‹‹በሁሉም አቅጣጫ ያሉትን የሃገራችንን ህዝቦች እንዳይበታተኑ ያስተሳሰሩ፤ እንዳይለያዩ ያጣመሩ፣ እንዳይፈርሱ ያማገሩ በርካታና ጠንካራ ማጎች አገራችን ሁሉም ጫፎች በክብር እና በፍቅር እዚም እዚያም አሉ። ህዝቦቻችን በጋብቻ ተዛምደው፣ በማንነት ተዋህደው የኖሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው››ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐብይ አህመድ ባለፈው ዓመት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የሚገኙት የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች የሚያከብሩትን ‹ ‹ የ አ ሸ ን ድ ዬ ፣ ሶ ለ ል ፣ ሻ ደ ይ › › እ ን ዲ ሁ ም ‹‹አሸንዳ›› የልጅ አገረዶች በዓል አስመልክቶ ይህን ብለው ነበር ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት ሁለቱ የሰሜኑ የአገሪቷ ህዝቦች ከወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች በዘለለ የተሳሰረና የተጋመደ ማንነታቸውን የሚመሰክሩ የጋራ እሴት እና ባህል እንዳላቸው ለማሳየት ነው። ለበርካታ ሺ ዓመታት ይህ በዓል በህዝቦቹ መሀል ሲከበር የቆየ እና አሁንም ድረስ ሳይበረዝ የቀጠለ ነው።
ለምሳሌ ያህል በአማራ ክልል በሰቆጣ የሚከበረው ሻደይ ይህን አይነት አከባበር ይይዛል። ከዚህ ቀደም በሶስት የእድሜ እርከን ተከፍሎ ነበር። ከ10 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህፃናት፤ ከ10 እስከ 15 ዓመትና ከ15 ዓመት በላይ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ለህፃናት እንደተተወ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከ15 ዓመት በላይ የሆኑት ድኮት (የእጅ አምባር)፣ ሁለት አይነት መስቀል፣ በአንገታቸው ድሪ፣ የብር አልቦ እግራቸው ላይ ያጠልቃሉ፤ በጥልፍ ቀሚስ ተሽቆጥቁጠው ይሄዳሉ። ከ15 ዓመት በታች የሆኑት ከብር የተሰራ ድሪ፤ ትልልቅ ክብ ቀለበት ጆሮ ጌጥ፤ ከ10 ዓመት በታች የሆኑት ቁንጮና ጋሜ (መሀል ፀጉራቸው ተላጭቶ ዳርዳሩን ያደገ) የፀጉር ቁርጥ ይቆረጣሉ።
‹‹አስገባኝ በረኛ፣ አስገባኝ ከልካይ፤ እመቤቴን ላይ›› በማለት ማንጎራጎር ሲጀምሩ በሩ ይከፈትላቸዋል ‹‹ይሄ የማን አዳራሽ የጌታየ የድርብ ለባሽ፤ ይሄ የማን ደጅ የእመቤቴ የቀጭን ለባሽ›› በማለት ዘፈናቸውን ይቀጥላሉ። በእለቱ ከሚዘፈኑ ዘፈኖች መካከል በሰቆጣ ከተማ ታዋቂው ዘፈን ‹‹አሽከር አበባየ አሽከር ይሙት፣ ይሙት ይላሉ የኔታ አሽከር አይደለም ወይ የሚሆነው ጌታ›› እያሉ በስርቅርቅ ድምፃቸው ያዜማሉ። በር ተከፍቶላቸው ከገቡ በኋላ የቤቱን ባለቤቶች ማወደስ ይቀጥላሉ።
ከውደሳዎቹም መካከል ‹‹ከፈረስ አፍንጫ ይወጣል ትንኝ፤ እሰይ የኔ ጌታ ጤና ይስጥልኝ፤ ምድር ጭሬ፣ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ እሰይ የኔ እመቤት ድልድል ወይዘሮ›› የሚለው ይገኝበታል። ይቀጥሉናም ‹‹ስለለየ፣ ስለለየ …. እሰይ የኔ እመቤት የፈተለችው ሸማኔ ታጥቶ ማርያም ሰራችው›› በማለት ያንጎራጉራሉ። ዘፍነው ሽልማት ካልተሰጣቸው ወይ ከዘገየ ‹‹አንቱን አይደለም የማወሳሳው፤ ቀና ብለው እዩኝ›› በማለት በነገር ሸንቆጥ ያደርጓቸዋል። በዚያን ቀን ያው ሽልማት መስጠት ግድ ነው፤ እሱን ተቀብለው ‹‹አበባየ ነሽ አበባየ ጉዳይ ሰመረች በአንች ላይ›› እያሉ ወደ ሌላ መንደር ይሄዳሉ።
ከላይ ለመመልከት እንደሞከርነው ይህ ክብረ በዓል ጨዋታ፣ፍቅር፣የአዲስ ዓመት መውጫ እንዲሁም ፍፁም ያልተበረዘ የዘመናት ባህልን የሚያመለክት ይዘት ያለው ነው። በዋነኝነት ግን ሴቶች ያለምንም ተፅዕኖ እና ያለማንም ከልካይነት የሚጫወቱበት፤ እናቶች ደግሞ ባህላዊ አልባሳት እና ጌጣጌጦችን በመግዛት ልጆቻቸውን በደስታ በዓሉን እንዲያሳልፉ የሚረዱበት ልዩ ስነስርዓት ነው።
ይህን ድንቅ የአሸንዳ አሸንድዬ ሻደይና ሶለል በዓላትን አዲስ አበባ በድምቀት ለማክበር መሰናዶዋን እያጠናቀቀች መሆኑን የከተማዋ አስተዳደሩ አስታውቋል። በየዓመቱ በተለይም አማራና በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን ልዩ ልዩ ባህላዊ ትውፊቶች የሚያጎሉት የሻደይና አሽንዳ በዓላት በአዲስ አበባ ደረጃ በተናጠልና በጋራ እንደሚከበሩ ነው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ያስታወቀው። እነዚህን በዓላት በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መዲና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በድምቀትና በልዩ ድባብ ለማክበር የሚያስችል መርሃግብር መውጣቱን ገልጿል።
በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የሚከበረውን በዓል የአፍሪካ መቀመጫ እና የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በልዩ ድምቀት ለማክበር የተፈለገበትን ዋነኛ ቁም ነገር ለማወቅ የአስተዳደሩን የባህል፣ የኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ አቅንተናል፡፡ በቢሮው የኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሃት የዝግጅቱን አላማ እና መርሃ ግብር ምን እንደሚመስል እንዲህ ሲሉ ነግረውናል።
‹‹የሰሜን ኢትዮጵያ ልጅ አገረዶች ጨዋታ አሸንድዬ፣ሻደይ፣ሶለል እንዲሁም አሸንዳ ከአማራ ጀምሮ እስከ ትግራይ ድረስ የሚያካልል እና ለብዙ ሺ ዓመታት ሲከበር የቆየ ነው›› ያሉት ምክትል ቢሮ ሃላፊው፤ በትንሹም ቢሆን ሃይማኖታዊ መሰረት ያለው ክብረ በዓል መሆኑን ይገልፃሉ። ልጅ አገረዶች በነፃነት የቤተሰብ ጫና ሳያድርባቸው ለሳምንታት በውጪ ሆነው የሚያከብሩት መሆኑንም ያስረዳሉ። በባህላዊ አገላለፅ የተለያየ ቢመስሉም በአማራ እና በትግራይ የሚደረጉት እንቅስቃሴ ትርጓሜ ተመሳሳይነት እንዳለውም ያብራራሉ። በተለይ በሁለቱም ህዝቦች ውስጥ የሚገኙት እና የባህሉ ተሳታፊዎች አሸንዳ የሚባለውን ቄጤማ በሚያሸርጡበት ወቅት አንድ አይነት ይዘት እንዳለው ይናገራሉ። በተለይ ሁሉም ይህን ክብረ በዓል ሀይማኖታዊ መሰረት የሚያደርጉት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት መሰረት የቅድስት ድንግል ማሪያም ትንሳኤን መነሻ በማድረግ ነው።
ምክትል ቢሮ ሃላፊው ስለአከባበሩ ሲያስረዱ ‹‹አዲስ አበባ ከሁሉም አቅጣጫ ዜጎች ተሰባስበው የሚኖሩባት የተለያዩ ባህሎች የሚገኙባት እና የሚከበርባት ከተማ በመሆኗ እና አሸንድዬ፣ሶለል፣ሻደይ እንዲሁም አሸንዳም በተመሳሳይ መንገድ ለማክበር ለመጀመሪያ ጊዜ ዝግጅት ተደርጓል›› ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ ወጣቶች ይህን ክብረ በዓል ለማወቅ እንዲችሉ እድሉን ለመፍጠር ጭምር መሆኑን ያስረዳሉ።
አቶ ሰርፀ አዲስ አበባ ብዙ ባህሎችን አቅልጣ አንድ ልዩ ቀለም የፈጠረች ከተማ እንደሆነች ይናገራሉ። ከዚህ ባለፈ ልክ እንደ ሜክሲኮ፣ብራዚል እና ኩባ በርካታ ባህሎችን ወደ ዋና ከተማ በማምጣት የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ ፈጥረዋል። ይህም አገራቸውን በዓለም መድረክ ላይ ለማስተዋወቅ ረድቷቸዋል። ይህን ባህላዊ ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ ለማክበር የታሰበበት ዋነኛ አላማም እንደተጠቀሱት አገራት ተመሳሳይ ስኬት የማስመዝገብ ግብ የያዘ መሆኑን ተናግረዋል። አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም ይህን ትልሙን ለማሳካት የሀረሪ የሻወሊ ኢድ እንዲሁም የአዲስ ዓመት መለወጫ የሆነውን የሲዳማ ጨምባላላ ክብረ በዓላትን ማሰናዳቱን ገልፀዋል።
እንደ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሸንድዬ፣ሻደይ፣ሶለል እና አሸንዳ ባህላዊ የልጅ አገረዶች ስነ ስርአትን ‹‹የሰሜን ኢትዮጵያ የልጅ አገረዶች ክብረ በዓል›› ተብሎ ነሐሴ 19፣26 እና 30 በመዲናዋ በልዩ ድምቀት ያከብረዋል። በመጀመሪያው ቀን በአዲስ አበባ ያሉ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ነዋሪ የሆኑ የአማራ ብሄር ተወላጆች በሚሊኒየም አዳራሽ በደመቀ ዝግጅት የልጅ አገረዶቹን ክብረ በዓል ያከብሩታል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ የአሸንዳን በዓል የትግራይ ተወላጆች በዚያው በሚሊኒየም አዳራሽ የሚያከብሩት ይሆናል። በመጨረሻው ዝግጅት የሁለቱን ባህላዊ ክብረ በዓል ውህደት የሚያሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ በአዳራሹ ያከናውናል።
‹‹ይህ ባህላዊ ስነ ስርአት በከተማዋ በድምቀት መከበሩ ለህዝቦች እርስ በርስ መገነዛዘብ እና የቱሪዝም መዳረሻ ከመፍጠር አኳያ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል›› የሚሉት የቢሮው የኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ በተለይ ህዝቦች ከሚያለያያቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው በርካታ እሴቶች እንዳሏቸው የሚታይበት እና የሚማሩበት እንደሚሆን ይናገራሉ። በፖለቲካ ላይ የሚታዩ የተለያዩ ልዩነቶች ቢኖሩም በባህሉ ረገድ ግን ህዝቦች አንድ መሆናቸውን የሚያሳይ ዘርፈ ብዙ እሴቶች መኖራቸውንም ያስረዳሉ። በየትኛውም አግባብ ህዝቡ በተለይ ወጣቶች እና ታዳጊዎች በጋራ እሴቶቻቸው እና ባህሎቻቸው ሲግባቡና ሲጫወቱ ይስተዋላሉ እንጂ የፖለቲካ ቦርሳ ተሸክመው ልዩነት የሚፈጥር ጉዳይ ውስጥ እንደማይገኙም ይገልፃሉ። በአዲስ አበባ የሚከበረው ክብረ በዓልም ይህንኑ የአንድነት እሴት የሚያጎላ መሆኑን ይገልፃሉ።
አቶ ሰርፀ ቢሯቸው ባህላዊ ክብረ በዓሉን ሲያደርግ የየትኛውንም የፖለቲካ አጀንዳ እንደማ ያንፀባርቅ እና ፍፁም ገለልተኛ በሆነ መንገድ ባህሉ ላይ ብቻ እንደሚያተኩር አስገንዝበዋል። እኩይ አላማ ያላቸው ሰዎችም ይህን ከዚህ መሰል ድርጊት ራሳቸውን ማራቅ እንዳለባቸው መክረዋል። በተለይ የሰሜን ኢትዮጵያ የልጅ አገረዶች ባህልን ንፅህና ለማህበረሰቡ መተው እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት። የጥበብ፣ የቱሪዝም እና ባህል ጉዳዮች ከፖለቲካ ነፃና የህዝብ ብቻ መሆናቸውን አስምረውበታል።
‹‹የአሸንድዬ፣ ሶለል፣ ሻደይ›› እንዲሁም ‹‹አሸንዳ›› የልጅ አገረዶች ባህላዊ ክብረ በዓል በዩኒስኮ የማስመዝገቡ እንቅስቃሴ ከዓመታት በፊት መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ባህል በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ሲከበር የቅርስ እና ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን እና የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለምዝገባ ሂደቱ መፋጠን እንደ ግብአት እንደሚጠቀሙበት ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 /2011
ዳግም ከበደ