በኢትዮጵያ ገጸ ምድር መሃል ላይ የሚገኝ ታሪካዊ ሥፍራ ነው ሸዋ። ለብዙ መቶ ዓመታት በሉዐላዊነት በራሱ መሪዎች ሲተዳደር የኖረ የኢትዮጵያ አካል ሲሆን፣ ርዕሰ ከተማው በሰሜን ሸዋ ውስጥ በየጊዜው በተለያዩ ሥፍራዎች ሲፈራረቅ ቆይቶ ባለፉት ከመቶ በላይ ዓመታት ግን አዲስ አበባ ሆናለች። ደብረ ብርሃን፤ አንኮበር፤ አንጾኪያ፤ ልቼ እና እንጦጦ በተለያዩ ጊዜያት የሸዋ ርዕሰ ከተማዎች ነበሩ።
የሸዋ ገጸ ምድር እምብርት በአሁኗ ኢትዮጵያ መሃል የሚገኙት ተራራዎች ናቸው። በአህመድ ግራኝ ወረራ ጊዜ የባሌ ክፍለ ሀገር ከተወሰደ በኋላ የሸዋ ድንበር የኢትዮጵያ የደቡብ ምሥራቅ ድንበር ነበር። የግዛቱ ተራራማነት የተፈጥሮ መከላከያ በመሆን ከውጭ ወረራ ለመላ አገሪቱ ደጀን የነበረና በፍትህ የአስተዳደር ዝናውም ለሌላ የኢትዮጵያ ዜጋዎች መጠጊያና መሸሸጊያም ነ
አንዳንዴም በወራሪ ሕዝቦች ምክንያት ከቀሪው የኢትዮጵያ ግዛቶች ተግንጥሎም አብዛኛው የሰሜን ሸዋ ግዛቶች፣ ማለትም ሰላሌ(ግራሪያ)፤ መርሃቤቴ፤ ደራ፤ መንዝ፤ ተጉለት፤ ይፋት፤ ምንጃር እና ቡልጋ ሕዝብ ክርስቲያን አማራ እና ኦሮሞዎች ናቸው። ደቡብ እና ምሥራቅ ሸዋ ግን አብዛኛው የኦሮሞ ብሔር እና የእስልምን ኃይማኖት ተከታዮች ናቸው። በሰሜን ሸዋ ብዙ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ይገኛሉ። ከነዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው፣ አቡነ ተክለ ኃይማኖት በሰላሌ ወረዳ የመሠረቱት ታዋቂው የደብረ ሊባኖስ ገዳም ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የቆየ ታሪክ ካላቸው አካባቢዎች አንዱ የሰሜን ሸዋ ዞን ነው፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን በሁለት የከተማ አስተዳደሮችና በሃያ ሁለት ወረዳዎች ተከፋፍሎ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ የሚኖርበት ሲሆን ውርጭ፣ ቆላ፣ ደጋና ወይና ደጋ የአየር ንብረቶችን አካቶ ይዟል። አዋሳኞቹም በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ክልል፣ በሰሜን ምስራቅ አፋር፣ በሰሜን ደቡብ ወሎና ኦሮሚያ ዞኖች ናቸው።
ዞኑ ከቅድመ ታሪክ ጀምሮ እስከ ታሪክ ዘመን ያሉ አሻራዎች የሚገኙበት ስለመሆኑ የሥነ ቅርስ ግኝቶች ይጠቁማሉ። ከ 1270 ዓ.ም እስከ 1527 ዓ.ም ድረስ «የሰሎሞን ስርወ መንግሥት» የመራሄ መንግሥቱ ዋና ማዕከል እንደነበረም የተለያዩ የታሪክ ምንጮች ይገልፃሉ።
የሰሜን ሸዋ ምሥራቃዊ ክፍል ዋነኛው የእስልምና ስርወ መንግሥት መቀመጫ ከመሆኑ ባሻገር ከ12ኛው እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የይፋት ስርወ መንግሥት የማዕከላዊ መንግሥቱ ተቀናቃኝ ኃይል እስከመሆን ደርሶ ነበር። በመጨረሻም ከሌሎች ታሪካዊ ሁኔታዎች ጋር ተደማምሮ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስልምናው ኃይል በግራኝ አህመድ መሪነት በማየሉና በማሸነፉ ማዕከላዊ መንግሥቱ ከሸዋ ወደ ጎንደር ለመዛወር ተገዷል።
በ1996 ዓ.ም በመንዝ የተንቀሳቀሰው የሸዋ ስርወ መንግሥት እንደገና ማዕከላዊ መንግሥቱ ወደ ሸዋ በመመለሱ በዘመናዊ ታሪካችን ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በእነዚህ የታሪክ ሂደቶችም ሰሜን ሸዋ የበርካታ ጥንታዊ የታሪክና የባህል ነፀብራቅ የሆኑ አሻራዎች ባለቤት ሊሆን ችሏል።
በተለምዶ የሙሽራ ድንጋዮች በመባል የሚታወቁት ትክል ድንጋዮች ከአጣዬ ከተማ በምዕራብ በኩል 21 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ልዩ ሥፍራው ገድሎ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይገኛሉ። ገድሎ ሜዳ ደጃዝማች ምኒልክ በ1875 ዓ.ም ከመቅደላ እስር ቤት አምልጠው ሲሄዱ በምትካቸው በአጼ ቴዎድሮስ ተሹመው ከነበሩት አቶ በዛብህ ጋር ጦርነት ያደረጉበት ሥፍራ ነው። ጦርነቱም በአፄ ምኒልክ አሸናፊነት ተጠናቋል።
“ሙሽራ ድንጋዮች” በገድሎ ሜዳ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ የሚገኙ የሰው ቅርጽ ያላቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው። ትክል ድንጋዮቹ ቆመውና ካሉበት ሳይነሱ የሚገኙ 21 በሥፍራው ወድቀው የሚገኙ 2 ከሥፍራው ተነስተው ገበሬዎች ለእርሻ ድንበር መለያ የተጠቀሙባቸው 44 ናቸው።
ስለስያሜው እና አመጣጡ ግለጽ የሆነ የተጻፈ ሰነድ ባይኖርም በህብረተሰቡ ዘንድ ሶስት መላ ምቶች አሉ፡፡ አንደኛው የሙሽራ ድንጋዮች ስያሜቸውን ያገኙበት በአንድ ወቅት በመንገድ ላይ እያሉ ሙሽሮችና ሠርገኞች ባደረጉት ከልክ ያለፈ ጭፈራ እግዚአብሔርን በማሳዘናቸው ተረግመው ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ወደ ድንጋይነት ተቀይረው በዚያው ቀሩ በሚል የሚነገር ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የሙሽራ ድንጋዮች ታሪካዊ አመጣጥ ከላይ በተገለጸው አኳኋን የተለየ ጥንታዊ ሰዎች ለአንድ ዓላማ ያቆሟቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው ተብሎ ይታመናል።
ሶስተኛው የትክል ድንጋይ ቃላዊ መረጃ ደግሞ ምናልባትም ከአክሱም ዘመን በፊት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ የእደ ጥበብ ውጤት ነው የሚል ግምት ነው። የሙሽራ ድንጋዮች በአብዛኛው ከደቡብ ኢትዮጵያ የጥያ ትክል ድንጋዮች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። እነዚህ ምስጢርን ያዘሉ የታሪካችን አሻራዎች ለጥናትና ምርምር የሚጋብዙና ለተመልካች ደግሞ የሚያዝናኑ ናቸው። ፅሑፉን ለማዘጋጀት አማራ ብሔራዊ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ እንዲሁም ዊኪፒዲያን ተጠቀምን ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 /2011
አብርሃም ተወልደ