ከአንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደመሆኑ ራሱን በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም፣ በአፍሪካም ታላቅና በዓለምም ታዋቂ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ በመማር ማስተማር ሥራው እያከናወነ ባለው ተግባርም እስካሁን ካፈራቸው በርካታ ሙያተኞች ባሻገር በአሁኑ ወቅት 42ሺ500 ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃግብሮች በማስተማር ላይ ነው፡፡ በጥናትና ምርምር ሥራዎቹም ሆነ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶቹም አንቱታን ማትረፍ ችሏል፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው ጅማ ዩኒቨርሲቲ፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን አንድ ታላቅ ሥነሥርዓት አስተናግዶ ነበር፡፡ ዝግጅቱም በአንድ በኩል ለዓመታት ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ያስመረቀበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለመማር ማስተማር፣ ለምርምርና ለማህበራዊ አገልግሎት ሥራ አሳላጭ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በሦስት አገራት መሪዎች ማለትም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ በሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር እና በጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኦማር ጌሌ አማካኝነት ያስመረቀበት ነበር፡፡
በዚህ ሥነሥርዓት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አዱላ በቀለ እንዳሉት፤ የአገሪቱን የትምህርት መስክ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት በተነደፈው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ውይይት በማድረግ የ2011ዓ.ም የትምህርት ዘመንን የጀመረው ዩኒቨርሲቲው፤ በ2011 የትምህርት ዘመን የአካዳሚክ የቅበላ አቅሙን በማሳደግ 42ሺ500 ተማሪዎችን በ70 የቅድመ ምርቃ፣ በ160 የሁለተኛ ዲግሪ እና በ40 የሦስተኛ(ፒ.ኤች) ዲግሪ መርሃ ግብሮች በጠቅላላው በ270 ፕሮግራሞች በመደበኛ፣ በተከታታይና በርቀት መርሃ ግብሮች እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ የዕለቱ ምሩቃንም ከጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት፣ ከግብርናና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፣ ከተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ፣ ከሶሻል ሳይንስና ሂዩናሚቲስ ኮሌጅ እና ከሕግና አስተዳደር ኮሌጅ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን በብቃት ያጠናቀቁ ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር አዱላ ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲው ትምህርትን በጥራት ለማስተላለፍ እያደረገ ባለው ጥረትና የልህቀት ማዕከል በሆነባቸው በማስተማር፣ ሥልጠናና በፋርማሲቲካል ሳይንስ ዘርፍ በብቃት ከመሥራቱም ባሻገር የተጣለበትን አገራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንጻር ከተለያዩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የግልና የመንግሥት ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም በመማር ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ ፕሮጀክቶችን በመደገፍና ወደ ተግባር በመቀየር አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ በሚያከናውናቸው የጥናትና ምርምር ተግባራም የአካባቢውን፣ የክልሉንና የአገሪቱን ህዝቦች መሰረታዊ ችግሮች የሚቀርፉ ምርምሮችን በማካሄድና ህብረተሰቡን በማሳተፍ አበረታች ውጤት እየተመዘገቡ ሲሆን፤ ማህበራዊ ኃላፊነቱንም ከመወጣት አንጻር በአገራዊና አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ካስመዘገባቸው አመርቂ ውጤቶች አንዱና ዋነኛው በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዓመታዊ የዕቅድና ግምገማ ሶፍትዌር አዘጋጅቶ በሥራ ላይ በማዋሉ ዕቅድና ሪፖርትን ከማንኛውም የወረቀት አሰራር አላቆ በሁሉም የሥራ ክፍሎች ወደ ኦንላይን ሥርዓት መግባት ችሏል፡፡ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትም በዚሁ መሰረት ተካሂዶ ውጤታማነቱ ታይቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎች በባለሙያዎች አማካኝነት ከመካሄዳ ቸውም ባሻገር፤ ዩኒቨርሲቲው ለማህበረሰቡ እየሰጣቸው የሚገኙ ግልጋሎቶችን ለመገምገም በሚያስችል መልኩ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በተደረገ ውይይት ሊቀጥሉ የሚገባቸው ጠንካራ ጎኖችና መታረም የሚገባቸው ጉድለቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል፡፡ የዕለቱ ምረቃ ሥነ ሥርዓትም ለየት የሚያደርገው ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ጥቂት ዓመታት ሲያስገነባቸው የነበሩ ታላላቅ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ማስመረቁ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል፣ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ የሲቪክ ማዕከል፣ የኮንፍረንስ ማዕከልና የስፖርት አካዳሚ ይገኙበታል፡፡
በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የህዝቡን እድገት ለማረጋገጥና በጅምር ያሉ አገራዊ አጀንዳዎችን ለማስፈጸም ዩኒቨርሲቲያችን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በትጋት የሚንቀሳቀስ ይሆናል ያሉት ዶክተር አዱላ፤ የአገሪቱ የወደፊት ዕጣ በአብዛኛው የሚወሰነውም ዛሬ በተመረቁት ወጣት ምሑራን ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ አገሪቱም ለእነዚሁ ወጣት ምሩቃን እድሎችን እያመቻቸች መሆኑን በመጠቆምም፤ ምሩቃን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ልምድና እውቀት ለአገርና ህዝባቸው ጥቅምና ለውጥ ሊያውሉት ስለሚገባ በዚሁ ልክ መዘጋጀትና መሥራት ይጠበቅባ ቸዋል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት በርካታ ዓመታት በማያቋርጥ የእድገት ሂደት ውስጥ እየተጓዘ የሚገኝ ሲሆን፤ በአገሪቱ መሪ፣ በአፍሪካም ታላቅና በዓለምም የታወቀ ዩኒቨርሲቲ የመሆን ራዕይ ሰንቆ የሚንቀሳቀስና ይሄንንም ራዕይ ለማሳካት በትጋት የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ በዕለቱም ከተማሪዎች ምረቃ ጎን ለጎን ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ጥቂት ዓመታት ሲያስገነባቸው የቆዩ ታላላቅ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ማስመረቁ የዚሁ ተግባሩ ማሳያ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው እያከናወናቸው ከሚገኙ አንኳር ተግባራት አንዱ ተቋሙን ደረጃውን በጠበቁ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ማደራጀት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማትም የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ፣ የምርምር ሥራዎችን ለማስፋፋትና ከምንም በላይ ጥራቱን የጠበቀ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ቁልፍ ሚና ከመጫወታቸውም በላይ፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአገልግሎት መዳረሻ ሆነው ማገልገል በሚያስችል የጥራትና የስፋት ደረጃ ታንጸው የተዘጋጁ ናቸው፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ በዚህ ደረጃ ተገንብተው በዕለቱ ከተመረቁት ተቋማት መካከል ደረጃውን የጠበቀና እስከ 800 የሚደርሱ ታካሚዎችን አስተኝቶ ማከም የሚያስችልና በዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች የተደራጀ ብሎም በተለያዩ የሕክምና መስኮች አገልግሎት መስጠት የሚችል ሆስፒታል አንዱ ነው፡፡ እስከ 7ሺ500 ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለውና የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማድረግ የሚያስችለው የሲቪክ ማዕከል፣ እስከ 4ሺ500 ተሳታፊዎችን የሚይዝና ለጅማ ከተማና አካባቢዋ የኮንፍረንስ ማዕከል በመሆን የሚያገለግል፤ እስከ 1ሺ500 ሰዎችን መያዝ የሚችል መመገቢያ አዳራሽ ያለውና የድምጽ ሲስተም ያላቸው ሌሎች አነስተኛ አዳራሾች ያሉት የኮንፍረንስ ማዕከልም ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በዓይነቱ ለየት ያለና እስከ 40ሺ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችል ስታዲዮምና ሌሎችም የስፖርት ውድድር ሜዳዎች ማለትም የቅርጫት ኳስ፣ የመረብ ኳስ፣ የሜዳ ቴኒስ፣ ዋና እና ሌሎችም የስፖርት አይነቶችን ያካተተ የስፖርት አካዳሚ ግንባታም አጠናቅቆ ወደሥራ ለማስገባት ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡ የእነዚህ የአገልግሎትና የትምህርት መስጫ ማዕከላት ተጠናቅቀው ወደሥራ መግባታቸውም ለዩኒቨርሲቲው ሁለንተናዊ የሥራ እንቅስቃሴና ራዕይ መሳካት የጎላ ሚና ይኖራቸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ተወዳዳሪና መሪ ተቋምነቱን ለማስቀጠል እያከናወናቸው የሚገኙ የልማትና የእድገት ሥራዎችን ከዚህ በበለጠ በማጠናከር አገሪቱ የጣለችበትን ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ የማህበረሰብ ችግር ፈቺ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ማከናወንና ማህበረሰቡን የማገልገል ተልዕኮ ለመወጣት በሚያስችለው የተሻለ ቅርጽና ቁመና ላይ ለመገኘት ያልተቆጠበ ጥረት እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምሩቃንም አገሪቱ የወደፊት ተስፋ በእናንተ ድካምና ጥረት ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመገንዘብ አገር ከእናንተ የምትጠብቀውን ሁሉ በማበርከት ህዝባችሁን በንቃትና በታማኝነት በማገልገል የራሳችሁን፣ የቤተሰባችሁንና የማህበረሰባችሁን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በርትታችሁ መሥራት ይኖርባችኋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትሯ ዶከተር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው እንዳሉት፤ ተማሪዎች ከብዙ ልፋት፣ ውጣውረድና ችግር በኋላ ለዚህ ስኬት መድረሳቸው ለህልማቸው መሳካት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ መልኩ ችግሮችን በጽናት ተቋቁመው ለእዚህ ውጤት የበቁ የእለቱ ተመራቂዎችም ሙያቸው ታላቅ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ አንድም በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ባገኙት እውቀት፤ አንድም ከዩኒቨርሲቲው በቀሰሙት ልምድና ተሞክሮ ታግዘው በተሰማሩበት መስክና ቦታ ሁሉ ከራስ በፊት ለአገርና ህዝብ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥትም በዚሁ አግባብ እየሠራ ሲሆን፤ በተለይ ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ አኳያ ውጤታማ ሥራ ካከናወነበት የትምህርት ሽፋንን ከማሳደግ ተግባሩ በተጓዳኝ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርምርና የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደሥራ ገብቷል፡፡ በዚህ መሰረት ዩኒቨርሲቲዎች የሰው ኃይል ማፍሪያ ብቻ ሳይሆኑ በሳይንሳዊ ጥናት ታግዘው የህብረተሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚሠራ ሲሆን፤ ከዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ ተማሪዎችም በዚሁ አግባብ በህዝባዊ ወገንተኝነትና ኃላፊነት እንዲሠሩ ይጠበቃል፡፡
የዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎችም ደስታቸውን ከመግለጽ ባለፈ፣ በሙያቸው አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ለእውቀት፣ ለምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የሚሰጠው ትኩረት አንጋፋነቱን የበለጠ የሚያሳድግለት ብቻ ሳይሆን ለእነርሱም ትልቅ ልምድና ግብዓት ሆኖ የሚያገለግላቸው ነው፡፡ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል የሜዲካል ተመራቂዋ ዶክተር ሊሊ ደመቀ፤ የህክምና ትምህርት ረዥም ጉዞን ታልፎ ለውጤት የሚበቃበት እንደመሆኑና ይሄን ጉዞ አልፎ ለዚህ ቀን መድረስ እጅጉን የሚያስደስት መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ይሁን እንጂ ይሄን ረዥም ጉዞ በትጋት ጨርሶ ለውጤት መብቃት ብቻውን ደስታን ሙሉ እንደሚያደርግ ትናገራለች፡፡ በመሆኑም አገርና ህዝብ ከሙያው የሚጠብቁብኝን ተግባርና ኃላፊነት በትጋትና ሙያዊ ሥነምግባሩን ተከትዬ ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ፤ በዛው ልክም እሠራለሁ ስትልም የቀጣይ እቅዷን ታብራራለች፡፡
እንደ ዶክተር ሊሊ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ህክምና ያልተዳረሰባቸው ገጠራማ ቦታዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ደግሞ የእናቶች ሞት በጣም ትልቅ ነው፡፡ እናም በእነዚህ ቦታዎች ላይ ሄዳ መሥራትና የድርሻዋን መወጣት ትፈልጋለች፡፡ በዚህ መልኩ መሥራትና በገጠር ያሉ እናቶችን መርዳት ከቻለች ደግሞ ደስታዋ ሙሉ ይሆናል፡፡ ሌሎች ተማሪዎችም በዚህ መልኩ ሠርተው ለውጤት መብቃት እንዲችሉ የመጡበትን ማህበረሰብ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡበትን ዓላማ መዘንጋትም የለባቸውም፡፡ ይህ ሲሆን ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን አገር ከእነርሱ የምትጠብቀውን ማበርከት ይችላሉ፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲም የጀመረውን ጉዞ ማስቀጠልና የበለጠ ውጤታማ የመሆን ሂደቱን ማፋጠን ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8.2011
ወንድወሰን ሽመልስ