የአገራችን ኢኮኖሚ ሲነሳ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አብረውት የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ። እድገቱ፣ ሙስናው፣ ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍሉ፣ ግሽበቱ፣ ግብርናው፣ ድህነት፣ የስራ እድሉ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ ኢንቨስትመንቱ ወዘተ ሁሉ በዙሪያቸው ያሉና በዘርፉ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡
እነዚህ የሁልጊዜ የመወያያ ርእሰ-ጉዳይ ይሁኑ እንጂ ሁለት ጉዳዮች ግን ጎልተው መውጣታቸው አልቀረም። እድገት እና ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል።
ዛሬ በጥቅል የምናነሳውና የዚህ ፅሁፍ ትኩረት የሆነው አቢይ ጉዳይ የህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፤ በተለይም የሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ጉዳይ ሲሆን ዘርፉን በቀዳሚነት ከሚመራውና ሀላፊነት ካለበት ተቋም ያገኘነው መረጃ ዋቢያችን ነው። በተለይም የሴቶች፤ ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አድነው አበራ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰጡት ማብራሪያና ያደረጉት ትብብር ለተጠቀምንባቸው መረጃዎች ትልቅ ድርሻን አበርክቷል።
የሴቶች፤ ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱ የ11 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የታቀዱ ግቦች እና አመለካከቾች፣ አንኳር አፈፃፀምን፣ በአፈፃፀም የታዩ ጥንካሬዎች እና ድክመቶችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን እና የተወሰዱ መፍትሄዎችን በዘረዘረበት የሪፖርት ሰነዱ እንዳስታወቀው ባሳለፍነው አመት በርካታ ስራዎች መስራቱን ገልጿል።
እንደ ሚኒስቴሩ ከሆነ እንደሌሎቹ ሁሉ በሴቶች፤ ህፃናት እና ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ስራዎች ተሰርተዋል። ከተሰሩት ስራዎች መካከልም 315ሺህ 593 በራስ አገዝ እና 174ሺህ 574 በህብረት ስራ ማህበራት፤ እንዲሁም 940ሺህ 893 በግብርና እና 354ሺህ 727 በገጠር ከግብርና ስራ ውጭ ባሉ የስራ መስኮች፤ በድምሩ 1ሚሊዮን 943ሺህ 540 ሴቶችን በኢኮኖሚው መስክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ፤ በተጨማሪም ለ5ሺህ 656 ሴቶች የመስሪያና የመሸጫ ቦታ በማዘጋጀት እንዲሁም ለ66ሺህ 517 ሴቶች የገበያ ትስስር የተፈጠርላቸው መሆኑ የሚጠቀሱ ናቸው።
ከነዚህም ሌላ ከተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጋራ በተቀረጹ የኢኮኖሚ ፕሮግራሞች 270 ሚሊዮን ብር ሀብት በማሰባሰብ 6ሺህ 809 ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ6ነጥብ4 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተመርቀው ስራ ላላገኙ 2ሺህ 409 ሴቶች 48ሚሊዮን 180ሺህ ብር የመነሻ ካፒታል ተለቆላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ፤ እንዲሁም በአማራ እና ሱማሌ ክልሎች ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገውን የ“RWEE” /በፆታ፣ በግብርናና በሃብት ፈጠራ ላይ የሚሰራው ዓለምአቀፍ ፕሮጀክት/ ለማስቀጠል በተሰራው ስራ 405ሺህ 310 ዶላር (11 ሚሊዮን 604ሺህ 025 ብር) በማስለቀቅ ፕሮጀክቱ እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል፡፡
ከስርዓተ-ፆታ እና አየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የ2ሺህ 400 ሴቶችን የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በኖርዌይ መንግስት የበጀት ድጋፍ እና በNEPAD አስተባባሪነት የሚተገበረውን የGCCASP ፕሮጀክት ተግባር ድርጅቶችን በመለየት እና ሁለተኛውን የአጋር አካላት ፎረም /Second round partnership platform/ በመካሄድ ለፕሮግራሙ 120ሺህ ዶላር በማስመደብ ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገባ መደረጉም የዚሁ በጀት አመት አፈፃፀም ነው፡፡
በሙከራ (pilot) ደረጃ ሁለት ክልሎች (ኦሮሚያ እና አፋር) ላይ ሁለት ሺህ ሴቶችን በማደራጀትና አዋጭ በሆኑ የስራ ዘርፎች በማሰማራት ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል።
የሴቶችን ቁጠባ ባህል በማዳበር እና በብድር አጠቃቀም ዙሪያ በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ 6ሚሊዮን 768ሺህ 136 ሴቶች ብር 4ቢሊዮን 251ሚሊዮን 635ሺህ 238 እንዲቆጥቡ፤ እንዲሁም 579ሺህ 721 ሴቶች 3ቢሊዮን 375ሚሊዮን 361ሺህ 610 ብር በረጅምና በአጭር ጊዜ የሚከፈል ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የማጎልበት ስራ መሰራቱን፤ 1ሚሊዮን 065ሺህ 572 ሴቶችን የተስማሚ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ከአቅራቢው አካል ጋር ትስስር በመፍጠር 339ሺህ 449 ሴቶችን የጊዜና ጉልበት ቆጣቢ ተስማሚ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ከሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ባለ ፈም ህፃናት በተለያዩ ዘርፎች መብታቸው እንዲከበርና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል። በዚሁ መሰረት በበጀት አመቱ ለ713ሺህ 812 ህጻናት በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ እና ክብካቤ፣ ለ17ሺህ 833 ህጻናት የመልሶ ማቀላቀል እና የማዋሃድ፣ 211ሺህ 238 የስፖንሰርሺፕ እድል፣ 7ሺህ 990 ህጻናት የአደራ ቤተሰብ አገልግሎት፣ 1ሺህ 551 ህጻናትን የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። እንዲሁም 501ሺህ 734 በፕሮጀክት በተገኘ ድጋፍ፤ 23ሺህ 808 የባህላዊ/ተቋጥሮ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ እንደተቻለ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም 111ሺህ 995 ህጻናት በመንግስት እና ከመንግስት ሰራተኞቸ መዋጮ፤ 26ሺህ 740 ህፃናት ለድንገተኛ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት፣ ምንም አይነት አማራጭ ያልተገኘላቸውን 3ሺህ 963 ህፃናት በተቋም እንዲደገፉ፣ 38ሺህ 476 ህፃናት የልዩ ድጋፍ ትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉም በዘገባው ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
የሴቶች፤ ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱ ከሴቶችና ህፃናት በተጨማሪ ወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የተለያዩ ስራዎችን ስለመስራቱ አስፍሯል።
ሚኒስቴሩ እንደሚለው የወጣቶችን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ታስቦ በተጣለው ግብ መሰረት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ከነዚህም መካከል በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በህብረት ስራ ማህበራት፣ በግብርና እና ከግብርና ስራ መስክ ውጭ ባሉ የስራ መስኮች በድምሩ 519ሺህ 098 ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ፤ ለ6ሺህ 225 ወጣቶች የመስሪያና የመሸጫ ቦታ በማዘጋጀት፤ እንዲሁም ለ9ሺህ 987 ወጣቶች የገበያ ትስስር በመፍጠር፤ 181ሺህ 031 ወጣቶች 154 ሚሊዮን 940ሺህ 615 ብር እንዲቆጥቡ፤ 18ሺህ 325 ወጣቶች ደግሞ 765ሚሊዮን 797ሺህ 573 ብር በረጅምና በአጭር ጊዜ የሚከ ፈል ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 13 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት በመንግስትና በህብረተሰቡ ሊወጣ የሚችል ከ4ቢሊዮን 770ሚሊዮን 718ሺህ ብር በላይ ወጪን ማዳን ተችሏል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች አማካኝነት 27ሺህ 409 (ወንድ 3ሺህ 043፤ ሴት 24ሺህ 366) ወጣቶች (በሀዋሳ 23ሺህ 710፣ በመቐለ 2ሺህ 056፣ በኮምቦልቻ 1ሺህ 641) የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በመስራት ላይ ይገኛሉ።
የሚኒስቴሩን የበጀት አፈፃፀም በተመለከተም በሪፖርቱ ተመልክቷል። የመደበኛ በጀት አፈፃፀም 87 በመቶ ሲሆን፤ ከተራድኦ የተገኘ የበጀት ድጋፍ አፈፃፀሙም 63 በመቶ መሆኑ ተገልጿል። ባለሙያዎች እንደሚሉት የዚህ አይነቱ የበጀት አፈፃፀም የሚበረታታ አይደለም። ተቋማት በጀትን በአግባቡ መጠቀም፤ ለዚህም ከበጀት ጋር የተጣጣመ እቅድ ማዘጋጀትና መስራት እንደሚገባ ይመክራሉ። ሌላው ቢቀር ከረድኤት ድርጅቶች የተገኘውን የበጀት ድጋፍ አሟጦ መጠቀምና ሌላ ዙር ድጋፍ የሚገኝበትን እድል ከወዲሁ ማመቻቸት (ብዙ ጊዜ የተደረገለትን ድጋፍ ተመላሽ ላደረገ ሌላ ድጋፍ ስለማያደርጉ) ብልህነት መሆኑንም ይመክራሉ።
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው የሴቶች፣ ወጣቶችና የህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ከሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አኳያ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ያመላክታል። በቂ ነው/አይደለም የሚለው ለባለሙያዎች የሚተው ሆኖ የተሰሩ ስራዎች ግን ምን ገፅታ እንዳላቸው፣ የተጠቀሱት የህብረተሰብ ክፍሎች ከኢኮኖሚ አኳያ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት ምን ይመስላል ከሚለው አኳያ ከአንባቢያን ጋር የተወሰኑ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ጥረት ተደርጓል። ይህም በተለይ መረጃን ለባለቤቱ፤ ማለትም ለህዝቡ ተደራሽ ከማድረግ አኳይ የሚኒስቴሩ ኮሚዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ላደረገልን ትብብር ሊመሰገን ይገባዋል።
በአጠቃላይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢኮኖሚ ጉዳይ የሁሉም ነገር ቁልፍ ነው። በመሆኑም ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት፣ የንግግርና ውይይት ርእሰ-ጉዳይ ሊሆን የግድ ነው። በተለይ እንደኛ አገር ከፍተኛ የስራ ፈላጊና የስራ እጥረት ባለበት ሁኔታ ስለ ኢኮኖሚ ደግሞ ደጋግሞ መስራት፣ ማሰራት፣ መነጋገር፣ መፍጠር፣ መመራመር የግድ ነው። ከሁሉም በላይ “ሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ” ሆኖ ሳለ ማሰብ አለመቻል፤ በተቋም ደረጃ አለመንቀሳቀስ አሁን ካለው ምናልባተም የወደፊት አደጋ የመሆን እድሉ ሰፊ የሆነውን የስራ አጥነት ችግር ከመቅረፍና ዜጎችን፤ በተለይም ወጣቶችን በኢኮኖሚው ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል እንላለን።
ይህንን የሚያጠናክርልን ደግሞ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የክልሎችንና የፌዴራል የስራ ኃላፊዎችን ሰብስበው በሚቀጥለው አመት ለማሳካት የታቀደውን ከሶስት ሚሊዮን በላይ የስራ እድል በተመለከተ ሲያወያዩ ያሉትን ጠቅሰን እንውጣ። “የቀጣዩ አመት ዋንኛው የኢኮኖሚ እድገት መለኪያ የስራ እድል ፈጠራ ይሆናል። ማንኛውም ተቋም የሚመዘነውም በዚህ አፈፃፀሙ ነው።”
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13/2011
ግርማ መንግሥቴ