ትራምፕ ቲክቶክን የሚገዛ የቱጃሮች ቡድን እንዳላቸው ገለጹ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ውስጥ የብሔራዊ ደህንነት አደጋን ይፈጥራል በሚል የታገደውን ቲክቶክን (TikTok) የሚገዛ የቱጃሮች ቡድን አለኝ አሉ። ትራምፕ፤ ከ‘ፎክስ ኒውስ’ (Fox News) ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያውን “ለመግዛት ፈቃደኛ የሆኑ በጣም ሀብታም ሰዎች” አሉ ብለዋል። “ከሁለት ሳምንት በኋላ እነግራችኋለሁ” ሲሉም ጠቁመዋል።

መተግበሪያውን ለመሸጥ የቻይና መንግሥት ይሁንታ ያስፈልጋል። ትራምፕ፤ ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ “ያደርጉታል” ብለው እንደሚያስቡ ለጣቢያው ተናግረዋል።

ትራምፕ በእዚህ ወር ቲክቶክ እንዲሸጥ የሚያስገድደው ሕግ ተግባራዊ እንዳይሆን ለሦስተኛ ጊዜ አራዝመውታል። ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገው ማራዘሚያ የቲክቶክ እናት ኩባንያ የሆነው ‘ባይትዳንስ’ በቀጣዩ መስከረም አጋማሽ መተግበሪያውን ለመሸጥ ስምምነት ላይ እንዲደርስ ይጠይቃል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ቲክቶክን ለአንድ አሜሪካዊ ገዢ ለመሸጥ የተደረሰው ስምምነት፤ አሜሪካ ቻይና ላይ የጣለችውን ታሪፍ ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ ፈርሷል። ትራምፕ አሁን ገዢዎች አሉኝ ያሉት ከሦስት ወር በፊት ለመግዛት ሲጠብቅ የነበረው አካል ስለመሆኑ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።

የአሜሪካ ኮንግረስ ቲክቶክ እንዲሸጥ የሚያስገድድ ሕግ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ሲያጸድቅ የመተግበሪያው እናት ኩባንያ ‘ባይትዳንስ’ የአሜሪካ ተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው የገለጸ ቢሆንም፤ ቲክቶክ ግን ስጋቱን ውድቅ አድርጓል። ኮንግረሱ ያሳለፈው ሕግ ባለፈው ጥር 19 ተግባራዊ መሆን የነበረበት ቢሆንም ትራምፕ ግን በፊርማቸው በተደጋጋሚ አዘግይተውታል። ይህም ከኮንግረሱ ሕግ አውጪዎች ተቃውሞ እና ትችትን አስከትሏል።

ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው መተግበሪያውን ተችተውት ነበር። ነገር ግን በ2024 በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፋቸው እንደ አንድ ምክንያት አድርገው ስለሚመለከቱት አሁንም በአሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ መዋሉን ደግፈዋል።

ቲክቶክ ሕጉ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲል ተቃውሞውን ለአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያሰማም፤ ፍርድ ቤቱ ቲክቶክ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አድርጎታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You