ፅንስ ማቋረጥ ሴቶችንና ወንዶችን እንደ ግለሰብ ብሎም የማህበረሰብ አባላትን የሚያካትት ሰብዓዊ ጉዳይ በመሆኑ ከህክምና፣ ሥነምግባርና ከህግ ሁኔታዎች በላይ መሆኑ ይገለጻል።
በኢትዮጵያ ፅንስ የማቋረጥ ጉዳይ አሁንም አወዛጋቢና በርካታ ክርክሮች የሚቀርቡበት መሆኑ ይታወቃል። የጤናና የህግ ባለሙያዎችም በየጊዜው የየራሳቸውን አስተያየት ሲሰጡበት ይደመጣል።
የፅንስ ማቋረጥን ጉዳይ አንዳንዶች ‹‹ከእምነትም ከሞራልም አኳያ የሚወገዝ ነው።›› ብለው ሲከራከሩ፤ በህክምናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ደግሞ ‹‹ፅንስ ማቋረጥ በምክንያት ከሆነ ተገቢ ነው።›› ይላሉ። እንደውም ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ይመሰክራሉ።
አብዛኛዎቹ የጤና ባለሙያዎች፤ የደም መፍሰስ፣ የምጥ መቆየት፣ የደም ግፊት፣ ኢንፌክሽንና ፅንስ ማቋረጥ እናቶችን ለሞት የሚያበቁ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በተለይ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ /unsafe abortion/ ለእናቶች ሞት ቀዳሚውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ይናገራሉ።
በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጀ በየዓመቱ ከሚከሰቱ 208 ሚሊዮን እርግዝናዎች ውስጥ 59 በመቶ የሚሆኑት የታቀዱ ሲሆኑ፣ 41 በመቶዎቹ ደግሞ ያልታቀዱ ናቸው። በሌላ በኩል 22 ሚሊዮን ወይም 49 በመቶ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 47 ሺ የሚሆነው የእናቶች ሞት የሚከሰተው ከፅንስ ማቋረጥ ጋር በተያያዘ ነው። ይህም ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ለእናቶች ሞት ዋነኛው መንስኤ መሆኑን ያሳያል።
በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከሚከሰተው አራት ሚሊዮን እርግዝና 500 ሺ በሚሆነው ላይ ምክንያታዊና ምክንያታዊ ያልሆኑ ፅንስ ማቋረጦች እንደሚካሄዱ የጤና ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2014 ያካሄደው ጥናት ያመለክታል። ከዚህ ጋር በተያያዘም 32 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ጥንቃቄ በጎደለው የፅንስ ማቋረጥ ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍም ጥናቱ ያሳያል።
ከጤና ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በ1997 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣውን ህግ ተከትሎ እንደ ኤም.ቪ.ኤ /MVA/ እና ሜዲኬሽን አቦርሽን /medication abortion/ ያሉ ዘዴዎች በመምጣታቸው፣ ለመካከለኛና ከፍተኛ ጤና ባለሙያዎች ደህንነቱን በጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ ዙሪያ ስልጠና በመሰጠቱና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ዝግጁነት ማደግ ከፅንስ ማቋረጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ አስችሏል።
በ2000 ዓ.ም የተካሄደ አገር አቀፍ ጥናትም ከፅንስ ማቋረጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የእናቶች ሞት ምጣኔ ከስድስት እስከ ዘጠኝ በመቶ ዝቅ ማለቱን ያሳያል። ይሁንና የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንደልብ ተደራሽ ባለመሆኑ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ አሁንም ለእናቶች ሞት ምክንያት ሆኗል።
ወይዘሮ ብሌን ረዘነ በአይፓስ ኢትዮጵያ በስነተዋልዶ ጤና የወጣቶች ፕሮግራም አማካሪ ሲሆኑ፣ ‹‹ፅንስ ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የስነተዋልዶ ጤና ጉዳዮችን ማህበረሰቡ የሚያይበት የራሱ መነፅርና አስተሳሰብ አለው።›› ይላሉ። ከያዛቸው እሴቶች አኳያ እንዲሆንለት የሚፈልጋቸው ጉዳዮች እንዳሉም ይጠቁማሉ።
በተለይም ማህበረሰቡ ወሲብና ወጣትነትን የሚያይበት መንገድ የተለየ ነው።ይህም ከማህበረሰቡ አስተሳሰብና አመለካከት አኳያ የሚታይ በመሆኑ ወጣቶች በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ በቂና ግልፅ መረጃ በማግኘት ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዳያሳልፉ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩን አማካሪዋ ያመለክታሉ።
ወጣቶች ጠቃሚም ሆነ ጎጂ መረጃዎችን የሚያገኙት ከማህበራዊ ድረገፆችና ከጓደኞቻቸው በመሆኑ ላልተፈለገ እርግዝናና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ከዚህ አለፍ ሲልም ደህንነቱ ላልተጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ እንደሚዳረጉ ይገልፃሉ።በዚህ የተነሳም ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉም ነው አማካሪዋ ያስገነዘቡት።
እንደ ወይዘሮ ብሌን ገለፃ፤ አሁን ባለው ሁኔታ በተለይ ካልተፈለገ እርግዝና ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ የጎደለው ፅንስ ማቋረጥ በብዛት በወጣቶች ላይ እየታየ ይገኛል። ይህም የሆነው በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ወጣቶች በቂ መረጃ ስለማያገኙ ነው። ከዚህም ባለፈ በወጣቶች ዘንድ የመወሰን ብቃትና አቅም አለማዳበርና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት በትክክል የት እንደሚሰጥ ያለማወቅ ጥንቃቄ ለጎደለው ፅንስ ማቋረጥ ምክንያት ነው።
ከሁሉ በፊት ማህበረሰቡ ያመጣቸውን እሴቶችና አስተሳሰቦችን ማክበር እንደሚገባ የሚገልጹት አማካሪዋ፤ የህብረተሰቡን እሴትና አስተሳሰብ በማይጋፋ መልኩ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ለወጣቶች በስፋት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ። በጉዳዩ ዙሪያ ግልፅ የሆነ የውይይት ባህል ማዳበር እንደሚያስፈልግና ይህም ወጣቶች በተለይ ባልተፈለገ እርግዝና ምክንያት ደህንነቱ ያልተጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ እንዳያካሂዱ አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚረዳም አማካሪዋ ይገልፃሉ።
የአይፓስ ኢትዮጵያ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ደረጀ ወንድሙ እንደሚሉት፤ የስነ ተዋልዶ ጤና ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ ያለው ጉዳይ ቢሆንም ፅንስ ማቋረጥ አንዱና ዋነኛው ዘርፍ ነው። በተለይም የፅንስ ማቋረጥ የሚመጣው የቤተሰብ እቅድ ፕሮግራም በበቂ ሁኔታ ባለመዳረሱ ወይም መረጃውን ሴቶች ባለማግኘታቸው በመሆኑ ትልቅ ጉዳይ ያደርገዋል። በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ በቂ መረጃዎች አለመኖር፣ የወሊድ መከላከያ እንደልብ ያለመገኘት፣ የባህል ተፅእኖ፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚና የትምህርት ደረጃ ላይ መገኘት በተለይ ወጣቶች አገልግሎቱን እንዳያገኙ የሚያደርጉ ዋና ምክንያቶች ናቸው።
እንደ አማካሪው ገለፃ፤ ከፅንስ ማቋረጥ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት እየወጡ ያሉ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና አሰራሮች አንዲት ሴት ከአቅሟ በላይ በሆነ ምክንያት ፅንስ ማቋረጥ ብትፈለግ የሚፈቅዱ ናቸው። ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ፅንሱን ካቋረጠች በኋላም ዳግም እንዲህ አይነቱ ችግር እንዳያጋጥማት የምክር አገልግሎት እንድትጠቀም ያስችላታል።
አማካሪው እንደሚሉት፤ የጤና ሚኒስቴር ያወጣውና ደህንነቱ የተጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችለው መመሪያ ላይ ማንኛውም የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ፈልጋ የምትመጣ ሴት የምክር አገልግሎት የሚሰጣት ቢሆንም ወዲያውኑ የእርግዝና መከላከያ ላይሰጣት ይችላል። ፅንስ ከተቋረጠ በኋላም የተወሰነ ጊዜ ልትቆይ ትችላለች።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትና የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት በጥምረት የሚሰጥ በመሆኑ የጤና ባለሙያዎች ሁለቱንም አገልግሎቶች መስጠት ይችላሉ። ዋናው ጉዳይ ግን ፅንስ ማቋረጥ በተለያየ ምክንያት አነጋጋሪና የተገለለ በመሆኑና ሴቶችም ፅንሱ ከተቋረጠ በኋላ ችግራቸው መቃለሉን ብቻ ስለሚያዩና ከዛ በኋላ ያለውን ነገር ስለማያስተውሉ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቱን ማቋረጥ የለባቸውም።
‹‹መንግሥት ከፅንስ ማቋረጥ ጋር በተያያዘ ህግ ሲያወጣ ፅንስ ማቋረጥ መፍትሄ ነው ብሎ አይደለም።›› የሚሉት አማካሪው፤ ‹‹በቅድሚያ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉና ፅንስ ማቋረጥ እንደመጀመሪያ አማራጭ መታየት አይኖርበትም።›› ይላሉ። ‹‹ይሁንና የጤና ችግር ለገጠማቸውና ሌሎች አሳማኝ ምክንያት ላላቸው ሴቶች አግባብ ባለውና ህጉ በሚፈቅደው መጠን ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ ፅንስ እንዲያቋርጡ ይደረጋል።›› በማለት ነው ማብራሪያ የሰጡት።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ከሁሉ በፊት ግን ከትምህርት ቤት ጀምሮ ለወጣቶች በተለይ ለሴቶች በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ በቂ የምክር አገልግሎትና ግንዛቤ ሊሰጣቸው ይገባል። አገልግሎቱ በስርዓት ትምህርት ውስጥ ጭምር ተካቶ መሰጠት ይኖር በታል። በተለያየ መልኩ በተለይም በሚዲያዎች ግንዛቤ መስጠት ያስፈልጋል።
ዋናውና ትልቁ ጉዳይ ደግሞ የቤተሰብ እቅድ ፕሮግራም በሰፊው እንዲዘረጋ በጉዳዩ ላይ እውቀትም በሰፊው እንዲኖር አድርጎ የተጠቃሚዎችን ቁጥር መጨመር በመሆኑ በዚህ ረገድ ጠንካራ ሥራዎችን መስራት የግድ ይላል። ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይኖርና ወደ ፅንስ ማስወረድ እንዳይኬድም አስቀድሞ መከላከል ላይ በስፋት መሰራት ይኖርበታል። ይህን አልፎ የመጣ ከሆነና ሴቷን አደጋ ላይ የሚጥላት ከሆነ ግን ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥን እንደአማራጭነት ልታገኘው ይገባል።
የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪምና በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት አማካሪ ዶክተር ዮናስ ጌታቸው እንደሚሉት፤ ፅንስ ማቋረጥ ደህንነቱን ባልጠበቀ መልኩ ሲሆንና ይህን ተከትሎ ሌሎች ችግሮችን ሲያመጣ ለእናቶች ሞት አንዱ ምክንያት ይሆናል። የዚህም ምክንያት ይህን ድርጊት የሚፈፅሙ ሰዎች የሰለጠኑ ባለመሆናቸው፣ የሚጠቀሙበት መሳሪያ ተገቢ ያልሆነ፣ የሚሰሩበት አካባቢም ያልፀዳ በመሆኑ ነው።
እንደ ዶክተር ዮናስ ገለፃ፤ ደህንነቱ ያልተጠበቀ የፅንስ ማቋረጥን ለመከላከል በተለይ ሴቶች ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይኖር ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። በእርግዝና መከላከያ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙም ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም ሆኖ እርግዝና ከተከሰተ ሴቶች ደህንነቱ ወደተጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት መሄድ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። ፅንሱ ከተቋረጠ በኋላም በሌላ ጊዜ ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይከሰት የእርግዝና መከላከያ የሚጠቀሙበት ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል። ይህም ከፅንስ ማቋረጥ ጋር በተገናኘ ያለውን የእናቶች ሞት ሊቀንስ ይችላል።
‹‹በመጀመሪያ ደረጃ ፅንስ ማቋረጥ የሚደገፍ ነገር አይደለም።›› የሚሉት ዶክተር ዮናስ፤ ‹‹በፅንሱ ላይ ችግር ካለ፣ የእናቲቱን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ከተፈጠረ ፅንሱን ማቋረጥ ተገቢ ነው።›› ይላሉ።
ፅንስ የማቋረጥ ሥራ እንደአገሪቱ ህግ እንደሚታይም ዶክተር ዮናስ ይገልጻሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ፅንስ ማቋረጥ የህክምና ሥራ ብቻ ባለመሆኑና ህጎችም ያሉት በመሆኑ እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይከናወናል። ህጉ ፅንስ ማቋረጥን የሚከለክል ቢሆንም በህግ አግባብ ፅንስን ማቋረጥ የሚፈቀድባቸው ምክንያቶችም ይኖራሉ። ለአብነትም አንዲት ሴት ተገዳ ከተደፈረች፣ ያለእ ድሜዋ ከፀነሰች፣ እርግዝናው በጤናዋ ላይ አደጋ የሚፈጥር ከሆነ በህጉ መሰረት ፅንሱ እንዲቋረጥ ይደረጋል።
ከፅንስ ማቋረጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰት የእናቶች ሞትን ለመቀነስ በሴቶች በኩል ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይከሰት ማድረግ ትልቁ መሳሪያ ነው። ለዚህም የስነ ተዋልዶ ጤና ፕሮግራሞችንና የምክር አገልግሎቶችን በተለይ ለወጣቶች በስፋት ማድረስ እንደሚገባም ዶክተር ዮናስ ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2011
አስናቀ ፀጋዬ