
ዜና ሐተታ
“ደቂቃ ላለመታገስ ሕይወታቸውን ያጣሉ፣ የአካል ጉዳተኛ ይሆናሉ። ከብዙዎች ላይ የታዘብኩት ወደ አስፋልት ዘለው የሚገቡት በችኮላ ነው” የሚለው የትራፊክ ተቆጣጣሪ የሆነው ወጣት ዘላለም ሞሲሳ፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጸው፤ ወቅቱ የክረምት ወቅት እንደመሆኑ የትራፊክ መጨናነቅ ይፈጠራል። እግረኞች ከዝናብ ለማምለጥ ሮጠው ለመሻገር ወደ አስፋልት ይገባሉ። አሽከርካሪዎች በዝናብ ምክንያት የተዘጋጋው መንገድ ስለሚያሰለቻቸው ትንሽ ክፍተት እንዳገኙ ቶሎ ለማለፍ ይጣደፋሉ። በእንዲህ ዓይነት የአሽከርካሪና የእግረኛ የችኮላ አጋጣሚዎች አደጋዎች እንደሚፈጥሩ መታዘቡን ገልጿል።
አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች ለአደጋ የሚጋለጡት የደቂቃ ትዕግስት በማጣት እንደሆነ ይናገራል። “አስቸኳይ ጉዳይ ሊኖር ይችላል፤ ዳሩ ግን ራስን ለአደጋ በሚያጋልጥ መንገድ መሆን የለበትም” የሚለው ወጣት ዘላለም፤ በተደጋጋሚ እንደታዘበው፤ ዝናብ በሌለበት ወቅት ሳይቀር ሰዎች አስፋልት ለመሻገር ይጣደፋሉ። በተለይም የኮሪዶር ልማት በተሠራባቸው አካባቢዎች አስፋልቱ ምቹ ስለሆነ አሽከርካሪዎች በፍጥነት ያሽከረክራሉ። በእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ አደጋ እንዳይፈጠር እግረኞችም ሆኑ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ያሳስባል።
በተለይም ወቅቱ የክረምት ወቅት ስለሆነ እግረኞች ከዝናብ ለማምለጥ በሚያደርጉት ሩጫ አደጋ እንዳይፈጠር አሽከርካሪዎችም ሆኑ ወጣቶች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሦስት ወራት የሚቆይ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ንቅናቄ ባለፈው ቅዳሜ በይፋ አስጀምሯል። በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ከሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የተውጣጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ታድመዋል።
ወጣት ሰለሞን ነጋ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት፤ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስለቆሻሻ ማውራት ለወጣቱ አሳፋሪ ሊሆን ይገባል። ወጣቱ በቆራጥ ወኔ እና በቁጭት ይህን አመለካከት ሊያስወግድ ይገባል። የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢ የሚሆኑት ተማሪዎችና ወጣቶች ጽዱ አዲስ አበባን እና ጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል በማድረግ ለትውልድ ማስተላለፍ አለባቸው ብሏል።
በጥቂቶች የሚጀመር ዘመቻ ተከታታይነት ካለው ባሕል ይሆናል፤ ለእዚህም ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል ያለው
ወጣት ሰለሞን እንደታዘበው፤ የቆሻሻ ማስቀመጫ በተዘጋጀባቸው ቦታዎች ላይ ሳይቀር ሰዎች በግዴለሽነት ቆሻሻ መንገድ ላይ ይጥላሉ። ይህ የሆነው የሠለጠነ ባሕልና ልማድ ባለመኖሩ ነው። ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ባሕል እስከሚሆን ድረስ አስገዳጅ ሕጎች እና ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ያሳስባል።
“ፅዱ፣ ውብ እና ደህንነቷ የተጠበቀች አዲስ አበባ” በሚል መሪ ሃሳብ ባለፈው ቅዳሜ በተጀመረው የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ማስተግበሪያ የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ፤ ዘመቻው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከውጭ ሀገር የሚመጡ ሰዎች የመንገድ ዳር ቆሻሻዎችን ሲታዘቡ እንዳስተዋሉ የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የቆሸሹ አካባቢዎችን የማፅዳት፣ የመንገድ መብራት ሽፋን የማሳደግ፣ የውሃና ፍሳሽ መሠረተ ልማት ሽፋን የማሳደግ እና የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓትን የማዘመን ሥራ በቀጣይ ዘጠና ቀናት በስፋት እና በልዩ ትኩረት የሚሠሩ ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የተጀመረው የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ንቅናቄ የጽዳት ዘመቻ ብቻ አይደለም። የዘመናዊ እና የሥልጡን ዜጋ ዘመናዊ አኗኗር ለመፍጠር በሁሉም አገልግሎቶች የሚደረግ ንቅናቄ ነው። የዜጎችን ክብር የሚመጥን አገልግሎት እና ልማት መፍጠር ነው ብለዋል።
ጽዳት፣ ውበት፣ እና ደህንነት ባሕል የሚሆንበት ሁኔታ መፍጠር ነው። የንቅናቄ ሥራው ወንዞች ንጹህ እስከሚሆኑ፣ የመንገድ ዳርቻዎች ንጹህ እና አረንጓዴ እስከሚሆኑ፣ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እስከሚሆኑ ድረስ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
“ሕዝቦቿ ባለቤቷ የሆኑባት ከተማ እስከምትሆን ድረስ እንሠራለን” ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፤ ደህንነቷ የተጠበቀ እና ውብ የሆነች አዲስ አበባን መፍጠር የሚቻለው ግን ባለቤቷ የሆነው ነዋሪ በትጋት እና በባለቤትነት ሲሠራ እንደሆነ ይገልጻሉ።
እንደ ኢንጂነር ወንድሙ ገለጻ፤ አንዳንድ አካባቢዎች በምሽት ስጋት ያለባቸው፣ የትራፊክ ፍሰቶች የአደጋ ስጋት ያለባቸው፣ ያለጥንቃቄ የመንገድ ማቋረጥ ግዴለሽነቶች የሚታዩባቸው ናቸው። አካባቢያዊ ደህንነት እና የሠለጠነ የትራፊክ ፍሰት መፍጠር የሚቻለው የከተማዋ ነዋሪ በሠለጠነ መንገድ ሲገለገል እና ሲተባበር ነው ብለዋል። የንቅናቄ ፕሮጀክቱም የመንግሥት ፕሮጀክት ሳይሆን የማህበረሰብ ፕሮጀክት መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሌሊሴ ነሜ እንደተናገሩት፤ ዜጎች ምቹ እና ጽዱ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ ማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊነት ነው። ጽዱ እና ምቹ አካባቢን መፍጠር የሚቻለው ግን በቁጥጥር እና በትዕዛዝ ብቻ ሳይሆን ጽዳትን ባሕል በማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነት ንቅናቄዎችም ሁሉንም ክልሎች ተደራሽ ያደርጋሉ። ጽዳት እና ደህንነትን መጠበቅ በንቅናቄ ሳይሆን በባሕል መሆን እንዳለበት ነው የጠቆሙት።
የአሁኑ ንቅናቄ ማስጀመሪያ እና ማነቃቂያ ደወል ነው። ባሕል እስከሚሆን ድረስ ግን ቁጥጥሮች እንደሚደረጉ እና ርምጃዎች እንደሚወሰዱ አሳስበዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም