደበዝዝም ሳምንቱን በሙሉ ይቆያል። በጊዜው የወንዶች ጀግንነት እና ኃላፊነትን የመወጣት አቅምም ይፈተሻል። በሴቶቹ ያልተመረጡ ወንዶች ያለፈቃዳቸው ሴቶችን እንዳይተናኮሉ በማድረግ በኩል የጠባቂ ወንዶቹ ሚና ከፍተኛ ነው፤ ጠባቂዎቹ የሻደይ ሴቶች ሰላም አስከባሪ ናቸውና።
በሻደይ ጨዋታ ሌላም ትዕይንት አለ። ወንዶች ‹‹ከዓመት ዓመት ያድርሰን!›› በማለት የሻደይ ቅጠልን ከልጃገረዶች ወገብ ላይ ይቆርጣሉ። ወግ ደርሶት፣ እንዲያው ተሳክቶለት፣ የፍቅር ነገር ነካክቶት ከሆነ ወንዱ ከሚፈልጋት ሴት ወገብ ላይ የሻደይ ቅጠሉን ለመበጠስ ቀኑን ሙሉ ባይኑ እያማተረ፣ የከጀላትን ልጅ እየተከተለ ቀንቶት ሻደዩን ሲቆርጥ ፈገግ ብላ ካየችው ድል ማድረጉን ያረጋግጣል። ምንም ምላሽ ካላገኘ ደግሞ ከንቱ ድካም ስለሚሆንበት ዕጣ ፈንታውን በሌሎች ላይ መሞከር አለበትና ሳይረፍድበት ወዲያውኑ ምልስ ይላል።
ሴቶቹ እና ወንዶቹ በሻደይ ሲደምቁ፣ ሲጨዋወቱ ይሰነብቱና በቆይታቸው ካገኟቸው በረከቶች ቀንሰው ነሐሴ 21 ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ። ቀሪውን ደግሞ ለምግብነት የሚውለውን አዘጋጅተው በጋራ ይመገባሉ። ከምግቡ በፊት ግን አንድ መከወን ያለበት ባህላዊ ጨዋታ አለ። በቂጣ፣ በቅቤ፣ በአይብ፣ በጨው… የሚሠራ ‹‹አስኩር›› የሚባል ምግብ ሴቶች ከቤት ውስጥ ሠርተው ወንዶች እንዳያገኙት ይደብቁታል። ወንዶች ወደ ቤት እንዳይገቡም ከበር ላይ ሆነው ይከላከላሉ።
ወንዶችም አስኩሩን ለማግኘት ብርቱ ትግል ያደርጋሉ፤ ካገኙት በኋላም በደስታ ተሻምተው ይበሉታል፤ ሌላው ምግብም በስርዓት መሰጠት ይጀምራል።
ዝግጅቱ ሲጠናቀቅም ልጃገረዶቹ እና ወንዶች በሻደይ ጨዋታው ጊዜ ያጠፉት ጥፋት ካለ ይቅርታ በመጠያየቅ ‹‹ከዓመት ዓመት ያድርሰን›› በማለት ለቀጣይ ዓመት ጨዋታ ቃል ገብተው ይለያያሉ።
የበዓላቱ መንፈሳዊ እሴት
የሻደይ፣ አሸንዳ እና አሸንድዬ በዓል ከኦርቶዶክስ ተዋሐዶ እምነት ጋርም ትስስር እንዳለው ይነገራል። አጀማመሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻም አለው።
የአዳም ከገነት መባረር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ ከዘመን መለወጫ፣ ከመጥመቀ- መለኮት ከቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቆረጥ፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣዔ (ፍልስታ) እና ከመስፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ጋር በማስተሳሰር የሚያስቀምጡ አሉ። በማኅበረስቡ አባቶችና ሊቃውንቱ ዘንድ ጎልቶ የሚነገረውና የሚተረከው ግን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣዔ (ፍልስታ) በዓልን መሠረት ያደረገ ነው።
አዳም በገነት ሳለ ሕግ በመተላለፉ ጸጋ እግዚአብሔር ርቆት እርቃኑን በሆነ ጊዜ አካሉን ለመሸፈን ቅጠል መጠቀሙን ለማሰብ ያች አዳምና ሔዋን ክብራቸውን ተገፈው ከገነት የተባረሩባትን ዕለትን በማሰብ በወቅቱ ያገለደሙትን ቅጠል በምልክትነት በመውሰድ የሻደይ ቅጠልን በገመድ ላይ ጎንጉነው በወገባቸው አገልድመው (አስረው) አዳምና ሔዋን ከገነት ከመውጣታቸው በፊት ፆታዊ ግንኙነት ያልጀመሩ ደናግላን ስለነበሩ ያንን በመከተልና በምሳሌነት በመውሰድ ያላገቡ የአገው ልጃገረዶች ተሰባስበው ያችን ዕለት ወይም ቀን በመታሰቢያነት ለመቁጠር ወይም ለመዘከር የሻደይ ጨዋታን መጫወት ወይም ማክበር እንደጀመሩ የሚናገሩም አሉ።
ከኖኅ ዘመን ታሪክ ጋር ያለው ግንኙነት ደግሞ ከጥፋት ውኃ በኋላ ውኃው የመጉደሉን ምልክት ርግብ ለኖኅ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣት በምድር ሠላም እንደሆነ የምሥራች አብሥራለች። ከዚሁ ጋር በተገናኘ በዓሉን ያንን ለምለም ቅጠል ወገባቸው ላይ በማሰር ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋገርን ሲሉ ማክበር እንደጀመሩ ከታሪኩ ጋር አያይዘው ያስቀምጡታል። ከመስፍኑ ዮፍታሔ ታሪክ ጋርም ቢሆን የሻደይ በዓል እንዴት ግንኙነት እንዳለው ሲያስቀምጡ ዮፍታሔ ወደ ጦርነት በሄደ ጊዜ በድል ከተመለሰ ለአምላኩ መስዋዕትን ለማቅረብ ስዕለት ገበቶ ነበር።
ይህም ከቤቱ ሲመለስ መጀመሪያ የሚቀበለውን እንደሚሠዋ ሲሆን በዚህ ጊዜ ያለ ወትሮዋ ልጁ እየዘፈነች ልትቀበለው ወጣች በዚህም በጣም አዘነ። ልጁም ለአምላኩ የገባውን ስዕለት እንዳያስቀር ሁለት ወር ስለ ድንግልናዋ አልቅሳ ስዕለቱን እንዲፈጽም ጠይቃው ከሁለት ወር በኋላ ስዕለቱን የፈጸመ ሲሆን አባቷ የገባውን ቃል ኪዳን እንዳያጥፍ ያበረታታችውንና መሥዋዕትነትን ለሀገር፣ ለህዝብ፣ ለአባትና ለፈጣሪዋ የከፈለችውን የዮፍታሔን ልጅ በየዓመቱ ለአራት ቀናት ሙሾ በማውጣት አስበው ይውላሉ።
በዚህ መሠረት በበዓሉ ላይ ከሚፈጸሙ ተግበራት ጋር አዛምደው መነሻው ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደሆነ ይናገራሉ። “ጽዮንን ክበቡዋት በዙሪያዋም ተመላለሱ…በብርታቷ ልባችሁን አኑሩ፣ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ” መዝ 48፥12
የሻደይ በዓል አጀማመርን በተመለከተ ከላይ ከተቀመጡት ታሪኮች በተጨማሪ በአካባቢው ሕዝብና በቤተ-ክርስቲያን ሊቃውንቶች ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሳው ታሪክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓል ሲሆን ይኸውም እግዚአብሔር አምላክ ለአዳምና ሔዋን ከ5500 ዘመን በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኃጢያት እሥራት ነፃ እንደሚያወጣቸው ቃል-ኪዳን ስለመግባቱ ያስረዳል።
እንደመቋጫ
ዘንድሮ የአሸንዳ የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላትን በዩኔስኮ በጋራ ለማስመዝገብ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ስምምነት ማድረጋቸው ተሰምቷል። በዚህም መሠረት የአሸንዳ፣ የሻደይ፣ አሸንድየ እና ሶለል ባሕላዊ የልጃገረዶች ጨዋታ በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ የተንቀሳቃሽ ምስል፣ የፎቶ፣ የጥናት ምርምሮች እና የፊርማ ናሙናዎችን ለዩኔስኮ መቅረቡ ታውቋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የአማራ እና ትግራይ የሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን በጋራ በመሆን ለዩኔስኮ እንዲመዘገብ ስምምነት ላይ በመደረሱ መጠሪያው ‹‹የኢትዮጵያ ልጃገረዶች ጨዋታ›› በሚል በቅንፉ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በሚል እንዲገለጽ መደረጉም ተሰምቷል።
እናም የሰሜን ኢትዮጵያ ይህ ልዩ የልጃገረዶች ጨዋታ (በዓል) በዩኔስኮ መመዝገቡ የቀደመ ባሕሉ የሆነው የልጃገረዶቹ ጨዋታ ለትውልድ እንዲተላለፍ እና የተረሱ እሴቶች እንዲታወሱ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ ጥበቃ እንዲያገኝም የሚረዳ ይሆናል። በተጨማሪም ይህን አስደናቂ የዓለም ቅርስ ለማየትና በበዓሉም ላይ ለመታደም በየዓመቱ የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር ያግዛል። እግረ መንገድም የባህል ልውውጥ እንዲፈጠር፣ የቱሪዝም ገቢ እንዲያድግ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታመናል።
በዓሉ እንደከዚህ በፊቱ በትግራይና በአማራ ክልሎች ብቻ ከመከበሩ በተጨማሪ ዘንድሮ በዋና ከተማዋ አዲስአበባ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከበር መታሰቡ ባህሉን፣ ትውፊቱን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ እና የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። (የጸሐፊው ማስታወሻ፡ – ለዚህ ዘገባ ጥንቅር የአማራ መገናኛ ብዙሃን፣ የራያ ቲዩብ፣ የቢቢሲ፣ የዊኪፒዲያ፣ የማህበረ ቅዱሳን..ዜናና መረጃዎችን በግብዐትነት መጠቀሜን ከምስጋና ጋር እገልጻለሁ። )
አዲስ ዘመን ነሃሴ 12/2011
ፍሬው አበበ