
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በጎ ፈቃደኞች የማጠናከሪያ ትምህርትና በስፖርት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በስነ ጥበብ ዙሪያ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ከ98ሺ በላይ ለሆኑ ተማሪዎች እየሰጡ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮ የበጎ ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ትዛዙ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በ114 ትምህርት ቤቶች ከ5ኛ ክፍል እስከ 10 ክፍል ላሉ 62ሺ 700 ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል። እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በኪነ ጥበብ፣ በስፖርትና ኢትዮጵያዊነት ዙሪያም ለ36ሺ ተማሪዎች ለሁለት ወራት ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ስለ ኢትዮጵያዊነት የእንግዳ አቀባበል ስነምግባር፣ አብሮ የመኖር እሴቶች ፣የተለያዩ የስፖርት አይነቶች፣ ስነ ጥበብና በማጠናከሪያ ትምህርት ዙሪያ ከሶስት ሺ 200 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዘንድሮው ክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው እያስተማሩና እያሰለጠኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያ ታሪክና ባህላዊ እሴቶችን የሚያትቱ መፅሀፎችን ከማንበብ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠምዶ የሚውል መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተው ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚሰጠው ስልጠናም ወጣቱ በስሜት የሚነዳ ሳይሆን ምክንያታዊ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚረዳ አመልክተዋል።
የበጎ ፈቃድ ትምህርትና ስልጠና ከሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች መካከልም ዳግማዊ ምኒልክ፣ ጥቁር አንበሳ፣ ኮከበ ጽብሀ እንደሚገኙባቸው ጠቅሰዋል። ትምህርቱም እስከ ነሀሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሰጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚዘጋጅ የማጠቃለያ መርሀ ግብር የእውቅና ሰርተፍኬት የሚሰጣቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አክሊሉ የትምህርትና የስልጠናው ዋና አላማም ተማሪዎች የዕረፍት ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ በማሰብና የተሻለ ዝግጅት በሚያስፈልጋቸው የትምህርት መስኮች በቂ እውቀት እንዲቀስሙ ለማስቻል ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የክረምት ወቅቶች የማጠናከሪያ ትምህርት ብቻ በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ሲሰጥ መቆየቱን አውስተው የዘንድሮው ግን ብዛት ያላቸው በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉበት መሆኑና የሚሰጡት ትምህርቶችና ስልጠናዎች የተለያዩ መሆናቸው የተለየ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል። ትምህርትና ስልጠናውም ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 6፡30 ሰዓት ድረስ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 6/2011
ጌትነት ምህረቴ