ሳይንስ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ማመንጫና ማበልፀጊያ ማዕከል ነው፡፡ ምርምር እና ፈጠራ መፍትሄን አመንጪ፤ ያልታሰበ ነገር አስገኚ ነውና አለምን በተሻለ የዛሬ ገፅታዋ ላይ የራሱ ትልቅ በጎ ሚና ተጫውቷል፡፡
የፈጠራ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ከሚመለከቱት አካባቢያዊ ሁኔታ መነሻነት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመፍጠር ለተመለከቱት ችግር መፍትሄ ያበጃሉ፡፡
የምርምርና የፈጠራ ስራዎች የማህበረሰቡ ችግር በመቅረፍ ትልቅ አስተዋፅዖ አላቸው፡፡ አንድ የፈጠራ ስራ በሌላ ቦታ ተሽሎና ሌላ ታክሎበት ለተሻለ ግልጋሎት ሊውል ይችላል፡፡ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቁ መሄድ የሰው ልጅ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን ማሳያዎች ናቸው፡፡
የምርምርና የፈጠራ ስራዎቹ በየአለማቱ ጥግ በአጭርና በተወሰነ ጊዜ ደርሰው ተገልጋዩ ሲጠቀምባቸው እና ተግባር ላይ ሲያውላቸው መመልከት አዲስ አይደለም፡፡
የአለም አሁናዊ ገፅታን በመቀየር ለሰው ልጆች ህይወት መቅለልና የአኗኗር ስርዓት መልካም አጋጣሚ የሳይንስን ያህል ተፅዕኖ የፈጠረ መኖሩ እስክንጠራጠር ድረስ ሳይንስና ውጤቶቹ ተቆጣጥረውናል፡፡ በየጊዜው የሚወጡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርቶች መነሻው የግለሰቦች ምርምርና ፈጠራዎች ናቸው፡ ፡ እነዚህ ምርምሮች የሚያስገኙት ውጤት አድሮ መልካም ፋይዳ ያበረክታል፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች መበራከትና የምርምር ስራዎች መስፋፋት ለአገር ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ለዚህም ነው እንደ አገር ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ የሚገኘው፡፡ በጥራቱና በልዩ ትኩረቱ የተፈለገውን ያህል ባይሆንም በመስኩ ውጤት መመዝገቡ አልቀረም፡፡
ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች መበራከት ለአገር ብስራት ለሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ደግሞ የምስራች ነው፡፡ ከወጣትነታቸው ጀምረው ብዙ ፈጠራና ምርምሮችን ማድረግ መቻላቸው በረዘመ ቆይታቸው የሚያገኙት ችግር ፈቺ ግኝት ደግም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ መልካም ሁኔታ በመፍጠር የሚኖራቸው ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡
በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶቹ የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡ ፡ የዛሬ ሳይንስ አምዳችን የሚያስተዋውቀን ወጣት የ12 ክፍል ተማሪና በፈጠራ ስራዎቹ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማቶችን ያገኘ የአርሲ ቦቆጂ ፍሬ ነው፡፡ ይህ በእድሜው ገና ለጋ የሆነው ወጣት ከእድሜው በመቅደም በተቸሩት ብሩህ አዕምሮ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በግል ጥረቱ ተግባራዊ ማድረግ ችሏል፡፡
ተመራማሪ ተማሪ አስራት እንዳለ ይባላል፡፡ ገና ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ የራሱን የፈጠራ ስራ የመስራት ውስጣዊ ፍላጎት የተጫረበት አስራት ከስድስት ያላነሱ የፈጠራ ስራዎችን ማበርከት ችሏል፡፡ በምርምር ሙያ የተለየ ስልጠና ሳያገኝ በተደጋጋሚ ሙከራ በዘርፉ ላይ ያለውን ፈተና ተቋቁሞ የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የፈጠራና የምርምር ስራዎችን በመስራት ስኬታማ መሆን ችሏል፡፡ በእድሜው ለጋና በቀለም ትምህርቱም ብረቱ ከሆኑት መካከል የሆነው ወጣት አስራት፤ በምርምርና ፈጠራ ስራዎቹ ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን መፍጠርና መሞከር የሚያዘወትር ለወደፊትም ከፍ ያለ ቦታ መድረስ ያለመ ባለ ራዕይ ነው፡፡
የፈጠራ ባለሙያው አስራት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የወዳደቁ እቃዎችን በማንሳት እና በመገጣጠም መምህሩ የሚሰጡት የቤትና የክፍል ስራ በፈጠራ መልክ በማቅረብ የጀመረው ልምድ ወደ ፈጠራ ስራ አሳድጎ ዛሬ ላይ ቀላል ያልሆኑ የፈጠራ ስራዎችን በግል ትጋት መፍጠር ችሏል፡፡ የሰራኋቸው ስራዎች ጅምር እንጂ የመጨረሻ ግኝቶቼ አይደሉም የሚለው ወጣት አስራት፤ ዛሬ ላይ በጥረቱ ከውጤት ያደረሳቸው የፈጠራ ስራዎቹ ነገ በመስኩ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሚሆኑ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
የፈጠራ ስራው ምንነት
በወጣትነት ዕድሜው በተሰጠው ብሩህ አዕምሮው እስካሁን ከሰራቸው የፈጠራ ስራዎቹ መካከል የሄሊኮፕተር ሞዴል፣ በውሀ፣ በንፋስና በሰው ሀይል የሚሰራ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጨት፣ ድሮን ካሜራ፣ የንብረት ክፍል መቆጣጠሪያ መሳሪያ፣ በሶላር የሚሰራ የሃይል ማመንጫ፣ ትራንስፎርመር የፈጠራ ስራ ውጤቶቹ የትጋቱ ግኝቶች ናቸው፡፡ እነዚህ በዋናነት ጠቀስን እንጂ የሰራቸው የፈጠራ ስራዎች በፊት በሌሎች የተሰሩና የተሻሉ ቁሳቁሶች በርካታ መሆናቸውን ተመራማሪው ይገልፃል፡፡
ለፈጠራ ባለሙያው አስራት ቤተሰቦቹ ገጠር አካባቢ መገኘታቸውና እዚያ ደግሞ የሀይል እጥረት ዋንኛ ጉዳይ መሆኑ ትኩረት የሀይል ምንጮች ላይ እንዲሆን እንዳደረገው ይገልፃል፡፡ የሰራቸው የፈጠራ ስራዎቹም በእራሱ ቤተሰቦች ቤት ግልጋሎትን እየሰጡ እንደሆነና የአካባቢው ሰው የፈጠራ ስራውን እየተመለከተ አድናቆትና ማበረታቻ እየሰጠው መሆኑን ይናገራል፡፡ የቤተሰቦቹ መገኛ አካባቢ ጨለማን የመግፈፍ ውጥኑ ዛሬ ላይ መብራትን መፍጠር፤ ብርሃንን ማጎናፀፍ አስችሎታል፡፡
ለፈጠራ ስራው ያነሳሳው ምክንያት፡–
ብዙው ጊዜ የፈጠራ ስራዎች መነሻ ከአካባቢ ወይም ካሉበት ማህበረሰብ የሚከሰት ችግር እሱን ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ የወጣቱ ተመራማሪ ገጠመኝ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የመምህሩ ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ስራ መስጠትና ደጋግሞ በተለያየ ቅርፅና ይዘት ሙከራውን ማድረግ መቻሉ እሱንም ተከትሎ ያገኛቸው ውጤቶች ጥሩ መሆናቸው የምርምርና ፈጠራ ስራው መነሻ ሆኖታል፡፡
ከመምህሩ የሚሰማቸው ምክሮችን ተከትሎ ሳይሰለች በፈጠራ ሙከራ ስራ መቀጠሉ ዛሬ ላይ ያገኛቸው ፈጠራዎች መድረሻ ድልድይ መሆኑን የሚናገረው ተማሪና የፈጠራ ባለሙያው አስራት በፈጠራ ስራው ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በሂደት የገጠመውን ምቹ ገጠመኝ ተጠቅሞ ማለፍ መቻሉ እንደሆነ በማሳያነት ይጠቅሳል፡፡
በፈጠራ ስራው የተገኘ እውቅናና ሽልማት
ተማሪና የፈጠራ ባለሙያው አስራት የምርምር ስራው ብዙ እውቅናና ሽልማት ከተለያዩ ተቋማት አስገኝቶለታል፡፡ ከትምህርት ቤት፣ ከወራዳ፣ ከዞንና ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሽልማቶችንና የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን በፈጠራና ምርምር ስራው ያገኛቸው እውቅናና ሽልማት አጠናክሮት በአገር አቀፍ ደረጃ ለሁለት ጊዜ በምርምርና በፈጠራ ስራ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚዘጋጀው የፈጠራ ስራ ውድድር ሁለት ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አግኝቷል፡፡
በተጨማሪም ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ በተለያዩ የፈጠራና የምርምር ስራዎች በክልል በዞንና በወረዳ ደረጃ ተወዳድሮ በማሸነፍ ያገኛቸው እውቅናና ሽልማቶችም ለስራዎቹ ምስጋናና ማበረታቻዎቹ ለወደፊት የሚሰራቸው የፈጠራ ስራዎች ተነሳ ሽነትን የሚፈጥሩለት መሆኑን ይገልፃል፡፡
የፈጠራ ስራው አሁን ያለበት ደረጃ
አንድ የፈጠራ ወይም የምርምር ስራ ተግባራዊ ሆኖ ማህበራዊ ችግርን መቅረፍ ካልቻለ በመፈጠሩ ብቻ የሚያስገኘው ጠቀሜታ የለም፡፡ በመሆኑም የፈጠራ ባለሙያዎች የአዕምሮ ውጤት የሆኑት ፈጠራዎች ተግባራዊ በማድረግ ለጥቅም ለማዋል መስራት ይገባል፡፡ ነገር ግን የፈጠራና ምርምር ስራዎች በተመራማሪው የገንዘብና የቁሳቁስ አቅም ውስንነት የተነሳ ብዙ ጊዜ ማህበረሰቡ ጋር ሳይደርሱ ይቀራሉ፡፡
የወጣቱ ፈጠራ ባለሙያው አስራት ስራዎች ተግባራዊነታቸው ተፈትሾ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጡ በተሳተፈባቸው መድረኮች ሁሉ አስተያየት ቢሰጠውም፤ ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ያለበት የቁሳቁስና የገንዘብ እጥረት የፈጠራ ስራዎቹ በማምረትና በማዘጋጀት ለማህበረሰቡ ማድረስ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ወጣት ሆኖ በምርምርና ፈጠራ ስራ ተግቶ የተሻለ ውጤት ማስገኘት መቻል በራሱ ትልቅ እርዳታ ነው፡፡ ለወጣቶች ሞራል ለተመራማሪዎች ተስፋ ሊሆን የሚችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደ አገር ሊወጡት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
በፈጠራ ስራው የገጠመው ፈተና
ወደ ምርምር ስራ አዲስ ሆኖ የሚቀርብ ባለሙያ ፈተናዎች መጋፈጡ አይቀሬ ነው፡፡ እነዚያን ፈተናዎች ተቋቁሞ ከውጤት መድረስ ደግሞ የራስ ጥንካሬና ብርቱ የሆነ ፅናት ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያው አስራት ለምርምር ስራ የተሻለ ውጤት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ የሚገባ መሆኑን ካለው ተሞክሮ እያጣቀሰ ይናገራል፡፡ ለወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ አስራት በፈጠራ ስራው እዚህ ደረጃ ለመድረስ መንገዱ ሰምሮና ተደላድሎ አልጠበቀውም፡ ፡ ፈተናዎቹን ተቋቁሞ የነገ መድረሻውን እያለመ በፅናት አልፏቸዋል፡፡
ለወጣቱ የፈጠራ ባለሙያው አስራት ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል ምርምር ስራ ምቹ የሆነ አካባቢያዊ ሁኔታ አለመኖር፣ ለምርምር ስራው ቁሳቁሶች አለመኖር የሚሰጠው የፈጠራ እና ምርምር ማድረጊያ ጊዜ ማጠር የመሳሰሉት ለፈጠራ ስራው የገጠሙት ዋንኛ ችግሮች እንደነበሩ ይጠቁማል፡፡
ለጀማሪ የፈጠራ ስራ
ባለሙያዎች መልዕክት
በምርምርና በፈጠራ ስራ የተሰማራና በዘርፉ አዲስ ሆነው ለሚቀላቀሉ ባለሙያዎች የምርምር ስራቸው መልካም ስምረትና ውጤት ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ አስራት ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ለወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ብርቱና ፅኑ አላማ ይዘው መነሳት እንዳለባቸው ምክሩን ይለግሳል፡፡
እንደ ተመራማሪ በምርምር ስራ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆን እመንደሚገባ፤ የፈጠራና ምርምር ስራዎች ወሳኝ እንደሆኑና መንግስትና ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ወጣቱ አስራት ማሳያዎችን በመጥቀስ ያስረዳል፡፡ ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ወደፊት በፈጠራና ምርምር ስራ ብዙ መስራት እንደሚፈልግና ለዚህም ጥረት እያደረገ መሆኑን ይናገራል፡፡ እኛም ለወጣቱ ተመራማሪ በስራው ስኬትን ለዓላማው ስምረትን ተመኘን፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011
ተገኝ ብሩ